አንድን አህጉር ማቋረጥ ከ120 ዓመታት በላይ ፈጀ
አንድን አህጉር ማቋረጥ ከ120 ዓመታት በላይ ፈጀ
አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
የካቲት 3, 2004 ርዝመቱ 1.1 ኪሎ ሜትር ገደማ የሆነ ባቡር ብዙ ሰው በማይኖርበት የአውስትራሊያ ሰሜናዊ ክፍል ወደሚገኘው ዳርዊን ባቡር ጣቢያ እያዘገመ ደረሰ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በባቡሩ መምጣት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ በቦታው ተገኝተው ነበር። ዘ ጋን ተብሎ የሚጠራው ይህ ባቡር በሁለት ቀናት ውስጥ 2,979 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አህጉሩን ከደቡብ እስከ ሰሜን በማቋረጥ የመጀመሪያ ጉዞውን ማጠናቀቁ ነበር።—“ከስሙ በስተጀርባ ያለው አፈ ታሪክ” የሚለውን በገጽ 25 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ከ2,000 የሚበልጡ ሰዎች ካሜራቸውን ይዘው በሐዲዱ ዳርና ዳር ላይ ተሰብስበው ስለነበር ባቡሩ ወደ ዳርዊን ከተማ ሲቃረብ ፍጥነቱን መቀነስ ነበረበት። በመሆኑም ባቡሩ የደረሰው 30 ደቂቃ ዘግይቶ ነበር። ይሁን እንጂ በመዘግየቱ የተማረረ ሰው አልነበረም። የአውስትራሊያ ሕዝብ ይህን ቀን ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲጠብቀው ቆይቷል። በምድር ላይ ካሉት በጣም ደረቅ፣ ሞቃታማና ጭር ያሉ አካባቢዎች መካከል የሚመደቡትን የአገሪቱን ክፍሎች የሚያቋርጠውን ከአድሌድ እስከ ዳርዊን የሚዘልቀውን የባቡር መሥመር የመዘርጋት ሥራ ለማጠናቀቅ 126 ዓመታት ፈጅቷል።
የባቡር መሥመር ያስፈለገበት ምክንያት
በ1870ዎቹ መገባደጃ ላይ፣ ግሬት አውስትራሊያን ባይት ተብሎ በሚጠራው ሰፊ የባሕር ወሽመጥ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ትንሿ የአድሌድ ግዛት ነዋሪዎች በክልሉ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲኖር የማድረግና ርቆ እስከሚገኘው ሰሜናዊ ክፍል የሚደርስ የተሻለ የንግድ መንገድ የመክፈት ሕልም ነበራቸው። በ1869 ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአገሪቷን ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ጠረፎች የሚያገናኘውን የባቡር መንገድ ግንባታ አጠናቅቃ ነበር። የአድሌድ ዜጎችም እንዲህ ዓይነት የባቡር መሥመር እንደሚያስፈልጋቸው በማሰብ ግዛታቸውን በዚያን ጊዜ የዳርዊን ወደብ ተብላ ትጠራ ከነበረችው የዛሬዋ ዳርዊን ጋር የሚያገናኝ ሐዲድ ለመዘርጋት ፈለጉ። ይህ የባቡር መሥመር ወደ አገሪቱ መካከለኛ ክፍል መጓዝ ይበልጥ ቀላል እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ወደ እስያና አውሮፓ ለመጓዝ የሚፈጀውን ጊዜ በእጅጉ ይቀንሰዋል።
