የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ያለብኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ያለብኝ ለምንድን ነው?
ከሁለት ጓደኞችሽ ጋር በትምህርት ቤታችሁ ካፊቴሪያ ውስጥ ምግብ እየተመገባችሁ ነው እንበል። ከመካከላችሁ አንዷ፣ የሆነን ልጅ ትኩር ብላ እየተመለከተችው ነው።
ከዚያ አንደኛዋ “ልጁ በጣም ወዶሻል፤ አስተያየቱ ራሱ ያስታውቃል። ዓይኑን እኮ ከአንቺ ላይ መንቀል አልቻለም!” አለችሽ።
ሌላኛዋ ደግሞ ወደ አንቺ ጠጋ ብላ “ደስ የሚለው የሴት ጓደኛ የለውም!” በማለት ሹክ ትልሻለች።
ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ “ጓደኛ ያለኝ መሆኑ ነው እንጂ ዛሬ አያመልጠኝም ነበር!” አለች።
ቀጥላም መቼም ቢሆን መስማት የማትፈልጊውን ነገር ተናገረች።
“ለመሆኑ የወንድ ጓደኛ የማትይዥው ለምንድን ነው?”
መጀመሪያውኑም ቢሆን እንዲህ ያለው ጥያቄ እንደሚነሳ ታውቆሻል። እውነቱን ለመናገር አንቺም የወንድ ጓደኛ ቢኖርሽ ደስ ይልሻል። ይሁንና ለማግባት ዝግጁ ከመሆንሽ በፊት የወንድ ጓደኛ መያዝ ጥሩ እንዳልሆነ ተነግሮሻል። ባይሆንማ ኖሮ . . .
ሁለተኛዋም ልጅ ቀበል አድርጋ “በሃይማኖትሽ ምክንያት ነው አይደል?” ብላ ጠየቀችሽ።
በልብሽ ‘ምን እያሰብኩ እንደነበር አወቀች እንዴ?’ አልሽ።
ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ “አንቺ ደግሞ ነጋ ጠባ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትያለሽ። ምናለበት አንዳንዴ እንኳ ዘና ብትዪ?” በማለት አሾፈችብሽ።
ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች እንዲህ ያለው ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። አንተስ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ለመከተል ጥረት በማድረግህ ጓደኞችህ አሹፈውብህ አያውቁም? ታዲያ ምላሽ የሰጠኸው እንዴት ነበር?
▪ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያለህን አቋም በድፍረት ተናገርክ?
▪ ፈራ ተባ እያልክ ስለምታምንባቸው ነገሮች የምትችለውን ያህል ለማስረዳት ሞከርክ?
▪ ወይስ የትምህርት ቤት ጓደኞችህ ትክክል እንደሆኑና አንድ ነገር እንደቀረብህ ተሰማህ?
‘የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል በእርግጥ ጥቅም አለው?’ የሚል ጥያቄ መጥቶብህ ያውቃል? ዲቦራ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ያለ ጥያቄ ተፈጥሮባት ነበር። * እንዲህ ብላለች:- “እኩዮቼ የፈለጉትን ነገር ማድረግ ይችላሉ። ምንም ቢያደርጉ የሚጠይቃቸው ሰው ያለ አይመስልም። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ደግሞ የማያፈናፍኑ ይመስላሉ። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ያላቸው ነፃነት ያስቀናኝ ነበር።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያላቸውን ጠቀሜታ መጠራጠሩ ስህተት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው አሳፍ አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር ጠቃሚ መሆኑን የተጠራጠረበት ጊዜ ነበር። አሳፍ “ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣ በዐመፀኞች መዝሙር 73:3, 13
ቀንቼ ነበር” በማለት ጽፏል። እንዲያውም “ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!” እስከማለት ደርሶ ነበር።—በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አምላክ፣ ሰዎች የእሱን መመሪያ መከተላቸው ያለውን ጠቀሜታ ላይገነዘቡ እንደሚችሉ ያውቃል። የአሳፍ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲመዘገብ ያደረገው ለዚህ ነው። በመጨረሻ ግን አሳፍ የአምላክን ሕጎች መታዘዝ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገንዝቧል። (መዝሙር 73:28) አሳፍ እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነው? ጠቢብ ስለነበረ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ያደረገው መከራ ስለደረሰበት ሳይሆን ከሌሎች ስህተት በመማሩ ነው። (መዝሙር 73:16-19) አንተስ የአሳፍን ምሳሌ መኮረጅ ትችል ይሆን?
