በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የሆነችው ጋቦን

ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የሆነችው ጋቦን

ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የሆነችው ጋቦን

ጋቦን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሞቃታማ በሆነው የባሕር ዳርቻ ላይ ዝሆኖች ቅጠላ ቅጠል ሲበሉ፣ ጉማሬዎች እንዲሁም በርከት ያሉ ዓሣ ነባሪዎችና ዶልፊኖች ሲዋኙ ይታያሉ! በአፍሪካ የጠረፍ አካባቢ በሚገኙ እስከ 100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርዝመት ባላቸው የባሕር ዳርቻዎች ላይ እንዲህ ዓይነቶቹን ትዕይንቶች ማየት የተለመደ ነው።

ይህ ልዩ የሆነ አካባቢ ለሰዎች መስህብ የሆነውን ማራኪ ውበቱን ይዞ እንዲቀጥል ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ መስከረም 4, 2002 የጋቦኑ ፕሬዚዳንት ድንግል ውበት ያላቸውን የባሕር ዳርቻዎች ጨምሮ 10 በመቶ የሚሆነው የጋቦን ክፍል በብሔራዊ ፓርክነት እንደሚከለልና ጥበቃ እንደሚደረግለት መግለጻቸው ያስደስታል።

ጥበቃ የሚደረግላቸው እነዚህ አካባቢዎች ወደ 30,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያላቸው ሲሆን ቀልብ የሚስቡ መልክዓ ምድሮችና ማራኪ የሆኑ እንስሳት ይገኙባቸዋል። የጋቦኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ ኦንዲምባ “ጋቦን፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በምድር ላይ ያሉትን የመጨረሻዎቹን አስደናቂ የተፈጥሮ ገጽታዎች ለማየት የሚጎርፉባት የተፈጥሮ መስህብ ትሆናለች” ብለዋል።

እነዚህ ፓርኮች በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? ወደ 85 በመቶ የሚጠጋው የጋቦን ክፍል አሁንም ድረስ በደን የተሸፈነ ሲሆን በዚህ ደን ውስጥ ከሚገኙት የዕፅዋት ዝርያዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት በየትኛውም የምድር ክፍል አይገኙም። ከዚህም በላይ ጥቅጥቅ ያለው ደን በዝቅተኛ አካባቢ ለሚኖሩ ጎሪላዎች፣ ቺምፓንዚዎች፣ የጫካ ዝሆኖችና ዝርያቸው ሊጠፋ ለተቃረቡ ሌሎች እንስሳት ምቹ መኖሪያ ነው። በቅርቡ የተቋቋሙት ፓርኮች ጋቦን የአፍሪካን ብዝሃ ሕይወት በመንከባከብ ረገድ ተጠቃሽ አገር እንድትሆን ያደርጓታል።

ሎአንጎ—ተወዳዳሪ የሌለው የባሕር ዳርቻ

ሎአንጎ ብሔራዊ ፓርክ በአፍሪካ ውስጥ የዱር እንስሳትን መመልከት ከሚቻልባቸው አሉ የተባሉ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ፓርክ ውስጥ በሚገኙት ጨዋማ ባልሆኑት ኩሬዎችና ጥቅጥቅ ባለው ደን አቅራቢያ ተፈጥሯዊ ውበታቸውን የጠበቁ የባሕር ዳርቻዎች አሉ። ይሁንና የሎአንጎን የባሕር ዳርቻዎች ልዩ የሚያደርጓቸው በአካባቢው የሚታዩት እንደ ጉማሬ፣ የጫካ ዝሆን፣ ጎሽ፣ አቦ ሸማኔና ጎሪላ የመሳሰሉት እንስሳት ናቸው።

እነዚህ የዱር እንስሳት ወደ ባሕር ዳርቻው የሚመጡት ለምንድን ነው? ነጣ ብሎ የሚታየው የሎአንጎ አሸዋማ የባሕር ዳርቻ ለጉማሬና ለጎሽ ተስማሚ የግጦሽ ቦታ ነው። ከረሜላ ልጆችን እንደሚስባቸው ሁሉ የጫካ ዝሆኖችም በባሕሩ ዳርቻ ላይ በሚበቅለው ሮንዬ በተባለው የዘንባባ ዛፍ ፍሬዎች ይማረካሉ። እንስሶቹን ከሁሉም በላይ የሚማርካቸው ግን አካባቢው ጸጥታ የሰፈነበት መሆኑ ነው። በአሸዋው ላይ የሚታየው የእንስሶቹ ዱካ ብቻ ነው።

