በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብራዚል ሕንዶች ከምድር ገጽ ሊጠፉ ተቃርበዋል?

የብራዚል ሕንዶች ከምድር ገጽ ሊጠፉ ተቃርበዋል?

የብራዚል ሕንዶች ከምድር ገጽ ሊጠፉ ተቃርበዋል?

በብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የሺንጉ ብሔራዊ ፓርክ ማቶ ግሮሶ በተባለው የብራዚል ግዛት ውስጥ ይገኛል። ብሔራዊ ፓርኩ 27,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከቡሩንዲ ጋር የሚተካከል የቆዳ ስፋት አለው። የ14 ጎሳዎች አባላት የሆኑ ወደ 3,600 የሚጠጉ ሕንዶች የሚኖሩበት ይህ ፓርክ፣ በሳተላይት በተነሱ ፎቶግራፎች ሲታይ “ግዙፍ የፑል ማጫወቻ ጠረጴዛ” በሚመስል አካባቢ መሃል ላይ የሚገኝ ለምለም ቦታ ነው። በፓርኩ ዙሪያ ያለው ደን፣ አንድም ለገበያ የሚሆን ጣውላ ለማግኘት ሲባል ተቃጥሏል፤ አሊያም ብዛት ላላቸው የቀንድ ከብቶች የግጦሽ መሬት እንዲሆን ተመንጥሯል።

በ1960ዎቹ ዓመታት የብራዚል መንግሥት የተወሰኑ አካባቢዎችን የአገሩ ተወላጅ ለሆኑት ሕንዶች መኖሪያ እንዲሆኑ መከለል ጀመረ። የተከለሉት ቦታዎች በአብዛኛው የሚገኙት በአማዞን ክልል ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላው የብራዚል መሬት 12 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ። መንግሥት ለሕንዳውያኑ መኖሪያ የሚሆኑ ቦታዎችን መከለሉ አስገራሚ ለውጥ እንዲታይ አድርጓል፤ ካለፉት 500 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በብራዚል ያሉት ሕንዶች ቁጥር እየጨመረ ነው! በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ሦስት መቶ ሺህ ገደማ እንደሚደርስ ይታሰባል። ይሁን እንጂ በ1500 ብዛታቸው ከሁለት እስከ ስድስት ሚሊዮን ያህል እንደነበረ ይገመታል፤ ከዚያ አንጻር ሲታይ የአሁኑ ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ነው።

አንድ ደራሲ እንደጻፉት ከሆነ ባለፉት 500 ዓመታት ውስጥ “በሕዝቡ ብዛት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቷል።” የብራዚል ሕንዶች ቁጥር እንዲህ ባለ አስደንጋጭ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደረገው ምንድን ነው? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው መጨመሩ የብራዚል ሕንዶች የተደቀነባቸው የመጥፋት አደጋ ተወግዷል ማለት ነው?

ቅኝ ግዛት የጀመረው እንዴት ነው?

በ1500 ብራዚል የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ከሆነች በኋላ፣ በመጀመሪያዎቹ 30 ዓመታት ውስጥ ቅኝ ገዥዎቹ ያተኮሩት ብራዚልዉድ ተብሎ በሚጠራው ቀይ ቀለም የሚያስገኝ እንጨት ላይ ነበር። ብራዚል ስሟን ያገኘችው ከዚህ ዛፍ ነው። የዚህ ዛፍ እንጨት በአውሮፓ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው ሲሆን አውሮፓውያን ይህንን እንጨት ዋጋቸው ርካሽ በሆነ ትንንሽ ጌጣጌጦች ይለውጡት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የብራዚል አየር ጠባይ ለሸንኮራ አገዳ ምርት በጣም ምቹ እንደሆነ ታወቀ። ይሁን እንጂ ሥራውን ለማከናወን እንቅፋት የሚሆን ነገር ነበር። ሸንኮራ አገዳን ማልማት በጣም ብዙ ሠራተኞች የሚጠይቅ ሥራ ነበር። በዚህም የተነሳ ባሪያዎች ይበልጥ ይፈለጉ ጀመር። አዲስ የመጡት ሰፋሪዎች ባሪያዎች ለማግኘት ሩቅ መሄድ አላስፈለጋቸውም! ከአገሩ ተወላጆች በቂ ሠራተኞች ማግኘት ይችሉ ነበር።

ባርነት እንዴት ተጀመረ?

