በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች—የተጻፉበት ጊዜ የሚታወቀው እንዴት ነው?

በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች—የተጻፉበት ጊዜ የሚታወቀው እንዴት ነው?

በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች​—የተጻፉበት ጊዜ የሚታወቀው እንዴት ነው?

ኮንስታንቲን ፎን ቲሸንዶርፍ የተባለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር በ1844 ግብጽ ውስጥ በሲና ተራራ ግርጌ ወደሚገኘው ሴይንት ካተሪና ገዳም ሄዶ ነበር፤ በገዳሙ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ሲመለከት ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የብራና ጽሑፎች አገኘ። የፓሊዮግራፊ * ተመራማሪ የነበረው ቲሸንዶርፍ እነዚህ ጽሑፎች ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ የተገነጠሉ ገጾች እንደሆኑ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። ሰብዓ ሊቃናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም “የብሉይ ኪዳን” ግሪክኛ ትርጉም ነው። ቲሸንዶርፍ “ከእነዚህ የሳይናይቲክ ገጾች የበለጠ ዕድሜ ያላቸው ቅርሶች አይቼ አላውቅም” ሲል ጽፏል።

ከጊዜ በኋላ ሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት (ኮዴክስ ሳይናይቲከስ) ተብሎ የተጠራው ጽሑፍ ክፍል የሆኑት እነዚህ ገጾች በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፉ ተገምቷል። ይህ የሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ምሑራን ጥናት ከሚያደርጉባቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል አንዱ ነው።

ጥንታዊ የግሪክኛ ጽሑፎች ጥናት እድገት

በግሪክኛ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎችን በዘዴ በማጥናት ረገድ መሠረት የጣሉት በርናር ሞንትፎኮን (1655-1741) የተባሉ የቤነዲክት ሃይማኖት መነኩሴ ናቸው። ከእሳቸው በኋላ ደግሞ ሌሎች ምሑራን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቲሸንዶርፍ በአውሮፓ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ዝርዝር አዘጋጅቷል። ይህ ሰው ከዚህ ከባድ ሥራ በተጨማሪ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተደጋጋሚ በመመላለስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን ከመረመረ በኋላ ስለደረሰበት ግኝት የሚያትት ጽሑፍ አውጥቷል።

በ20ኛው መቶ ዘመን ደግሞ በዚህ መስክ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ለምርምር የሚያገለግሉ ሌሎች መሣሪያዎችን አገኙ። ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል ማርሴል ሪሻር ያዘጋጀው 900 የሚያህሉ ካታሎጎችን የያዘው ዝርዝር ይገኝበታል። ይህ ዝርዝር 820 በሚያክሉ በሰዎች እጅና በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ 55,000 ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎችን ይጠቅሳል፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከዚያ የተለዩ ናቸው። ይህ ሰፊ የመረጃ ጥንቅር ለተርጓሚዎች ጠቀሜታ ያለው ከመሆኑም በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ጥንታዊ ቅጂዎቹ የተጻፉበትን ጊዜ በትክክል ለመገመት ይረዳቸዋል።

ጥንታዊ ቅጂዎች የተጻፉበትን ጊዜ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

በአንድ ጥንታዊ ቤት ውስጥ የሚገኝን አንድ ክፍል እያጸዳህ ሳለህ በዕድሜ ብዛት የወየበና ቀን ያልተጻፈበት ደብዳቤ አገኘህ እንበል። በዚህ ጊዜ ‘ይህ ደብዳቤ ምን ያህል ዕድሜ ይኖረው ይሆን?’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ ደብዳቤ አገኘህ። የዚህ ደብዳቤ የአጻጻፍ ስልት፣ የፊደሎቹ አጣጣል፣ ሥርዓተ ነጥቦቹና ሌሎች ገጽታዎቹ ከመጀመሪያው ደብዳቤ ጋር ይመሳሰላል። ደስ የሚለው ሁለተኛው ደብዳቤ ቀን ተጽፎበታል። የመጀመሪያው ደብዳቤ የተጻፈበትን ዓመት በእርግጠኝነት ማወቅ ባትችልም እንኳ ጊዜውን ለመገመት የሚያስችልህ ፍንጭ አገኘህ ማለት ነው።

አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ገልባጮች በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ሥራቸውን የጨረሱበትን ጊዜ አላሰፈሩም። ምሑራን የእነዚህን ጽሑፎች የፊደል አጣጣልና ሥርዓተ ነጥብ እንዲሁም አሕጽሮተ ቃላትንና ሌሎች ነገሮችን ዕድሜያቸው በትክክል ከሚታወቁ ሌሎች ሰነዶች ጋር በማስተያየት የተጻፉበትን ጊዜ መገመት ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ ዕድሜያቸው በትክክል የሚታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች ይገኛሉ። እነዚህ የግሪክኛ ጽሑፎች ከ510 እስከ 1593 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባሉት ዘመናት ውስጥ የተጻፉ ናቸው።

የፊደል አጣጣል በዚህ ረገድ የሚረዳው እንዴት ነው?

ተመራማሪዎች ጥንታዊውን የግሪክኛ አጻጻፍ ስልት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍሉታል። አንደኛው የሚያምረውና በመደበኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው የቁም ጽሕፈት (book hand) ሲሆን ሁለተኛው በሥነ ጽሑፍ ደረጃ ጥቅም ላይ የማይውለው ቅጥልጥል (cursive) የሚባለው የአጻጻፍ ዓይነት ነው። በተጨማሪም ግሪካውያን ጸሐፊዎች ካፒታል (ትላልቅ ፊደላት)፣ አንሺያል (የትላልቅ ፊደላት ዓይነት)፣ ከርሲቭ እና ሚኒስክዩል ተብለው ከሚጠሩት የአጣጣል ስልቶች የሚፈረጁ የአጻጻፍ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። አንሺያል አንደኛው የቁም ጽሕፈት ዓይነት ሲሆን ጥቅም ላይ የዋለው ከአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ ስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ነበር። ሚኒስክዩል የሚባለው የፊደላት አጣጣል ዘዴ ደግሞ ከ8ኛው ወይም ከ9ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ ተንቀሳቃሽ የማተሚያ መሣሪያ ጥቅም ላይ እስከዋለበት እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ድረስ አገልግሏል። ይህ የአጻጻፍ ዘዴ ቶሎ ቶሎ እንዲሁም ፊደላቱን አጠጋግቶ ለመጻፍ የሚያስችል በመሆኑ ጊዜና ብራና እንደሚቆጥብ ይታመን ነበር።

ተመራማሪዎች በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎችን ዕድሜ ለመገመት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። በአብዛኛው የሚያደርጉት ግን፣ በመጀመሪያ ጽሑፉን ጠቅለል ባለ መልኩ ይመለከታሉ፤ ከዚያ በኋላ እያንዳንዱን ፊደል ቀረብ ብለው በጥልቀት ይመረምራሉ። አብዛኛውን ጊዜ በአጻጻፍ ስልት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚታየው ከረጅም ጊዜ በኋላ በመሆኑ በጥልቀት የሚደረገው ምርመራ፣ የተጻፈው ከዚህ እስከዚህ ነው ብሎ ለመገመት ካልሆነ በስተቀር ጊዜውን በትክክል ለማወቅ አይረዳም።

ደስ የሚለው ግን እንደተጻፈ የሚገመትበትን ጊዜ ይበልጥ በትክክል ለማወቅ የሚያስችሉ ሌሎች ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንድ የአጻጻፍ ልማዶች የጀመሩበትን ጊዜ ለይቶ ማወቅ ይገኝበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ900 ወዲህ በነበሩት ዓመታት በግሪክኛ ጽሑፎች ላይ ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሆሄያትን አገጣጥሞ መጻፍ እየተዘወተረ መጥቶ ነበር። በተጨማሪም ጸሐፊዎች አንዳንድ ፊደላትን ከመስመር ወረድ አድርገው መጻፍና ቃላትን በትክክል ለማንበብ የሚረዱ ምልክቶችን ማከል ጀምረው ነበር።