ሐሳቡ ቀላል ቢመስልም ሐዲዱ፣ አስቸጋሪ የሆኑ በርካታ ዓለታማ ኮረብታዎችንና የተራራ ሰንሰለቶችን እንዲሁም ጥቅጥቅ ያሉ ጥሻዎችንና በአሸዋና በድንጋይ የተሸፈኑ ምድረ በዳዎችን ማቋረጥ ነበረበት፤ ከእነዚህ ምድረ በዳዎች ከፊሎቹ ዝናብ ሲዘንብ ማጥ ይሆናሉ አሊያም በኃይለኛ ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ። ጆን ስቱዋርት የተባለው አሳሽ በ1862 ባደረገው ሦስተኛ ሙከራ፣ ለጉዞ አስቸጋሪ የሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለውን ይህን አካባቢ ማቋረጥ ችሏል። ይሁን እንጂ እሱና አብረውት የነበሩት ሰዎች በጉዞ ላይ ሳሉ ምግብና ውኃ በማጣት ሊሞቱ ተቃርበው ነበር።
ኃይለኛ ሙቀት፣ የአሸዋ ውሽንፍርና ደራሽ ውኃ
ከግንባታው ጋር በተያያዘ የተለያዩ እንቅፋቶች ቢኖሩም የአድሌድ ዜጎች ከጥረታቸው ወደኋላ አላሉም። በ1878 ከኦገስታ ወደብ ጀምረው ሐዲዱን የመዘርጋቱን ሥራ ተያያዙት። ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ የባቡር ሐዲድ ሠራተኞች በእጅ በሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች፣ በፈረሶችና በግመሎች ብቻ እየተጠቀሙ አበርጅኒዎች ያወጡትን የእግር መንገድ በመከተል ፍሊንደርስ ተብለው የሚጠሩትን የተራራ ሰንሰለቶች አቋርጠው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሐዲዱን መዘርጋት ቀጠሉ። በእንፋሎት የሚሠሩ ባቡሮች ለመንቀሳቀስ ውኃ ስለሚያስፈልጋቸው ይህ የባቡር መሥመር የተዘረጋው በአካባቢው በሚገኙት የውኃ ጉድጓዶች አቅራቢያ ነበር።
የመጀመሪያውን 100 ኪሎ ሜትር የባቡር ሐዲድ ለመዘርጋት ሁለት ዓመት ተኩል ፈጀ። በበጋ ወቅት አንዳንድ ጊዜ ሙቀቱ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። ደረቅ በሆነው በዚህ ሞቃታማ አየር ሰዎቹ ጥፍራቸው ይሰነጠቅ ነበር፤ ብዕር ቀለም ውስጥ ነክረው ገና ወረቀት ላይ መጻፍ ሳይጀምሩ ይደርቃል እንዲሁም የባቡር ሐዲዶች ከሙቀቱ የተነሳ ይጣመማሉ። ባቡሮች መሥመራቸውን መሳታቸው የተለመደ ነገር ነበር። የአሸዋው ውሽንፍር ካለፈ በኋላ ሠራተኞቹ ብዙ ኪሎ ሜትሮች እየሄዱ
በሐዲዱ ላይ የተከመረውን የአሸዋ ቁልል ማጽዳት ነበረባቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ውሽንፍሩ እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያለው የአሸዋ ቁልል ይፈጥራል። ብዙውን ጊዜም ሌላ ውሽንፍር መጥቶ ሠራተኞቹ ባጸዱት ሐዲድ ላይ እንደገና አሸዋ በመከመር ልፋታቸውን መና ያደርግባቸው ነበር።ከዚያ ደግሞ ዝናብ ይመጣል። የደረቁት ወንዞች በደቂቃዎች ውስጥ ይሞላሉ፤ በዚህ ወቅት የሚኖረው ኃይለኛ ጎርፍ ሐዲዱን ያጣምመው አልፎ ተርፎም ለወራት የተለፋበትን ሥራ ጠራርጎ በመውሰድ ተሳፋሪዎችን የጫኑት ባቡሮች መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ያደርጋቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንድ የባቡር ሹፌር መንገደኞቹን ለመመገብ ሲል የሜዳ ፍየሎችን ማደን ነበረበት። ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ አንድ ባቡር በጉዞው ላይ እንዲህ ዓይነት እንቅፋት አጋጥሞት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ለተሳፋሪዎቹ ከአውሮፕላን ምግብ ተወርውሮላቸዋል።
