በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድርን መንከባከብ ያለብን ለምንድን ነው?

ምድርን መንከባከብ ያለብን ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ምድርን መንከባከብ ያለብን ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የፕላኔቷ ምድራችንን ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጉዳት ላይ እየጣሉት መጥተዋል። እንደ አካባቢ ሙቀት መጨመር ያሉ ችግሮች ይበልጥ አሳሳቢ እየሆኑ ስለመጡ ሳይንቲስቶች፣ መንግሥታትና ኢንዱስትሪዎች እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።

እኛስ ምድርን ለመንከባከብ በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለብን? ከሆነ፣ እስከ ምን ድረስ? መጽሐፍ ቅዱስ የምናደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ምድርን የሚጎዳ መሆን እንደሌለበት አጥጋቢ ምክንያቶችን ይሰጠናል። ይሁንና በዚህ ረገድ ሚዛናዊ እንድንሆንም ይረዳናል።

ከፈጣሪያችን ዓላማ ጋር መተባበር

ይሖዋ አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች ውብ የመኖሪያ ስፍራ አድርጎ ሠርቷታል። ሥራውም ሁሉ ‘እጅግ መልካም’ እንደነበር ተናግሯል። በተጨማሪም ሰው ምድርን “እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት” ኃላፊነት ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 1:28, 31፤ 2:15) አምላክ፣ ምድር አሁን ስላለችበት ሁኔታ ምን ይሰማዋል? የሰው ልጆች ምድርን ተገቢ በሆነ መንገድ ባለመያዛቸው እጅግ እንደሚያዝን ግልጽ ነው። በራእይ 11:18 ላይ ‘ምድርን ያጠፏትን የሚያጠፋበት ዘመን እንደሚመጣ’ አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው። ስለዚህ በምድር ላይ ስለተጋረጠው አደጋ ግድ የለሾች መሆን አይገባንም።

አምላክ ‘ሁሉን ነገር አዲስ የሚያደርግበት’ ጊዜ ሲመጣ የሰው ልጅ ያስከተላቸውን ጉዳቶች በሙሉ እንደሚያስተካክል መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። (ራእይ 21:5) ይሁንና አምላክ ያሰበው ጊዜ ሲደርስ ምድርን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ስለሚመልሳት አሁን የምናደርጋቸው ነገሮች ምንም ለውጥ አያመጡም ብለን መደምደም የለብንም። በእርግጥ ለውጥ ያመጣሉ! አምላክ ለምድራችን ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳለንና ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ እንደምንደግፍ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

ምድር ንጹሕ እንድትሆን የበኩላችንን ማድረግ

የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የተወሰነ መጠን ያለው ቆሻሻ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ቆሻሻ በማስወገድ አየሩ፣ ውኃውና አፈሩ ንጹሕ እንዲሆን የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ ዑደቶችን በጥበብ አዘጋጅቷል። (ምሳሌ 3:19) የምናደርጋቸው ነገሮች ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ሂደቶች ጋር የሚስማሙ መሆን ይገባቸዋል። ስለዚህ በምድር ላይ ለሚደርሰው ጉዳት መባባስ አስተዋጽኦ እንዳናደርግ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። እንዲህ ያለው ጥንቃቄ ባልንጀሮቻችንን ወይም በአጠቃላይ ሰዎችን እንደራሳችን እንደምንወድ የሚያሳይ ነው። (ማርቆስ 12:31) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተፈጸመ አንድ ግሩም ምሳሌ እንመልከት።

አምላክ እስራኤላውያን “ከሰፈር ውጭ” ዐይነ ምድር ከወጡ በኋላ አፈር እንዲመልሱበት አዟቸው ነበር። (ዘዳግም 23:12, 13) ይህ ደግሞ ሰፈሩ ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ዐይነ ምድሩን ወደ ብስባሽነት የመቀየሩን ሂደት ያፋጥነዋል። በተመሳሳይም ዛሬ እውነተኛ ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት ቆሻሻ በፍጥነትና በተገቢው መንገድ ለማስወገድ ጥረት ያደርጋሉ። መርዛማ የሆኑ ነገሮችን ስናስወግድ ልዩ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።

ብዙ ተረፈ ምርቶች በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። በምንኖርበት አገር ውስጥ ተረፈ ምርቶች እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያዙ ሕጎች ካሉ እነዚህን ሕጎች መታዘዛችን “የቄሣርን ለቄሣር” እንደሰጠን የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 22:21) ተረፈ ምርቶችን እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል ተጨማሪ ጥረት ሊጠይቅ ይችላል፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ጥረት ማድረጋችን ምድር ምንጊዜም ንጹሕ እንድትሆን ያለንን ፍላጎት ያሳያል።

