በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ስለሚዘግብ አንዳንዶች የታሪክ መጽሐፍ አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ለዚህም አምላክ ሕግ ነክ ጉዳዮችን፣ የቤተሰብ ሕይወትን፣ ሥነ ምግባርንና ሃይማኖትን አስመልክቶ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ከ600 የሚበልጡ ሕጎችና ደንቦች እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስን አምላክ ምን አስተሳሰብ እንዳለው የሚገልጽ መንፈሳዊ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩትም አሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነገሩት እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ምንም ስህተት የለባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስም ስለ ራሱ ሲናገር “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በእርግጥም ታሪካዊ ዘገባዎችን፣ ሕጎችንና መንፈሳዊ ምክሮችን ጨምሮ በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ጠቃሚ ነው።

ይሁን እንጂ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚ መረጃዎችን አሰባስቦ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ብቻ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ የሚያደርገው ነገር ይሖዋ አምላክ ሐሳቡን የገለጸበት መጽሐፍ መሆኑ ነው። ዕለታዊ ሕይወታችንን ለመምራት የሚያስችሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ጠቃሚ ምክሮችን ይዞልናል። በተጨማሪም ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ እንዲሁም የመከራ ምንጭ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያስወግድበት መንገድ ይገልጽልናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሆን ተብሎ ያለ ስሙ ስም እንደተሰጠው ይናገራል፤ አክሎም አምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ይዘት ላለው ለዚህ ግድድር እንዴት እልባት እንደሚያበጅ ይገልጽልናል።

አምላክ ውሸታም እና መጥፎ ገዢ ተብሏል

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን በአእምሮም ሆነ በአካል ፍጹም አድርጎ እንደፈጠራቸውና በጣም ምቹ በሆነ አካባቢ እንዳስቀመጣቸው ይናገራል። ከዚያም ምድርንና በላይዋ ያሉትን እንስሳት በሙሉ እንዲገዙ ሥልጣን ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:28) አዳምና ሔዋን የአምላክ ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የሰማዩ አባታቸውን እስከታዘዙ ድረስ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሁንና አምላክ አንድ እገዳ ብቻ ጥሎባቸው ነበር። ይሖዋ አዳምን “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር።—ዘፍጥረት 2:16, 17

ይሁን እንጂ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር “መሞት እንኳ አትሞቱም” በማለት አምላክ የተናገረውን ሐሳብ የሚቃረን ነገር ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:1-5) አምላክን ተቃውሞ የተነሳው ሰይጣን ፈጣሪን ውሸታም ብሎ በመጥራት ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ አገዛዙ ትክክል እንዳልሆነና ሰው ያለ አምላክ እርዳታ ራሱን በራሱ ቢያስተዳድር እንደሚበጀው በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግሯል። ሰይጣን ዲያብሎስ ሔዋን አምላክን ሳትታዘዝ መቅረቷ ነፃነትና በራሷ ፈቃድ የመመራት መብት እንደሚያጎናጽፋት በመናገር አሳመናት። “እንደ እግዚአብሔር” ልትሆን እንደምትችል ነገራት! በዚህ መንገድ ሰይጣን በይሖዋ ጥሩ ስምና ዓላማ ላይ ጥቃት ሰነዘረ።

ሰይጣንና ሔዋን ያደረጉት ይህ የቃላት ልውውጥ ከባድ መዘዝ አስከትሏል። እንዲያውም ዋነኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ይሖዋ ስሙን ከደረሰበት ነቀፋ የሚያነጻ መሆኑን የሚናገር ነው። ይህ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ አባታችን ሆይ እየተባለ በሚጠራው የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ውስጥ ጠቅለል ተደርጎ ተገልጿል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ . . . በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል።—ማቴዎስ 6:9, 10

አምላክ ስሙን ከስድብ የሚያነጻው እንዴት ነው?

ሰይጣን እንደሚከተሉት ያሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አስነስቷል:- ለመሆኑ እውነት የተናገረው ማን ነው? ይሖዋ ነው ወይስ ሰይጣን? ይሖዋ ፍጥረታቱን የሚገዛበት መንገድ ትክክልና መልካም ነው? ሰዎች እንዲታዘዙት የመጠየቅ መብት አለው? ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ ይሻላቸው ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይሖዋ ሰዎች ለጊዜውም ቢሆን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቀደ።

ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በኤደን ውስጥ ያ ውሸት ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ታሪክ በመከራና በሥቃይ የተሞላ ሆኗል፤ ይህ ደግሞ ሰይጣን ክፋት የተጠናወተው ውሸታም እንደሆነና ከአምላክ ተነጥሎ ራስን በራስ ማስተዳደር ችግር ከማምጣት በቀር ምንም ፋይዳ እንደሌለው አረጋግጧል። ይሁን እንጂ፣ ይሖዋ በፍቅሩና ወሰን በሌለው ጥበቡ አማካኝነት በኤደን የጀመሩትን ችግሮች በሙሉ በመሻር ስሙን ከስድብ የማንጻት ዓላማ አወጣ። ይህን የሚያደርገው በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ነው። ይህ መንግሥት ምንድን ነው?