አካባቢው ሰው የማይኖርበት መሆኑ፣ ዝርያቸው ሊጠፋ ለተቃረቡት ቆዳ መሰል ሽፋን ላላቸው የባሕር ኤሊዎች እንቁላላቸውን ለመጣል ምቹ ቦታ ሆኖላቸዋል። ሮዚ ቢ-ኢተርስ የተባሉት የወፍ ዝርያዎች ጎጇቸውን ለመሥራት የሚመርጡት እንዲህ ያለውን ስፍራ ነው። ወፎቹ፣ ማዕበል ሲነሳ ውኃው ከሚደርስበት ቦታ ትንሽ ራቅ ብለው በአሸዋው ውስጥ ጎጇቸውን ይሠራሉ። በበጋ ወራት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሃምፕባክ የተባሉት ዓሣ ነባሪዎች የመራቢያ ጊዜያቸው ሲደርስ ጸጥታ ወደሰፈነበት ወደ ሎአንጎ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ይመጣሉ።

በሎአንጎ የባሕር ዳርቻና ጥቅጥቅ ባለው ደን መካከል ሁለት ትላልቅ ኩሬዎች የሚገኙ ሲሆን ኩሬዎቹ ለአዞዎችና ለጉማሬዎች ተስማሚ መኖሪያ ናቸው። በርካታ ዓሣዎች የሚገኙባቸው እነዚህ ኩሬዎች በማንግሮቭ ዛፎች ተከበዋል። ጭልፊቶችና ዓሣ አዳኝ የሆኑት የአፍሪካ ንስሮች በተንጣለለው ኩሬ ላይ ምግባቸውን ፍለጋ ሲያንዣብቡ ይታያሉ። በቀለማት የተዋቡ የተለያዩ የዓሣ ዓመቴ ዝርያዎች ዓሣ ፍለጋ በባሕሩ ዳርቻ አካባቢ በሚገኘው ጥልቀት በሌለው ውኃ ላይ ሲንሳፈፉ ይታያሉ። ውኃ የሚወዱት ዝሆኖች የሚወዱትን ፍሬ ለመመገብ ኩሬውን በዋና ያቋርጣሉ።

ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ዝንጀሮዎች በዛፎቹ ቅርንጫፎች ላይ ሲንጠላጠሉና በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ቢራቢሮዎች ፀሐያማ በሆነው ገላጣ አካባቢ ሲበሩ ይታያሉ። ፍሩት ባትስ የተባሉት የሌሊት ወፎች ቀኑን በዛፎች ላይ ተኝተው የሚያሳልፉ ሲሆን ሲመሽ ደግሞ የዕፅዋትን ዘር በደኑ ውስጥ የማሰራጨት ሥራቸውን ይያያዙታል። ሰንበርድስ የተባሉት አንጸባራቂ ቀለም ያላቸው ወፎች በጫካው አቅራቢያ ከዛፎቹ አበቦችና ከቁጥቋጦዎች ላይ የአበባ ማር ሲቀስሙ ይታያሉ። በእርግጥም ሎአንጎ “በምድር ወገብ አቅራቢያ ያሉት የአፍሪካ አካባቢዎች ምን እንደሚመስሉ ማየት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ ቦታ” መባሉ ተገቢ ነው።

ጎሪላዎች በብዛት ከሚገኙባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው ሎፔ

በሎፔ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ጥቅጥቅ ያለ ደን ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በፓርኩ ሰሜናዊ ክፍል በሳር የተሸፈኑ ሰፋፊ ሜዳዎችና በወንዝ ዳርቻ ላይ የበቀሉ ችምችም ያሉ ዛፎች ይታያሉ። ተፈጥሮን የሚያደንቁ ጎብኚዎች ጎሪላዎችን፣ ቺምፓንዚዎችን ወይም ማንድሪል የተባሉትን ዝንጀሮዎች ማየት የሚችሉበት ምቹ ቦታ ነው። ወደ 5,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሆነው የተከለለ አካባቢ ውስጥ ከ3,000 እስከ 5,000 የሚደርሱ ጎሪላዎች ይኖራሉ።

