በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወሊድ መከላከያ መጠቀም ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል?

የወሊድ መከላከያ መጠቀም ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የወሊድ መከላከያ መጠቀም ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል?

አንተስ ምን ይመስልሃል? ባለትዳሮች የወሊድ መከላከያ ቢጠቀሙ ስህተት ነው? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ በሃይማኖታዊ እምነትህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ላለመውለድ ተብሎ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ “ኃጢአት ነው” ብላ ታስተምራለች። በካቶሊክ ቀኖና መሠረት፣ ባልና ሚስት የጾታ ግንኙነት በሚያደርጉበት ጊዜ ሁሉ ጽንስ እንዳይፈጠር የሚያግድ ምንም ነገር መኖር የለበትም። በመሆኑም አንዳንድ ሃይማኖቶች የወሊድ መከላከያ መጠቀም “ከሥነ ምግባር አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው” ያምናሉ።

በርካታ ሰዎች ይህን አመለካከት መቀበል ይከብዳቸዋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ፒትስበርግ ፖስት ጋዜት እንዲህ ብሏል:- “በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩት ካቶሊኮች ሦስት አራተኛ የሚሆኑት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተፈጥሯዊ ያልሆነ የወሊድ መከላከያ መጠቀምን መፍቀድ እንዳለባት ይናገራሉ። . . . በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በየቀኑ ይህንን እገዳ ይጥሳሉ።” ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው ሊንዳ የተባለች የሦስት ልጆች እናት፣ የእርግዝና መከላከያ እንደምትጠቀም በግልጽ የተናገረች ሲሆን “ኃጢአት እየሠራሁ እንዳለሁ አይሰማኝም” ብላለች።

ስለዚህ ጉዳይ የአምላክ ቃል ምን ይላል?

ሕይወት ውድ ነው

አምላክ የአንድን ሕፃን ሕይወት ገና በተጸነሰ በመጀመሪያዎቹ ወራትም እንኳ ውድ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። . . . ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ።” (መዝሙር 139:13, 16) ሕይወት የሚጀምረው ጽንስ ሲፈጠር ነው፤ የሙሴ ሕግ አንድ ሰው በእናት ማሕፀን ውስጥ ባለ ጽንስ ላይ ጉዳት ካደረሰ ተጠያቂ እንደሚሆን ያሳያል። ዘፀአት 21:22, 23 ሁለት ሰዎች ሲጣሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ወይም በማሕፀኗ ውስጥ ባለው ጽንስ ላይ ለሞት የሚያደርስ ጉዳት ቢያስከትሉ ጉዳዩ በተሾሙ ፈራጆች ፊት መቅረብ እንዳለበት ይገልጻል። ፈራጆቹም ሁኔታውንና ሰዎቹ ጉዳቱን ያደረሱት ሆን ብለው መሆን አለመሆኑን ይገመግማሉ፤ የሚሰጡት ፍርድ “ሕይወት በሕይወት” ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ጽንስን የሚያስወርዱ በመሆናቸው እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከወሊድ መከላከያዎች ጋር በተያያዘም ይሠራሉ። እነዚህን የመሳሰሉ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች ለሕይወት አክብሮት ስለ ማሳየት ከሚናገሩት መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይጋጫሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የእርግዝና መከላከያዎች ጽንስ የሚያስወርዱ አይደሉም። ታዲያ እነዚህን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች መጠቀምን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ክርስቲያኖች እንዲባዙ የሚያዝ ሕግ የለም። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲሁም ለኖኅ ቤተሰብ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” ብሏቸው ነበር። ሆኖም ይህ ትእዛዝ ለክርስቲያኖች አልተሰጣቸውም። (ዘፍጥረት 1:28፤ 9:1) በመሆኑም ባልና ሚስት ልጆች ስለ መውለድም ሆነ ስንት ልጆች እንደሚወልዱ እንዲሁም መቼ መውለድ እንደሚፈልጉ የራሳቸውን ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተመሳሳይም ቅዱሳን መጻሕፍት የእርግዝና መከላከያ መጠቀምን አያወግዙም። እንግዲያው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር አንድ ባልና ሚስት ጽንስን የማያስወርድ የወሊድ መከላከያ ዘዴ መጠቀም አለመጠቀማቸው በግል የሚያደርጉት ውሳኔ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ አንዳንድ ሃይማኖቶች የወሊድ መከላከያ መጠቀምን የሚያወግዙት ለምንድን ነው?

ሰብዓዊ ጥበብ ከመለኮታዊ ጥበብ ጋር ሲነጻጸር

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የኢስጦኢክ ፍልስፍና ሕግጋትን የተቀበሉት በሁለተኛው መቶ ዘመን ሲሆን በዚህ ፍልስፍና መሠረት በጋብቻ ውስጥ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ሕጋዊ ሊሆን የሚችለው ባልና ሚስቱ እንዲህ የሚያደርጉበት ዓላማ ልጆች ለመውለድ ከሆነ ብቻ ነው። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ይህ አመለካከት የተመሠረተው በፍልስፍና እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አይደለም። በመለኮታዊ ጥበብ ሳይሆን በሰብዓዊ ጥበብ ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህ ፍልስፍና ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናትም የቀጠለ ሲሆን የተለያዩ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሑራንም ይህን ሐሳብ አዳብረውታል። * ይህ ትምህርት፣ እርካታ ለማግኘት ብቻ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ኃጢአት ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲስፋፋ አድርጓል፤ በመሆኑም ልጅ የመውለድ አጋጣሚ እንዳይኖር በማድረግ የጾታ ግንኙነት መፈጸም የሥነ ምግባር ብልግና ነው የሚል አመለካከት አለ። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ብለው አያስተምሩም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጸመው የጾታ ግንኙነት የሚያስገኘውን እርካታ እንደሚከተለው በማለት በቅኔያዊ አነጋገር አስቀምጦታል:- “ከገዛ ማጠራቀሚያህ ውሃ፣ ከገዛ ጕድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ። . . . ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። እርሷ እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቋ ናት፤ ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።”—ምሳሌ 5:15, 18, 19

በባልና ሚስት መካከል የሚፈጸመው የጾታ ግንኙነት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ባልና ሚስት የጾታ ግንኙነት ሲፈጽሙ ዓላማቸው ልጅ ለመውለድ ብቻ አይደለም። የጾታ ግንኙነት ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽም ያስችላቸዋል። በመሆኑም አንድ ባልና ሚስት የወሊድ መከላከያ በመጠቀም እርግዝናን ለመከላከል ቢፈልጉ ይህ የራሳቸው ምርጫ ስለሆነ ይህን በማድረጋቸው ማንም ሊኮንናቸው አይገባም።—ሮሜ 14:4, 10-13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ “ሊቀ ጳጳሱ የወሊድ መከላከያ መጠቀምን በመቃወም የደነገጉት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ሕግ” በማለት የጠራውን ደንብ ግሪጎሪ ዘጠነኛ ያወጡት በ13ኛው መቶ ዘመን ነበር።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጸመው የጾታ ግንኙነት ኃጢአት ሊሆን ይችላል?—ምሳሌ 5:15, 18, 19

▪ ክርስቲያኖች የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙ ከሆነ ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?—ዘፀአት 21:22, 23

▪ የእርግዝና መከላከያ የሚጠቀሙ ባልና ሚስትን ሌሎች ሰዎች ምን ሊያደርጓቸው አይገባም?—ሮሜ 14:4, 10-13

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲሁም ለኖኅ ቤተሰብ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” ብሏቸው ነበር። ሆኖም ይህ ትእዛዝ ለክርስቲያኖች አልተሰጣቸውም