ለመንሸራተት ከሚያስችል “ምቹ ማዕበል” የበለጠ ነገር
ለመንሸራተት ከሚያስችል “ምቹ ማዕበል” የበለጠ ነገር
ካርል ሂንትስ ሽወረር እንደተናገረው
የተወለድኩት በ1952 በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩ ኤስ ኤ ሲሆን ያደግኩት ፍሎሪዳ ውስጥ በምትገኘው ኒው ስመርነ ቢች የምትባል ከተማ ውስጥ ነው። ወጣት ሳለሁ የውኃ ላይ ሸርተቴ (surfing) የመጫወት ከፍተኛ ምኞት ነበረኝ። እንዲያውም ይህ ስፖርት ከጊዜ በኋላ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ ነበር።
በ1970 ፓይለት ለመሆን ከነበረኝ ፍላጎት የተነሳ በፍሎሪዳ ግዛት ዴይቶና ቢች በምትባል ከተማ ውስጥ የሚገኝ ኤምብሪ-ሪድል የሚባል የበረራ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። ሆኖም በቬትናም ላይ ጦርነት አውጆ የነበረው የመንግሥታችን ሁኔታ በጣም ያበሳጨኝ ጀመር፤ ምክንያቱም ጦርነቱ ኢፍትሐዊ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። በጊዜው እንደነበሩት ሌሎች ወጣቶች ሁሉ እኔም ሥርዓቱ አንገፍግፎኝ ስለነበር ትምህርቴን አቋርጬ የሂፒዎችን የአኗኗር ዘይቤ መከተል ጀመርኩ። ፀጉሬን አስረዝሜ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዕፅ እወስድ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ሥዕል የመሳልና ፎቶግራፍ የማንሳት ከፍተኛ ተሰጥኦ ካላት ሱዛን ከምትባል ደፋር ልጅ ጋር ተዋወቅሁ። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ በዓመት ውስጥ ከስድስት እስከ ስምንት ወር በፍሎሪዳ የግንባታ ሥራ ከሠራሁ በኋላ የቀረውን ጊዜ በሜክሲኮና በመካከለኛው አሜሪካ በሚገኘው የፓስፊክ የባሕር ዳርቻ ላይ ድንኳን ውስጥ ማሳለፍ እንችላለን የሚል ሐሳብ ነበረኝ።
መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልገን ገባኝ
በሚያምረው ሞቃታማ የባሕር ዳርቻ ላይ ሱዛን የሥዕል ሥራዋን እየሠራችና ፎቶግራፍ እያነሳች እኔ ደግሞ የውኃ ላይ ሸርተቴ እየተጫወትኩ ያለ አንዳች ጭንቀት ያሳለፍነው ሕይወት በእርግጥም የሚያስደስት ነበር። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሕይወታችን እርካታ እንደሌለው እየተገነዘብን መጣን። አንድ የሆነ ነገር እንደጎደለን ተሰማን። ስለዚህ በ1975 አጋማሽ ላይ በኮስታሪካ የፓስፊክ ባሕር ዳርቻ ሳለን መንፈሳዊ እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። በምሥራቁ ዓለም ስላሉ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች የሚያወሱ በወቅቱ ተወዳጅ የነበሩ መጻሕፍትን አነበብኩ።
አነብባቸው የነበሩት መጻሕፍት የሚያስተምሩት ትምህርት እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማስረጃ ይጠቅሱ ስለነበር ለእውነት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ሰዎች በቁም ቅዠት ውስጥ እንዲገቡ በሚያደርግ እንጉዳይ አንድ ያረጀ የኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለወጥኩ። እስከ ምሳ ሰዓት ያለውን ጊዜ የውኃ ላይ ሸርተቴ ስጫወት ከቆየሁ በኋላ ሁልጊዜ ከሰዓት ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ቅዱሴን አነብብ ነበር። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ጉጉት የነበረኝ ቢሆንም የማነበውን ነገር ብዙም መረዳት አልቻልኩም።
“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አሉህ?”