የአንድ ሰው የፊደል አጣጣል ዕድሜውን ሙሉ አይለወጥም ለማለት ይቻላል። በመሆኑም አንድ ጽሑፍ ተጽፏል ተብሎ የሚገመትበትን የጊዜ ልዩነት ከ50 ዓመት በታች ማውረድ አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በላይ አንዳንድ ጸሐፊዎች ከእነሱ ዘመን በፊት የተጻፉ ጽሑፎችን አስመስለው የሚገለብጡበት ጊዜ አለ። ይህ ደግሞ ግልባጩ ከመጀመሪያው ቅጂ የበለጠ ዕድሜ ያለው ያስመስለዋል። ምንም እንኳ በርካታ ተፈታታኝ ችግሮች ቢኖሩም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ዋና ዋና ቅጂዎች የተጻፉበትን ጊዜ ለማወቅ ተችሏል።

ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች የተጻፉበት ጊዜ

በአሁኑ ጊዜ በብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አሌክሳንድሪን ማኑስክሪፕት (ኮዴክስ አሌካሳንድሪኑስ) በምሑራን እጅ ከገቡት ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል የመጀመሪያው ነው። ይህ ቅጂ አብዛኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ያካተተ ሲሆን ከፍተኛ ጥራት ባለው ብራና ላይ በትላልቅ ግሪክኛ ፊደላት የተጻፈ ነው። ይህ ኮዴክስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደተጻፈ ተገምቷል። ለዚህ በዋነኝነት እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰው በአምስተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን መካከል በትላልቅ ፊደላት የአጻጻፍ ዘዴ ላይ ለውጥ መከሰቱ ነው። የተጻፈበት ዘመን በእርግጠኝነት የሚታወቀው የቪየናው ዲዮስኮሪደስ * የተባለው ሰነድ እንዲህ ላለው ለውጥ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናል።

ሁለተኛው ደግሞ ቲሸንዶርፍ ከሴይንት ካተሪን ገዳም ያገኘው ሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት (ኮዴክስ ሳይናይቲከስ) ነው። በግሪክኛ ትላልቅ ፊደላት በብራና ላይ የተጻፈው ይህ ኮዴክስ ከሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የተገለበጡ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በከፊል እንዲሁም የክርስቲያን ግሪክኛ መጻሕፍትን በሙሉ ያካተተ ነው። ከዚህ ኮዴክስ ውስጥ 43ቱ ገጾች በጀርመን አገር በላይፕሲግ ከተማ የሚገኙ ሲሆን 347ቱ ገጾች ለንደን ባለው ብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም የሦስት ገጾች ቅዳጅ በሩስያ ሴይንት ፒተርስበርግ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ጥንታዊ ቅጂ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ እንደተጻፈ ይገመታል። ይህ ግምት የቂሳሪያው ዩሲቢየስ በአራተኛው መቶ ዘመን እንዳዘጋጀው በሚታወቀው የወንጌሎች የሕዳግ ማመሳከሪያ አማካኝነት ተረጋግጧል። *

ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሦስተኛው ሥራ ደግሞ መጀመሪያ ላይ መላውን የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ የነበረው ቫቲካን ማኑስክሪፕት ቁ. 1209 (ኮዴክስ ቫቲካኑስ) የሚባለው ግልባጭ ነው። ይህ ኮዴክስ በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ባሉት መጻሕፍት ዝርዝር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰፈረው በ1475 ነው። ከፍተኛ ጥራት ባላቸው 759 የብራና ገጾች ላይ በትላልቅ የግሪክኛ ፊደላት የተጻፈው ይህ ኮዴክስ ከዘፍጥረት መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል፣ ግማሽ ከሚያህለው የመዝሙር መጽሐፍ እንዲሁም ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎች በስተቀር ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይዟል። ምሑራን ይህ ግልባጭ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደተጻፈ ገምተዋል። እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ የቻሉት እንዴት ነው? የአጻጻፍ ስልቱ በዚያው በአራተኛው መቶ ዘመን ከተጻፈው ከሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ነው። ይሁን እንጂ ቫቲካኑስ ትንሽ በዕድሜ እንደሚበልጥ ይገመታል። ለዚህ እንደ ማስረጃ ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ የዩሲቢየስን ጽሑፍ ዓይነት ማመሳከሪያ የሚጎድለው መሆኑ ነው።

