በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጀልን ማስቀረት ይቻል ይሆን?

ወንጀልን ማስቀረት ይቻል ይሆን?

ወንጀልን ማስቀረት ይቻል ይሆን?

“ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ብዙዎቹ ልማደኛ ወንጀለኞች ከእስር ከተለቀቁ በኋላም እንኳን በማኅበረሰቡ ላይ ወንጀል መፈጸማቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን በገንዘብ ብቻ ሊተመን የማይችል እጅግ ከፍተኛ ኪሳራ ያደርሳሉ።”—በዶክተር ስታንተን ሳሜኖ የተዘጋጀው ኢንሳይድ ዘ ክሪሚናል ማይንድ

የምንኖረው በየትኛውም የዓለም ክፍል ይሁን በእያንዳንዱ ቀን አዳዲስ ዘግናኝ ወንጀሎችን እንሰማለን። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ያሉት የወንጀል መከላከያ ዘዴዎች ማለትም ከባድ ቅጣቶች፣ የእስራት ፍርዶችና ወዘተ . . . ለውጥ እያስገኙ ነው? ብሎ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው። መታሰር ወንጀለኞች ለውጥ እንዲያደርጉ ይረዳል? ከሁሉም በላይ ደግሞ ኅብረተሰቡ የወንጀል ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ነገር አግኝቶታል?

ዶክተር ስታንተን ሳሜኖ በአሁኑ ጊዜ ወንጀልን ለመከላከል ስለሚሠራባቸው ዘዴዎች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- ‘ወንጀለኛው አንድ ጊዜ ታስሮ ከተፈታ በኋላ ይበልጥ መሠሪና ጠንቃቃ ይሆናል እንጂ ሌሎችን መጠቀሚያ ከማድረግና ወንጀል ከመፈጸም አይታቀብም። እንደገና በወንጀል ድርጊት ስለተካፈሉ ሰዎች የሚገልጹ አኃዛዊ መረጃዎች የሚያካትቱት በድጋሚ ወንጀል ሲሠሩ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ብቻ ነው። ሆኖም አንዳንድ ወንጀለኞች ከወኅኒ ቤት ከወጡ በኋላ እንደገና ላለመያዝ በጣም ጠንቃቆች ስለሚሆኑ ይህ አኃዝ ትክክለኛውን መረጃ አያስተላልፍም።’ በመሆኑም ብዙውን ጊዜ ወኅኒ ቤት ወንጀለኞቹ ፀረ ኅብረተሰብ ሙያቸውን ተክነው የሚወጡበት ትምህርት ቤት ይሆንላቸዋል።—“እስር ቤቶች ‘የወንጀል ትምህርት ቤቶች’ ናቸው?” የሚለውን በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ከዚህም በላይ ብዙ ወንጀሎች ያለ ቅጣት መታለፋቸው ጥፋተኞቹ ወንጀል መፈጸም እንደሚያዋጣ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ይህም ወንጀለኞቹ ይብሱን ዓይን ያወጡ እንዲሆኑና በዚህ አካሄድ እንዲገፉበት ሊያደርጋቸው ይችላል። አንድ ጠቢብ ንጉሥ “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል” በማለት ጽፏል።—መክብብ 8:11

ወንጀለኞች የሆኑት ወደው ነው ወይስ በሁኔታዎች ተገደው?

አንዳንድ ሰዎች ለመኖር ወንጀል ከመፈጸም ሌላ አማራጭ የላቸውም? “ወንጀለኞቹ ከተዘፈቁበት የድህነት አረንቋ፣ ከሚገኙበት ያልተረጋጋ ሕይወትና ከሚያጋጥማቸው ተስፋ መቁረጥ አንጻር ወንጀል የተለመደና ምናልባትም ተገቢ ድርጊት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” በማለት ሳሜኖ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ሰፊ ጥናት ካካሄዱ በኋላ ግን ሐሳባቸውን ለውጠዋል። “ወንጀለኞች ወንጀል የሚፈጽሙት በውዴታቸው ነው” ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። “የወንጀል . . . ‘መንስኤ’ [የግለሰቡ] ማኅበራዊ ሁኔታ ሳይሆን አስተሳሰቡ ነው።” ሳሜኖ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ምግባር በአመዛኙ የአስተሳሰብ ውጤት ነው። የምናደርገው ነገር ሁሉ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ከአስተሳሰባችን ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው።” ስለዚህ ሳሜኖ ወንጀለኞች ምርጫ የሌላቸው ሰዎች ሳይሆኑ “ወንጀለኝነትን በፈቃዳቸው የመረጡና ሌሎችን የሚያሠቃዩ ሰዎች ናቸው” ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። *