ከሌሎች ስህተት መማር
ከአሳፍ በተቃራኒ ንጉሥ ዳዊት የአምላክን መመሪያዎች ችላ የሚሉ ሰዎች ከባድ ችግር እንደሚያጋጥማቸው የተገነዘበው በሕይወቱ ከደረሰበት መከራ ነው። ዳዊት ከአገልጋዩ ሚስት ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ሁኔታውን ለመደበቅ ሞከረ። በዚህም ምክንያት አምላክንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን የጎዳ ሲሆን እሱ ራሱም በከባድ ጭንቀት ተውጧል። (2 ሳሙኤል 11:1 እስከ 12:23) ይሖዋ፣ ዳዊት ንስሐ ከገባ በኋላ የተሰማውን ስሜት በመዝሙር እንዲገልጽ በመንፈሱ ያነሳሳው ሲሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይህ መዝሙር እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። (መዝሙር 51:1-19፤ ሮሜ 15:4) ስለዚህ ከሌሎች ስህተት መማር ጥበብ ከመሆኑም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረታታው ጉዳይ ነው።
በአንድ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ ብለው የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን ሐሳብ መመልከትህ የአሳፍን ምሳሌ እንድትኮርጅና ዳዊት የሠራውን ዓይነት ስህተት ከመፈጸም እንድትርቅ ይረዳሃል። ከተለያዩ አገራት የተውጣጡት እነዚህ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል። ልክ እንደ ዳዊት እነሱም ከኃጢአታቸው ንስሐ በመግባት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም መያዝ ችለዋል። (ኢሳይያስ 1:18፤ 55:7) እስቲ ምን እንዳሉ ተመልከት።
ንቁ!:- በአስተሳሰባችሁና በድርጊታችሁ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ምንድን ነው?
ዲቦራ:- “ትምህርት ቤት ውስጥ ሰዉ በሙሉ የወንድና የሴት ጓደኛ ያለው ከመሆኑም በላይ ሁሉም ሲታይ ደስተኛ ይመስላል። ከእነሱ ጋር በምሆንበት ጊዜ ሲሳሳሙና ሲተቃቀፉ ስመለከት የቅናትና የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል። ብዙውን ጊዜ ስለወደድኩት ልጅ ቁጭ ብዬ በማሰብ ረጅም ሰዓት አሳልፋለሁ። ይህ ደግሞ ከእሱ ጋር ለመሆን ያለኝን ፍላጎት የጨመረው ከመሆኑም በላይ ይህን ፍላጎቴን ለማሟላት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዳልል ገፋፍቶኛል።”
ማይክ:- “የጾታ ስሜትን የሚያነሳሱ ጽሑፎችን አነብ እንዲሁም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እከታተል ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ስለ ጾታ ግንኙነት ማውራቴ የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም የነበረኝን ፍላጎት ይበልጥ አነሳሳው። ከዚያም ከአንዲት ልጅ ጋር ብቻችንን ስንሆን የጾታ ግንኙነት እስካልፈጸምን ድረስ የፈለግነውን ነገር ማድረግ እንደምንችል ተሰማኝ፤ የጾታ ግንኙነት የምፈጽምበት ደረጃ ላይ ሳልደርስ ማቆም እንደምችል አስቤ ነበር።”
አንድሪው:- “በኢንተርኔት የሚሰራጩ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ልማድ የነበረኝ ከመሆኑም በላይ የአልኮል መጠጦችን በብዛት መጠጣት ጀመርኩ። እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ደንታ ከሌላቸው ልጆች ጋር ጭፈራ ቤት መሄድ ጀመርኩ።”
ትሬሲ:- “የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ከመሆን ሌላ የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት መሆኑን ባውቅም ያን ያህል ጥላቻው አልነበረኝም። ከማግባቴ በፊት የጾታ ግንኙነት እፈጽማለሁ ብዬ አላሰብኩም፤ ይሁንና ስሜቴ አስተሳሰቤን አዛባው። ለተወሰነ ጊዜ ሕሊናዬ ደንዝዞ ስለነበር ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማኝም ነበር።”
ንቁ!:- ይህ ያሳለፋችሁት ሕይወት ደስታ አስገኝቶላችኋል?