አምላክ መፍትሔ ለማምጣት የሚጠቀምበት መንግሥት

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አባታችን ሆይ የተሰኘውን ጸሎት ዘወትር ይደግማሉ። እስቲ አንድ አፍታ ቆም በልና ስለ ትርጉሙ አሰላስል። “መንግሥትህ ትምጣ” የሚሉትን ቃላት አስብባቸው። (ማቴዎስ 6:10) ይህ መንግሥት አንዳንዶች እንደሚያስቡት በልብ ውስጥ ያለ የማይጨበጥ ሁኔታን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ንጉሥ” የሚለው ቃል እንደሚያመለክተው “የነገሥታት ንጉሥ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ ሰማያዊ መስተዳድር ነው። (ራእይ 19:13, 16፤ ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) ኢየሱስ በመላው ምድር ላይ እንደሚገዛና ሁሉም ሕዝቦች በሰላምና በስምምነት እንዲኖሩ እንደሚያደርግ እንዲሁም ምድርን ከክፋት ሁሉ እንደሚያጸዳት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10) በዚህ መንገድ የአምላክ መንግሥት “ፈቃድህ . . . በምድር ትሁን” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል፤ እንዲህ ሊያደርግ የሚችል አንድም ሰብዓዊ መንግሥት የለም።

ኢየሱስ እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ሲል የአዳምን ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 6:23) በመሆኑም በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የአዳም ኃጢአት ያስከተለው ውጤት ተሽሮ ሰዎች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ሲደርሱ ለማየት ይበቃሉ። (መዝሙር 37:11, 29) ከዚያ በኋላ በተለይ እርጅናን ተከትለው ከሚመጡ የተለያዩ ችግሮች እንገላገላለን። ሌላው ቀርቶ ሕመምና ሞት በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ የሚያስከትሉት ስሜታዊ ሥቃይ እንኳ ‘ያለፈ’ ታሪክ ይሆናል።—ራእይ 21:4

አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ነው። (ገጽ 9ን ተመልከት።) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት በእውነታዎች ላይ ያልተመሠረተ ጭፍን አመለካከት ስላላቸው ሳይሆን አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶችና በርካታ ማስረጃዎች ስላሏቸው ነው።—ዕብራውያን 11:1

በዘመናችን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር

መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት የሚሰጠን ከመሆኑም በተጨማሪ በዛሬው ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል ስለ ትዳር፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት፣ ከሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት፣ ደስታ ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድና ስለ ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተወዳዳሪ የሌለው ተግባራዊ ምክር ይሰጣል። እስቲ ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ከመናገርህ በፊት አስብ። “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።”—ምሳሌ 12:18

ቅናትን አስወግድ። “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል፤ ቅናት ግን ዐጥንትን ያነቅዛል።”—ምሳሌ 14:30

ለልጆችህ ተግሣጽ ስጥ። “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።” “የተግሣጽ በትር ጥበብን ታጐናጽፋለች፤ መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል።”—ምሳሌ 22:6፤ 29:15

ይቅር ባይ ሁን። ኢየሱስ “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:7) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞንም “ፍቅር ግን ስሕተትን ሁሉ ይሸፍናል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 10:12) አንድ ሰው የፈጸመብህ በደል በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ይቅር ብለህ መርሳት ካልቻልክ መጽሐፍ ቅዱስ “ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው” በማለት ይመክራል።—ማቴዎስ 18:15

ከፍቅረ ንዋይ ራቅ። “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ . . . ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ገንዘብን ሳይሆን ‘የገንዘብ ፍቅርን’ መሆኑን ልብ በል።

ከሰማዩ አባታችን የተላከ “ደብዳቤ”