ነሐሴ 1975 እኔና ሱዛን ከኮስታሪካ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እየተጓዝን እያለ ኤልሳልቫዶር ውስጥ መድኃኒት ለመግዛት ወደ አንድ መድኃኒት ቤት ጎራ አልን። ከሚያስተናግደን ሰው ጋር ለመግባባት ተቸግረን ስለነበር፣ መድኃኒት ልትገዛ የመጣች ጄኒ የተባለች አንዲት ልጅ ረዳችን። ይህች ልጅ ስፓንኛ አቀላጥፋ የምትናገር የ16 ዓመት አሜሪካዊት ነች። እሷና ወላጆቿ የይሖዋ ምሥክር እንደሆኑና ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ወደ ኤልሳልቫዶር እንደመጡ ነገረችን።
ጄኒ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አሉህ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“አዎ፣ አለኝ!” በማለት መለስኩላት። ምንም እንኳ ገጽታችን የሂፒዎች ዓይነት ቢሆንም ጄኒ ምንም ሳታመነታ ከወላጆቿ
ጋር ልታስተዋውቀን ወደ ቤቷ እንድንሄድ ጋበዘችን። ወላጆቿ ጆው እና ናንሲ ትሬምብሊ ይባላሉ፤ እኛም ግብዣዋን ተቀበልን። የከሰዓት በኋላውን ጊዜ በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ስንጠይቃቸው ቆየን፤ ጆው እና ናንሲ ለጥያቄዎቻችን መልስ የሰጡበት መንገድ በጣም የሚያስገርም ነበር። መልስ በሚሰጡን ጊዜ ሁሉ “ይህን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ላይ አውጡና አንብቡት” ይሉን ነበር።ሳናውቀው በጣም መሽቶ ስለነበር ቤታቸው እንድናድር ጋበዙን። ሆኖም እኔና ሱዛን በሕግ ስላልተጋባን አንድ ክፍል ውስጥ እንድናድር አልፈቀዱልንም። ማታ ሱዛንና ጄኒ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ለሰዓታት ቆዩ። በውይይታቸው ያልዳሰሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል።
አረንጓዴው መጽሐፍ ቅዱስ
በሚቀጥለው ቀን ከተማውን ለቅቀን ከመውጣታችን በፊት ጆው እና ናንሲ በርከት ያሉ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን፣ ጥቂት መጽሐፎችን እንዲሁም አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጡን። መጽሐፍ ቅዱሱ በወቅቱ በአረንጓዴ ጠንካራ ሽፋን ይታተም የነበረው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ነበር። ጆው መንግሥት አዳራሹን ወስዶ አሳይቶን ነበር። አዳራሹ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚሰበሰቡበት ቀለል ያለ ሕንፃ ነበር። ‘ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም ከማይማሩባቸው ሆኖም አሸብርቀው ከሚታዩት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንዴት የተለየ ነው’ ብዬ አሰብኩ።
ያን ዕለት ድንበሩን አልፈን ወደ ጓቲማላ ከመግባታችን በፊት ፍተሻ ጣቢያ ላይ በቆምንበት ጊዜ አረንጓዴው መጽሐፍ ቅዱስ በፍተሻ ሠራተኞቹ ላይ ትንሽ ግራ መጋባት ፈጥሮባቸው ነበር። መጽሐፉን የሚያዩት ብዙውን ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች እጅ ነው። እኛ ደግሞ ፈጽሞ የይሖዋ ምሥክር አንመስልም። ገጽታችን የይሖዋ ምሥክር እንደሆንን ባያሳይም እንኳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንድንሄድ ፈቀዱልን። ይህ ሁኔታ ግራ አጋባን፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ አደንዛዥ ዕፅና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲሉ መኪናችንንና ጓዛችንን ይፈትሹ ነበር። ስለዚህ አረንጓዴውን መጽሐፍ ቅዱስ ምትሐታዊ ኃይል እንዳለው አድርገን ማየት ጀመርን።