እዚህ ላይ የምናተኩርበት ቃል “የመረጡ” የሚለውን ነው። እንዲያውም በቅርቡ በአንድ የብሪታንያ ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ “ወንጀል የተሻለ ነገር ለማግኘት የሚጓጉ ወጣት የከተማ ወንዶች የሚመርጡት ሥራ ነው” በማለት ዘግቧል። ሰዎች ነፃ ምርጫ ስላላቸው በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ሊከተሉት የሚፈልጉትን አካሄድ መምረጥ ይችላሉ። በየዕለቱ ከፍትሕ መዛባትና ከድህነት ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ወይም እርስ በርስ ስምምነት በሌላቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ አይካድም፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ወንጀለኞች አልሆኑም። “ወንጀልን የሚፈጥሩት ወንጀለኞች እንጂ መጥፎ ሠፈሮች፣ ኃላፊነታቸውን በብቃት ያልተወጡ ወላጆች፣ . . . ወይም ሥራ አጥነት አይደሉም” ይላሉ ሳሜኖ። “ወንጀል በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚፈጠር እንጂ በማኅበራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚመጣ አይደለም።”

ወንጀል የሚጀምረው ከአስተሳሰብ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ለመጥፎ ድርጊት ዋናው መንስኤ አንድ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ ሳይሆን ውስጣዊ ማንነቱ እንደሆነ ይገልጻል። ያዕቆብ 1:14, 15 እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” አንድ ሰው በመጥፎ ሐሳቦች ላይ የሚያውጠነጥን ከሆነ በውስጡ መጥፎ ምኞቶች ያድጋሉ። እነዚህ ምኞቶች ደግሞ ወደ ጎጂ ድርጊቶች ሊመሩት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው አልፎ አልፎም እንኳን ቢሆን ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን መመልከቱ የኋላ ኋላ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድም ቢሆን ይህን ምኞቱን ለማርካት እስኪነሳሳ ድረስ አስተሳሰቡ በጾታ ስሜት ብቻ እንዲሞላ ሊያደርገው ይችላል።

ሌላው ከግምት መግባት ያለበት ነገር ደግሞ ይህ ዓለም፣ ለራስ ፍላጎትና ለገንዘብ እንዲሁም ለተድላና ስሜትን ወዲያውኑ ለማርካት የሚሰጠው ትኩረት ነው። ያለንበትን ጊዜ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል:- “በመጨረሻው ዘመን . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ . . . [እንዲሁም] ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ዓለም በፊልሞች፣ በቪድዮ ጨዋታዎች፣ በሥነ ጽሑፍና መጥፎ ምሳሌ በሚሆኑ ሰዎች አማካኝነት እንደነዚህ ያሉትን ባሕርያት የሚያስፋፋ መሆኑ በጣም ያሳዝናል፤ እነዚህ ነገሮች ወንጀል እንዲበዛ ከማድረግ ውጪ የሚፈይዱት ነገር የለም። * ይሁንና ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደነዚህ ባሉት ተጽዕኖዎች ላለመሸነፍ ሊወስኑ ይችላሉ። እንዲያውም በአንድ ወቅት እንደነዚህ ባሉ ተጽዕኖዎች ተሸንፈው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አመለካከታቸውንና አኗኗራቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጠዋል።

ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ!

አንዴ ወንጀለኛ የሆነ ሰው ምንጊዜም ወንጀለኛ ሆኖ ይቀራል ማለት አይደለም። ኢንሳይድ ዘ ክሪሚናል ማይንድ የተሰኘው መጽሐፍ አንድ ሰው የወንጀለኝነትን ሕይወት እንደሚመርጥ ሁሉ እሱ ወይም እሷ “አቅጣጫቸውን በመቀየር ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ታማኝ ሰዎች ለመሆን ሊመርጡ ይችላሉ” በማለት ይናገራል።