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ብዙ ነገሮች ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት የሚናገረው ስለ አምላክና ስለ ዓላማው ነው። ይሁን እንጂ ስለ እኛ ስለ ሰዎችም ይናገራል፤ አሁንም ሆነ ወደፊት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር እንዴት በደስታ መኖር እንደምንችል የሚናገረው ሐሳብ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሰማያት ከሚኖረው አባታችን’ ከይሖዋ የተላከ ደብዳቤ ነው ልንለው እንችላለን። (ማቴዎስ 6:9) በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ይሖዋ ውድ የሆኑ አስተሳሰቦቹን ያካፈለን ከመሆኑም በላይ ፈቃዱንና ግሩም የሆኑ ባሕርያቱን ገልጾልናል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ በማሰላሰል የአምላክን ትክክለኛ ማንነት “ማየት” መጀመር እንችላለን፤ ይህም ልባችን በአድናቆት እንዲሞላ በማድረግ ከእሱ ጋር በፍቅር እንድንተሳሰር ይገፋፋናል። (ያዕቆብ 4:8) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ፣ የትንቢትና የሕግ መጽሐፍ ብቻ አይደለም። ከአምላክ ጋር ስለምንመሠርተው የግል ዝምድናም ጭምር ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስን በእርግጥ ልዩና በጣም ውድ የሚያደርገውም ይህ ነው።—1 ዮሐንስ 4:8, 16

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በኢየሱስ የናሙና ጸሎት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ግሩም በሆነ ሁኔታ ጠቅለል ተደርጎ ተገልጿል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚቻልበት መንገድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም የሚያስደስት ነው። እንዲያውም ታሪኮቹና ሥነ ምግባራዊ ትምህርቶቹ በጣም የታወቁ ከመሆናቸው የተነሳ በብዙ ቋንቋዎች በተዘጋጁ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን የሆነውን ይሖዋ አምላክን እንድናውቀው ይረዳናል። በተጨማሪም ጥበብ የሚገኝበት ምንጭ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት” ይላል። (ምሳሌ 4:7) ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የተሻለ ጥቅም ልታገኝ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በጣም ንቁ የምትሆንበትን ሰዓት ምረጥ። የምታነበውን ነገር ገረፍ ገረፍ እያደረግህ አትለፍ። የምታነብበት ዓላማ አእምሮህን በአምላክ ሐሳቦች ለመሙላትና ከራስህ ጋር ለማዋሃድ መሆን ይኖርበታል። በእያንዳንዱ ዕለት ንባብህን ከጨረስህ በኋላ ባነበብከው ሐሳብ ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ከዚህ በፊት ከምታውቀው ነገር ጋር አወዳድረው። እንዲህ ማድረግህ ጥልቀት ያለው ማስተዋል እንዲኖርህና አድናቆትህ እንዲጨምር ያስችልሃል።—መዝሙር 143:5

አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስን ከየት ጀምሬ ባነብ ይሻለኛል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እርግጥ ከዘፍጥረት ልትጀምር ትችላለህ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንበብ የሚጀምሩ አንዳንድ ሰዎች ንባባቸውን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ከሚናገሩት ወንጌሎች፣ ማለትም ከማቴዎስ፣ ከማርቆስ፣ ከሉቃስና ከዮሐንስ መጀመሩን ቀላል ሆኖ አግኝተውታል። ከዚያም ውብ በሆነ መንገድ ወደተጻፉትና ጥበብን ወደተሞሉት የመዝሙር፣ የምሳሌና የመክብብ መጻሕፍት መሸጋገር ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ሌሎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የማንበብ ጉጉት ያድርብህ ይሆናል። (ከታች ያለውን ተመልከት።) ማንበብ የሚያስፈልግህ በተለምዶ አዲስ ኪዳን እየተባለ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻ ነው የሚሉ ሰዎችን የተሳሳተ አስተሳሰብ አትቀበል። ‘ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውና ጠቃሚ እንደሆኑ’ አስታውስ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይበልጥ ውጤታማ የሆነው ዘዴ ርዕስ በርዕስ መመርመር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝባዊ አገልግሎታቸው ላይ የሚጠቀሙበት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ “የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?”፣ “አምላክ የሚቀበለው አምልኮ” እና “ሙታን የት ናቸው?” እንደሚሉት ያሉ ርዕሶችን አካትቶ ይዟል።—በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስን ርዕስ በርዕስ ማንበብ

የሕይወት አጀማመርና የሰው ልጅ በኃጢአት የወደቀበት ሁኔታ ዘፍጥረት

የጥንቷ እስራኤል አመሠራረት ከዘፀአት እስከ ዘዳግም

ልብ የሚመስጡ ታሪኮች ከኢያሱ እስከ አስቴር

ስሜት ቀስቃሽ ግጥሞችና መዝሙሮች ኢዮብ፣ መዝሙርና ማሕልየ መሓልይ

ለኑሮ ጠቃሚ የሆነ ጥበብ የያዙ መጻሕፍት ምሳሌና መክብብ

ትንቢትና የሥነ ምግባር መመሪያ የያዙ መጻሕፍት ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ እና ራእይ

የኢየሱስ ሕይወትና ያስተማራቸው ትምህርቶች ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ

የክርስትና መመሥረትና መስፋፋት የሐዋርያት ሥራ

ወደ ጉባኤዎች የተላኩ ደብዳቤዎች ከሮሜ እስከ ይሁዳ