መጽሐፍ ቅዱሱንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ማንበባችንን ስንቀጥል ስለ አምላክ እውነቱን እንዳገኘን ተረዳን። ሜክሲኮ ውስጥ በመኪናችን እየተጓዝን ሳለ በጣም በምወደው ፖርቶ ኤስኮንዲዶ በሚባል ቦታ ላይ ለሁለት ሳምንት የውኃ ላይ ሸርተቴ ለመጫወት ጓጉቼ ነበር። የውኃ ላይ ሸርተቴ ለመጫወት የሚያስችል “ምቹ ማዕበል” በሚገኝበት በዚህ ቦታ ላይ እስኪወጣልኝ ድረስ ከተዝናናሁ በኋላ ወደ ፍሎሪዳ ተመልሼ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን ቆርጬ ነበር።
ከዚያ በኋላ ያሉትን ሁለት ሳምንታት የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ በውኃ ላይ በመንሸራተት የከሰዓት በኋላውን ጊዜ ደግሞ በባሕሩ ዳርቻ ሆኜ መጽሐፍ ቅዱሴንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን በማንበብ አሳለፍኩ። አንድ ቀን እያነበብኩ እያለ አረንጓዴው መጽሐፍ ቅዱስ የአንዲትን የስምንት ዓመት ልጅ ትኩረት ሳበ። ከዚያም ልጅቷ አመሻሹ ላይ አንድ ቦታ ይዣችሁ ካልሄድኩ ብላ ወተወተችን። የት ይዛን ልትሄድ እንደፈለገች ሊገባን ባይችልም ከአረንጓዴው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተረድተን ነበር። ለመሄድ ፈቃደኞች እንዳልሆንን ብንገልጽላትም ልጅቷ ግን በየጊዜው መጠየቋን አላቋረጠችም። በመጨረሻ አንድ ቀን አብረናት ለመሄድ ወሰንን። የወሰደችን ከቀርከሃ ወደተሠራና የሣር ክዳን ወዳለው አንድ አነስተኛ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ነበር። እዚያ የነበሩት በሙሉ የድሮ ወዳጆቻቸውን ያገኙ ይመስል እጃችንን በመጨበጥና በማቀፍ ሰላም አሉን።
ሁሉም ተሰብሳቢዎች በነበራቸው ግሩም ጠባይ ተደነቅን። አንዳንድ ልጆች ከዚያ በፊት እንደ እኛ ያለ ረጅም ወርቃማ ፀጉር ያላቸው ሰዎች አይተው ስለማያውቁ ነው መሰለኝ፣ ትኩር ብለው ያዩን ነበር። ወላጆቻቸው ስብሰባውን በትኩረት እንዲከታተሉ በተደጋጋሚ ጠቆም ያደርጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ የመጀመሪያችን በሆነው በዚህ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ የረዳን እንደነሱ ባለች ትንሽ ልጅ ነው።
ይሖዋን ለማገልገል ቆረጥን
በጣም ምቹ በሆነው ማዕበል ላይ ለሁለት ሳምንታት እየተንሸራተትኩ ስዝናና ከቆየሁ በኋላ መንሸራተቻዬን በመሸጥ በቀጥታ ወደ ፍሎሪዳ አቀናን። እዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርን ሲሆን በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠን ስለነበር አብረን መኖራችንንም ሆነ ከቀድሞ ጓደኞቻችን ጋር የነበረንን የተቀራረበ ግንኙነት አቆምን። እኔ ጢሜን ተላጨሁ እንዲሁም ፀጉሬን ተስተካከልኩ። ሱዛን ደግሞ ጥቂት ቀሚሶችን ገዛች። ከአራት ወር በኋላ የተጋባን ሲሆን ሚያዝያ 1976 አምላክን ለማገልገል መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን።
አሁን ሕይወታችን ዓላማ ያለው ነው። ላገኘናቸው በረከቶች ሁሉ ይሖዋን ለማመስገን ስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወደሆነ አገር ሄደን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ከፍተኛ ጉጉት ነበረን። ሆኖም የጉባኤያችን ሽማግሌዎች “አሁን አትሂዱ። እዚያ ላሉት ልታካፍሏቸው የምትችሉት ነገር እንዲኖራችሁ መጀመሪያ ራሳችሁን በመንፈሳዊ ገንቡ” በማለት መከሩን። እኛም ምክራቸውን ተቀበልን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ማለትም አቅኚዎች ለመሆን ግብ አወጣን።
ሱዛን ጥር 1978 አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። እኔም የዚያን ጊዜ አቅኚነት ለመጀመር ፈልጌ ነበር፤ ሆኖም በዩኒቨርሲቲ ክፍያ ምክንያት ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቄ ነበር። በዚህ ጊዜ አንድ ቀላል የመፍትሔ ሐሳብ መጥቶልኝ ነበር። ያሰብኩት ቤሳ ቤስቲን የለኝም ብዬ ማመልከቻ በማስገባት ከዕዳ ነጻ ከሆንኩ በኋላ አቅኚነት ለመጀመር ነበር።
