በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

▪ “መንስኤው ከምድር ሙቀት መጨመር ጋር የተያያዘ ይሁን ወይም ሌላ፣ ከአየር ንብረት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው መቅሠፍቶች ቁጥር በ1970ዎቹ እና በ1990ዎቹ መካከል ባሉት ጊዜያት ከነበረው በሦስት እጥፍ ጨምሯል።”—ዚ ኢኮኖሚስት፣ ብሪታንያ

▪ በኢሊኖይ፣ ዩ ኤስ ኤ ግዛት የሚኖር የ10 ወር ዕድሜ ያለው አንድ ሕፃን የጦር መሣሪያ ለመያዝ የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጠው። በአባትየው ጥያቄ መሠረት የጦር መሣሪያ ፈቃድ ያገኘው ይህ ሕፃን ሁለት ጫማ ከሦስት ኢንች ቁመትና 7.5 ኪሎ ግራም ክብደት እንዳለው ተገልጿል። በኢሊኖይ የጦር መሣሪያ ለመያዝ የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻ በሚያቀርቡ ሰዎች ላይ የተጣለ የዕድሜ ገደብ የለም።—ኬብል ኒውስ ኔት ወርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

▪ የሳይንስ ሊቃውንት “ውኃ መፍላት ከሚችልበት የሙቀት መጠን በላይ ያለውን ውኃ” በማመቅ ሙቀቱን እንደያዘ ወደ በረዶነት መለወጥ ቻሉ። “ከተለመደው” በረዶ በተጨማሪ “በተለያየ የሙቀት ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢያንስ 11 ዓይነት በረዶዎች” አሉ።—ሳንዲያ ናሽናል ላብራቶሪስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በጆርጂያ የሃይማኖት ነፃነት ተረጋገጠ

የጆርጂያ መንግሥት በሃይማኖት የተነሳ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚፈጸመውን በደል ችላ ብሎ በመመልከቱ የአውሮፓ ሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ብያኔ አስተላለፈበት። ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች ከታወቁ የክርስትና ሃይማኖቶች መካከል የሚመደቡ እንደመሆናቸው መጠን ለአምልኮና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የመሰብሰብ መብት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ፣ ተበዳዮቹ በክሱ ሂደት ላወጡት ወጪና ለደረሰባቸው ሥቃይ ካሣ እንዲከፈላቸው ትእዛዝ አስተላልፏል። ከጥቅምት 1999 እስከ ኅዳር 2002 ባሉት ጊዜያት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ 138 የኃይል ጥቃቶች የተሰነዘሩባቸው ሲሆን 784 አቤቱታዎችን ለጆርጂያ ባለ ሥልጣናት አቅርበው ነበር። ይሁን እንጂ ባለ ሥልጣናቱ የቀረቡትን አቤቱታዎች ለማጣራት ትኩረት ሰጥተው ምርመራ አላደረጉም። እንዲያውም ፖሊሶች ጥቃቱ በሚፈጸምበት ወቅት ጣልቃ ለመግባትና ተበዳዮቹን ከጥቃት ለመከላከል እምቢተኞች ነበሩ። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው በደል ከኅዳር 2003 ወዲህ በእጅጉ ቀንሷል።

በፔሩ የተገኘው ጥንታዊ የፀሐይ ምርምር ጣቢያ

በአሁኑ ጊዜ፣ የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪዎች በፔሩ የተገኘው 2,300 ዓመት ዕድሜ ያለው ምንነቱ በግልጽ ያልታወቀ ፍርስራሽ ከፊሉ የፀሐይ የምርምር ጣቢያ በመሆን ያገለግል እንደነበር ሐሳብ አቅርበዋል። ቻንኪሎ በመባል የሚጠራው ይህ ስፍራ በአንድ ተረተር ላይ የሚገኝ ሲሆን እንደ “ጥርስ” መደዳውን የተደረደሩ 13 ማማዎች አሉት። ሳይንስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “በዓመት ውስጥ በሁለት የተወሰኑ ቀናት ፀሐይዋ ማለዳ ላይ በአንደኛው ጫፍ ባለው ማማ በኩል ወጥታ ምሽት ላይ በሌላኛው ጫፍ ባለው ማማ በኩል ትጠልቃለች፤ ይህም የዓመቱን መጀመሪያና አጋማሽ ለማወቅ ያስችላቸዋል።” በመሃል ላይ ያሉት ማማዎች በሌሎቹ ወቅቶች ፀሐይዋ ስትወጣና ስትጠልቅ የምታርፍባቸውን ቦታዎች ያመለክታሉ። በዚህ ደረቅ አካባቢ እህል መቼ መዘራት እንዳለበት ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ “ሰዎች ጊዜውን በትክክል ማወቅ [ያስፈልጋቸው] ነበር።”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቀኑ የሚረዝምበትና ሌሊቱ የሚያጥርበት ጊዜ (ሰኔ)

ሌሊቱና ቀኑ እኩል ርዝመት የሚኖራቸው ጊዜ

ቀኑ የሚያጥርበትና ሌሊቱ የሚረዝምበት ጊዜ (ታኅሣሥ)

የፀሐይ ምርምር ጣቢያ

[ምንጭ]

REUTERS/Ivan Ghezzi/Handout

በሴቶች ላይ መጥፎ ስሜት የሚፈጥሩ ፍቶዎች

በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ከሚዙሪ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የወጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ሁሉም ሴቶች ውፍረታቸው፣ ቅርጻቸው፣ ቁመታቸው ወይም ዕድሜያቸው ምንም ይሁን ምን፣ በመጽሔት ሽፋን ላይ የሚወጡ የተዋቡ ቀጫጭን ሴቶችን ፎቶግራፍ ማየታቸው ስለራሳቸው ሰውነት መጥፎ ስሜት ያሳድርባቸዋል።” የትምህርት መምሪያ፣ የትምህርት ቤትና በሥነ ልቦና ትምህርት ምክር መስጫ ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሎሬ ሚንትስ እንዳሉት ከሆነ “ወፍራም ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚታዩትን ማራኪ የሆኑ ቀጫጭን ሴቶችን ፎቶግራፎች ሲመለከቱ ቀጠን ካሉት ይልቅ መጥፎ ስሜት ይሰማቸዋል ተብሎ ይታሰብ ነበር።” ይሁን እንጂ ሚንትስ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ስሜት ከውፍረት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ደርሰንበታል። እነዚህን ፍቶግራፎች መመልከት በሁሉም ሴቶች ላይ መጥፎ ስሜት ይፈጥራል።”