በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

አንድ ነጋዴ አንድን ዕቃ እንድትገዛው በሚያግባባህ ጊዜ ወይም አንድ ፖለቲከኛ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት እንዲህ አደርጋለሁ እያለ ተስፋ በሚሰጥበት ወቅት ራስህን ‘ይህ ሰው የሚናገረውን ነገር ማመን ይኖርብኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ምንም ጥቅም ለሌለው ዕቃ ወይም ወሬ ብለህ ገንዘብህንም ሆነ ጊዜህን ማባከን እንደማትፈልግ እሙን ነው።

በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ‘ይህ መጽሐፍ እኔን ሊጠቅም የሚችል ነገር ይዟል? ይህን መጽሐፍ ባነበውና ባጠናው ለዚያ የማውለው ጊዜና ጉልበት ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚረዳንን ቁልፍ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለ አንድ ጥቅስ ላይ ማግኘት እንችላለን። ጥቅሱ “የጥበብ ትክክለኛነት በሥራዋ ይገለጣል” ይላል። (ማቴዎስ 11:19 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ሰዎች አንድን ዓይነት ምክር ወይም “ጥበብ” ተግባራዊ ካደረጉ በኋላ የሚያገኙት ውጤት ምክሩ በእርግጥ ጠቃሚ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላቸዋል። ጊዜ መድበው መጽሐፍ ቅዱስን የተማሩ ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል። እነሱ የሰጡት አስተያየት አንተም በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ይህን መጽሐፍ ማንበብና ማጥናት ይኖርብህ እንደሆነ ለመወሰን ይረዳሃል።

ስለ ሞትና ከዚያ በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት የሚነሱ ጥያቄዎች

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ካረን ከጥቂት ጊዜያት በፊት እናቷን በሞት አጥታ ነበር። ይህች ሴት ከልጅነቷ አንስቶ ጥሩ ሰዎች በሙሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚል እምነት ነበራት። ይሁንና ይህ እምነት ብዙም አላጽናናትም። ‘አሁን ሰማይ ላይ የምትገኘው እናቴ ምን ትመስል ይሆን? ሰማይ በምሄድበት ጊዜ እሷን ፈልጌ ላገኛት የምችለው እንዴት ነው? ስሞት እናቴን ወደማላገኝበት ቦታ እሄድ ይሆን?’ ብላ ትጠይቅ ነበር።

ካረን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ጀመረች። በዚህ ጊዜ ሙታን በሰማይ እንዳልሆኑና ከከባድ እንቅልፍ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተማረች። መክብብ 9:5 “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል። የሆነ ሆኖ እናቷን እንደገና ታገኛት ይሆን?

ካረን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ከሚናገረው ሐሳብ መጽናኛና ተስፋ አገኘች:- ‘በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የክርስቶስን] ሰምተው የሚወጡበት ጊዜ ይመጣል።’ (ዮሐንስ 5:28, 29) ካረን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ በልጁ አማካኝነት ሙታን እዚሁ ምድር ላይ እንደገና በሕይወት እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ተማረች። “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞትና ስለ ትንሣኤ የሚያስተምረውን ትምህርት መረዳት በጣም ቀላል ነው” በማለት ተናግራለች።

ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው ነው?

አንጄላ የምትባል አንዲት ሩማንያዊት ወጣት የ14 ዓመት ልጅ ሳለች አንድ የጰንጠቆስጤ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መንፈስ ቅዱስ እንድትቀበል ጸለየላትና በልሳን መናገር ጀመረች። ወላጆቿ ግን ይህ እምነት የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይስማሙ ተሰማቸው። የዚህ ቤተሰብ አባላት የጰንጠቆስጤ እምነት ተከታዮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆሙና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።

አንጄላ መጀመሪያ ላይ ሁኔታው ቢያበሳጫትም በቀድሞ ሃይማኖቷ ውስጥ በሚደረጉ ነገሮችና መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምራቸው ትምህርቶች መካከል ልዩነት መኖሩን ለመመልከት ጊዜ አልወሰደባትም። ለምሳሌ ያህል፣ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” የሚለውን በዮሐንስ 17:3 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበበች። አንጄላ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙ ሰዎች በመጀመሪያ ስለ እሱ ማወቅ እንዳለባቸው ተገነዘበች። “ስለ እሱ ምንም ነገር ሳላውቅ እንዲህ በመሰለ ልዩ መንገድ መንፈስ ቅዱስን እንዴት ልቀበል እችላለሁ?” ብላ ራሷን ጠየቀች። አንጄላ “ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ አማካኝነት እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቼ እንዳውቅ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ” በማለት ተናግራለች።

የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥ ምክር

በሕንድ የሚኖረው ጋብርኤል “በጣም ግልፍተኛ ሰው ነበርኩ” በማለት ይናገራል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው የሚያናድድ ነገር ሲናገረኝ ወይም ሲያደርግብኝ እጮኻለሁ፣ ያገኘሁትን ዕቃ እወረውራለሁ አልፎ ተርፎም እሳደባለሁ ወይም እማታለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ቁጣዬን እንድቆጣጠር ረድቶኛል። በአሁኑ ጊዜ በጣም የሚያበሳጭ ሁኔታ በሚያጋጥመኝ ጊዜም እንኳ ራሴን መግዛት እችላለሁ።”

ጋብርኤል በምሳሌ 16:32 ላይ እንደሚገኘው “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል” እንደሚለው ያሉ ጥቅሶችን ማንበቡ ጠቅሞታል። የግልፍተኝነት ባሕርይውን ያሸነፈ ዲራጅ የሚባል ሌላ ሰውም “በቁጣ መገንፈል የደካማነት ምልክት እንደሆነ፣ ቁጣን መቆጣጠር ግን የጥንካሬ መለኪያ መሆኑን እንድገነዘብ የረዳኝ ይሄ ጥቅስ ነው” በማለት ተናግሯል።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ፊሊፕ ወሮበላ ነበር። ድብድብ፣ ዝርፊያና የብልግና ቃላት መናገር የሕይወቱ ክፍል ሆነው ነበር። በየጊዜው በሚሠራቸው ወንጀሎች ምክንያት ይታሰራል። ይሁንና ፊሊፕ እንዲህ ያለ ባሕርይ ቢኖረውም አምላክን የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ በኋላ አምላክን የማገልገል ፍላጎት ስላደረበት ሕይወቱን ለማስተካከል ወሰነ። መጥፎ ልማዶቹን እርግፍ አድርጎ ከመተዉም በላይ ወንጀል ከሚፈጽሙ ጓደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጠ። በሕይወቱ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሱት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች በዮሐንስ 6:44 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት አሳዩት። ጥቅሱ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም” ይላል። ፊሊፕ “ይሖዋ በውስጤ አንድ ዓይነት ጥሩ ነገር ስላየብኝ ግሩም የወንድማማች ኅብረት ወደመሠረቱት ሕዝቦቹ ሳበኝ” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም ፊሊፕ፣ ይሖዋ ስላደረጉት መጥፎ ነገር ለተጸጸቱ ሰዎች ምሕረት እንደሚያደርግ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ልብ ማለት ጀመረ። ፊሊፕ “እነዚህ ታሪኮች ይሖዋ፣ ንስሐ ከገቡ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያታዊ መሆኑን እንድገነዘብ ረድተውኛል” ብሏል።—2 ሳሙኤል 12:1-14፤ መዝሙር 51

ዋድ የሚባል አንድ አውስትራሊያዊ ወጣት የአልኮል መጠጥና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ ከመሆኑም በላይ ቁማር ይጫወት እንዲሁም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ በርካታ ድርጊቶችን ይፈጽም ነበር። ይሁንና ይሄ ሁሉ ደስታ ሊያስገኝለት አልቻለም። አንድ ቀን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተነጋገረና መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማጥናት እንደሚችል የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። ታዲያ ምን ተማረ?

ዋድ “ኢየሱስ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ እጅግ አስደነቀኝ” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ኢየሱስ ልጆችን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ደግነት፣ ርኅራኄና ፍቅር አሳይቷል። ስለ እሱ ብዙ ባወቅሁ መጠን ይበልጥ እሱን የመምሰል ፍላጎት አደረብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ወንድ መሆን እንዲሁም ባሕርዬን ማሻሻል የምችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮኛል።” ይሁን እንጂ ቀድሞ የሠራው ያ ሁሉ መጥፎ ነገርስ? ዋድ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ለሠራሁት ኃጢአት ንስሐ ገብቼ ጠባዬን ካስተካከልኩ አምላክ ይቅር እንደሚለኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬአለሁ። እንዲያውም በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር እችላለሁ። በመጨረሻ ተስፋ ያለኝ ሰው ሆንኩ!” (ማቴዎስ 5:5) ዋድ አኗኗሩን አስተካክሎ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና በማምለክ ላይ ይገኛል።