ዝናቡን ተከትሎ የበረሃ ዕፅዋት የሚያቆጠቁጡ ሲሆን ይህ ደግሞ የአንበጣ መንጋዎችን ይስባል። በአንድ የአንበጣ ወረራ ወቅት በሐዲዱ ላይ በተጨፈለቁት አንበጦች የተነሳ ሐዲዱ በጣም ያዳልጥ ስለነበር ከኋላ ሆኖ ፉርጎዎቹን የሚገፋ ሌላ ባቡር አስፈልጎ ነበር። የአይጦች መንጋም ሌላ ችግር ፈጥሮ ነበር። አይጦቹ ያገኙትን ሁሉ ማለትም የሐዲዱን ሠራተኞች ቀለብ፣ ሸራዎችን፣ የእንስሳት ልጓሞችንና ቦት ጫማዎችን ሳይቀር እንክት አድርገው ይበሉ ነበር። የባቡር መሥመር የመዘርጋቱ ሥራ በተጀመረበት ወቅት ተነስቶ የነበረውን የአንጀት ተስቦ ወረርሽኝ የሚያስታውስና በካምፑ ውስጥ ንጽሕና የጎደለው ሁኔታ እንደነበረ የሚጠቁም አንድ ብቸኛ የመቃብር ስፍራ በሐዲዱ አቅራቢያ ይገኛል።
የባቡሩ ሠራተኞች ለመዝናናት ሲሉ ሰዎችን የሚያስደነግጥ ነገር በማድረግ ይቀልዱ ነበር። በአንድ ወቅት አሊስ ስፕሪንግስ የሚባለው አካባቢ በጥንቸል መንጋ በተወረረበት ጊዜ የባቡሩ ሠራተኞች ጥንቸሎቹን ዘ ጋን ወደተሰኘው ባቡር አስገቧቸው። በማግሥቱ መንገደኞቹ ወደ ቁርስ ለመሄድ የክፍላቸውን በር ሲከፍቱ መተላለፊያው “በደነበሩ ጥንቸሎች ተሞልቶ” እንደነበር ዘ ጋን—ከአደሌድ እስከ አሊስ የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል። በሌላ ጉዞ ደግሞ አንድ ሰው በመኝታ ፉርጎዎቹ ውስጥ የካንጋሮ ግልገል አስገብቶ ነበር።
ሩቅ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖሩት አበርጅኒዎች አንዳንድ ጊዜ ባቡሩ ሲያልፍ ወደ ሐዲዱ ይቀርቡ ነበር። አበርጅኒዎቹ ወደ ባቡሩ ብዙም ሳይጠጉ በውስጡ ያሉትን ሰዎች ይመለከታሉ። መጀመሪያ ላይ ባቡሩን በጥርጣሬ ዓይን ተመልክተውት እንዲያውም አንዳንዶቹ ፈርተውት ነበር። አንዳንዶች “አንድ ግዙፍ የዲያብሎስ እባብ” ተሳፋሪዎቹን ከነሕይወታቸው እንደዋጣቸው አስበው ነበር!
ሥራው ለረጅም ጊዜ ተቋረጠ
የሐዲዱ ሠራተኞች በጣም ከባድ የሆነውን የባቡር መሥመር የመዘርጋት ሥራ ለ13 ዓመታት ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ የባቡር ሐዲዱ አሊስ ስፕሪንግስ ሊደርስ 470 ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው ገንዘብ አለቀባቸው። አውስትራሊያን ጂኦግራፊክ የተባለው ጽሑፍ “እንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ሥራ . . . ከግዛቱ አቅም በላይ ነበር” ይላል። በ1911 የፌዴራሉ መንግሥት ይህን ሥራ ተረክቦ ሐዲዱን እስከ አሊስ ስፕሪንግስ አደረሰው። ሐዲዱን በስተ ሰሜን 1,420 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ዳርዊን ለማድረስ የነበረው እቅድ ግን ለሌላ ጊዜ ተላለፈ።
ዘ ጋን የተባለው ባቡር በ1929 ለመጀመሪያ ጊዜ አሊስ ስፕሪንግስ ሲደርስ በወቅቱ 200 ገደማ የሚሆነው የከተማው ሕዝብ በሙሉ ደስታውን ለመግለጽ ወጥቶ ነበር። የከተማው ነዋሪዎች እንደ ምግብ ቤት የሚያገለግለውን ፉርጎ ሲመለከቱ የተደነቁ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረታቸውን የሳበው ግን በጣም የሚያምረው መታጠቢያ ቤት ነበር። በዚያ ወቅት ባቡር ውስጥ ባኞ መኖሩ አዲስ ነገር ከመሆኑም በላይ እንደ ቅንጦት ይታይ ነበር። እስከ 1997 ድረስ በስተ ሰሜን በኩል የባቡር ሐዲዱ የመጨረሻ መድረሻ አሊስ ስፕሪንግስ ነበረች። በዚያ ዓመት ግን የክልሉና የፌዴራሉ መንግሥት፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን ከአሊስ ስፕሪንግስ ወደ ዳርዊን የሚወስድ የባቡር መሥመር የመዘርጋት ሥራ ለማጠናቀቅ ተስማሙ። በመሆኑም ሥራው በ2001 ተጀመረ።
አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ የሚፈጀውን ይህን ሥራ ግዙፍ በሆኑ አውቶማቲክ የግንባታ መሣሪያዎች በመጠቀም ማከናወን ጀመሩ፤ በቀን 1.6 ኪሎ ሜትር ያህል የባቡር ሐዲድ ይዘረጉ የነበረ ሲሆን ሐዲዱ በመንገዱ ላይ ቢያንስ 90 የሚያህሉ ጎርፍን መቋቋም የሚችሉ አዳዲስ ድልድዮችን አቋርጧል። “በአውስትራሊያ በጣም ትልቁ የመሠረተ ልማት ሥራ” ተብሎ የተሰየመው ይህ 1,420 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር መሥመር ከተመደበለት ባጀት ባነሰ ወጪ እንዲሁም ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ በጥቅምት 2003 ተጠናቀቀ።
የአውስትራሊያ የገጠር አካባቢ ውበት
ዛሬም ቢሆን ዘ ጋን የተባለው አህጉር አቋራጭ ባቡር፣ ከቀትር በኋላ ጉዞውን የሚጀምረው ከዘመናዊቷ የአድሌድ ከተማ
ነው። አርባ ያህል ፉርጎዎችን የሚጎትቱት ጥንድ ባቡሮች የከተማዋን ዳርቻዎች ወደኋላ በመተው አቀበታማ በሆነው መንገድ ላይ የስንዴ ማሳዎችን አቋርጠው እየተምዘገዘጉ ከአድሌድ በስተ ሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የኦገስታ ወደብ ያቀናሉ። ባቡሩ እዚህ ሲደርስ በአካባቢው የሚታየው ነገር በእጅጉ ይለወጣል፤ ተሳፋሪዎቹ የሚመለከቱት ለእይታ የማይማርክ አሸዋማ መሬት፣ ጥሻና በዳዋ የተሸፈነ መሬት ይሆናል።ዘ ጋን የተባለው ባቡር የኦገስታን ወደብ ካለፈ በኋላ የሚጓዝበት አዲስ ሐዲድ የተሠራው፣ ቀደም ሲል ከነበረው ለጎርፍ የተጋለጠ ሐዲድ በስተ ምዕራብ 250 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ሲሆን በማንኛውም የአየር ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ይችላል። በረሃውን ሲያቋርጡ ቀኑ ስለሚመሽ ባቡሩ ጨዋማ የሆኑትን ሐይቆች ወደኋላ እየተወ ሲገሰግስ ተሳፋሪዎቹ ይተኛሉ፤ እነዚህ ሐይቆች በዓመት ውስጥ በአብዛኞቹ ወራት ክው ብለው ቢደርቁም ዝናብ ከጣለ በኋላ ግን በጨረቃ ብርሃን ሲታዩ ያንጸባርቃሉ። ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ይታያሉ። ሐዲዶቹ ቶሎ ቶሎ መጠገን እንዳያስፈልጋቸው ለማድረግ ሲባል ወጥ ሆነው ስለተሠሩ ቀደም ሲል ባቡር ሲያልፍ የሚሰማው የሚንገጫገጭ ድምፅ አሁን ቀርቷል።
ጎሕ ሲቀድ በአሊስ ስፕሪንግስ አካባቢ ያለው በረሃ ቀይና ወርቅማ ብርሃን ይላበሳል። አንድ ተሳፋሪ “አካባቢው የሚያስደንቅ ነው” በማለት ተናግሯል። “በባቡሩ ውስጥ ሆኜም እንኳ የፀሐይዋ ሙቀት ይሰማኝ ነበር። ፀሐይዋ ለዓይን በሚያታክተው በጣም ሰፊ፣ በቀለማት ያሸበረቀና ጭር ከማለቱ የተነሳ ውጦ የሚያስቀር በሚመስለው አስፈሪ ምድረ በዳ ላይ ስትፈነጥቅ መመልከት ይመስጣል። ይህን ቦታ የሚያይ ሰው ኢምንት እንደሆነ ይሰማዋል።”
ከገጠራማ አካባቢዎች ወደ ሐሩር ክልሎች መሻገር
