በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማራኪ የሆኑት የአፍሪካ ጽጌረዳዎች

ማራኪ የሆኑት የአፍሪካ ጽጌረዳዎች

ማራኪ የሆኑት የአፍሪካ ጽጌረዳዎች

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“እስካሁን ካየኋቸው አበቦች ሁሉ በውበቱ ተወዳዳሪ የለውም!” “ለሚወዱት ጓደኛ የሚሰጥ ምርጥ ስጦታ።” “‘የፍቅርና የአሳቢነት’ መግለጫ።”

እነዚህን ቃላት የተናገሩት በናይሮቢ፣ ኬንያ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ምናልባት አንተም የእነሱን ሐሳብ ትጋራ ይሆናል። በዱር ከሚበቅሉትም ሆነ ሰዎች ከሚተክሏቸው አበቦች መካከል የጽጌረዳን ያህል በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ የሆነ አበባ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የጽጌረዳ አበባ ለዘመናት የሰዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል። ገጣሚዎች ግጥም ጽፈውለታል፤ የሥነ ጥበብ ሰዎች ደግሞ በሥራዎቻቸው ገልጸውታል። ሼክስፒርም ሮሚዮ ኤንድ ጁልዬት በተባለው ታዋቂ የጽሑፍ ሥራው ላይ “ስም ምን ፋይዳ አለው? ጽጌረዳን ምንም ብለን ብንጠራው መዓዛው ምንጊዜም ጣፋጭ ነው” በማለት አሞካሽቶታል። ሰዎች ጽጌረዳ አበባን በመስጠት አዲስ ወዳጅነት ይመሠርታሉ፣ ወዳጅነታቸውን ያጠናክራሉ፣ የሻከረ ግንኙነታቸውን ያድሳሉ እንዲሁም የታመሙ ሰዎችን ያጽናናሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ጽጌረዳ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው። ለአበባ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጠባይ ላላቸው አገሮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ኬንያ በቅርቡ ወደ ውጭ ከላከቻቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ አበቦች መካከል 70 በመቶ የሚሆነው ጽጌረዳ ነው። ይህም አገሪቱ በዓለም ላይ ካሉ ዋነኛ የጽጌረዳ አምራች አገሮች ጎን እንድትሰለፍ አድርጓታል።

ጥንት፣ ሰዎች የጽጌረዳን ማራኪነት ከማስተዋላቸው በፊት ይህ አበባ በየጫካው እንደልብ ይገኝ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን በጥንቃቄ በሚካሄድ የማዳቀል ዘዴ አማካኝነት ከ100 የሚበልጡ የጫካ ዝርያዎችን እርስ በርስ በማዳቀል በሺህ የሚቆጠሩ የጽጌረዳ ዓይነቶችን ማግኘት ተችሏል። በዚህም ምክንያት ይህ አበባ በዓለም ዙሪያ የታወቀ ሲሆን በየትኛውም አገር ይገኛል። ከእነዚህ መካከል በሰፊው የሚመረተውና በብዙዎች ዘንድ የሚወደደው ሃይብሪድ ቲ ሮዝ የተባለው ዝርያ ነው።

ከእርሻ ቦታ ቤትህ እስኪገባ ያለው ሂደት

ብዙ ሰዎች ጽጌረዳ የሚገዙት ከአበባ መሸጫ ሱቅ ወይም ከሱፐርማርኬት ነው። እነዚህ አበቦች በትላልቅ የእርሻ ቦታዎች ላይ ለንግድ ዓላማ ሲባል የሚለሙ ሲሆን ሰዎች በጓሯቸው ከሚተክሏቸው ሌሎች አበቦች የበለጠ ጥንቃቄ ይሻሉ። በናይሮቢ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የአበባ እርሻ ያደረግነው ጉብኝት አበባ ለገበያ እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ የሚደረግለትን ከፍተኛ ጥንቃቄ አስገንዝቦናል።

