ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በ2006 “ጋዜጠኞችን” እንዲሁም እንደ ሾፌሮችና አስተርጓሚዎች የመሳሰሉትን “ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች [ጨምሮ በድምሩ] 167 ሰዎች ዜና ለመዘገብ ሲጥሩ ሕይወታቸውን አጥተዋል።” አብዛኞቹ የሚዘግቡት ስለ ወንጀል፣ ምግባረ ብልሹነት ወይም በአንድ አካባቢ ስለተነሳ ግጭት ነበር። ከእነዚህ መካከል አንድ መቶ ሠላሳ ሦስቱ የሞቱት ተገድለው ነው።—ኢንተርናሽናል ኒውስ ሴፍቲ ኢንስቲትዩት፣ ቤልጅየም
▪ በየዓመቱ ከ10 እስከ 14 ቢሊዮን ጊዜ ሊተኮሱ የሚችሉ ጥይቶች የሚመረቱ ሲሆን ይህም “በዓለም ላይ ያለውን እያንዳንዱን ሰው ሁለት ጊዜ ተኩሶ ለመግደል ያስችላል።”—ሮያል ሜልቦርን ኢንስቲትዩት ኦቭ ቴክኖሎጂ፣ አውስትራሊያ
ሰው ሠራሽ የመሬት መናወጦች?
የሰው ልጆች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ከ200 በላይ ኃይለኛ የመሬት መናወጦች እንዲከሰቱ ማድረጋቸውን ዲ ጻይት የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። ከእነዚህ የመሬት መናወጦች ውስጥ ለግማሹ መንስዔ የሆነው ማዕድን የማውጣት ሥራ ነው። ለመሬት መናወጥ ምክንያት የሚሆኑት ሌሎች ነገሮች ደግሞ ከመሬት ውስጥ ጋዝ፣ የነዳጅ ዘይት ወይም ውኃ ለማውጣት የሚደረግ ጥረት እንዲሁም ጥልቅ ወደሆኑ ጉድጓዶች ፈሳሽ ማስገባትና ሰው ሠራሽ ሐይቅ መሥራት ናቸው። በ1989 አውስትራሊያ ውስጥ በኒው ካስል ከተማ በተከሰተው የመሬት መናወጥ ሳቢያ 13 ሰዎች ሲሞቱ 165 ሰዎች ቆስለዋል፤ እንዲሁም ግምቱ 3.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ንብረት ወድሟል። የሳይንስ ሊቃውንት የዚህ መናወጥ መንስዔ ከመሬት ውስጥ የድንጋይ ከሰል ለማውጣት የሚደረገው ጥረት እንደሆነ ይናገራሉ። በዚያ የመሬት መናወጥ ምክንያት የደረሰው ኪሳራ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት በኒው ካስል የድንጋይ ከሰል ማውጣት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከተገኘው አጠቃላይ ገቢ እንደሚበልጥ ተሰልቷል።
በፈረንሳይ የካቶሊክ እምነት የሚገኝበት ሁኔታ
በ1994 በፈረንሳይ ከሚኖሩ ሰዎች 67 በመቶ የሚሆኑት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ዛሬ ይህ አኃዝ ወደ 51 በመቶ እንዳሽቆለቆለ ለ ሞንድ ዴ ሬሊዥዮ የተባለው መጽሔት ይገልጻል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በፈረንሳይ ከሚኖሩት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መካከል ግማሽ ያህሉ እንደ ሠርግ ባሉ ለየት ያሉ ክንውኖች ላይ ለመገኘት ካልሆነ በቀር ፈጽሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም። ሰማንያ ስምንት በመቶ የሚሆኑት አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በቃላቸው እንደሚያውቁት ቢናገሩም 30 በመቶ የሚሆኑት ጨርሶ አይጸልዩም። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ከሆኑት ሰዎች ግማሽ ያህሉ በቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም ይህ ሲባል ግን ያነቡታል ማለት አይደለም።
የልጆች የንግግር ችሎታ መዛባት
“ዘግይተው መናገር የሚጀምሩና የተወሰኑ ቃላትን ብቻ የሚጠቀሙ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ነው” በማለት ቭፕሮስት የተሰኘ የፖላንድ መጽሔት ዘግቧል። “ይህ የሆነው አዋቂዎች ስለማያነጋግሯቸው ነው።” እናቶች በቀን ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በአማካይ 30 ደቂቃ ሲሆን አባቶች ደግሞ “ሰባት ደቂቃ ብቻ” ነው። በመሆኑም ከአምስት ልጆች ውስጥ አንዱ “በወላጆቹ ቸልተኝነት ምክንያት የሚመጣ ከንግግር ችሎታ ጋር የተያያዘ አንድ ዓይነት ችግር ያጋጥመዋል።” በሲሌሲያን ዩኒቨርሲቲ ከንግግር ችሎታ ጋር የተያያዘ ችግር ሐኪምና የቋንቋ ምሑር የሆኑት ሚካው ቢትኒዮክ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃሉ:- “እንደዚህ ዓይነት ልጆች ችግሩ ሥር ከመስደዱ በፊት እርዳታ ካላገኙና በዚያው ከቀጠሉ ይህ እክል በትምህርት ቤትም ሆነ ትልልቅ ሰዎች በሚሆኑበት ጊዜ ችግር ያስከትልባቸዋል።”
በጃፓን በአጉል እምነት መጠቀም
በጃፓን በተከለከለ ቦታ ላይ ቆሻሻ መጣል ከፍተኛ ችግር ሆኗል። በቀን እየተዘዋወሩ የሚጠብቁ የጸጥታ ኃይሎችም ይህን ተግባር ሊያስቆሙት አልቻሉም። ሰዎች ቆሻሻቸውን በማታ እያመጡ ይጥላሉ። አሁን ግን የአካባቢው ባለሥልጣኖች ቶሪ በመባል የሚታወቁትን የሺንቶ ሃይማኖት ቅዱስ ሥፍራዎች በር እንዲመስሉ ተደርገው የተሠሩ ቀይ የእንጨት በሮች በማቆም በአጉል እምነት ተጠቅመው ይህን ተግባር ለመከላከል እየጣሩ ነው። አሳሂ ሺምቡን የተሰኘው ጋዜጣ “ጽንሰ ሐሳቡ በጣም ቀላል ነው” ይላል። “በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ቶሪን እንደ ቅዱስ ነገር ስለሚቆጥሩት በአቅራቢያው ቆሻሻ መጣል እርግማን ያመጣል ብለው ያምናሉ።” እንደተጠበቀውም ሰዎች ከዚያ ወዲህ በቶሪ አካባቢ ቆሻሻ መጣል አቆሙ። ጋዜጣው “ጥቂት ራቅ ብለው ግን መጣላቸውን አልተዉም” ብሏል።