ዘ ጋን ቀትር ላይ በአሊስ ስፕሪንግስ እረፍት ካደረገ በኋላ ካተሪን በተባለችው ከተማ አልፎ በስተ ሰሜን ወደሚገኘው መድረሻው ማለትም በሞቃት ክልል ውስጥ ወዳለው የዳርዊን ከተማ ጉዞውን ይቀጥላል። ዘ ጋን ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ጉዞውን ባደረገበት ወቅት የባቡሩ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ላሪ ይራስ እንደተናገሩት “ዘ ጋን” በተባለው ባቡር ውስጥ የአየር ማቀዝቀዣዎች በመኖራቸው “ተሳፋሪዎቹ በከፍተኛ ምቾት” መጓዝ ይችላሉ። ተሳፋሪዎቹ በመስኮቶቻቸው አሻግረው ሲመለከቱ የቀድሞዎቹን የሐዲዱን ሠራተኞች ሁኔታ ከመገመት በቀር ያሳለፏቸውን አደገኛ ሁኔታዎችና ችግሮች መረዳት አይችሉም።
ዘ ጋን፣ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ ከማድረጉና በዓለም ላይ ካሉት ታላላቅ የባቡር መሥመሮች አንዱ በመሆን አገልግሎት ከመስጠቱም በተጨማሪ የዘመናዊው ዓለም አንድ ገጽታ ርቀው ወደሚገኙት የአውስትራሊያ ገጠራማ አካባቢዎች እንዲገባ አድርጓል። ባቡሩ በየካቲት ወር 2004 የመጀመሪያ ጉዞውን ሲያደርግ የተመለከተች አንዲት የ19 ዓመት አበርጅናዊት ወጣት “በሕይወቴ ሙሉ ባቡር አይቼ አላውቅም ነበር። በጣም ደስ ይላል” በማለት ተናግራለች።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከስሙ በስተጀርባ ያለው አፈ ታሪክ
ዘ ጋን የሚለው ስያሜ ዚ አፍጋን ኤክስፕረስ የሚለው ቅጽል ስም አሕጽሮተ ቃል ነው። ባቡሩ፣ የአፍጋኒስታንን ባለ ግመሎች የሚያመለክተው ይህ ስም የተሰጠው ለምን እንደሆነ በውል አይታወቅም። ይሁን እንጂ ስያሜው ርቀው ወደሚገኙት የአውስትራሊያ ገጠራማ አካባቢዎች መድረስ እንዲቻል አስተዋጽኦ ያደረጉትን እነዚያን ችግር የማይበግራቸው ስደተኞች የሚያስታውስ ነው። እነዚህ ሰዎች በጥቅሉ የአፍጋኒስታን ተወላጆች ተብለው ይጠሩ እንጂ ብዙዎቹ የመጡት እንደ ባሉቺስታን፣ ግብጽ፣ ሰሜናዊ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ፋርስና ቱርክ ካሉት የተለያዩ ቦታዎች ነበር።
የግመሎቹ ባለቤቶች “ሁሽታ!” ብለው ሲያዟቸው በእሺ ባይነት ዝቅ የሚሉት ወይም ከተቀመጡበት የሚነሱት ግመሎች በአውስትራሊያ ገጠራማ አካባቢዎች ዋነኛ መጓጓዣ ነበሩ። እስከ 70 ያህል ግመሎች ያሉበት ቅፍለት በሰዓት 6 ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ ሰዎችን ወይም ጭነትን ያጓጉዝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የባቡርና የመኪና መጓጓዣዎች በመምጣታቸው በግመሎች መጠቀም ሲቀር አፍጋኒስታናውያኑ እንስሶቻቸውን ነፃ ለቀቋቸው። በዛሬው ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት የእነዚያ ግመሎች ዝርያዎች በማዕከላዊ አውስትራሊያ ይፈነጫሉ።—የሚያዝያ 8, 2001 (እንግሊዝኛ) ንቁ! ገጽ 16-17 ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Northern Territory Archives Service, Joe DAVIS, NTRS 573
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የባቡር ፎቶዎች:- Great Southern Railway