የብራዚል ሕንዶች የሚያመርቱት ለዕለት ጉርሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ያህል ብቻ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ወንዶቹ አዳኞችና ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። ደኑን የመመንጠሩን አድካሚ ሥራም ያከናውኑ ነበር። የሚዘሩት ምርቱን የሚሰበስቡትና ምግብ የሚያዘጋጁት ሴቶቹ ነበሩ። ሕንዶቹ ለሀብት ግድየለሽ መስለው መታየታቸውና ከስግብግብነት ነፃ መሆናቸው በተማሩት አውሮፓውያን ዘንድ አድናቆት አትርፎላቸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ አውሮፓውያን ሰፋሪዎች፣ ሕንዶቹን ሰነፎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።

ሰው ወዳዶቹ ሕንዶች፣ ሰፋሪዎቹን ከጥቃት እንዲጠብቋቸውና የጉልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ሲባል በፖርቹጋላውያኑ ሠፈር አቅራቢያ እንዲኖሩ ይበረታቱ ነበር። ሕንዳውያኑ በዚህ ሐሳብ እንዲስማሙ በማድረግ ረገድ ጀስዊቶችና ሌሎችም ሃይማኖቶች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እነዚህ ሃይማኖቶች፣ ይህ ቅርርብ ሕንዶቹን ምን ያህል ሊጎዳቸው እንደሚችል አልተገነዘቡም። ሕጉ የሕንዶቹ መሬት እንዳይነካባቸውና ነፃነታቸው እንዳይገፈፍ የሚያዝዝ ቢሆንም ሐቁ እንደሚያሳየው ሕንዶቹ ለሰፋሪዎቹ ባሪያዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ይገደዱ ነበር። ለሥራቸው ክፍያ የሚያገኙት ወይም በራሳቸው እርሻ ላይ ለመሥራት የሚፈቀድላቸው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር።

የፖርቹጋል የዘውድ አገዛዝ ባርነትን ለማስቆም ያደረገው ሙከራ እምብዛም ውጤት አላስገኘም። አብዛኛውን ጊዜ ሰፋሪዎቹ ባሪያ አሳዳሪነትን ከሚከለክለው ሕግ የሚያመልጡበት ዘዴ ይቀይሱ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ እንደ ጠላት የሚታሰቡትን “በፍትሐዊ ጦርነት” የተማረኩ ሕንዶች ባሪያ ማድረግ ወይም ለባርነት መሸጥ ተቀባይነት ያለው ተግባር እንደሆነ ይቆጠር ነበር። በሌሎች ጎሳዎች ተማርከው የተያዙ ሕንዶችንም በገንዘብ ገዝቶ ወይም “ዋጅቶ” ባሪያ ማድረግ ይቻል ነበር።

ከሁኔታዎቹ ለማየት እንደሚቻለው ቅኝ ግዛቱን ውጤታማ ያደረገው የስኳር ኢንዱስትሪ ነበር። በዚያ ዘመን ደግሞ የስኳር ኢንዱስትሪው የተመሠረተው በባሪያዎች ጉልበት ላይ ነበር። በመሆኑም ብዙውን ጊዜ የፖርቹጋል የዘውድ አገዛዝ ትርፍ ለማጋበስ ሲል የባሪያ አሳዳሪውን ሥርዓት ለመቀበል ይገደድ ነበር።

የቅኝ ገዢዎች ፉክክር—ፖርቹጋል ከፈረንሳይና ከሆላንድ ጋር ያደረገችው ትግል

በቅኝ ገዢዎቹ መካከል ግጭት ሲፈጠር ዋነኞቹ ተጎጂዎች ሕንዶቹ ነበሩ። ፈረንሳዮችና ሆላንዳውያን ብራዚልን ከፖርቹጋል መቀማት ፈለጉ። እነዚህ መንግሥታት የብራዚል ሕንዶች እነሱን እንዲደግፏቸው ለማድረግ ሲሉ ከፖርቹጋል ጋር መፎካከር ያዙ። ሕንዶቹ፣ የቅኝ ገዢዎቹ እውነተኛ ፍላጎት መሬታቸውን መውሰድ መሆኑ አልገባቸውም ነበር። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ግጭቶች፣ ጠላቶቻቸው የሆኑትን ሌሎች የሕንድ ጎሳዎች ለመበቀል አጋጣሚ እንደፈጠሩላቸው ስለተሰማቸው ቅኝ ገዢዎቹ በሚያደርጉት ውዝግብ ውስጥ ማንም ሳያስገድዳቸው በፈቃዳቸው ይገቡ ነበር።