በኬንያ ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ሌሎቹ የአበባ እርሻዎች ሁሉ በዚህም ቦታ ላይ የሚገኙት ሰፋፊ የፕላስቲክ ዳሶች (ግሪን ሐውስ) ቦታው የአበባ እርሻ መሆኑን ይጠቁማሉ። (በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን ፎቶ ተመልከት።) ይህ ትልቅ ዳስ በርካታ አገልግሎት ይሰጣል። አዲስ የተዳቀሉት ጽጌረዳዎች ችግር መቋቋም ስለማይችሉ ከመጥፎ አየር ከለላ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ከባድ ዝናብና ነፋስ ሲያገኛቸው ወይም የፀሐይ ብርሃን በቀጥታ ሲያርፍባቸው ለከፍተኛ ጉዳት ይዳረጋሉ። ዳሱ ቋሚ የሆነ የሙቀት መጠን እንዲኖረው ቀዝቃዛ አየር በቀላሉ እንዲገባና የሞቀው አየር እንዲወጣ መደረግ አለበት።

በዚህ ዳስ ውስጥ በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አበቦች በመደዳ ተተክለው ይታያሉ። በእርሻው ውስጥ ከ70 ሴንቲ ሜትር ትንሽ ከፍ ሲል ከሚቆረጠው ሃይብሪድ ቲ ሮዝ ከሚባለው ጽጌረዳ አንስቶ 35 ሴንቲ ሜትር ላይ ሲደርስ እስከሚቆረጠው ስዊትሃርት የተባለ ጽጌረዳ ድረስ የተለያዩ የጽጌረዳ ዓይነቶች ይለማሉ። ስዊትሃርትም የሃይብሪድ ቲ ሮዝ ዝርያ ነው። አንድ ሄክታር መሬት እስከ 70,000 አበቦች ሊያበቅል ይችላል።

አበቦቹ ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ነገር የሚያገኙት እንዴት ነው? አበቦቹ የሚተከሉት በማንኛውም ዓይነት አፈር ላይ አይደለም። የአበባ መትከያው መደብ የሚዘጋጀው ከእሳተ ገሞራ በተገኘ አሸዋማ አፈር ሲሆን ከመደቡ ሥርም ሰፊ ፕላስቲክ ይነጠፋል። የእሳተ ገሞራው አፈር ከማንኛውም ዓይነት አፈር ወለድ በሽታ የጸዳ በመሆኑ እንዲህ ያለው ዘዴ በጣም ጠቃሚ ነው። ተክሎቹ ውኃ የሚጠጡት ድሪፕ ኢሪጌሽን በተባለ ዘዴ ነው። በዚህ ዘዴ አማካኝነት ትናንሽ የፕላስቲክ ቱቦዎች በመደቡ ላይ ተዘርግተው አበቦቹ ውኃም ሆነ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች በተፈለገው መጠን እንዲደርሳቸው ይደረጋል። አሸዋማው አፈር ውኃ የማስረግ ባሕርይ ስላለው ከተክሎቹ የተረፈው ውኃ ከሥር ከተነጠፈው ፕላስቲክ ላይ እየተንጠፈጠፈ ይወርዳል። ከዚያም ውኃው ተጠራቅሞ እንደገና ጥቅም ላይ ይውላል።

ምንም እንኳ ጽጌረዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግለትም በበርካታ በሽታዎች በተለይም በፈንገሶች ሊጠቃ ይችላል። ከእነዚህ መካከል የተክሉን ቅጠልና ግንድ የሚያጠቁት ቦትራይተስ የተባሉት ፈንገሶችና ሻጋታዎች ይገኙበታል። ክትትል ካልተደረገ በስተቀር እነዚህ በሽታዎች የአበባውን ጥራት በእጅጉ ሊቀንሱት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ፀረ ፈንገስ የሆኑ መድኃኒቶችን በመጠቀም ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል።