ነገር ግን ሽማግሌዎች እንዲህ ያለው ሐሳብ ‘በሁሉም መንገድ በሐቀኝነት እንድንኖር’ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር እንደሚጋጭ ገልጸው እንዲህ ያለ ነገር እንዳላደርግ በጥበብ መከሩኝ። (ዕብራውያን 13:18 NW) ስለዚህ ዕዳዎቼን ለመክፈል መሥራቴን ቀጠልኩ። በመጨረሻ መስከረም 1979 እንደ ሱዛን አቅኚ የመሆን ግቤ ላይ ደረስኩ። ከዚያ በኋላ አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ ለሕይወታችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንዲያስችለን በሳምንት ውስጥ ጥቂት ቀናት ብቻ መሥራት ነበረብኝ።
በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል
በአቅኚነት አንድ ዓመት ለማይሞላ ጊዜ አብረን ካገለገልን በኋላ ሚያዝያ 1980 ላይ አንድ ያልጠበቅነው ሐሳብ ቀረበልን። ቀደም ሲል የግንባታ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ በቀረበው ጥሪ መሠረት በቤቴል ማለትም ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገል ማመልከቻ አስገብተን ነበር። በዚህ ጊዜ በ30 ቀን ውስጥ ብሩክሊን ወደሚገኘው ቤቴል ሄደን ሪፖርት እንድናደርግ የሚገልጽ አንድ ደብዳቤ ደረሰን! በአንድ በኩል ግብዣው ቢያስደስተንም በሌላ በኩል ደግሞ የአቅኚነት አገልግሎትን በጣም ወደነው ስለነበረ ሁኔታው አሳዘነን። ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ስለገባን ጉዳዩን ከሁለት ሽማግሌዎች ጋር ተነጋገርንበት። እነሱም በእርግጥ ትልቅ መብት የቀረበልን መሆኑን እንድናስተውል ረዱን። ከዚያም “ሂዱና ለአንድ ዓመት በቤቴል አገልግላችሁ ሞክሩት” በማለት መከሩን። ስለዚህ ያለንን ንብረት በሙሉ በመሸጥ ወደ ብሩክሊን አመራን።
ለሁለት ዓመት ግንባታ ላይ ከሠራሁ በኋላ በሕንፃ ግንባታ ምህንድስና ቢሮ ውስጥ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ፤ እዚህ ክፍል ውስጥ ስለ ዲዛይን አወጣጥ ብዙ ሥልጠና አግኝቻለሁ። ሱዛን በጽሑፍ ጥረዛ ክፍል ለአንድ ዓመት ካገለገለች በኋላ ወደ ግራፊክስ ክፍል ተዛወረች። በየዓመቱ የጋብቻ ቀናችንን በምናከብርበት ጊዜ ያለፈውን ዓመት እንቅስቃሴዎቻችንን እንዲሁም ሁኔታዎቻችንንና ፍላጎቶቻችንን ገምግመን በቤቴል ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብን እንደሆነ እንወስናለን።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግሩም ባሕርያት ያሏቸው አንዳንድ የቅርብ ወዳጆች ማፍራት ችለናል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋንና ዓለም አቀፉን የወንድማማች ኅብረት ይበልጥ ትርጉም ባለው መንገድ ለማገልገል በሚያስችለን በቤቴል ለመቆየት ባደረግነው ውሳኔ ጸንተናል። በ1989 ስፓንኛ ቋንቋ መማር ጀመርን፤ ይህም ብሩክሊን በሚገኝ ስፓንኛ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል አስችሎናል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሁለት የአገልግሎት መስኮች ማለትም በቤቴልና በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የማገልገል ግሩም አጋጣሚ እንዳስገኘልን ይሰማናል።
በአንድ አጋጣሚ ቀደም ሲል የጠቀስኳት ጄኒ ብሩክሊን ቤቴል መጥታ ጠይቃን ነበር፤ በዚህ ወቅት ኤልሳልቫዶር ውስጥ ከእኛ ጋር ልትገናኝ የቻለችበትን አጋጣሚ መስማት መቻላችን በጣም የሚያስደስት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራች ሳለ የሕመም ስሜት ይሰማታል። ወደ ቤት በምትመለስበት ወቅት መድኃኒት ለመግዛት ትወስናለች። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባታውቀውም ከዚያ በፊት መድኃኒት