ከቆሻሻ ክምር ውስጥ የተገኘ ውድ ሀብት

በ1920 ማንቸስተር፣ እንግሊዝ የሚገኘው የጆን ራይላንድስ ቤተ መጻሕፍት ከአንድ ጥንታዊ የግብጻውያን የቆሻሻ ክምር ውስጥ በቁፋሮ የወጡ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ፓፒረሶች አገኘ። ኮለን ሮበርትስ የተባሉ አንድ ምሑር ደብዳቤዎችን፣ ደረሰኞችንና የሕዝብ ቆጠራ ሰነዶችን አካትቶ የያዘውን ይህን ግኝት ሲመረምሩ የሚያውቁት ጥቅስ ያለበትን አንድ ቁራጭ አገኙ። ጽሑፉ የዮሐንስ ምዕራፍ 18ን ጥቂት ቁጥሮች ይዟል። ይህ ግልባጭ እስከዚያ ድረስ ከተገኙት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ጥንታዊው ነው።

ቅጂው ጆን ራይላንድስ ፓፒረስ 457 ተብሎ የተጠራ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ P52 በሚለው ስያሜ ይታወቃል። በትላልቅ የግሪክኛ ፊደላት የተጻፈው ይህ ቅጂ የተጻፈው በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ማለትም የዮሐንስ ወንጌል ከተጻፈ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ ነበር! ጽሑፉ ከረጅም ጊዜ በኋላ ከተገለበጡት ሌሎች የዚህ መጽሐፍ ቅጂዎች ጋር አንድ ዓይነት ነው ለማለት ይቻላል።

ጥንታዊ ቢሆንም ትክክለኛ ነው!

ብሪታንያዊው የሥነ ጽሑፍ ተንታኝ ሰር ፍሬድሪክ ኬንየን ዘ ባይብል ኤንድ አርኪኦሎጂ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚመለከት “የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አስተማማኝነት እና አጠቃላይ ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል” በማለት ጽፈዋል። በተጨማሪም ዊልያም ግሪን የተባሉ ምሑር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እርስ በርስ ያላቸውን ስምምነት አስመልክተው ሲናገሩ “የዚህን ያህል ትክክል የሆኑ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል።

እነዚህ አስተያየቶች ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሱናል።—1 ጴጥሮስ 1:24, 25

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 “ፓሊዮግራፊ . . . ጥንትና በመካከለኛው ዘመን በእጅ ስለተጻፉ ጽሑፎች የሚያጠና የምርምር መስክ ሲሆን በዋነኝነት እንደ ፓፒረስ፣ ብራና ወይም ወረቀት ባሉ በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ መሣሪያዎች ላይ በተጻፉ ጽሑፎች ላይ ያተኩራል።”—ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ

^ አን.16 የቪየናው ዲዮስኮሪደስ የተጻፈው በ527 ወይም በ528 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለሞተችው ጁሊያና አኒሲያ የተባለች ሴት ነው። ይህ ሰነድ “መቼ እንደተጻፈ ማወቅ የሚቻል ከመሆኑም በላይ በብራና ላይ በትላልቅ ፊደላት በመጻፍ ረገድ የመጀመሪያው ነው።”—በኢ. ኤም. ቶምሰን የተዘጋጀው አን ኢንትሮዳክሽን ቱ ግሪክ ኤንድ ላቲን ፓሊዮግራፊ

^ አን.17 ይህ የዩሲቢየስ ሥራ “በአንድ ወንጌል ውስጥ የሚገኝ ዘገባ በሌላ ወንጌል ውስጥ ከሚገኝ ከየትኛው ዘገባ ጋር እንደሚመሳሰል የሚያሳይ” የማመሳከሪያ ሰንጠረዥ ነው።—በብሩስ መትስገር የተዘጋጀው ማኑስክሪፕትስ ኦቭ ዘ ግሪክ ባይብል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ተመራማሪዎች፣ ዕድሜያቸው የማይታወቅ የጽሑፍ ሥራዎችን የተጻፉበት ጊዜ ከሚታወቅ ጥንታዊ ቅጂዎች ጋር በማመሳከር የተጻፉበትን ጊዜ መገመት ችለዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የኢሳይያስ መጽሐፍ የሙት ባሕር ጥቅልል የተጻፈበትን ጊዜ ማወቅ

