በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በበረዶ መሃል ተመቻችቶ መኖር

በበረዶ መሃል ተመቻችቶ መኖር

በበረዶ መሃል ተመቻችቶ መኖር

ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በሰሜን ዋልታ አካባቢ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የክረምት ወቅት የሚሞቅ ልብስና ጫማ ካላደረጉ ብርዱን መቋቋም በጣም የሚያስቸግራቸው ከመሆኑም በላይ ሊሞቱ ይችላሉ። ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ እንስሳት ግን የወቅቶች መለዋወጥ ተጽዕኖ ሳያደርግባቸው ተመቻችተው ይኖራሉ። እነዚህ እንስሳት ብርድ የሚከላከል ወፍራም የላባ ወይም የሱፍ ካባ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በረዶው በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ቅዝቃዜ ይከላከልላቸዋል።

በረዶ የሚሠራው ከውኃ ተን ከሚፈጠሩ ቅንጣቶች ሲሆን 25 ሴንቲ ሜትር በረዶ 2.5 ሴንቲ ሜትር ውኃ ይወጣዋል። ስለዚህ በበረዶ ቅንጣቶች መካከል ብዙ አየር አለ። በረዶ እንዲህ ያለ አስደናቂ ንድፍ ያለው በመሆኑ ኃይለኛ ቅዝቃዜን በመከላከል ረገድ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ የዕፅዋት ዘሮችና ተክሎች በጸደይ ወራት ሙቀት እስኪያገኙ ድረስ በረዶው ብርድ ይከላከልላቸዋል። ጸደይ ሲመጣ ደግሞ እንደ ግዙፍ የውኃ ማጠራቀሚያ በገጸ ምድሩ ላይ ተጋግሮ የቆየው በረዶ ይቀልጥና አፈሩን ያጠጣል እንዲሁም ወደ ምንጮችና ወንዞች ይጎርፋል።

“ከብርድ ልብሱ” በታች ያለው ሕይወት

ከበረዶው በታች በሚገኙት በጣም ብዙ ጉድጓዶች ውስጥ ሰውነታቸው በፀጉር የተሸፈነ በርካታ ትናንሽ እንስሳት የዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን ይርመሰመሳሉ፤ የእነዚህ እንስሳት ዋነኛ ዕለታዊ ተግባር ምግባቸውን መፈለግ ነው። ከበረዶው በታች ከሚርመሰመሱት ከእነዚህ እንስሳት መካከል የአይጠ መጎጥ ዝርያዎች እንዲሁም በአብዛኛው በምሽት የሚንቀሳቀሱና ትናንሽ ነፍሳትን የሚበሉ ሽሩው የተባሉ የፍልፈል ዝርያዎች ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ አይጦች ፍራፍሬ፣ ለውዝ እንዲሁም የትናንሽ ዛፎችን ለስላሳ ቅርፊት ለማግኘት በረዶው ላይ ሲራወጡ ይታያሉ።

በመጠን አነስተኛ የሆኑት አጥቢ እንስሳት ሰውነታቸው ትክክለኛ የሙቀት መጠን እንዲኖረው የሚያደርጉት እንዴት ነው? ብዙዎቹ ሙቀት የሚሰጥ የክረምት ካባ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሰውነታቸው የሚመገቡትን ምግብ በፍጥነት ወደ ኃይል በመለወጥ ሙቀት ያመነጫል። በዚህም የተነሳ ብዙ መብላት እንደሚያስፈልጋቸው መገመት አያዳግትም። ለምሳሌ፣ ሽሩው የሚባሉት የፍልፈል ዝርያዎች በየቀኑ የሚበሉት እጭና የነፍሳት መጠን የራሳቸውን ክብደት ያህላል። ፒግሚ ሽሩው የምትባለው በጣም ትንሽ እንስሳ እንኳ ከመጠኗ አንጻር ከሌሎቹ የበለጠ ትበላለች። በዚህም የተነሳ ከእንቅልፍ ሰዓታቸው ውጭ ያለውን ጊዜ በሙሉ የሚያሳልፉት አላንዳች እረፍት ምግብ በመፈለግ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት እንደ ጉጉትና ዊዝል ላሉት አዳኝ እንስሳት ተወዳጅ ምግብ ናቸው። እንደ ልብ መተጣጠፍ የሚችሉትና ሸንቀጥ ያለ ሰውነት ያላቸው ዊዝሎች፣ ከበረዶ በታች በተሠሩ ስውር ጉድጓዶች ውስጥ ተዘዋውረው ምግባቸውን ለማደን የሚያመች አካል አላቸው። ዊዝሎች በግዝፈት የሚበልጧቸውን ጥንቸሎች እንኳ ሳይቀር አድነው ይመገባሉ።

