በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ወላጆቼ ሲጨቃጨቁ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረው ጭቅጭቅ በአንተ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ደግሞም ወላጆችህን ስለምትወዳቸውና የሚያስፈልጉህን ነገሮች የሚያሟሉልህ እነሱ ስለሆኑ እርስ በርስ ተስማምተው መኖር እንዳቃታቸው በሚሰማህ ጊዜ በጣም ብትጨነቅ አያስደንቅም። አንዳንድ ጊዜ ወላጆችህ ፈጽሞ መጣጣም የማይችሉ የሚመስለው ለምንድን ነው?

የአመለካከት ልዩነቶች

ኢየሱስ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ “አንድ ሥጋ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:5) ይህ ሲባል ግን አባትህና እናትህ ሁልጊዜ ስለተለያዩ ነገሮች አንድ ዓይነት አመለካከት ይኖራቸዋል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። በሁለት ሰዎች፣ አንድነት ባላቸው ባልና ሚስት መካከልም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ነው።

በወላጆችህ መካከል የአመለካከት ልዩነት ስላለ ብቻ ትዳራቸው አበቃለት ማለት አይደለም። ምንም እንኳ አልፎ አልፎ አንዳቸው ሌላውን የሚያበሳጭ ነገር ቢያደርጉም አሁንም ይዋደዳሉ። ታዲያ የሚጨቃጨቁት ለምንድን ነው? ይህ የሚሆነው ምናልባት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው አመለካከት ስለሚለያይ ነው። ይህ ደግሞ ሁልጊዜ ስህተት አሊያም ትዳራቸው እንደሚፈርስ የሚጠቁም ምልክት ነው ማለት አይደለም።

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ከቅርብ ጓደኞችህ ጋር ፊልም ተመልክታችሁ አንተ ስለ ፊልሙ ያደረብህ አመለካከት ከጓደኞችህ አመለካከት ተለይቶብህ አያውቅም? ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። በጣም የሚቀራረቡ ሰዎችም እንኳ ነገሮችን የሚመለከቱበት አቅጣጫ ሊለያይ ይችላል።

በወላጆችህ መካከል የሚፈጠረው ሁኔታም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ሁለቱም የቤተሰቡ የገቢ ሁኔታ ያሳስባቸው ይሆናል፤ ሆኖም የገንዘብ አወጣጥን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ሊለያይ ይችላል። ሁለቱም በቤተሰብ ደረጃ የሚዝናኑበትን ዝግጅት ማድረግ ይፈልጉ ይሆናል፤ ይሁንና እያንዳንዳቸው ስለ መዝናኛ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ሁለቱም አንተ በትምህርትህ ተሳክቶልህ ለማየት ይጓጉ ይሆናል፤ ሆኖም ለአንተ ማበረታቻ የሚሰጡበት መንገድ በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሁለት ሰዎች አንድ ናቸው ሲባል በሁሉም ነገር ፍጹም ተመሳሳይነት አላቸው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። በጋብቻ ተቆራኝተው ‘አንድ ሥጋ የሆኑ’ ሁለት ሰዎች እንኳ ነገሮችን የሚመለከቱበት አቅጣጫ ሊለያይ ይችላል።

ይሁንና አልፎ አልፎ በወላጆችህ መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቶ እስከ መጨቃጨቅ የሚያደርሳቸው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ሌላኛው ወገን በቅንነት የተናገረው ሐሳብ ውይይቱ ወደ ከፍተኛ ጭቅጭቅ እንዲያመራ የሚያደርገውስ ለምን ይሆን?

አለፍጽምና ያለው ድርሻ

በወላጆች መካከል የሚነሱት አብዛኞቹ አለመግባባቶች በአለፍጽምና ምክንያት የሚመጡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም በብዙ ነገር እንሰናከላለን፤ በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ . . . ፍጹም ሰው ነው” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 3:2) አንተም ሆንክ ወላጆችህ ፍጹማን አይደላችሁም። አንዳንዴ ሁላችንም ለማለት ያልፈለግነውን ነገር የምንናገር ሲሆን አልፎ አልፎም ቃላቶቻችን ‘እንደሚወጋ ሰይፍ’ ሌሎችን ሊጎዱ ይችላሉ።—ምሳሌ 12:18

ምናልባት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ከምትቀርበው ሰው ጋር የተጋጫችሁበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። ማሪ * የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “የማይጋጭ ሰው የለም። እንዲያውም በጣም የሚያበሳጭ ነገር የሚያደርጉብኝ በጣም የምወዳቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባትም ይህ የሚሆነው ከእነሱ ብዙ ስለምጠብቅ ይሆናል!” ክርስቲያን ባልና ሚስቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ከፍተኛ መሥፈርቶች ስለተማሩ አንዳቸው ከሌላው ብዙ ቢጠብቁ አያስገርምም። (ኤፌሶን 5:24, 25) ሆኖም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ስለሆኑ ሁለቱም መሳሳታቸው አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል።—ሮሜ 3:23፤ 5:12

