ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ “በብሪታንያ አንድ ልጅ ስድስት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፈው ጊዜ ቢደመር አንድ ዓመት የሚሞላ ሲሆን ሦስት ዓመት ከሆናቸው ሕፃናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መኝታ ቤታቸው ውስጥ ቴሌቪዥን አላቸው።”—ዚ ኢንዲፔንደንት፣ ብሪታንያ
▪ ቻይና ውስጥ በአንድ ጥናት ላይ ከተካፈሉት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች መካከል 31.4 በመቶ የሚሆኑት ሃይማኖተኞች እንደሆኑ ተናግረዋል። ይህ በመላ አገሪቱ ያለውን ሁኔታ የሚጠቁም ከሆነ “300 ሚሊዮን የሚሆኑት ሃይማኖተኞች ናቸው። ይህም [በአገሪቱ ያሉት ሃይማኖተኛ ሰዎች] 100 ሚሊዮን እንደሚሆኑ መንግሥት ካወጣው መግለጫ በጣም የራቀ ነው።”—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና
ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዘነ
ከጥቂት ዓመታት በፊት የደች ፖለቲከኞችና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ የተፈጥሮ ሀብትን የማያሟጥጥ የኃይል ምንጭ ያገኙ መስሏቸው ነበር፤ በተለይም በተምር ዘይት በመጠቀም የኃይል ማመንጫዎችን ለማንቀሳቀስ አስበው ነበር። ሆኖም ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ተስፋ ያደረጉት ነገር ‘በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት’ እንደሚያስከትል ገልጿል። “በአውሮፓ የተምር ዘይት ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሰፊ ቦታ የሚሸፍኑ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች እንዲመነጠሩና በአካባቢው የኬሚካል ማዳበሪያ ከልክ በላይ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ ነው።” ረግረጋማ መሬትን በማድረቅና በማቃጠል የእርሻ ቦታ ለማግኘት ጥረት ስለሚደረግ “ከፍተኛ መጠን” ያለው የካርቦን ጭስ ወደ ከባቢ አየር ይገባል። በዚህም የተነሳ “የሳይንስ ሊቃውንት ለምድር ሙቀት መጨመር መንስኤ እንደሆነ የሚያምኑትን የካርቦን ጭስ በመልቀቅ ረገድ [ኢንዶኔዥያ] ከዓለም የሦስተኝነትን ደረጃ” እንደያዘች ታይምስ ዘግቧል።
“የጥፋት ቀን ሰዓት” ወደፊት እንዲሄድ ተደርጓል
ቡሌቲን ኦቭ አቶሚክ ሳይንስ የተባለው ጋዜጣ የሰው ልጅ በኑክሌር ለመጥፋት ምን ያህል እንደተቃረበ ለማመልከት ያዘጋጀው ሰዓት በሁለት ደቂቃ ወደፊት እንዲሄድ በመደረጉ እኩለ ሌሊት ማለትም “የሥልጣኔን መጥፋት የሚጠቁመው ምሳሌያዊ ሰዓት” ላይ ለመድረስ የቀረው አምስት ደቂቃ ነው። ይህ ሰዓት በ60 ዓመት ዕድሜው ውስጥ የተስተካከለው 18 ጊዜ ብቻ ነው። ሰዓቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተስተካከለው ኒው ዮርክ በሚገኘው የዓለም የንግድ ማዕከል ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ በየካቲት 2002 ነበር። ከዚያ በኋላ የተከናወኑት ሁኔታዎችና የኑክሌር የጦር መሣሪያዎች መኖር እንዲሁም ኑክሌር ለመሥራት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች እንደልብ እንዳይገኙ ማድረግ አለመቻሉ “በምድር ላይ ከምንም በላይ አጥፊ የሆነው ቴክኖሎጂ ለሚያስከትላቸው ችግሮች መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ የሚጠቁም” መሆኑን ቡሌቲን ኦቭ አቶሚክ ሳይንስ ገልጿል። ጋዜጣው አክሎም “የአየር ንብረት ለውጥም የኑክሌር የጦር መሣሪያ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ያህል የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል” ብሏል።
በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የመንፈስ ጭንቀት
በቅርቡ በተደረገ ጥናት እንደተደረሰበት አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከትዳር ጓደኛዋ ጋር በሚፈጠር ጭቅጭቅ ወይም ባለቤቷ በሚፈጽምባት ጥቃት የተነሳ የሚያጋጥማት የመንፈስ ጭንቀት የሽሉን አእምሯዊ እድገት ክፉኛ ሊጎዳው ይችላል። በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ቪቬት ግሎቨር የተባሉ ሴት እንዲህ ብለዋል:- “ሴትዮዋ ነፍሰ ጡር እያለች ባሏ ስሜቷን የሚጎዳ ነገር የሚፈጽምባት ከሆነ በጽንሱ የወደፊት እድገት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ደርሰንበታል። በዚህ ረገድ አባትየው ትልቅ ሚና ይጫወታል።” ፕሮፌሰር ቪቬት እንደገለጹት ከሆነ ወላጆች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት “በእናቲቱ ሰውነት ውስጥ ባሉት የሆርሞንና ኬሚካላዊ ቅመሞች ላይ ተጽዕኖ አለው፤ ይህ ደግሞ በበኩሉ የልጁን አንጎል እድገት ይነካል።”
ልማዳዊ አሽከርካሪዎች
በየቀኑ በአንድ መንገድ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ብዙውን ጊዜ መኪና ሲነዱ ማሰብ የሚጠይቀውን የአንጎላቸውን ክፍል እንደማይጠቀሙበት በጀርመን የዱዊስበርጌሰን ዩኒቨርሲቲ የትራፊክ ሳይንስ ምሑር የሆኑት ሚካኤል ሽክሬከንበርግ ይናገራሉ። አሽከርካሪዎች በለመዷቸው መንገዶች ላይ ሲያሽከረክሩ አእምሯቸውን በመንገዱ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ፈንታ ሌሎች ነገሮችን ያስባሉ። በመሆኑም አደገኛ ሁኔታዎችን ለማየት ጊዜ ይወስድባቸዋል። ሽክሬከንበርግ፣ ሁልጊዜ በአንድ መንገድ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች አእምሯቸው ንቁ እንዲሆንና ከመንገዱ ላይ ትኩረታቸው እንዳይሰረቅ ለማድረግ አዘውትረው ራሳቸውን እንዲያሳስቡ ያበረታታሉ።