ከላይ ያነበብካቸው ተሞክሮዎች ሕይወታቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ችግሮቻቸውን ለማስተካከልና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ይረዳቸው እንደሆነ ለማየት መጽሐፉን ሥራዬ ብለው መረመሩት። ያገኙት ጥሩ ውጤት ተግባራዊ ሊሆን በሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ላይ እምነት መጣል እንደሚችሉ በሚገባ አሳመናቸው። አንተም ብትሆን ልትተማመንበት ትችላለህ።

ከረጅም ጊዜ በፊት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ አንድ ሐሳብ እንዲህ ይላል:- “ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረጅም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ።”—ምሳሌ 3:13-18

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ አንድን እስረኛ ረዳው

ቢል የተባለ አንድ ሰው ትዳር መሥርቶ በደስታ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ አግብቶ ዓመት እንኳ ሳይሞላው ከዓመታት በፊት በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ወደ ወህኒ ወረደ።

ቢል እንደልብ የመንቀሳቀስ ነፃነቱን ማጣቱ ከፈጠረበት ድንጋጤ ሲረጋጋ በእስር በሚያሳልፈው ጊዜ ትርጉም ያለው ነገር ለማከናወን ወሰነ። “በአልጋዬ ላይ ሆኜ መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብና ሳጠና እውላለሁ” በማለት ይናገራል። እንዲሁም የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ያውለው ነበር። “አብረውኝ የታሠሩት ሰዎች እነሱ በሚያደርጓቸው መጥፎ ተግባሮች ልተባበራቸው እንደማልፈልግ የተገነዘቡ ሲሆን እኔም ለእነሱ ደግነት በማሳየት ልግባባቸው እጥር ነበር። እኔን በሚመለከት ‘ቢል ጊዜውን እሱ በፈለገው መንገድ ይኸውም ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ሊጠቀምበት ይፈልጋል። በማንም ላይ ችግር መፍጠር የሚፈልግ ሰው አይደለም’ ይባባሉ ነበር።

“በሌሎች እስረኞች ዘንድ ጥሩ ስም ስላተረፍኩ በጭቅጭቆችና ደስ በማይሉ ሌሎች ጉዳዮች ውስጥ እንድገባ ለማድረግ አይሞክሩም ነበር። ጠባቂዎቹ ምንም ዓይነት ችግር እንደማልፈጥርባቸው ተገነዘቡ። በዚህም ምክንያት ከእስር ቤቱ ውጪ የሚሠሩ ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት እንዲሰጠኝ የድጋፍ ሐሳብ አቀረቡልኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ማዋሌ ጥበቃ ሆኖልኛል።”

ቢል በወህኒ ቤት ውስጥ በሚደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ከመገኘቱም በላይ እየተማረ ያለውን ነገር ለሌሎች እሥረኞች በግለት ይናገር ነበር። የእስራት ዘመኑን ከመጨረሱ በፊት ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ያሳለፈውን ተሞክሮ በሚመለከት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ከዕድሜዬ ውስጥ ወደ 50 የሚጠጉ ዓመታት አባክኛለሁ፤ ስለዚህ ለውጥ ለማድረግ ፈለግኩ። አንድ እሥረኛ ለውጥ ማድረግ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን በሥራ ላይ በማዋል ብቻ መሆኑን ተረድቻለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መማር የሚቻለው ደግሞ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያስተምረው የእነሱ ሃይማኖት ብቻ ነው። ከዚህ ሌላ ምንም ማለት አልችልም።”

ከእስር ነፃ የወጣው ቢል በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ በቅንዓት በማገልገል ላይ ይገኛል። እሱና ባለቤቱ የአምላክን ቃል ማጥናታቸውንና የተማሩትን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በኢሳይያስ 48:17, 18 ላይ ለሚገኘው ሐሳብ ልባዊ አድናቆት አላቸው:- “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካረን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንጄላ፣ ሩማንያ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጋብርኤል፣ ሕንድ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዲራጅ፣ ሕንድ

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፊሊፕና ቤተሰቡ፣ ደቡብ አፍሪካ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋድ፣ አውስትራሊያ