በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስንሞት ምን እንሆናለን?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

አምላክ የሰው ልጆች እንዲሞቱ ዓላማ አልነበረውም። (ሮሜ 8:20, 21) እንዲያውም ይሖዋ፣ ለአዳም ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ሞት የነገረው፣ ለሰው ልጅ የማይቀርለት የመጨረሻ ውጤት እንደሆነ አድርጎ ሳይሆን አምላክን ባለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት መሆኑን ነው። (ዘፍጥረት 2:17) አዳም እንስሳት ሲሞቱ ያይ ስለነበር ሞት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያውቃል።

ከጊዜ በኋላ አዳም ኃጢአት ሠራ፤ በዚህም የተነሳ በ930 ዓመቱ በመሞት የሠራው ኃጢአት ያስከተለበትን ውጤት አጭዷል። (ዘፍጥረት 5:5፤ ሮሜ 6:23) አዳም ባለመታዘዙ ከአምላክ ቤተሰብ ስለተባረረ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ መታየቱ ቀረ። (ዘዳግም 32:5) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሁኔታ በሰው ዘር ላይ ስላስከተለው አሳዛኝ ውጤት ሲናገር “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ” ይላል።—ሮሜ 5:12

ስንሞት የማሰብ ችሎታችን ምን ይሆናል?

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው፤ አንዱ እንደሚሞት፣ ሌላውም እንዲሁ ይሞታል። ሁሉ አንድ ዐይነት እስትንፋስ አላቸው፤ ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነው። ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ሁሉም ከዐፈር እንደ ሆኑ፣ ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ።” (መክብብ 3:19, 20) ተመልሰው ወደ አፈር ይሄዳሉ ሲባል ምን ማለት ነው?

“ተመልሰው ወደ አፈር ይሄዳሉ” የሚለው አገላለጽ አምላክ ለመጀመሪያው ሰው “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” በማለት የነገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (ዘፍጥረት 3:19) ይህ ሲባል ሰዎችም ልክ እንደ እንስሳት ሥጋ የለበሱ ፍጥረታት ናቸው ማለት ነው። ሰዎች ስንባል ሥጋዊ አካል የለበስን መንፈሳዊ ፍጥረታት አይደለንም። አካላችን ሲጠፋ የማሰብ ችሎታችንም አብሮ ይጠፋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሟች የሆኑ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር “መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” ይላል።—መዝሙር 146:4

ስንሞት እንዲህ የምንሆን ከሆነ ሙታን የሚገኙበት ሁኔታስ ምን ይመስላል? የአምላክ ቃል “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጣል። (መክብብ 9:5) ሞት፣ ወደተሻለ ሕይወት እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ የሚቀበል ጓደኛ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ስለሚገታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የመጨረሻው ጠላት” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:26፤ መክብብ 9:10) ይህ ሲባል ግን የሞቱ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው?

ሞትን አስመልክቶ የተነገረ ምሥራች

ሞት በእንቅልፍ ስለተመሰለ ሞተው የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚነቁበት ጊዜ ይመጣል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ በሞት የተለያቸውን ወዳጃቸውን አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ፣ አልዓዛር ወደተቀበረበት መቃብር እየተጓዘ ሳለ ተሰብስበው የሚያለቅሱ ሰዎችን ተመለከተ። እዚያ ሲደርስ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ እንዲከፍቱት ካደረገ በኋላ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ተጣራ። ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረው ሰው ከመቃብሩ ወጣ። (ዮሐንስ 11:11-14, 39, 43, 44) የአልዓዛር አካል መበስበስ ጀምሮ ስለነበር ኢየሱስ ይህን ተአምር በመፈጸም አምላክ የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ እያንዳንዱን ነገር ማለትም ስብዕናቸውን፣ ትዝታቸውንና አካላዊ ገጽታቸውን ሁሉ ማስታወስ እንደሚችል አረጋግጧል። አምላክ እንደገና በሕይወት እንዲኖሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። በአንድ ሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29

መጽሐፍ ቅዱስ “የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው” በማለት ተጨማሪ ምሥራች ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) በሐዘን የተደቆሱ ሰዎች የሚወዱትን ሰው ለመቅበር ዳግመኛ ወደ መካነ መቃብር አይሄዱም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” ይላል። (ራእይ 21:4) ታዲያ በምንሞትበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ሐሳብ የሚያጽናና ነው ቢባል አትስማማም?

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ሙታን የሚያውቁት ነገር አለ?—መክብብ 9:5

▪ የሞቱ ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ነው?—ዮሐንስ 5:28, 29

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” —መዝሙር 146:4