በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በብዙ መንገዶች ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግን ሙት የሆነ ባሕር!

በብዙ መንገዶች ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግን ሙት የሆነ ባሕር!

በብዙ መንገዶች ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግን ሙት የሆነ ባሕር!

እስራኤል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በጨዋማነቱና ዝቅተኛ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በመላው ምድር ተወዳዳሪ የሌለው ባሕር ነው። አንዳንዶች ደግሞ በፈዋሽነቱ የሚተካከለው እንደሌለ ይሰማቸዋል። ባለፉት መቶ ዘመናት የሚገማው ባሕር፣ የዲያብሎስ ባሕር እንዲሁም የአስፋልት ሐይቅ እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የጨው ባሕር እና የዓረባ ባሕር ሲል ይጠራዋል። (ዘፍጥረት 14:3፤ ኢያሱ 3:16) የበርካታ ምሑራንን አመኔታ ያተረፈ አንድ አፈ ታሪክ ሰዶምና ገሞራ የተቀበሩት በዚህ ባሕር ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል። በዚህም ምክንያት የሰዶም ባሕር ይባላል፤ እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ በተባሉት ከተሞች ላይ ስለደረሰው ጥፋት በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ ዋነኛ ባለ ታሪክ በነበረው በሎጥ ስም ይጠራል።—2 ጴጥሮስ 2:6, 7

ከእነዚህ ስያሜዎች አንዳንዶቹ አንድ ሰው ይህ ባሕር ሊታይ የሚገባው ውብ ቦታ እንደሆነ አድርጎ እንዳያስብ ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በዛሬው ጊዜ ሙት ባሕር ወይም የጨው ባሕር ተብሎ የሚጠራውን ይህን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕር ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ይጎርፋሉ። ይህ ባሕር ይህን ያህል ጨዋማ የሆነው ለምንድን ነው? በእርግጥ ሕይወት ያለው ፍጡር የማይገኝበት ሆኖም ውኃው ለጤና ተስማሚ የሆነ ባሕር ነው?

በዝቅተኛ ስፍራ ላይ የሚገኝ በመሆኑና በጨዋማነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ባሕር

ሙት ባሕር የሚገኘው በስተ ደቡብ አቅጣጫ በተዘረጋውና እስከ ምሥራቅ አፍሪካ በሚዘልቀው በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ነው። የዮርዳኖስ ወንዝ ከበስተ ሰሜን ቁልቁል እየተጠማዘዘ ሲወርድ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ በመላው ምድር በዝቅተኛነቱ ተወዳዳሪ ወደሌለውና ከባሕር ወለል በታች 418 ሜትር ጥልቀት ወዳለው ሥፍራ ይደርሳል። በዚህ ወቅት ይህ ወንዝ በግራና በቀኝ በስምጥ ሸለቆ ግድግዳዎች የሚታጠር ሲሆን በስተ ሰሜን የይሁዳ ኮረብቶች፣ በስተ ምሥራቅ ደግሞ በዮርዳኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የሞአብ አምባ ያዋስኑታል።

ይሁን እንጂ ሙት ባሕርን ይህን ያህል ጨዋማ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? በዋነኝነት ማግኒዝየም፣ ሶዲየምና ካልሲየም ክሎራይድ የተባሉትን ማዕድናት የያዙ ጨውነት ያላቸው ንጥረ ነገሮች በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲሁም በሌሎች ጅረቶችና ምንጮች እየታጠቡ ወደ ሙት ባሕር ይገባሉ። የዮርዳኖስ ወንዝ ብቻ በየዓመቱ 8,500,000 ኩንታል ጨው ተሸክሞ እንደሚመጣ ይገመታል። ባሕሩ የሚገኘው በጣም ረባዳማ በሆነ ቦታ ላይ በመሆኑ ከወንዞቹ የሚመጣው ውኃ መውረጃ ስለማያገኝ ይታቆራል። ውኃው ሊጎድል የሚችለው በትነት አማካኝነት ብቻ ነው። ሞቃታማ በሆነ በአንድ የበጋ ቀን ሰባት ሚሊዮን ቶን የሚያክል ውኃ እንደሚተን ይገመታል። ይህም የሐይቁ መጠን የማይጨምረው ለምን እንደሆነ ለመገንዘብ ያስችለናል። ውኃው በትነት ሊቀንስ ቢችልም ጨዉና ሌሎቹ ማዕድናት ግን እዚያው ዘቅጠው ይቀራሉ። በዚህ ምክንያት ሙት ባሕር ከውቅያኖሶች ብዙ እጥፍ የሚበልጥ የጨው ይዘት ያለው ባሕር ሊሆን ችሏል። ከውኃው 30 በመቶ የሚያህለው ጨው ነው።