ጉጉቶችም ለአደን ይሰማራሉ። ትልቁ ግራጫ ጉጉት፣ ከፍተኛ የመስማት ችሎታ ስላለው የበረዶው ግግር በጣም ወፍራም ካልሆነ ከበረዶው በታች የሚንቀሳቀስን አይጠ መጎጥ እንቅስቃሴ መስማትና ተከታትሎ መያዝ ይችላል። ጉጉቱ፣ የሚያድነው እንስሳ የት እንዳለ ካወቀ ወደ በረዶው ጠልቆ በመግባት እንስሳውን በማያፈናፍኑ ጥፍሮቹ አንቆ ያወጣዋል። የበረዶው ግግር በጣም ወፍራም ከሆነ ግን ብዙ አዳኝ እንስሳት ለረሃብና ለችጋር ከከፋም ለእልቂት የሚዳረጉ ሲሆን ታዳኞቹ እንስሳት ደግሞ ከመጠን በላይ ይባዛሉ።

ብዙዎቹ እንስሳት ምግብ እንደ ልብ በማይገኝበት የክረምት ወቅት ለረሃብ እንዳይጋለጡ ሞቃት በሆኑት ወራት በአካላቸው ውስጥ ያጠራቀሙትን ስብ ይመገባሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚቀማምሱት ምግብ አያጡም። ለምሳሌ፣ አጋዘኖች የዛፎችን፣ በተለይም የጥድ ዛፍ ቀንበጦችን ይቀነጣጥባሉ። ሽኮኮዎች በየጓዳቸው ያከማቹትን አዝርዕት የሚመገቡ ሲሆን ጥንቸሎች ደግሞ ለጋ ቅርፊቶችን፣ ቀንበጦችንና ቁጥቋጦዎችን ይበላሉ። አንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎች በረዶ የሆኑ ፍራፍሬዎችንና የጥድ ቀንበጦችን ያጣጥማሉ።

ወደ በረዶ መጥለቅ

በርካታ አእዋፍ ቀን ላይ ማረፍ ወይም ሌሊት ማንቀላፋት ሲፈልጉ ቅዝቃዜውን ለመቋቋም እንዲረዳቸው በረዶው ውስጥ ይገባሉ። ከእነዚህ የአእዋፍ ዝርያዎች መካከል ቡናማ ቀለም ያላት ዶሮ፣ ጥቁር ጅግራ፣ ታርሚጋን የተባለው የጅግራ ዝርያ እንዲሁም እንደ ሊኔት፣ ቡልፊንችና ድንቢጥ ያሉት ትናንሽ ወፎች ይገኙበታል። በረዶው ጥልቀት ያለውና ለስላሳ ከሆነ አንዳንዶቹ ወፎች ባሕር ውስጥ ዘለው እንደሚገቡ አእዋፍ በረዶው ውስጥ ተወርውረው ይጠልቃሉ። ይህ ዘዴ አዳኞቻቸው የእግራቸውን ዱካ ተመልክተው ወይም ጠረናቸውን አሽትተው እንዲከታተሏቸው የሚያደርግ ምልክት ስለማይተው በጣም ይጠቅማቸዋል።

ወፎቹ የበረዶው ክምር ውስጥ ከገቡ በኋላ እስከ ሦስት ጫማ ርዝመት ያለው ጉድጓድ ወደጎን ይቆፍራሉ፤ ይህ ጉድጓድ በፊንላንድ ቋንቋ ክዬፒ ይባላል። የሌሊቱ ነፋስ ከበረዶው ክምር በታች ሕይወት ያለው ነገር እንደሚኖር የሚያሳየውን ማንኛውም ምልክት ጠራርጎ ያጠፋዋል። በእግር ለመንሸራሸር የወጡ ሰዎች ወደ እነዚህ የአእዋፍ ጉድጓዶች ሲጠጉ በረዶውን ሲረግጡት የሚፈጠረው ድምፅ ወፎቹን ያባንናቸዋል። በዚህ ጊዜ ወፎቹ በድንገት በረዶውን ጥሰው በመውጣት ክንፎቻቸውን ማራገብ ሲጀምሩ በቦታው እንዲህ ዓይነት ነገር ሊያጋጥመው እንደሚችል ያልጠበቀው እግረኛ በድንጋጤ ክው ማለቱ አይቀርም።