የመጀመሪያው የኢሳይያስ መጽሐፍ የሙት ባሕር ጥቅልል የተገኘው በ1947 ነበር። ይህ ጥቅልል በቅድመ ማሶሬቶች ዘመን ጥቅም ላይ ይውል በነበረው የዕብራይስጥ አጻጻፍ ስልት በቆዳ ላይ የተጻፈ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ እንደተጻፈም ይገመታል። ምሑራን እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ የቻሉት እንዴት ነው? ምሑራኑ ጽሑፉን ከሌሎች የዕብራይስጥ ቅጂዎችና በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ከተገኙ ጽሑፎች ጋር ካወዳደሩት በኋላ ከ125 እስከ 100 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ተናግረዋል። ካርቦን-14 በሚባለው ጥንታዊ ነገሮች ያላቸውን ዕድሜ ለመመርመር በሚያስችል ዘዴ አማካኝነት የተገኘው ውጤትም በዚህ ጊዜ ውስጥ መጻፉን ያረጋግጣል።

የሚገርመው፣ የሙት ባሕር ጥቅልል ከብዙ ዓመታት በኋላ ማሶሬቶች ተብለው በሚጠሩት አይሁዳውያን ጸሐፊዎች አማካኝነት ከተጻፈው ከማሶሬቶች ቅጂ ጋር ሲወዳደር ምንም ዓይነት የመሠረተ ትምህርት ልዩነት አልተገኘበትም። * ከተገኙት ልዩነቶች ውስጥ ብዙዎቹ የፊደልና የሰዋስው ግድፈቶች ናቸው። ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም የሚወክሉት አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት በኢሳይያስ መጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ በብዙ ቦታዎች መገኘታቸው ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.34 ጽሑፍ የመገልበጥ ሥራቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ ያከናውኑ የነበሩት ማሶሬቶች የኖሩት ከ500 እስከ 1,000 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ዘመን ውስጥ ነው።

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ግሪክኛ የእጅ ጽሑፍ

የቁም ጽሕፈት (አንሺያል)

ከ4ኛው መቶ ዘመን ከክ.ል.በፊት እስከ 8ኛው ወይም 9ኛው መቶ ዘመን ከክ.ል.በኋላ

ሚኒስክዩል

ከ8ኛው ወይም ከ9ኛው መቶ ዘመን ከክ.ል.በኋላ እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ከክ.ል.በኋላ

ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቅጂዎች

400

200

የሙት ባሕር ጥቅልል

ከክ.ል.በፊት 2ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ

ከክ.ል.በፊት

ከክ.ል.በኋላ

100

ጆን ራይላንድስ ፓፒረስ 457

125 ከክ.ል.በኋላ

300

ቫቲካን ማኑስክሪፕት ቁ. 1209

4ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ

ሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት

4ኛው መቶ ዘመን

400

አሌክሳንድሪን ማኑስክሪፕት

5ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ

500

700

800

[በገጽ 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ:- ኮንስታንቲን ፎን ቲሸንዶርፍ

በስተቀኝ:- በርናር ሞንትፎኮን

[ምንጭ]

© Réunion des Musées Nationaux/ Art Resource, NY

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የሙት ባሕር ጥቅልል:- Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

የቫቲካን ማኑስክሪፕት ቁ. 1209 ቅጂ:- From the book Bibliorum Sacrorum Graecus Codex Vaticanus, 1868; የሳይናይቲክ ማኑስክሪፕት ቅጂ:- 1 Timothy 3:16, as it appears in the Codex Sinaiticus, 4th century C.E.; አሌክሳንድሪን ማኑስክሪፕት:- From The Codex Alexandrinus in Reduced Photographic Facsimile, 1909, by permission of the British Library