በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበት ጊዜ ቀርቧል

የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበት ጊዜ ቀርቧል

የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበት ጊዜ ቀርቧል

የመሬት መናወጥ፣ ጦርነት፣ ረሀብና በሽታ ኢየሱስ የምንኖርበት ሥርዓት “መጨረሻ” ምልክቶች እንደሆኑ ከተናገራቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8፤ ሉቃስ 21:7, 10, 11) እርግጥ ነው፣ እነዚህን ክስተቶች ያመጣቸው አምላክ አይደለም። ኢየሱስም ሆነ አባቱ ይሖዋ አምላክ ለተፈጥሮ አደጋዎች በኃላፊነት አይጠየቁም።

ይሁን እንጂ እነዚህ ክስተቶች ምልክት የሆኑላቸው ነገሮች፣ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተዳድረው በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት የሚመጣውም ሆነ የይሖዋን ሉዓላዊነት የማይቀበሉ ሰዎች ሁሉ የሚጠፉት በአምላክ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) ከዚያ ወዲያ ምድር የተፈጥሮ አደጋ የማያሰጋት ሰላማዊ ቦታ ትሆናለች። አምላክ “ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል” በማለት የሰጠው ተስፋ በተሟላ መልኩ ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳይያስ 32:18

አምላክን በመስማት ለዘላለም ኑር!

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተብራራው ማስጠንቀቂያዎችን ሰምቶ እርምጃ መውሰድ ሕይወትን ያተርፋል። ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎች በመስማት ረገድም የበለጠ ይሠራል። “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”—ምሳሌ 1:33

የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል አዘውትረው በማንበብና የሚያስተምረውን ነገር በሥራ በማዋል አምላክን ለማዳመጥ ይጥራሉ። አንተም እንደዚህ እንድታደርግ ይጋብዙሃል። አዎን፣ ይሖዋን በታዛዥነት የሚያዳምጡት ሁሉ መጪውን ጊዜም ሆነ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውን መቅሠፍት መፍራት አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ፤ በዚያም ‘በታላቅ ሰላም ሐሴት ያደርጋሉ።’—መዝሙር 37:10, 11

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን መጽናኛ

በተፈጥሮ አደጋ አሊያም በሌላ አሳዛኝ ሁኔታ የምትወዳቸውን ሰዎች በሞት ተነጥቀሃል? ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት፣ የኢየሱስ ወዳጅ የሆነው አልዓዛር በሞት ተቀጭቶ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲሰማ አልዓዛር ወደሚኖርባት ቢታንያ ወደተባለችው መንደር ሄደና ‘በእንቅልፍ’ ከተመሰለው ሞት አስነሳው።—ዮሐንሰ 11:1-44

ኢየሱስ ይህን ተአምር የፈጸመው አልዓዛርንና ቤተሰቡን ስለሚወዳቸው ብቻ ሳይሆን በመንግሥታዊ አገዛዙ ወቅት ‘መቃብር ውስጥ ያሉትን ሁሉ’ እንደሚያስነሳ የገባውን ቃል ለማረጋገጥም ጭምር ነው። (ዮሐንስ 5:28, 29) አዎን፣ ኢየሱስ በዔደን የተነሳው ዓመጽ ያስከተላቸውን ችግሮች ሁሉ በቅርቡ ምድር ገነት ስትሆን ያስተካክላቸዋል። *1 ዮሐንስ 3:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን ለመቋቋም የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርና የትንሣኤ ተስፋን በሚመለከት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የምትወዱት ሰው ሲሞት የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የመሬት መናወጥ የሕይወቴን አቅጣጫ ቀየረው

በ1971 ግሩም የኦፔራ ድምፃዊት ለመሆን የምመኝ ወጣት እናት ነበርኩ። በ1957 በምወደው የሙዚቀኝነት ሙያ ለመሰማራት እንዲመቸኝ ስል በማኒቶባ፣ ካናዳ የሚገኘውን ዊኒፔግ የተባለውን የተወለድኩበትን ከተማ ለቅቄ በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኘው ሆሊዉድ አቅራቢያ ተዛወርኩ።

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቴ ለዘጠኝ ዓመታት ከካናዳ እየመጣች ትጠይቀኝ ነበር። እናቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛ ለመሆን የሚረዱና ለቤተሰብ ሕይወት የሚጠቅሙ ግሩም ምክሮች እንደሚሰጥ ስለምታምን በመጣች ቁጥር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትነግረኝ ነበር። እናቴን ስለምወዳት የምትነግረኝን በአክብሮት ባዳምጣትም ሕይወቴ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እንደሆነ ይሰማኝ ስለነበር ተመልሳ ስትሄድ የሰጠችኝን ጽሑፎች እጥላቸው ነበር።

ከዚያም የካቲት 1971፣ ማክሰኞ ዕለት ማለዳ ላይ በሬክተር ስኬል ሲለካ 6.6 የደረሰ የመሬት መናወጥ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ጆሮ የሚያደነቁር ኃይለኛ ድምፅና ከፍተኛ መናወጥ ተሰማኝ። በጣም ደንግጬ እየሮጥኩ ወደ ልጄ ሄድኩ፤ አልጋው ላይ በሰላም ተኝቶ ሳገኘው እፎይ አልኩ። ነውጡ ሲቆም ወለሉ በተሰባበሩ መስተዋቶችና ቁም ሣጥኑ ውስጥ በነበሩት ነገሮች ተሸፍኖ ነበር፤ በመዋኛ ገንዳው ውስጥ የነበረው ውኃም ፈስሶ ጓሮውን አጥለቅልቆታል። ቤተሰቤ ደህና ቢሆንም ተመልሼ መተኛት አልቻልኩም።

እናቴ ስለ “መጨረሻው ዘመን” ትነግረኝ የነበረ ሲሆን ከምልክቶቹ አንዱ “ታላቅ የመሬት መናወጥ” እንደሆነም ጠቅሳ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ሉቃስ 21:7-11) በዚያው ዓመት እናቴ እንደተለመደው ልትጠይቀኝ ስትመጣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አላመጣችልኝም። ለዘጠኝ ዓመታት ብትመሠክርልኝም ውጤት ስላላገኘች ምንም ፍላጎት እንደሌለኝ አስባ ነበር። ሆኖም በጣም ተሳስታለች! ከመጣችበት ሰዓት ጀምሮ በጥያቄ አጣደፍኳት። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሙዚቀኛ መሆንና ዝና ማግኘት ብዙም ቦታ የማልሰጣቸው ነገሮች ሆኑ።

በዚያው ሳምንት ከእናቴ ጋር በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኘሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከስብሰባ የቀረሁባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ናቸው። እናቴ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር ዝግጅት አደረገችልኝ። በ1973 የተጠመቅሁ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በመስብኩ ሥራ በየወሩ በአማካይ 70 ሰዓት አሳልፋለሁ። (ማቴዎስ 24:14) አዎን፣ የመሬት መናወጥ በአምላክ ላይ ያለኝ እምነት እንዲጠፋ ከማድረግ ይልቅ እምነት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።—ኮሊን ኤስፓርዛ እንደተናገረችው