ለምሳሌ ያህል፣ ኅዳር 10, 1555 ኒኮላ ደ ቪሌገኞዮን የተባለ ፈረንሳዊ መኮንን ወደ ጉዋናባራ ባሕረ ሰላጤ (የአሁኗ ሪዮ ዴ ጄኔሮ) መጣና ምሽግ ሠራ። ከዚያም ታሞዮ ከሚባሉት የሕንድ ጎሳዎች ጋር ግንባር ፈጠረ። ፖርቹጋላውያን ደግሞ የቱፒናንባ ጎሳ የሆኑትን ሕንዶች ከባሂያ አመጡና በመጋቢት ወር 1560 የማይደፈር ይመስል በነበረው ምሽግ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። ፈረንሳውያኑ ሸሽተው ቢሄዱም ከታሞዮ ጎሳዎች ጋር የንግድ ግንኙነት ማድረጋቸውንና ፖርቹጋልን እንዲወጉ ማነሳሳታቸውን ቀጠሉ። በርካታ ውጊያዎችን ካደረጉ በኋላ የታሞዮ ጎሳዎች በመጨረሻ ተሸነፉ። ዘገባው እንደሚገልጸው ከሆነ በአንድ ጦርነት ብቻ 10,000 ሰዎች ሲገደሉ 20,000 ደግሞ ባሪያዎች ተደረጉ።

ከአውሮፓ የመጡ አሰቃቂ በሽታዎች

ፖርቹጋላውያን መጀመሪያ ሲመጡ ያገኟቸው የአገሩ ተወላጆች በጣም ጤነኞች ይመስሉ ነበር። የመጀመሪያዎቹ አሳሾች ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ ሕንዶች መቶ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናቸው እንደነበሩ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ሕንዶቹ ከአውሮፓም ሆነ ከአፍሪካ የመጡ በሽታዎችን የመከላከል አቅም አልነበራቸውም። ምናልባትም ከምንም ነገር በላይ ሕንዶቹ ከምድር ገጽ ለመጥፋት እንዲቃረቡ ያደረጓቸው እነዚህ በሽታዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።

በፖርቹጋላውያን መዛግብት ውስጥ፣ የሕንዶቹ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እንዲቀንስ ስላደረጉ ወረርሽኞች የሚገልጹ በርካታ አሰቃቂ ዘገባዎች ይገኛሉ። በ1561 የፈንጣጣ ወረርሽኝ ፖርቹጋልን ከመታ በኋላ አትላንቲክን ተሻግሮ በቅኝ ግዛት ወደያዘቻቸው አካባቢዎች ተዛመተ። ይህም ከፍተኛ እልቂት አስከትሏል። ጀስዊት የነበረው ሊዮናርዶ ዶ ቬል በግንቦት 12, 1563 ወረርሽኙ በብራዚል ያስከተለውን ሰቆቃ አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደሚከተለው ብሏል:- “ፈንጣጣው በጣም ቀፋፊና መጥፎ ሽታ ያለው በመሆኑ [ከሕመምተኞቹ] ሰውነት የሚወጣውን ክርፋት መቋቋም የሚችል ሰው አልነበረም። በዚህም የተነሳ ብዙዎች የሚያስታምማቸው አጥተው እንዲሁም ፈንጣጣው ባስከተለው ቁስል ላይ በሚፈጠሩና ለማየት በሚዘገንን ብዛትና መጠን በሚያድጉ ትሎች ተበልተው ይሞቱ ነበር።”

የተለያዩ ዘሮች ጋብቻ ጀስዊቶችን አስደነገጠ

የተለያዩ ዘሮች መጋባትም በርካታ ጎሳዎች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል። ሬድ ጎልድ—ዘ ኮንከስት ኦቭ ዘ ብራዚሊያን ኢንዲያንስ የተሰኘው መጽሐፍ “ፖርቹጋላውያንም ሆኑ የብራዚል ተወላጆች የተለያዩ ዘሮች በመጋባታቸው አልተከፉም ነበር” ይላል። ሕንዶቹ ሴቶቻቸውን፣ ብዙውን ጊዜም የራሳቸውን ሴቶች ልጆች ለእንግዶች ማቅረብን እንደ ጥሩ እንግዳ ተቀባይነት አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ይሁንና የመጀመሪያዎቹ ጀስዊቶች በ1549 ብራዚል ሲደርሱ በተመለከቱት ነገር ደንግጠው ነበር። ጀስዊት ማኖኤል ዳ ነብሬጋ “[ቀሳውስቱ] ከሕንዶቹ ሴቶች ጋር በኃጢአት መኖራቸው ሕጋዊ እንደሆነ በይፋ ይነግሯቸው ነበር” በማለት ቅሬታውን የገለጸ ሲሆን አክሎም “ሰፋሪዎቹ ሕንዶቹን ሴቶች [ባሪያዎቻቸውን] በሙሉ ቁባቶች አድርገዋቸው ነበር” ብሏል። በአንድ ወቅት የፖርቹጋል ንጉሥ፣ አንድ ፖርቹጋላዊ ሰፋሪ ‘በጣም ብዙ ልጆች፣ የልጅ ልጆች፣ የልጅ ልጅ ልጆችና ዝርያዎች ያሉት ከመሆኑ የተነሳ [ተናጋሪው] ብዛታቸውን ለግርማዊነትዎ ለመንገር አልደፍርም’ ማለቱን የሚገልጽ ዜና ደርሷቸው ነበር።

