አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይላል?
ምሕረት የላቀ ስፍራ ካላቸው የአምላክ ባሕርያት አንዱ ነው። (መዝሙር 86:15) አምላክ ምን ያህል መሐሪ ነው? አንድ መዝሙራዊ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ ኅጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።” (መዝሙር 130:3, 4) በአንድ ሌላ መዝሙር ላይ ደግሞ እንዲህ የሚል ሐሳብ ተገልጿል:- “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።”—መዝሙር 103:12-14
ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ምሕረት የሚያደርገው ሙሉ በሙሉ ሲሆን አንድን ሰው ይቅር ለማለትም አያመነታም። እንዲሁም ይሖዋ ለእኛ ምሕረት ለማድረግ “ትቢያ” መሆናችንን ማለትም ያለብንን የአቅም ገደብና ፍጹም አለመሆናችንን ግምት ውስጥ ያስገባል። አምላክ ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ ለማየት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቶስን ሦስት ጊዜ ክዶት ነበር። (ማርቆስ 14:66-72) ሐዋርያው ጳውሎስም ወደ ክርስትና ከመለወጡ በፊት የክርስቶስ ተከታዮችን አሳዷል። ጳውሎስ ከክርስቶስ ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹ እንዲገደሉ የተላለፈውን ውሳኔ ደግፏል፤ ሌላው ቀርቶ በእስጢፋኖስ መገደል እንኳ ተስማምቶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:1, 3፤ 9:1, 2, 11፤ 26:10, 11፤ ገላትያ 1:13) አንዳንድ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት ወደ ክርስትና ከመለወጣቸው በፊት ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የሆነ ሆኖ ሁሉም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። አምላክ ይቅር ያላቸው ለምን ነበር?
የአምላክን ምሕረት ለማግኘት የሚረዱ ሦስት እርምጃዎች
ጳውሎስ “ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረት ተደርጎልኛል” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ግልጽነት የተንጸባረቀበት ይህ የጳውሎስ አባባል፣ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። ይኸውም ስለ ይሖዋና ስለ መመሪያዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ያለማወቅን መጋረጃ መግለጥ ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በእርግጥም ፈጣሪያችንን በደንብ ካላወቅነው እሱን ማስደሰት አንችልም። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል:- “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3
ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ይህንን እውቀት ሲያገኙ ከዚህ ቀደም በሠሯቸው ስህተቶች በጣም የሚጸጸቱ ከመሆኑም በላይ ከልብ ንስሐ ለመግባት ይገፋፋሉ። የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት መወሰድ ያለበት ሁለተኛው እርምጃ ይህ ነው። የሐዋርያት ሥራ 3:19 “እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ” ይላል።
ይህ ጥቅስ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት መወሰድ የሚገባውን ሦስተኛ እርምጃም ጭምር ይጠቅሳል፤ ይህም መመለስ ነው። መመለስ ሲባል የቀድሞ አኗኗርንና አስተሳሰብን እርግፍ አድርጎ በመተው የአምላክን መመሪያና አመለካከት መከተል ማለት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 26:20) በአጭር አነጋገር አንድ ሰው አምላክን “ይቅር በለኝ” ብሎ የሚለምነው ከልቡ መሆኑ የሚታየው በአኗኗሩ ለውጥ ሲያደርግ ነው።
የአምላክ ምሕረት ገደብ አለው
አምላክ፣ አንዳንድ ሰዎች የሚሠሩትን ኃጢአት ይቅር አይልም። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- ‘የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድ ነው።’ (ዕብራውያን 10:26, 27) ‘ሆን ብሎ በኀጢአት ጸንቶ መመላለስ’ የሚለው አባባል አንድ ሰው ሥር የሰደደ የክፋት ባሕርይ እንዳለው እንዲሁም ሰውየው ልቡ ክፉ እንደሆነ ያመለክታል።
የአስቆሮቱ ይሁዳ እንዲህ ያለ የልብ ዝንባሌ ነበረው። ኢየሱስ፣ ይሁዳን አስመልክቶ ሲናገር “ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር” ብሏል። (ማቴዎስ 26:24, 25) በተጨማሪም ኢየሱስ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤. . . እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው።” (ዮሐንስ 8:44) እንደ ሰይጣን ሁሉ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎችም ክፋት ተጠናውቷቸው ነበር። በሠሩት መጥፎ ነገር አልተጸጸቱም፤ እንዲያውም ክፉ የነበረውን አካሄዳቸውን ይበልጥ ገፉበት። * እውነት ነው፣ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ከአለፍጽምና እንዲሁም ከድካም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ። ይሁን እንጂ ኃጢአት መሥራታቸው ብቻውን ሥር የሰደደ የክፋት ባሕርይ እንዳላቸው አያሳይም።—ገላትያ 6:1
እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ መሐሪ ነበር
ይሖዋ የሚያየው ግለሰቡ ኃጢአት መሥራቱን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየውን ዝንባሌ ጭምር ነው። (ኢሳይያስ 1:16-19) ከኢየሱስ አጠገብ ተሰቅለው የነበሩትን ሁለት ወንጀለኞች ለአንድ አፍታ ለማሰብ ሞክር። አንደኛው ሰው “እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው [ኢየሱስ] ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም” በማለት ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ሁለቱም ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል። የዚህ ወንጀለኛ አነጋገር ስለ ኢየሱስ የሚያውቀው ነገር እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን ይህ እውቀቱ በዝንባሌው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳስከተለ አያጠራጥርም። ኢየሱስን “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ መማጸኑ በእርግጥም ግለሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳመጣ ያሳያል። ክርስቶስ ልባዊ ለሆነው ለዚህ ልመና ምን ምላሽ ሰጠ? “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።—ሉቃስ 23:41-43
እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ቆም ብለህ አስብ:- ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሞት እንደሚገባው አምኖ ለተቀበለው ሰው የተናገረው ሐሳብ መሐሪ መሆኑን ያንጸባርቃል። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ከዚህ በመነሳት፣ ሰዎች ከዚህ ቀደም የፈጸሙት ነገር ምንም ይሁን ምን እውነተኛ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ኢየሱስም ሆነ አባቱ ይሖዋ ርኅራኄ እንደሚያሳዩአቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮሜ 4:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 በሐምሌ 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-20 ላይ የወጣውን “በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ የአምላክን ምሕረት እንዴት ትገልጸዋለህ?—መዝሙር 103:12-14፤ 130:3, 4
▪ አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን እርምጃዎችን መውሰድ አለበት?—ዮሐንስ 17:3፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19
▪ ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ ምን ቃል ገባለት?—ሉቃስ 23:43
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከባድ ኃጢአቶች ይቅር ሊባሉ እንደሚችሉ አሳይቷል