በመሆኑም በወላጆችህ መካከል ለተወሰነ ጊዜ ውጥረት ቢፈጠር የሚያስደንቅ አይደለም። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ያገቡ ሰዎች “ብዙ ችግር” ወይም ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እንደተረጎመው “መከራና ሐዘን” እንደሚገጥማቸው ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ጨቅጫቃ አለቃ፣ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲሁም የመብራት፣ የውኃ ወይም የስልክ ሒሳብ ድንገት ማሻቀብ በቤት ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ወላጆችህ ፍጹም አለመሆናቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚገቡበት ጊዜ መኖሩን መገንዘብህ በመካከላቸው ለሚፈጠረው አለመግባባት ሚዛናዊ አመለካከት እንድትይዝ ይረዳሃል። ማሪ ያስተዋለችውም ይህንኑ ነው። እንዲህ ብላለች:- “በወላጆቼ መካከል የሚፈጠረው ጭቅጭቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የመጣ ይመስለኛል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ‘ተሰለቻችተው ይሆን?’ ብዬ አስባለሁ። ይሁን እንጂ ቆም ብዬ አስብና ‘በትዳር ዓለም ለ25 ዓመት መቆየትና አምስት ልጆችን ማሳደግ እኮ እንዲህ ቀላል አይደለም!’ ብዬ ራሴን አሳምነዋለሁ።” ምናልባት አንተም ወላጆችህ ያሉባቸውን ተደራራቢ ኃላፊነቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ‘የእነሱ መከራ የአንተ እንደሆነ አድርገህ’ ማሰብ ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 3:8 የ1954 ትርጉም

ችግሩን እንዴት መቋቋም ይቻላል?

ወላጆችህ ፍጹማን አለመሆናቸውንና በየቀኑም የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው መቀበል አይቸግርህ ይሆናል። ያም ሆኖ ‘በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ምን ማድረግ እችላለሁ?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስብህ ይሆናል። እስቲ ቀጥሎ የተገለጹትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር:-

ጣልቃ አትግባ። (ምሳሌ 26:17) ትዳርን በተመለከተ ለወላጆችህ ምክር መስጠት ወይም በወላጆችህ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት የአንተ ኃላፊነት አይደለም። እንዲያውም በአለመግባባቱ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገው የትኛውም ሙከራ የተገላቢጦሽ ውጤት ሊኖረው ይችላል። የ18 ዓመቷ ሻርሊን “ከዚህ በፊት በወላጆቼ መካከል ጣልቃ ገብቼ ለመዳኘት ሞክሬ ነበር፤ እንዲህ ሳደርግ ብዙውን ጊዜ ወላጆቼ እኔን ምንም እንደማያገባኝ ይነግሩኛል” በማለት ተናግራለች። የተፈጠረውን ችግር ወላጆችህ እንዲፈቱት ተውላቸው።

ነገሮችን በሚዛናዊነት ተመልከት። (ቈላስይስ 3:13) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በወላጆችህ መካከል ጭቅጭቅ የማይጠፋ መሆኑ ትዳራቸው በቋፍ ላይ ነው ያለው ማለት አይደለም። በመሆኑም ትንሽ በተጨቃጨቁ ቁጥር ከመጠን በላይ አትረበሽ። የ20 ዓመቷ ሜላኒ “ወላጆቼ ቢጣሉ እንኳ ለቤተሰቡም ሆነ አንዳቸው ለሌላው ፍቅር እንዳላቸው አውቃለሁ። ችግሩን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ” በማለት ስለ ወላጆቿ ተናግራለች። በአንተም ወላጆች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ስለሚያስጨንቁህ ነገሮች ጸልይ። ስለ ጉዳዩ የሚሰማህን ጭንቀት አፍነህ መያዝ አይኖርብህም። መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” ይላል። (መዝሙር 55:22) ጸሎት ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ . . . ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” ብሏል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ለራስህ አስብ። ለውጥ ማምጣት በማትችለው ነገር ላይ ከልክ በላይ መጨነቅህ ተገቢ አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ማድረግህ በጤንነትህ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:25) ከሚያበረታቱ ጓደኞችህ ጋር አብረህ ጊዜ በማሳለፍና መንፈስን በሚያድሱ እንቅስቃሴዎች በመካፈል የሚሰማህን ጭንቀት ለማስታገስ ጣር።