ወደምትገዛበት መደብር ሳይሆን እኛ ወደነበርንበት መድኃኒት ቤት መጣች።በሌሎች አገሮች ማገልገል
በ1999 አንድ ቀን፣ በቤቴል እኔ የምሠራበት ክፍል የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም “በአካባቢ ግንባታ ቢሮ ውስጥ በአንድ ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት ለሦስት ወር ወደ አውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመሄድ ፈቃደኛ ነህ?” የሚል ያልታሰበ ጥያቄ አቀረበልኝ።
“አዎ” በማለት ያለ ምንም ማቅማማት መለስኩለት። ብዙም ሳይቆይ ወደ አውስትራሊያ የሄድን ሲሆን እዚያም ለሦስት ዓመት አገልግለናል። በምሥራቅ እስያና በደቡብ ፓስፊክ አካባቢ ለሚገኙ በርካታ አገሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመሥራት ንድፍ በማውጣቱ ሥራ ላይ እርዳታ ማበርከት መቻሌ አስደስቶኛል። በ2003 ወደ ብሩክሊን ስንመለስ ሌላ ያልጠበቅነው ነገር ገጠመን። ትልቅ ከተማ ከሆነችው ከሳኦ ፓውሎ ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኘው የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ባለ የአካባቢ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን።
አሁንም ድረስ የምንገኘው እዚህ ነው። ቢሮው በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የሚካሄዱትን የመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች በበላይነት ይቆጣጠራል። ሥራዬ ግንባታዎች ወደሚካሄዱባቸው ቦታዎች በመሄድ ድጋፍ መስጠትንና በፕሮጀክቶቹ ላይ የሚሠሩትን ወንድሞችና እህቶች ማበረታታትን ይጨምራል። በዚህ ወቅት ሱዛንም አብራኝ ትጓዛለች።
ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ማተኮር
አሁንም ቢሆን የውኃ ላይ ስፖርት ያስደስተኛል፤ ሆኖም ለመንሸራተት ከሚያስችል “ምቹ ማዕበል” የበለጠ ነገር አግኝቻለሁ። በመሆኑም ይህን ስፖርት እንደ አንድ መዝናኛ በመቁጠር ተገቢውን ቦታ ለመስጠት ጥረት አደርጋለሁ። ሱዛን በምትሰጠኝ ፍቅራዊ እርዳታ በመታገዝ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ይኸውም በአፍቃሪው አምላካችን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ለማተኮር ጥሬያለሁ።
በአሁኑ ጊዜ በዋነኝነት የሚያሳስበን ጉዳይ ሕይወታችንን እና ችሎታችንን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ እንዲሁም የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ ለማስፋፋት ማዋል ነው። በጣም አስፈላጊው ነገር ይሖዋን የምናገለግልበት ቦታ ሳይሆን በሙሉ ልባችን እሱን ማገልገላችን እንደሆነ ተምረናል።—ቈላስይስ 3:23
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አሁንም ቢሆን የውኃ ላይ ስፖርት ያስደስተኛል፤ ሆኖም ለመንሸራተት ከሚያስችል ‘ምቹ ማዕበል’ የበለጠ ነገር አግኝቻለሁ”
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በውኃ ላይ ስንሸራተት የሚያሳየው ይህ ፎቶግራፍ የበጋ የውኃ ላይ ሸርተቴ ስፖርት ፌስቲቫል ፖስተር ሆኖ አገልግሏል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሂፒዎች ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ መከተሌ እርካታ አላስገኘልኝም
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ:- በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ ስረዳ
በስተቀኝ:- በአሁኑ ጊዜ ከሱዛን ጋር