ከጥንት ጀምሮ ሰዎች እንግዳ በሆኑት የሙት ባሕር ገጽታዎች ሲገረሙ ኖረዋል። አርስቶትል የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ፣ ባሕሩ “በጣም ጨዋማና መራራ ከመሆኑ የተነሳ በውስጡ ምንም ዓሣ እንደሌለ” ሰምቶ ነበር። የጨዉ ይዘት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ተፈጥሯዊ የሆነ የማንሳፈፍ ችሎታ አለው፤ ስለሆነም ዋና የማይችል ሰው እንኳ በውኃው ላይ በቀላሉ ሊንሳፈፍ ይችላል። የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ቨስፔዢያን የተባለ አንድ ሮማዊ ጄኔራል ይህ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል የጦር እስረኞቹን ውኃው ውስጥ ከቷቸው እንደነበረ ዘግቧል።

ታዲያ፣ በውስጡ ምንም ፍጥረት የማይገኝበት እንዲህ ያለው ውኃ እንዴት ለጤና ተስማሚ ሊሆን ይችላል ብለህ ሳትገረም አትቀርም።

የሙት ባሕር ውኃ በእርግጥ ለጤና ተስማሚ ነው?

የመካከለኛው ዘመን አገር አሳሾች አእዋፍ፣ ዓሦች ወይም ዕፅዋት የማይገኙበት ሕይወት አልባ ባሕር እንዳለ የሚገልጹ ታሪኮችን ይናገሩ ነበር። እንዲያውም ከባሕሩ የሚወጣው መጥፎ ጠረን ያለው እንፋሎት እንኳ ሰው እንደሚገድል ይታሰብ ነበር። በዚህም ምክንያት ባሕሩ መጥፎ ሽታ ያለውና ሙት ነው የሚለው አመለካከት ሊዛመት ቻለ። እርግጥ ነው፣ በጣም ከፍተኛ የሆነ የጨው ክምችት በመኖሩ በዚህ ባሕር ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉት የተለየ ጥንካሬ ያላቸው እንደ ባክቴሪያ ያሉ ጥቃቅን ነፍሳት ብቻ ሲሆኑ ከላይ በሚወርደው ውኃ ተገፍቶ ወደ ባሕሩ የገባ ዓሣ ቢኖር እንኳ ወዲያውኑ ይሞታል።