በጊዜ ሂደት በጽጌረዳው ላይ ደማቅ የሆኑ ቀለማት መታየት ይጀምራሉ። ይህም ጽጌረዳው የሚሰበሰብበት ጊዜ መድረሱን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በዚህ ጊዜ አበባው ገና እምቡጥ እያለ ማለትም ገና ሳይፈነዳ በጥንቃቄ ይቆረጣል። አበባው በዚህ ደረጃ ላይ መቆረጡ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ ቀለሙን ጠብቆ እንዲቆይ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ የሚቆረጥበት ጊዜ ከአበባ አበባ ይለያያል። አበባውን ከፍተኛ እርጥበት በሚኖርበትና የመጠውለጉ አጋጣሚ በሚቀንስበት ጊዜ ላይ ይኸውም ማለዳ ወይም ምሽት ላይ መቁረጡ በጣም የተሻለ ነው። ከዚያም የተቆረጠው አበባ ቀዝቃዛ ወደሆነ ክፍል ይወሰዳል። ይህም ሳይጠወልግ ረጅም ጊዜ እንዲቆይ ይረዳዋል።

ከዚህ በኋላ አበባው አንድ ወሳኝ ደረጃ ይጠብቀዋል። በዚህ ደረጃ ላይ አበባው በቀለምና በመጠን ተለይቶ ይቀመጣል። ቀጥሎ ደንበኞች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የማሸጉ ሥራ ይከናወናል። በመጨረሻ አበባው ለገበያ ዝግጁ ይሆናል። የአበባ እርሻው ከሚገኝበት ቦታ ወደ ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊያ ይጓጓዝና በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኙት የአውሮፓ ከተሞች ይላካል። አበቦች ቶሎ የሚበላሹ እንደመሆናቸው መጠን ከተቆረጡበት ጊዜ አንስቶ በ24 ሰዓት ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ወደሚገኘው መሸጫ ቦታቸው መድረስ አለባቸው።

ወደፊት እቅፍ አበባ ስጦታ ቢሰጥህ ወይም ከሱፐርማርኬት አሊያም ከአበባ መሸጫ ሱቅ ብትገዛ የዚህ ማራኪ አበባ ፈጣሪ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ትንሽ ቆም ብለህ አስብ። ለእሱ ያለህን አድናቆት እንደሚያሳድግልህ ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 115:15

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ሰማያዊ ጽጌረዳ ይኖር ይሆን?

ጽጌረዳ ብዙ ለውጥ አድርጓል። ለውጡ አሁንም ያቆመ አይመስልም። ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በርካታ አዳዲስ የማዳቀያና አበባን የማልማት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። የጽጌረዳን ያህል የተለያየ ቀለም ያላቸው አበቦች በጣም ጥቂት ናቸው። አንተን በጣም የሚማርክህ የጽጌረዳ ዓይነት የትኛው ነው? ነጭ፣ ቢጫ፣ ሐምራዊ፣ ደማቅ ቀይ ወይስ ወይን ጠጅ? ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በማዳቀል ጥበብ የተገኙ ናቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ስለ “ቀይ” ጽጌረዳ ሲናገሩ ሰምተህ ይሆናል። ይሁንና እውነተኛው ቀይ ጽጌረዳ በተፈጥሮ እንዳልነበረ ታውቃለህ? የጽጌረዳ ዝርያዎች ቀይ ቀለም የሚያስገኘው ጂን የላቸውም። ደማቅ ቀይ ቀለም የተገኘው በ1930 በጄኔቲክ ሚውቴሽን አማካኝነት ሲሆን ይህ ግኝት ዛሬ ለምናያቸው ቀይ ጽጌረዳዎች መሠረት ሆኗል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜያት ሰማያዊ የጽጌረዳ ዓይነት አልነበረም። የጽጌረዳ አበባ ዝርያዎች በተፈጥሯቸው ሰማያዊ ቀለም የሚያስገኘው ዴልፊኒዲን የተባለው ጂን የላቸውም። ይሁን እንጂ የአውስትራሊያና የጃፓን ኩባንያዎች ለዓመታት ባደረጉት ምርምር በ2004 “ሰማያዊ” ጽጌረዳ ማግኘት ችለዋል። ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ለማግኘት ደግሞ ተጨማሪ ጥረት በመደረግ ላይ ነው።

[ሥዕል]

ከፕላስቲክ የተሠራው ዳስ (ግሪን ሐውስ)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመሰብሰብ የደረሰ አበባ