ዲቦራ:- “መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ነፃነት ተሰምቶኝ የነበረ ሲሆን እኩዮቼ የሚያደርጉትን ሁሉ ማድረግ በመቻሌ ተደስቼ ነበር። ይህ ደስታዬ ግን ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። በሥነ ምግባር እንደቆሸሽኩ፣ ንጽሕናዬን እንዳጣሁና ባዶ እንደሆንኩ ተሰማኝ። መልሼ ማግኘት የማልችለውን ድንግልናዬን በማጣቴ ከፍተኛ የጸጸት ስሜት አደረብኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ምንም ነገር አይደርስብኝም ብዬ አስቤ ነበር ማለት ነው?’ እያልኩ በተደጋጋሚ ራሴን እጠይቅ ነበር። በጣም ያስጨንቀኝ የነበረው ግን ‘የይሖዋን ፍቅራዊ መመሪያዎች ችላ ያልኩት ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ነው።”
ማይክ:- “አንዱ የሰውነቴ ክፍል በድን የሆነ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ጀመር። ያደረግኳቸው ነገሮች በሌሎች ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ ለመርሳት ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም አልተሳካልኝም። ራሴን ለማስደሰት ስል ሌሎችን መጉዳቴን ሳስብ በጣም
ይሰማኛል። እንቅልፍ የሚባል ነገር በዓይኔ አልዞር አለ። ውሎ አድሮ ደስታዬ እየጠፋ ሄዶ የተረፈኝ ነገር ሐዘንና ኀፍረት ብቻ ሆነ።”አንድሪው:- “መጥፎ ድርጊቶችን አንድ ጊዜ ከፈጸምኩ በኋላ እነዚያን ነገሮች ዳግመኛ መፈጸም እየቀለለኝ መጣ። ያም ሆኖ ግን ከፍተኛ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ስለነበር ራሴን ጠልቼው ነበር።”
ትሬሲ:- “ችግር ያጋጠመኝ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በጾታ ብልግና ምክንያት የወጣትነት ሕይወቴ ተበላሸ። ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ዓለማችንን የምንቀጭ መስሎኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንዳሰብኩት አልሆነም። የተረፈን ነገር ቢኖር ሐዘን፣ መከራና ሥቃይ ብቻ ነው። ‘ምናለ የይሖዋን ምክር በተከተልኩ ኖሮ’ በሚል ቁጭት ሌሊቱን ሙሉ ሳለቅስ አድር ነበር።”
ንቁ!:- የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ለሚሰማቸው ወጣቶች ምን ምክር ትሰጣላችሁ?