በፓርኩ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት ኦገስቲን የተባሉ ሰው ከጎሪላዎች ጋር በተያያዘ በ2002 ያጋጠማቸውን ለየት ያለ ሁኔታ እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “በጫካው ውስጥ እየሄድኩ ሳለ አራት አባላት ካሉት አንድ የጎሪላ ቤተሰብ ጋር ተገናኘሁ። በጀርባው ላይ ብርማ ቀለም ያለው 35 ዓመት ገደማ የሚሆነው ወንድ ጎሪላ ፊት ለፊቴ ቆመ። ጎሪላው ቢያንስ የእኔን ሶስት እጥፍ ያህል ይመዝናል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም ማድረግ እንደሚመከረው ለእሱ ተገዢ መሆኔን በሚያሳይ መንገድ ወዲያውኑ ቁጭ አልኩና አንገቴን አቀርቅሬ መሬት መሬት ማየት ጀመርኩ። ጎሪላው አጠገቤ ተቀመጠና እጁን ትከሻዬ ላይ አሳረፈ። ከዚያም እጄን ይዞ መዳፌን በጥንቃቄ መመልከት ጀመረ። በቤተሰቡ ላይ ምንም ጉዳት እንደማላደርስ ካረጋገጠ በኋላ እየተንጎማለለ ወደ ጫካው ገባ። በዚህ የማይረሳ ቀን እንስሳትን በሚኖሩበት አካባቢ ማግኘት አስደሳች ስሜት እንደሚፈጥር ተገነዘብኩ። ምንም እንኳ ሰዎች ጎሪላዎችን ለምግብነት የሚያድኗቸው ወይም አደገኛ እንስሳት ናቸው በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የሚገድሏቸው ቢሆንም ጎሪላዎች እንክብካቤ ሊደረግላቸው የሚገባ ሰላማዊ እንስሳት ናቸው።”

በሎፔ ፓርክ ውስጥ ማንድሪል የተባሉት ትልልቅ ዝንጀሮዎች በብዛት አንዳንዴም ከአንድ ሺህ በላይ ሆነው በቡድን ይጓዛሉ። እነኚህ በዓለም ከሚገኙት ትላልቅ የማንድሪል መንጋዎች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ከፍተኛ ጫጫታም ያሰማሉ። ከካሜሩን የመጣ አንደ ጎብኚ ከዚህ መንጋ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት የገጠመውን ሲናገር እንዲህ ብሏል።

“አስጎብኚያችን፣ ብዙዎቹ ማንድሪሎች በአንገታቸው ላይ በታሰረላቸው ጠቋሚ መሣሪያ አማካኝነት መንጋው የት እንዳለ ለማወቅ ቻለ። ከዚያም መንጋው ወደሚያልፍበት ቦታ በፍጥነት ሄድንና በቅጠላ ቅጠል ተሸፍነን የመንጋውን መምጣት መጠባበቅ ጀመርን። ለ20 ደቂቃ ያህል የወፎችና የተለያዩ ነፍሳትን ድምፅ ስናዳምጥ ቆየን። የማንድሪል መንጋው በአካባቢው ሲደርስ ይህ ሁኔታ ወዲያውኑ ተለወጠ። የዛፎቹ ቅርንጫፎች ሲሰባበሩ የሚሰማውን ድምፅና የእንስሶቹን ጩኸት ሳዳምጥ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ እየመጣ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። ይሁንና በቅድሚያ በቦታው የደረሱትን [ማንድሪሎች] ስመለከታቸው ፈር ቀዳጅ ወታደሮች ይመስሉ ነበር። ከፊት ከፊት የሚሄዱት ትላልቆቹ ወንዶች በጫካው ውስጥ በፍጥነት ይሹለከለካሉ። ሴቶቹ እና ልጆቹ ደግሞ ከዛፍ ዛፍ እየዘለሉ ይጓዛሉ። በዚህ ወቅት ከትላልቆቹ ማንድሪሎች መካከል አንዱ በድንገት ቆም አለና አካባቢውን በጥርጣሬ ዓይን ይቃኝ ጀመር። በቅርንጫፎቹ ላይ ከሚዘሉት ወጣት ማንድሪሎች መካከል አንዱ ተመለከተንና የማስጠንቀቂያ ድምፅ አሰማ። ማንድሪሎቹ በንዴት እየጮኹ በፍጥነት በመጓዝ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ። አስጎብኚው እንዳለው ከሆነ በአጠገባችን ያለፉት ማንድሪሎች 400 ገደማ ይሆናሉ።”