የክረምት ካባ ማጥለቅ

ወቅቶች በሚለዋወጡበት ጊዜ በአርክቲክ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ እንስሳት በበጋ ወቅት የነበራቸውን ፀጉር ወይም ላባ ትተው ከበረዶው ጋር የሚመሳሰል የክረምት ካባ በማጥለቅ በቀላሉ እንዳይታዩ ያደርጋሉ። በፊንላንድ የአርክቲክ ቀበሮዎች፣ የተራራ ጥንቸሎችና በርካታ የዊዝል ዝርያዎች በመፀው ወራት ነጭ ወይም ወደ ነጭ የሚጠጋ ጥቅጥቅ ያለ ፀጉር ያበቅላሉ።

በተመሳሳይ ታርሚጋን የሚባሉት የጅግራ ዝርያዎች በበጋ የነበራቸው ዥንጉርጉር ላባ ተለውጦ ደማቅ ነጭ ይሆናል። እንዲሁም ሞቃት በሆኑት ወራት ብዙም ላባ ያልነበራቸው የእግሮቻቸው ጣቶች በቅዝቃዜው ወቅት ጥቅጥቅ ባለ ላባ ስለሚሸፈኑ ግሩም “የበረዶ መከላከያ ጫማ” ሆነው ያገለግሏቸዋል። ታዳኞቹ እንስሳት ለብርድ የሚሆናቸውን ልብስ በሚቀይሩበት ጊዜም እንኳ የሚኖራቸው ቡራቡሬ መልክ፣ በከፊል በበረዶ በመሸፈኑ ዥንጉርጉር ከሚሆነው መሬት ጋር ስለሚመሳሰል ለአዳኞቻቸው ተጋልጠው አይታዩም።

ባዶ እግራቸውን በረዶ ላይ የሚሄዱ አእዋፍ ለምን በቅዝቃዜው እንደማይጎዱ ወይም ብርዱ እንደማያስቸግራቸው አስበህ ታውቃለህ? እነዚህ አእዋፍ የማይቀዘቅዛቸው እግራቸው ላይ አስደናቂ በሆነ ጥበብ የተሠራ የሙቀት ማስተላለፊያ ስላላቸው ነው። ከልባቸው የሚመነጨው ሞቅ ያለ ደም ወደ እግራቸው ይወርድና ከእግራቸው ወደ ላይ የሚመለሰውን ቀዝቃዛ ደም ያሞቀዋል።

በበረዶ በተሸፈኑት የምድር ዋልታዎችም ሆነ ከፍተኛ ሙቀት ባላቸው የሐሩር ክልሎች የሚኖሩት ፍጥረታት ሕይወት፣ በጣም አስቸጋሪ ከሆነው የአየር ንብረት ጋር በሚያደርጉት ትግል የተሞላ አይደለም። እነዚህ እንስሳት በአካባቢያቸው ተመቻችተውና ተደላድለው ይኖራሉ። እነዚህን ፍጥረታት ፈልገው የሚያገኙና ፎቶግራፍ የሚያነሷቸው ወንዶችና ሴቶች ብዙውን ጊዜ ለጥረታቸው ከፍተኛ ምስጋና ይቸራቸዋል፤ እንዲህ መደረጉም የሚገባቸው ነው! ይህ ከሆነ ታዲያ በምድር ላይ የሚገኙትን አስደናቂ ሕያዋን ፍጥረታት የፈጠረውን አምላክ ይበልጥ ልናወድሰው አይገባም? ራእይ 4:11 “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና” ይላል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ብርድ የማይበግራቸው ክርስቲያኖች!

በፊንላንድ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በበረዶ ወራት ለአየሩ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ልብሶችን በመልበስ የተለመዱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ያከናውናሉ። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ረጅም ርቀት ተጉዘው ነው። የሚገርመው ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ በሚቆየው የክረምት ወቅት በብርዱ ምክንያት የተሰብሳቢዎች ቁጥር አይቀንስም። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ሕዝባዊ አገልግሎታቸውን በትጋት ያከናውናሉ። በእርግጥም ስለ ፈጣሪያቸው ስለ ይሖዋ አምላክ መመሥከራቸውን እንደ ትልቅ መብት ስለሚቆጥሩት ሞቅ ካለው ቤታቸው በመውጣት የመንግሥቱን ምሥራች ይሰብካሉ።—ማቴዎስ 24:14

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፔትረል የተባሉት ወፎች በዋሻ ውስጥ

[ምንጭ]

By courtesy of John R. Peiniger

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤርሚን

[ምንጭ]

Mikko Pöllänen/Kuvaliiteri

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የውኃ ዶሮ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንቸል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአርክቲክ ቀበሮ