ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
ጋብቻ ማዕበሉን መቋቋም ይችል ይሆን? (ሐምሌ 2006) የንቁ! መጽሔት የዘወትር አንባቢ ነኝ። የካቶሊክ እምነት ተከታይ ብሆንም መጽሔታችሁ በጣም አስደሳችና ትምህርት ሰጪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይሁን እንጂ “በ1983 ቤተ ክርስቲያኗ የጋብቻ ጥምረትን በተመለከተ የነበራትን ሕግ ማላላቷ ካቶሊኮች በቀላሉ እንዲፋቱ በር ከፍቷል” በሚለው ሐሳብ እንዳልተስማማሁ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።
ጄ. ቪ. ኤም.፣ ዛምቢያ
የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- ይህን ስንል ቤተ ክርስቲያኒቱ ትመራበት በነበረው የ1983ቱ ሕግ ላይ የተደረጉትን አንዳንድ ለውጦች መጥቀሳችን ነበር። እነዚህ ለውጦች በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ማርክ ፒቫሮነስ እንደተናገሩት፣ በ1968 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የፈረሱት ጋብቻዎች ቁጥር 338 ብቻ ነበር። በ1990 ግን ቁጥሩ ወደ 62,824 አሻቅቧል። ቁጥሩ ሊጨምር የቻለው ለምንድን ነው?
ኤድዋርድ ፒተርስ የተባሉ የካቴድራል ጠበቃ እንዲህ ብለዋል:- “ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትመራበት በነበረው ሕግ ላይ ሥር ነቀል ለውጦች ተደርገዋል። እነዚህ ለውጦች የፍቺ ማመልከቻዎች የሚቀርቡበትና ውሳኔ የሚያገኙበት ሂደት የተቀላጠፈ እንዲሆን አድርገዋል።” ፒተርስ በሕጉ ላይ የተደረጉትን በርካታ ለውጦች ከጠቀሱ በኋላ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ቫቲካን በሕጉ ላይ ያደረገቻቸው እነዚህ ሁሉ ለውጦች የፍቺ ጥያቄዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ምንም ጥርጥር የለውም።” ዓላማው ምንም ይሁን ምን በሕጉ ላይ ለውጥ መደረጉ ቢያንስ ቢያንስ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ንቁ! መጽሔት የጠቀሰውን ውጤት አስከትሏል፤ ይኸውም ‘ቤተ ክርስቲያኒቱ ካቶሊኮች በቀላሉ እንዲፋቱ በር እንዲከፈት አድርጋለች።’
በእርግጥ ፈጣሪ አለ? (መስከረም 2006) ይህ የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም ድንቅ የሥራ ውጤት ነበር። የቀረቡት የማሳመኛ ነጥቦች ቀላል፣ ጠንካራና ምክንያታዊ ናቸው። መጽሔቱ አንድን ርዕሰ ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ የሚያብራራ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀበት መንገድ በጣም አስደስቶኛል።
ኤ. ቢ.፣ ስፔን
ግሩም በሆነ ሁኔታ ለተዘጋጀው ለዚህ ድንቅ መጽሔት አመሰግናችኋለሁ። የቀረቡት ዘርፈ ብዙ የማሳመኛ ነጥቦችና ማብራሪያዎች ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ ናቸው። ይሖዋ በዚህ መንገድ መወደሱ ተገቢ ነው።
አር. ቢ.፣ ስዊዘርላንድ
ፈጣሪ መኖሩን ለማስረዳት በቀረቡት ቀላልና አሳማኝ ማስረጃዎች ተማርኬያለሁ። የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ፈጠራ መሆኑን በጥላቻ መንፈስ ሳይሆን ሳይንሱ የሚጠይቀውን ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠት በግልጽ ተቀምጧል።
ኤል. ጂ.፣ ፈረንሳይ
ለዘመናት ሐዘንና ደስታ ሲፈራረቅባቸው የኖሩት ሮማዎች (ጥቅምት 2006) ሮማዎችን እወዳቸዋለሁ። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች አሁንም ለእነሱ ጭፍን ጥላቻ አላቸው። ያወጣችሁት ርዕሰ ትምህርት የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ የማያዳላ መሆኑንና ሮማዎችም የእሱ አምላኪዎች የመሆን መብት ማግኘታቸውን ማወቁ እንዴት የሚያጽናና ነው!
ቢ. ቢ.፣ ፈረንሳይ
እኛ ሮማዎች ነን። አባቴ የይሖዋ ምሥክር አይደለም፤ ጽሑፎችን የማንበብ ፍላጎትም የለውም። ነገር ግን ይህን መጽሔት ለማንበብ ፈልጓል። አሁን ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦለታል!
ኤ. ጄ.፣ ፊንላንድ