የተፈጥሮ ሀብቶችን አለማባከን

የምግብ፣ የመጠለያና የነዳጅ ፍላጎታችንን በማሟላት ሕይወታችንን ለማቆየት የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠቀም የግድ ነው። እነዚህን ሀብቶች ጥቅም ላይ የምናውልበት መንገድ በእርግጥ ከአምላክ እንዳገኘናቸው ስጦታዎች አድርገን የምንመለከታቸው መሆን አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ሥጋ ባማራቸው ጊዜ ይሖዋ ድርጭቶችን በብዛት ሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከመስገብገባቸው የተነሳ ድርጭቶችን ከመጠን በላይ ሰበሰቡ፤ ይህ ሁኔታ ይሖዋ አምላክን በእጅጉ አስቆጥቶታል። (ዘኍልቍ 11:31-33) ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። በመሆኑም ኃላፊነት የሚሰማቸው ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ላለማባከን ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ ደግሞም አባካኝነት የስግብግብነት ምልክት ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች የኃይል አቅርቦትን ወይም ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን እንደፈለጋቸው መጠቀም መብታቸው እንደሆነ ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን አንድን ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት እንደፈለግን ለመጠቀም የሚያስችል አቅም ስላለን ወይም ያ ነገር እንደልብ በመኖሩ ብቻ መባከን አይገባውም። ኢየሱስ ብዙ ቁጥር ያለውን ሕዝብ በተአምር ከመገበ በኋላ የተረፈውን ዓሣና ዳቦ እንዲሰበስቡ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። (ዮሐንስ 6:12) ኢየሱስ አባቱ የሰጠውን ምግብ ላለማባከን ጥንቃቄ አድርጓል።

በምናደርጋቸው ጥረቶች ረገድ ሚዛናዊ መሆን

በአካባቢያችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ምርጫዎች በየዕለቱ እናደርጋለን። ይሁንና ምድራችንን የሚያበላሽ ምንም ዓይነት ነገር ላለማድረግ ስንል ራሳችንን ከማኅበረሰቡ በማግለል የጽንፈኝነት አካሄድ መከተል ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ እንዲህ ያለውን አመለካከት አያበረታታም። እስቲ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ተመልከት። ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አኗኗሩ ከሌላው ሰው የተለየ አልነበረም፤ ይህም አምላክ የሰጠውን የስብከት ሥራ ከግብ ለማድረስ አስችሎታል። (ሉቃስ 4:43) በተጨማሪም ኢየሱስ ፖለቲካ በጊዜው የነበሩትን ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ይጠቅማል የሚል እምነት ስላልነበረው እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ እጁን ከማስገባት ተቆጥቧል። እንዲያውም “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” በማለት በግልጽ ተናግሯል።—ዮሐንስ 18:36

ይሁንና የምንገዛቸው የቤት ቁሳቁሶች፣ የምንጠቀምባቸው የመጓጓዣ ዓይነቶችና የመዝናኛ ምርጫችን አካባቢያችንን ይበክሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ቆም ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች በአካባቢ ላይ እምብዛም ጉዳት የማያስከትሉ ምርቶችን ለመግዛት ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ ብክለትን በሚያስከትሉ ወይም የተፈጥሮ ሀብት በእጅጉ እንዲባክን በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

አንድ ሰው ስለ አካባቢ ጥበቃ ያለውን አመለካከት ሌሎች እንዲከተሉ መጫን አይኖርበትም። እያንዳንዱ አካባቢም ሆነ ግለሰብ ያለበት ሁኔታ ይለያያል። ያም ሆኖ ግን ሁላችንም በግለሰብ ደረጃ ለምናደርጋቸው ውሳኔዎች ተጠያቂዎች ነን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋል።”—ገላትያ 6:5

ፈጣሪ፣ ሰዎች ምድርን እንዲንከባከቡ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ለዚህ ኃላፊነት ያለን አድናቆት እንዲሁም ለአምላክም ሆነ ለፍጥረት ሥራዎቹ ያለን አክብሮት ምድርን የምንይዝበትን መንገድ በተመለከተ አሳቢነትና ማስተዋል የታከለባቸው ውሳኔዎችን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ አምላክ በምድር ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል እርምጃ ይወስዳል?—ራእይ 11:18

▪ አምላክ ምድርን በተመለከተ ለሰው ልጆች ምን ኃላፊነት ሰጥቷል?—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15

▪ ኢየሱስ ክርስቶስ አባካኝነትን በማስወገድ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?—ዮሐንስ 6:12