በ17ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ፣ ቀደም ሲል በብራዚል ጠረፍ ሜዳማ ቦታዎች ላይ ተጨናንቀው ይኖሩ የነበሩት ሕንዶች ሞተው አልቀዋል፤ አሊያም ባሪያዎች ሆነዋል ወይም ከሌሎች ዘሮች ጋር በመቀላቀል ተውጠዋል። በአማዞን ክልል ይኖሩ የነበሩት ጎሳዎችም ብዙም ሳይቆይ ተመሳሳይ ዕጣ ገጠማቸው።

ፖርቹጋላውያን ወደ አማዞን መሄዳቸው የታችኛው አማዞን ነዋሪዎች እንዲጨፈጨፉ ምክንያት ሆኗል። የማራንሃኦ አስተዳዳሪ የነበሩት ማኑዌል ቴይክሴራ እንደገለጹት በጥቂት አሥርተ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ፖርቹጋላውያን በማራንሃኦና በፓራ ግዛቶች ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕንዶችን ገድለዋል። ይህ ቁጥር ምናልባት የተጋነነ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ የደረሰው ጥፋትና መከራ አሌ የሚባል አይደለም። በኋላ ደግሞ ከአማዞን ወንዝ ወደ መሃል ገባ ብለው የሚገኙት አካባቢዎች ተመሳሳይ እልቂት ደርሶባቸዋል። በ18ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩት ብቻ ሲቀሩ በአማዞን ክልል የነበሩ የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ሕንዶች በሙሉ ማለት ይቻላል ጠፍተዋል።

በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው መቶ ዘመን በአማዞን የሚገኙ ራቅ ያሉ አካባቢዎች እድገት ማድረጋቸው በሕይወት የተረፉት ተበታትነው የሚኖሩ የሕንድ ጎሳዎች ቀስ በቀስ ከነጮች ጋር እንዲገናኙ አድርጓል። ቻርልስ ጉድይርስ በ1839 ጎማ እንዲጠነክርና እንዲለጠጥ ለማድረግ የሚያስችል ዘዴ መፈልሰፉና ይህን ተከትሎም የተሽከርካሪዎች ጎማ መሠራቱ ሕዝቦች ጎማ ለማግኘት ወደዚህ አካባቢ እንዲጎርፉ አድርጓቸዋል። ነጋዴዎች ያልተጣራ ጎማ ወደሚገኝበት ብቸኛው ቦታ ማለትም ወደ አማዞን ክልል ጎረፉ። በዚህ ወቅት የአገሩ ተወላጅ የሆኑት ሕዝቦች በግፍ የተበዘበዙ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ቁጥራቸው በከፍተኛ መጠን አሽቆልቁሏል።

ሃያኛው መቶ ዘመን በሕንዶች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

በ1970 የብራዚል መንግሥት ሕዝቡ እንዲቀላቀል ለማድረግ አውራ ጎዳናዎች በመገንባት የተራራቁ የአማዞን አካባቢዎችን ለማገናኘት እቅድ ነደፈ። ከእነዚህ አውራ ጎዳናዎች አብዛኞቹ የሕንዶቹን ምድር አቋርጠው የሚያልፉ ሲሆን ይህም ሕንዶቹን የማዕድን ሀብት ፍለጋ ለሚመጡ ሰዎች ጥቃት ከማጋለጡም በላይ በገዳይ በሽታዎች እንዲጠቁ ምክንያት ሆኗል።

