በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሻርኮች የሚገኙበት አስጊ ሁኔታ

ሻርኮች የሚገኙበት አስጊ ሁኔታ

ሻርኮች የሚገኙበት አስጊ ሁኔታ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከሻርኮች ይበልጥ የሚያስፈሩ እንስሳት ቢኖሩ ጥቂት ናቸው። በመላው ዓለም ሻርኮች በአማካይ በየዓመቱ 75 ሰዎችን ማንም ሳይነካቸው እንደሚያጠቁ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች መካከል 10 ያህሉ ይሞታሉ። እነዚህ ክስተቶች በሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቁ መሆኑ እንዲሁም ስለ እነዚህ እንስሳት መጥፎ አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርጉ ፊልሞች መሠራታቸው ሻርኮች ሰው በሊታ እንደሆኑ ተደርገው እንዲታዩ አድርጓል። እርግጥ ነው፣ ከሻርኮች ጋር ያለን ግንኙነት ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ ሁኔታውን በትክክል ስንገመግመው፣ ሻርኮች በሚሰነዝሩት ጥቃት ከሚሞቱት ሰዎች ይልቅ በንቦች ተነድፈውና በአዞዎች ተበልተው የሚሞቱት ሰዎች ይበዛሉ።

በሌላ በኩል ግን ሻርኮች በሰው ልጆች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። አርገስ ማሪነር ኮንሳልቲንግ ሳይንቲስትስ በተባለ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ አንድ ተመራማሪ ፕሪሚየር በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በየዓመቱ 100 ሚሊዮን የሚሆኑ ሻርኮች የሚያዙ ሲሆን እነዚህ ሻርኮች እርስ በርስ ቢቀጣጠሉ ምድርን አምስት ዙር ይከቧታል።” በዚህ መንገድ በሻርኮች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት በተጨማሪ እነዚህ እንስሳት በተፈጥሯቸው ብዙ አለመውለዳቸው፣ ለመዋለድ ወደሚችሉበት ዕድሜ የሚደርሱት ዘግይተው መሆኑ፣ የእርግዝና ወራታቸው ረዥም መሆኑ እንዲሁም የሚወልዱባቸው አካባቢዎች መበከላቸው ቁጥራቸው በፍጥነት እንዲያሽቆለቁል አድርጓል። ቁጥራቸው በጣም ከቀነሰ ደግሞ ወደ ቀድሞ ብዛታቸው ለመመለስ ዓመታት ይፈጅባቸዋል።

አብዛኞቹ ሻርኮች የሚያዙት ለክንፋቸው ሲባል ነው፤ አንዳንድ እስያውያን የሻርክ ክንፍ ለመድኃኒትነትና የጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ ይረዳል የሚል እምነት ስላላቸው ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። * ከሻርክ ክንፍ የተሠራ አንድ ሳህን ሾርባ እስከ 150 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የቅንጦት ምግብ ነው! ይህ አትራፊ የእስያ ገበያ የሚያስፈልገውን ምርት ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት፣ ሻርክን ከነሕይወቱ ይዞ ክንፎቹን ከቆረጡ በኋላ በረሀብ ወይም ሰምጦ እንዲሞት መልሶ ወደ ውቅያኖሱ መጣልን የመሰለ ጭካኔ የተሞላበትና ብክነት የሚንጸባረቅበት ተግባር ወደመፈጸም አምርቷል።

ሻርኮችን ለመታደግ አንድ ነገር መደረግ አለበት

ሻርኮች የሚገኙበት አሳዛኝ ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል? ለዝሆኖች ወይም ለዌል ዝርያዎች የምናዝነውን ያህል ለሻርኮች ማዘን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሻርኮች የውቅያኖስን ሥነ ምህዳራዊ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የሚጫወቱትን ጠቃሚ ሚና መገንዘብ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ አመጋገባቸው በአሁኑ ጊዜ ሌሎቹ የዓሣ ዝርያዎች ከልክ በላይ እንዳይበዙ ለመቆጣጠር ይረዳል።

በብዙ አገሮች ሻርኮችን ስለ ማጥመድ የወጣ ሕግ የለም። ሻርኮች በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠመዱባቸው አገሮች አንዷ በሆነችው በሜክሲኮ በየዓመቱ ከ300,000 ኩንታል በላይ የሚመዝኑ ሻርኮች የሚያዙ ሲሆን በዚህች አገር ውስጥ አሥር ዓመት ከፈጀ ክርክር በኋላ የሻርኮችን ክንፍ ከቆረጡ በኋላ ሻርኮቹን ወደ ባሕር መጣልን የሚከለክል ሕግ ወጥቷል። የሻርኮች ቁጥር እንዳይመናመን የሚደረገውን ጥረት ከባድ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ፣ የሻርክ ክንፍ ተፈላጊነት በመጨመሩ የተነሳ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ ዓሣ ማጥመድ በተከለከለባቸው የውኃ አካሎች ውስጥ ሕገ ወጥ የዓሣ ማጥመድ ሥራ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የጋላፓጎስ ብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት ዲሬክተር እንደሚከተለው በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል:- “ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በጋላፓጎስ የሻርክ ክንፍ ለማግኘት ተብሎ የሚደረገው ሕገ ወጥ የማጥመድ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ንግዱ በጣም አትራፊ መሆኑ እዚህ ቦታ የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን እንዲፈጠር አድርጓል።”

