በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የምድር ከባቢ አየር ሙቀት መጨመሩ “አሌ የማይባል ሐቅ” ሲሆን ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ሰው መሆኑ “እሙን ነው።”—ኢንተርገቨርንመንታል ፓነል ኦን ክላይሜት ቼንጅ (IPCC)፣ ስዊዘርላንድ

ጀርመን ውስጥ ከ1.4 እስከ 1.9 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች “የመድኃኒት ሱሰኞች” ናቸው። የሁኔታው አሳሳቢነት የአልኮል ሱሰኝነት እያስከተለ ካለው ችግር ጋር የሚወዳደር ነው።—ታጋሳቹ፣ ጀርመን

በብሪታንያ ከሁሉም የዕድሜ ክልል ይበልጥ ለግድያ የተጋለጡት ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ናቸው። —ዘ ታይምስ፣ ብሪታንያ

በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ መካከል ያለው ድንበር የተወሰነ ክፍል በቁጥቋጦና በዛፎች ስለተዋጠ ባለ ሥልጣናቱ “ድንበሩን መለየት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።” የዓለም አቀፍ የድንበር ኮሚሽን ባልደረባ የሆኑት ዴኒስ ሾርናክ “ድንበሩን ለይታችሁ ልታውቁት ካልቻላችሁ ልታስከብሩት አትችሉም” ብለዋል።—አሶሼትድ ፕሬስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ሰውነት ራሱን እንዲፈውስ ሆኖ ተሠርቷል

“የሰው ሰውነት ከ60 እስከ 70 በመቶ ከሚሆኑት ሕመሞች ያለ ምንም እርዳታ ራሱን መፈወስ ይችላል” በማለት በጀርመን ኤሰን ከተማ በሚገኝ የማዕድን ቁፋሮ ሠራተኞች ሆስፒታል ውስጥ ዋና አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጉስታቭ ዶቦስ ይናገራሉ። ሰውነት ራሱን ለማከም ሲል ኮርቲዞንና የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር የሚከለክሉ ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ ከ30 እስከ 40 የሚያህሉ መድኃኒቶችን እንደሚያመርት ይታመናልተመራማሪዎች ሰውነት ራሱን በሚያክምበት ጊዜ የሚከናወኑትን አንዳንድ ሂደቶች መረዳት የቻሉ ቢሆንም አብዛኛውን ግን ገና አላወቁትም። የሳይንስ ሊቃውንት “ሆርሞኖች እንዲሁም በሽታ ተከላካይና ገዳይ ሴሎች ውስብስብ በሆነ መንገድ ተባብረው የሚሠሩበት ሁኔታ እንዳለ” እንዲሁም “የስሜት መለዋወጥም [moods] የራሱ ድርሻ እንዳለው” ማስተዋላቸውን ቪታል የተሰኘው መጽሔት ይናገራል። ይሁን እንጂ ውጥረትና የግል ችግሮች የአንድን ሰው “በሽታ የመከላከል አቅም በጊዜ ሂደት ሊያዳክሙት” እንደሚችሉ መጽሔቱ ጨምሮ ይናገራል።

ዓለም አቀፍ የሀብት ክፍፍል

“በፕላኔታችን ላይ ካለው ሀብት 40 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከዓለም ሕዝብ ውስጥ አንድ በመቶ በሚሆኑት ሀብታም ሰዎች እጅ ነው” ሲል የለንደኑ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል። “እጅግ በጣም ሀብታም ከሆኑት ግለሰቦች መካከል አብዛኞቹ ከገንዘብ ጋር በተያያዙ አገልግሎት መስጫዎችና በኢንተርኔት አማካኝነት በሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ ናቸው” በማለት ጋዜጣው ይናገራል። የተባበሩት መንግሥታት ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው እጅግ ሀብታም ከሆኑት ግለሰቦች መካከል 37 በመቶ የሚሆኑት በዩናይትድ ስቴትስ፣ 27 በመቶ የሚሆኑት በጃፓን እንዲሁም 6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በብሪታንያ የሚኖሩ ናቸው። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎች ከምድር ሀብት ውስጥ የሚደርሳቸው ከአንድ በመቶ ያነሰው ነው። በብሪታንያ ኦክስፋም የሚባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያደርገውን ጥናት በበላይነት የሚቆጣጠሩት ዱንካን ግሪን እንደሚከተለው ብለዋል:- “ይህን ያህል የሀብት መበላለጥ መኖሩ የሚያሰቅቅ ነው። . . . 800 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ጦማቸውን እያደሩ በጣም ጥቂት ሰዎች ይህን ያህል ሀብት ማከማቸታቸው ትክክል ነው ሊባል የሚቻልበት መንገድ የለም።”

በቻይና የወንዶችና የሴቶች ቁጥር አለመመጣጠን

በ2005 በቻይና አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ፆታ ሬሾ 118 ወንዶች ለ100 ሴቶች ነው። በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች “ቁጥሩ 130 ወንዶች ለ100 ሴቶች ደርሷል” በማለት ቻይና ዴይሊ የተሰኘው ጋዜጣ ይዘግባል። ለዚህ የወንዶችና የሴቶች ቁጥር አለመመጣጠን ምክንያት የሆነው የሽልን ፆታ ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ከተደረገ በኋላ በሴቶቹ ላይ የሚፈጸመው ውርጃ ነው። ይህ ክስተት በከተማ ውስጥ የሚኖሩት አብዛኞቹ ባልና ሚስት ከአንድ ልጅ በላይ እንዳይወልዱ ከሚያስገድደው ከቻይና የቤተሰብ ምጣኔ ፖሊሲ ጋር የተዛመደ መሆኑን ባለ ሥልጣናቱ ያምናሉ። ጋዜጣው “በ2020 ከሴቶቹ ቁጥር በ30 ሚሊዮን የሚበልጡ ለአቅመ አዳም የደረሱ ወንዶች ይኖራሉ” የሚል ሐሳብ ያሰፈረ ሲሆን ይህ አለመመጣጠን ደግሞ “ማህበራዊ ቀውስ ይፈጥራል” ብሏል።