ዲቦራ:- “የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ ካላችሁ ጥሩ ሕይወት አትመሩም። ይሖዋ ምክሮቹን ብትከተሉ ምን እንደሚሰማው አስቡ። እንዲሁም መመሪያዎቹን ችላ ማለታችሁ ስለሚያስከትለው መዘዝ ቆም ብላችሁ አሰላስሉ። የምታደርጉት ነገር እናንተን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይነካል። የአምላክን መመሪያዎች ችላ የምትሉ ከሆነ ራሳችሁን ትጎዳላችሁ።”
ማይክ:- “እኩዮቻችሁ የሚመሩት ሕይወት እንዲያው ከላይ ሲታይ ማራኪ እንደሚመስል አይካድም። ሆኖም ማንኛውንም ነገር ከማድረጋችሁ በፊት ምን ሊያስከትልባችሁ እንደሚችል አስቡ። ይሖዋ ከሰጣችሁ በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎች መካከል ክብራችሁና ንጽሕናችሁ ይገኙበታል። ራሳችሁን ባለመግዛታችሁ ምክንያት እነዚህን ስጦታዎች አሽቀንጥራችሁ ጣላችሁ ማለት ራሳችሁን በርካሽ ሸጣችሁ ማለት ነው። ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ወላጆቻችሁንና ሌሎች የጎለመሱ ሰዎችን አማክሯቸው። ስህተት ከሠራችሁ ጉዳዩን በግልጽ ለመናገርና ሁኔታውን ለማስተካከል ፈጣኖች ሁኑ። ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ካከናወናችሁ እውነተኛ ሰላም ይኖራችኋል።”
አንድሪው:- “ተሞክሮ የሚጎድላችሁ ከሆነ እኩዮቻችሁ የሚመሩት ሕይወት አስደሳች እንደሆነ ይሰማችኋል። የእነሱ አመለካከት ሊጋባባችሁ ስለሚችል ጓደኞቻችሁን በጥበብ ምረጡ። በይሖዋ በመታመን ከጸጸት መዳን ትችላላችሁ።”
ትሬሲ:- “‘እንዲህ ያለው ሁኔታ በእኔ ላይ አይደርስም’ ብላችሁ አታስቡ። እናቴ፣ የምከተለው ጎዳና ጉዳት እንደሚያስከትልብኝ ቁጭ አድርጋ በግልጽ ነግራኛለች። በወቅቱ በጣም የተበሳጨሁ ከመሆኑም ሌላ ከእሷ የተሻለ እንደማውቅ ተሰምቶኝ ነበር። ሐቁ ግን እንደዚያ አልነበረም። የይሖዋን መመሪያዎች ተከተሉ እንዲሁም እንደዚያ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ተቀራረቡ። ይበልጥ ደስተኛ መሆን የምትችሉት እንዲህ ካደረጋችሁ ነው።”
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በምን ትመስሏቸዋላችሁ? በካቴና ወይስ በመኪና ወንበር ቀበቶ?
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ለመከተል በመጣርህ ምክንያት እኩዮችህ ቢያፌዙብህ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘እነዚህ ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕግጋት መመራት የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን አንብበው ያውቃሉ? የአምላክን ሕግ መታዘዝ ጥቅም እንዳለው ተገንዝበዋል? እነዚህን ሕጎች ችላ ማለት የሚያስከትለውን መዘዝ በቁም ነገር አስበውበታል? ወይስ የሚከተሉት የብዙኃኑን አመለካከት ነው?’
ምናልባት ‘ብዙኃኑን የመከተል’ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች ታውቅ ይሆናል። (ዘፀአት 23:2) ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ አትፈልግም? ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነው የአምላክ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ እወቁ’ በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው። (ሮሜ 12:2) ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ስለሆነ አንተም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ መክብብ 11:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት መመሪያዎች አንተን የሚጠቅሙ ናቸው። እርግጥ ነው፣ እነዚህን ሕጎች ነፃነት እንደሚያሳጣ ካቴና አድርገህ ትመለከታቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ተሳፋሪዎችን ከአደጋ እንደሚጠብቅ የመኪና ወንበር ቀበቶ ናቸው።
በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ። በውስጡ የሰፈሩትን መመሪያዎች የምትከተል ከሆነ ይሖዋን የምታስደስት ከመሆኑም በላይ ራስህም ትጠቀማለህ።—ኢሳይያስ 48:17
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ቋሚ አምድ ሥር የወጡ ሌሎች ርዕሶችንም ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.17 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል አስቸጋሪ እንዲሆንብህ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?
▪ የአምላክን መመሪያ መከተል በጣም ጠቃሚ የሆነ የሕይወት መንገድ መሆኑን ራስህን ማሳመን የሚኖርብህ ለምንድን ነው?