ሻርኮችን ለመታደግ ሲባል አበረታች የሆነ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን ይኸውም የሻርኮችን ክንፍ መቁረጥ በአንዳንድ አገሮች እየታገደ ነው። ይሁን እንጂ የዓለም የዱር አራዊት ድርጅት የፖሊሲ ባለ ሥልጣን የሆኑት ሻርሎት ሞጌንሰን ከዚህ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ ሲያሳስቡ እንዲህ ብለዋል:- “ሻርኮች በመላው ዓለም በአደጋ ላይ ይገኛሉ። ዓሣ በማጥመድ ሥራ የተሠማሩ ድርጅቶች በሙሉ የሻርክ ክንፎችን መቁረጥን የሚከለክለውን ሕግ ብቻ ሳይሆን ሻርኮችን የሚመለከት መረጃ ማሰባሰብን፣ በስህተት የሚያዙ ሻርኮችን ቁጥር መቀነስንና የሻርኮች ቁጥር እንዲመናመን በማያደርግ መልኩ ማጥመድን በተመለከተ የወጡትን መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።”

ደስ የሚለው ነገር ግን እንስሳትን የፈጠረው አምላክ አስደናቂ በሆነው የፍጥረት ሥራው ላይ የሚደርሰው ገደብ የለሽ ጭፍጨፋ በቅርቡ እንዲያበቃ ያደርጋል። ከፍጥረታቱ መካከልም አስፈሪ ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሆነው ሻርክ አንዱ ነው።—ራእይ 11:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 የሚገርመው ነገር የሻርክ ክንፎች ከፍተኛ የሜርኩሪ ክምችት እንዳላቸው የተደረሰበት ሲሆን ይህም በወንዶች ላይ መካንነትን ሊያስከትል ይችላል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ስለ ሻርክ የሚገልጹ መረጃዎች

መጠን:- ከሻርኮች መካከል በጣም ግዙፍ የሆነው ዌል ሻርክ የሚባለው ዝርያ (ከላይ የሚታየው) ቁመቱ 18 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ብዙ ኩንታል ይመዝናል። ይሁን እንጂ ይህ ዝርያ የሚመገበው የውኃ ውስጥ ደቃቅ እፅዋትንና ትንንሽ ዓሦችን ሲሆን በሰዎች ላይ ጉዳት አያደርስም።

የእርግዝና ወራት:- ሻርኮች የሚወልዱት እስከ 22 ወራት ከሚደርስ የእርግዝና ጊዜ በኋላ ነው።

የመዋለድ ፍጥነት:- ሻርኮች በአንድ ጊዜ በአማካይ ከሁለት እስከ አሥር የሚደርሱ ጨቅላዎችን ይወልዳሉ። ብዙዎቹ ዝርያዎች በሕይወት ያሉ ጨቅላዎችን ሲወልዱ አንዳንዶቹ ግን እንቁላሎችን ይጥላሉ።

የሚያድጉበት ፍጥነት:- አብዛኞቹ ለመዋለድ ወደሚያስችላቸው ዕድሜ የሚደርሱት ከ12 እስከ 15 ዓመት በኋላ ነው።

የዕድሜ ርዝማኔ:- የብዙዎቹን የሻርክ ዝርያዎች የዕድሜ ርዝማኔ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፤ ይሁን እንጂ በኃይለኛነቱ የሚታወቀው ግዙፉ ነጭ ሻርክ (ከታች የሚታየው) እስከ 60 ዓመት እንደሚኖር ይገመታል።

[ምንጮች]

Seawatch.org

© Kelvin Aitken/age fotostock

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ካሉት ከ300 የሚበልጡ የሻርክ ዝርያዎች መካከል 62ቱ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል

[ምንጭ]

© Mark Strickland/SeaPics.com

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግማሽ ኪሎ ግራም የማይሞላ የሻርክ ክንፍ በ200 የአሜሪካ ዶላር ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ዋጋ ሊሸጥ ይችላል። የግዙፉ ነጭ ሻርክ መንገጭላዎች እስከ 10,000 የአሜሪካ ዶላር ሊያወጡ ይችላሉ

[ምንጭ]

© Ron & Valerie Taylor/SeaPics.com