ባሕሩ ሕይወት ላለው ፍጡር መኖሪያነት ተስማሚ አይሁን እንጂ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አካባቢው በአብዛኛው ደረቅ ምድረ በዳ ቢሆንም ፏፏቴዎችና ለምለም ደኖች ያሉባቸው አንዳንድ ቦታዎች አሉ። በተጨማሪም አካባቢው የበርካታ የዱር እንስሳት መኖሪያ እንደሆነ ይታወቃል። በባሕሩ አቅራቢያ በብዛት የሚታየውን ድኩላን፣ ሳንድ ካት የተሰኘውን የድመት ዝርያና አረቢያን ዎልፍ በመባል የሚጠራውን የተኩላ ዓይነት ጨምሮ 24 የሚያክሉ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች አሉ። በአካባቢው በሚገኙት ጨዋማ ያልሆኑ ወንዞችና ምንጮች ውስጥ በርካታ በየብስና በባሕር የሚኖሩ እንስሳት፣ ተሳቢ እንስሳትና ዓሦች ይገኛሉ። ሙት ባሕር የሚገኘው፣ አእዋፍ በየዓመቱ በሚያደርጉት የፍልሰት ጉዞ ዋነኛ መስመር ላይ በመሆኑ በዚህ ቦታ ላይ እንደ ጥቁርና ነጭ ሽመላ የመሰሉትን ጨምሮ ከ90 የሚበልጡ የአእዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ግሪፎን ቮልቸር እና ኢጅብሺያን ቮልቸር የተባሉ የጥንብ አንሣ ዝርያዎችን ማየት ይቻላል።

ሙት ባሕር ለጤና ተስማሚ የሆነው እንዴት ነው? በድሮ ጊዜ ሰዎች የፈዋሽነት ባሕርይ አለው በማለት ውኃውን ይጠጡ የነበረ ቢሆንም ይህ ዛሬ የሚመከር ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው! ከዚህ ይልቅ በጨዋማው ውኃ መታጠብ ሰውነትን እንደሚያጠራ ይታመናል። በተጨማሪም አካባቢው በአጠቃላይ መንፈስን የሚያድስ እንደሆነ ይነገርለታል። አካባቢው ረባዳ መሆኑ ከፍተኛ የሆነ የኦክሲጅን ይዘት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል። በአየሩ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ብሮማይድ መኖሩ ሰውነትን ዘና የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በባሕሩ ዳርቻዎች የሚገኙት በማዕድን የበለጸጉ ጥቁር ጭቃና ትኩስ የድኝ ፍል ውኃዎች የተለያዩ የቆዳና የመገጣጠሚያ በሽታዎችን ለመፈወስ ይረዳሉ። ከዚህም በላይ በአካባቢው ይበቅል የነበረው የበለሳን ዛፍ ለመድኃኒትነትና ለመዋቢያነት ሲያገለግል ቆይቷል።

ከባሕር የሚወጣ ሬንጅ

እጅግ አስደናቂ ከሆኑት የሙት ባሕር ክስተቶች አንዱ ቅጥራን ወይም ሬንጅ የሚተፋ መሆኑ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በባሕሩ ላይ ትልቅ የሬንጅ ግግር ተንሳፍፎ ይታያል። * በ1834 በባሕሩ ዳርቻ ላይ 2,700 ኪሎ ግራም የሚመዝን ትልቅ የሬንጅ ግግር ተንሳፍፎ እንደነበረ በ1905 የወጣው ዘ ቢቢሊካል ዎርልድ የተሰኘው መጽሔት ሪፖርት አድርጎ ነበር። ሬንጅ “የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገልግሎት ላይ ያዋለው የድፍድፍ ዘይት ውጤት” መሆኑ ይነገርለታል። (ሳውዲ አራምኮ ወርልድ ኅዳር/ታኅሣሥ 1984) አንዳንድ ሰዎች ከባሕሩ ሥር ባለው መሬት ላይ የሚገኘው ሬንጅ በመሬት መናወጥ ምክንያት ተቀርፎ በመውጣት ሊንሳፈፍ ችሏል ብለው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ ሬንጁ በተሰነጠቁ ወይም ዘርዘር ባሉ አለቶች ውስጥ ሰርጎ በማለፍ በባሕሩ ወለል ላይ ካሉት ጨዋማ አለቶች ጋር ይጣበቃል ብሎ ማሰብ ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆናል። ከዚያም ጨዉ ሲሟሟ የሬንጅ ግግሩ በውኃው ላይ ይንሳፈፋል።