ከማንድሪሎች የማይተናነስ ድምፅ የሚያሰሙት ቺምፓኒዚዎች ምግብ ፍለጋ በጫካው ውስጥ በፍጥነት ስለሚዘዋወሩ ያሉበትን ማወቅ አዳጋች ነው። በሌላ በኩል ጎብኚዎች ፑቲ-ኖዝድ የሚባሉትን የዝንጀሮ ዝርያዎች ከጫካው አቅራቢያ ባለው በሣር የተሸፈነ ሜዳ ላይ እንደልብ ማየት ይችላሉ። በሎፔ ፓርክ ውስጥ ካሉት እንስሶች መካከል ብቻውን ተነጥሎ መኖር የሚወደው ሰን-ቴልድ የተባለው የዝንጀሮ ዝርያ ሳይሆን አይቀርም። ጋቦን ውስጥ የሚገኘው ይህ ብርቅዬ እንስሳ መኖሩ የታወቀው ከ20 ዓመት ገደማ በፊት ነው።

ቱራኮ እና ሆርን ቢል የተባሉትን ዝርያዎች ጨምሮ በደኑ ውስጥ የሚኖሩት ትላልቅና በቀለማት ያሸበረቁ ወፎች መኖራቸውን ለማሳወቅ ይመስል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይንጫጫሉ። በፓርኩ ውስጥ 400 ገደማ የሚሆኑ የአእዋፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ይህም አእዋፍን ማየት ለሚወዱ ሰዎች የሚስብ ቦታ ነው።

ለተለያዩ ፍጥረታት ምቹ የሆነ መኖሪያ

ጋቦን ውስጥ ከሚገኙት 13 ብሔራዊ ፓርኮች መካከል የተመለከትነው ሎአንጎና ሎፔ የተባሉትን ብቻ ነው። ከእነዚህ ፓርኮች ውስጥ በአንዳንዶቹ የማንግሮቭ ደኖች፣ በሌሎቹ ደግሞ የተለያዩ ዕፅዋት የሚገኙ ሲሆን ፈልሰው ለሚመጡ ወፎች ማረፊያ የሆኑ ፓርኮችም አሉ። የዱር እንስሳት ጥበቃ ማኅበር ባልደረባ የሆኑት ሊ ዋይት እንዲህ ብለዋል:- “ጋቦን በመላ አገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ምርጥ አካባቢዎች እንዲጠበቁ አድርጋለች። እነዚህን አካባቢዎች ምርጥ ያሰኛቸው ስፋታቸው ሳይሆን በውስጣቸው ያለው ነገር ነው። በ2002፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ፍጥረታት ለመጠበቅ የሚያስችል ከብሔራዊ ፓርኮች ጋር የተያያዘ አመቺ አሠራር ተዘርግቷል።”

ፕሬዚዳንት ቦንጎ ኦንዲምባ በግልጽ እንደተናገሩት እቅዱን ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ችግሮችን ማለፍ ይጠይቃል። ፕሬዚዳንቱ እንደሚከተለው ብለዋል:- “እነዚህን የተፈጥሮ መስህቦች ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለንን ሕልም እውን ለማድረግ አሁንም ሆነ ወደፊት ብዙ መሥዋዕቶችን መክፈል እንደሚጠይቅብን ግልጽ ነው።”

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍሪካ

ጋቦን

የጋቦን 13ቱ ብሔራዊ ፓርኮች

ሎፔ ብሔራዊ ፓርክ

ሎአንጎ ብሔራዊ ፓርክ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪና ከአየር ላይ የተነሳ የሎአንጎ ፎቶግራፍ

[ምንጭ]

ዓሣ ነባሪ:- Wildlife Conservation Society

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ማንድሪል (በስተግራ) እና ጎሪላ (በስተቀኝ)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Robert J. Ross