ወላጆችህን አነጋግራቸው። በወላጆችህ መካከል በተፈጠረው ግጭት ውስጥ ጣልቃ መግባት ባያስፈልግህም እንኳ ሁኔታው በአንተ ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንዳሳደረ ልትነግራቸው ትችላለህ። አመቺ ጊዜ ፈልገህ አንዳቸውን ቀርበህ ለማነጋገር ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 25:11) ‘ትሕትናና አክብሮት’ በተሞላበት መንገድ ተናገር። (1 ጴጥሮስ 3:15) ወላጆችህን አትንቀፋቸው፤ ከዚህ ይልቅ ሁኔታው ምን ተጽዕኖ እንዳሳደረብህ ግለጽላቸው።

ከላይ የተገለጹትን ሐሳቦች ተግባራዊ እንድታደርጋቸው እናበረታታሃለን። ወላጆችህ ለምታደርገው ጥረት በጎ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። እነሱ ጥሩ ምላሽ ባይሰጡህ እንኳ ወላጆችህ በሚጨቃጨቁበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደምትችል ስለምታውቅ እርካታ ታገኛለህ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ቋሚ አምድ ሥር የወጡ ሌሎች ርዕሶችንም ማግኘት ይቻላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

ወላጆች አንዳንድ ጊዜ መግባባት የሚያቅታቸው ለምንድን ነው?

ታናናሾችህ የወላጆቻችሁ መጨቃጨቅ በጣም ቢያስጨንቃቸው ምን ብለህ ልታጽናናቸው ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

በትዳር ውስጥ አለመግባባቶች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። ችግሩን በመረጣችሁት መንገድ ልትፈቱት ትችላላችሁ። ይሁንና ወጣቶች በወላጆች መካከል በሚፈጠረው ጭቅጭቅ በእጅጉ ይጎዳሉ። ይህ ሁኔታ በጣም ሊያሳስባችሁ ይገባል፤ ምክንያቱም ልጆቻችሁ ወደፊት ቢያገቡ በእናንተ ትዳር ውስጥ የተመለከቷቸውን ነገሮች መኮረጃቸው አይቀርም። (ምሳሌ 22:6) በመካከላችሁ የሚነሱትን አለመግባባቶች፣ ግጭቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጋችሁ ለምን አትጠቀሙባቸውም? እስቲ የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ:-

አዳምጡ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንን እንዲሁም ለመናገርና ለቊጣ የዘገየን’ እንድንሆን ይነግረናል። (ያዕቆብ 1:19) ‘ክፉን በክፉ በመመለስ’ በእሳት ላይ ጭድ አትጨምሩ። (ሮሜ 12:17) የትዳር ጓደኛችሁ ሊያዳምጣችሁ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በሚሰማችሁ ጊዜም እንኳ እናንተ ማዳመጥ ትችላላችሁ።

ከመንቀፍ ይልቅ ሐሳባችሁን ለመግለጽ ጥረት አድርጉ። የትዳር ጓደኛችሁ ያሳየው ጠባይ እንዴት እንደጎዳችሁ በሰከነ መንፈስ ግለጹ። (“እንዲህ ብለህ በመናገርህ በጣም ተሰምቶኛል” ልትሉ ትችላላችሁ።) የትዳር ጓደኛችሁን ከመውቀስ ወይም ከመንቀፍ ተቆጠቡ። (“ድሮም አንተ የእኔ ነገር አያሳስብህም” ወይም “በጭራሽ አታዳምጠኝም” አትበሉ።)

ጉዳዩን ለጊዜው ተወት አድርጉት። አንዳንድ ጊዜ ውይይቱን ለጊዜው ማቆምና ንዴታችሁ በረድ ሲል መቀጠሉ በጣም የተሻለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 17:14

አንዳችሁ ሌላውን አስፈላጊ ከሆነም ልጆቻችሁን ይቅርታ ጠይቁ። ብሪያን የተባለች አንዲት የ14 ዓመት ልጅ “ወላጆቼ ከተጨቃጨቁ በኋላ ሁኔታው ምን ያህል እንደሚያስጨንቀን ስለሚያውቁ እኔንና ታላቅ ወንድሜን ይቅርታ ይጠይቁናል” ብላለች። ለልጆቻችሁ ከምታስተምሯቸው በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች ውስጥ አንዱ ትሑት ሆኖ “ይቅርታ” መጠየቅን ነው።

ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የጥር 2001 ንቁ! ገጽ 8-14ን እንዲሁም የሐምሌ—መስከረም 1996 ንቁ! ገጽ 3-12ን ተመልከቱ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቻችሁን አትንቀፏቸው። ከዚህ ይልቅ ምን እንደሚሰማችሁ ግለጹላቸው