ባለፉት መቶ ዘመናት ሬንጅ፣ ጀልባዎች ውኃ እንዳያስገቡ ለማድረግ፣ ለግንባታ ሥራና ተባዮችን ለማባረር ጭምር አገልግሏል። ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ግብጻውያን አስከሬን አድርቆ ለማቆየት ሬንጅ በብዛት መጠቀም እንደጀመሩ ይታሰባል። ይሁን እንጂ፣ ብዙ ሊቃውንት በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። በዚያ ዘመን በአካባቢው የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በሙት ባሕር አካባቢ ሠፍረው በነበሩ ናባታውያን በሚባሉ ዘላኖች ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር። እነሱም ቅጥራኑን ከባሕሩ ካወጡ በኋላ ቆራርጠው ወደ ግብጽ ይወስዱት ነበር።

ሙት ባሕር በእርግጥም በብዙ መንገዶች በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕር ነው። በጨዋማነቱ፣ በዝቅተኛ ስፍራ ላይ የሚገኝና ሕይወት አልባ በመሆኑ ምናልባትም ደግሞ በፈዋሽነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ባሕር ነው። በምድራችን ላይ ከሚገኙት እጅግ አስደናቂ ባሕሮች አንዱ ለመሆኑ አያጠራጥርም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ከድፍድፍ ዘይት ተጣርቶ የሚወጣው ሬንጅ አስፋልት ተብሎም ይጠራል። ይሁን እንጂ በብዙ አካባቢዎች አስፋልት የሚባለው ከአሸዋ ወይም ከደቃቅ ጠጠር ጋር የተለወሰ ለመንገድ ሥራ የሚያገለግል ውሁድ ነው። በዚህ ጽሑፍ ላይ ግን ያልተነጠረውን ጥሬ ውሁድ ለማመልከት ሬንጅ እና አስፋልት በሚሉት ቃላት ተጠቅመናል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በጨዋማው ባሕር ውስጥ ሳይበሰብስ የቆየ

የታሪክ ሊቃውንት ሙት ባሕር በአንድ ወቅት ሞቅ ያለ የንግድ መስመር እንደነበር ይዘግባሉ። ይህ አባባላቸው ትክክል መሆኑን በቅርብ በተገኙ ሁለት የእንጨት መልሕቆች ማረጋገጥ ተችሏል።

እነዚህ መልሕቆች የተገኙት የጥንቷ የአይንጋዲ ወደብ በነበረችበት አቅራቢያ ባለው የሙት ባሕር ዳርቻ ነው። አንደኛው 2,500 ዓመት የሚያክል ዕድሜ እንደሚኖረው የተገመተ ሲሆን በሙት ባሕር አካባቢ ከተገኙት መልሕቆች በሙሉ በዕድሜ ይበልጣል። ሁለተኛው 2,000 ዓመት ያህል እንደሚሆነው የሚገመት ሲሆን በዘመኑ በነበረው እጅግ የተራቀቀ የሮማውያን ቴክኖሎጂ የተሠራ እንደሆነ ይታመናል።

የእንጨት መልሕቆች ተራ በሆነ ባሕር ውስጥ ሲቆዩ የሚበሰብሱ ሲሆን የብረት መልሕቆች ግን ለረዥም ዘመን ይቆያሉ። ይሁን እንጂ በሙት ባሕር ውስጥ የሚገኘው አነስተኛ የኦክሲጅን መጠንና የውኃው ጨዋማነት እንጨቱ፣ ሌላው ቀርቶ በእንጨቱ ላይ የታሠረው ገመድ ሳይቀር በአስገራሚ ሁኔታ ሳይበላሽ እንዲቆይ አድርገዋል።

[ሥዕል]

ከ7ኛው እስከ 5ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት ጊዜያት ውስጥ እንደተሠራ የሚታመን የእንጨት መልሕቅ

[ምንጭ]

ፎቶ © Israel Museum, Courtesy of Israel Antiquities Authority

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፍል ውኃ ፏፏቴዎች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድ የጫካ ፍየል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጨው ባሕር ላይ ተንሳፍፎ ጋዜጣ ማንበብ