ለምሳሌ ያህል፣ ፓናራስ የሚባሉት ሕዝቦች ላይ የደረሰውን ተመልከት። የዚህ ጎሳ ሕዝቦች በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን በገጠማቸው ጦርነትና ባርነት ሳቢያ ቁጥራቸው ተመናምኖ ነበር። ጥቂት ቀሪዎች ወደ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ ሸሽተው በማቶ ግሮሶ ጫካ ውስጥ ዘልቀው መኖር ጀመሩ። ከዚያም በኋላ ምድራቸውን የሚያቋርጥ ኩይባ ሳንታሬም የተባለ አውራ ጎዳና ተሠራ።

ከነጮች ጋር መገናኘት ለሕንዶቹ አደገኛ ነበር። በአንድ ወቅት በጣም ብዙ ከነበሩት ከዚህ ጎሳ ሕዝቦች ውስጥ በ1975 የቀሩት 80 አባላት ብቻ ነበሩ። የፓናራስ ጎሳዎች ወደ ሺንጉ ብሔራዊ ፓርክ ተዛወሩ። በፓርኩ ውስጥ ከተወለዱበት ጫካ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አካባቢ ለማግኘት ቢሞክሩም ስላልተሳካላቸው ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ወሰኑ። በኅዳር 1, 1996 የብራዚል ፍትሕ ሚኒስቴር 495,000 ሄክታር የሚሆን መሬት “ለዘለቄታው የአገሩ ተወላጅ ሕዝቦች ይዞታ” እንዲሆን መከለሉን አወጀ። የፓናራስ ጎሳዎች ከምድር ገጽ ከመጥፋት የተረፉ ይመስላል።

ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣላቸው ይሆን?

እስካሁን በሕይወት ለተረፉት ሕንዶች የተወሰነ መሬት ተከልሎ መሰጠቱ ከመጥፋት ያድናቸው ይሆን? በአሁኑ ጊዜ የብራዚል ሕንዶች ጨርሶ የመጥፋት ሁኔታ እምብዛም አያሰጋቸውም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ መሬታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ማዕድንና የተፈጥሮ ሀብት የሚገኝበት ነው። በሰሜንና በማዕከላዊ ምዕራብ የብራዚል ክልል የሚገኙ ዘጠኝ ግዛቶችን በሚሸፍነው ሌጋል አማዞንያ ተብሎ በሚጠራው ምድር ውስጥ ወርቅ፣ ፕላቲነም፣ አልማዝ፣ ብረትና እርሳስን ጨምሮ አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ማዕድን እንደሚገኝ ተገምቷል። ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆነው የሕንዶች መኖሪያ የሚገኘው በዚህ ክልል ነው። አሁንም እንኳ በአንዳንድ የሕንዶች መሬት ላይ ሕገ ወጥ ማዕድን ፈላጊዎች እየታዩ ነው።

ከታሪክ እንደታየው ሕንዶቹ ከነጮች ጋር በነበራቸው ግንኙነት ምንጊዜም ተጎጂዎች ነበሩ። ወርቃቸውን በመስታወት፣ የብራዚልዉድ ጣውላዎችን በማይረቡ ጌጣጌጦች ይለውጡ ነበር፤ እንዲሁም ከባርነት ለማምለጥ ሲሉ በደኑ ውስጥ ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች ለመሸሽ ተገደዋል። አሁንም ታሪክ ራሱን ይደግም ይሆን?

ብዙ ሕንዶች እንደ አውሮፕላን፣ በሞተር የሚሠራ ጀልባና ሞባይል ስልክ በመሳሰሉ የዘመናችን ቴክኖሎጂ ያፈራቸው መሣሪያዎች መጠቀም ተምረዋል። ይሁን እንጂ ሕንዳውያኑ 21ኛው መቶ ዘመን የሚያመጣቸውን ሌሎች ችግሮች መቋቋም ይችሉ ይሆን? ይህን ሊያሳየን የሚችለው ጊዜ ብቻ ነው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሺንጉ ብሔራዊ ፓርክ

ለሕንዶች የተከለሉ ቦታዎች

ብራዚል

ብራዚሊያ

ሪዮ ዴ ጄኔሮ

ፍሬንች ጊያና

ሱሪናም

ጋያና

ቬኔዙዌላ

ኮሎምቢያ

ኢኳዶር

ፔሩ

ቦሊቪያ

ፓራጓይ

ኡራጓይ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነጋዴዎች በጎማ ተክል እርሻቸው ላይ የሚሠሩላቸው ባሪያዎች ለማግኘት ሲሉ ሕንዶቹን በዝብዘዋቸዋል

[ምንጭ]

©Jacques Jangoux/Peter Arnold, Inc.

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Line drawing and design: From the book Brazil and the Brazilians, 1857