ሰዎች ቀደም ሲል ያሳለፉት ሕይወት ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን ሊለወጡ እንደሚችሉ በተሞክሮ ታይቷል። * አንድ ሰው ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው ነገር አመለካከቱን፣ ውስጣዊ ግፊቱንና አስተሳሰቡን ተለዋዋጭ ከሆነው የሰዎች መሥፈርት ጋር ሳይሆን ፈጣሪ ካወጣቸው አስተማማኝ መሥፈርቶች ጋር ለማስማማት ፈቃደኛ መሆን ነው። ደግሞስ ከፈጣሪያችን ይበልጥ ማን ሊያውቀን ይችላል? ከዚህም በላይ አምላክ፣ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ጥሩ ወይም መጥፎ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ የመወሰን መብት የለውም? ፈጣሪ የእሱን መሥፈርቶች እንድናውቅ ሲል አምላካዊ ፍርሃት ያላቸውን 40 የሚያህሉ ሰዎች በመንፈሱ በመምራት ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ብለን የምንጠራውን መጽሐፍ አጽፎልናል፤ ይህ ግሩም መጽሐፍ የሰው ዘር ደስተኛና ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመራ የሚረዳ መመሪያ ተብሎ ሊጠራ ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

የኃጢአተኝነት ዝንባሌያችን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም ስለሚኖርብን አምላክን ለማስደሰት የሚያስፈልጉትን ለውጦች ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። እንዲያውም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በውስጡ የሚያደርገውን ትግል ‘ውጊያ’ በማለት ገልጾታል። (ሮሜ 7:21-25) ይህ ሰው በራሱ ኃይል ሳይሆን በአምላክ በመታመኑ በትግሉ ሊያሸንፍ ችሏል፤ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት ያጻፈው ቃሉ “ሕያውና የሚሠራ” በመሆኑ በትግሉ እንዲያሸንፍ ረድቶታል።—ዕብራውያን 4:12

ጤናማ “ምግብ” ያለው ኃይል

አካላችን ጤንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልገዋል። ከዚህም በላይ ምግቡ በደንብ ሊታኘክና ከሰውነት ጋር ለመዋሃድ በሚያስችለው መልኩ ሊፈጭ የሚገባ ሲሆን ይህ ደግሞ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ጤናማ እንድንሆን የአምላክን ቃል “በማኘክ” ከአእምሯችንና ከልባችን ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ አለብን። (ማቴዎስ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ [“ማሰባችሁን አታቋርጡ፣” NW]። . . .  የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።”—ፊልጵስዩስ 4:8, 9

አሮጌው ባሕርያችን ለአዲሱ ቦታ እንዲለቅ የምንፈልግ ከሆነ የአምላክን ሐሳቦች ‘ማሰባችንን ማቋረጥ’ እንደሌለብን ልብ በል። መንፈሳዊ እድገት በአንድ ጀምበር ስለማይመጣ ትዕግሥት ያስፈልጋል።—ቈላስይስ 1:9, 10፤ 3:8-10

በልጅነቷ በጾታ የተነወረችን አንዲት ሴት ሁኔታ ተመልከት፤ ይህች ሴት አደንዛዥ ዕፅና የአልኮል መጠጥ ትወስድ እንዲሁም ትምባሆ ታጨስ የነበረ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ወንጀሎች ፈጽማ በተመሠረተባት ክስ የተነሳ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባታል። በእስር ቤት እያለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረችና የምትማረውን ነገር ተግባራዊ አደረገች። ውጤቱስ ምን ሆነ? ቀስ በቀስ የቀድሞ ባሕርይዋ የክርስቶስን በሚመስል አዲስ ባሕርይ ተተካ። አሁን ይህች ሴት አጥፊ ለሆነ አስተሳሰብና መጥፎ ምግባር ባሪያ መሆኗ ቀርቷል። በጣም ከምትወዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ 2 ቆሮንቶስ 3:17 ሲሆን ጥቅሱ “ጌታ መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ ነጻነት አለ” ይላል። አዎን፣ ምንም እንኳ እስረኛ ብትሆንም ከዚህ ቀደም አግኝታው የማታውቀውን ነፃነት አግኝታለች።

አምላክ መሐሪ ነው

በይሖዋ አምላክ ዓይን፣ ‘ሊለወጥ አይችልም’ የሚባል ሰው የለም። * የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “ኀጢአተኞችን ወደ ንስሓ ልመልስ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም” ብሏል። (ሉቃስ 5:32) እውነት ነው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን፣ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ክርስቲያኖች የሚሰጡትን ፍቅራዊ ድጋፍ ጨምሮ አምላክ ከሚሰጠው እርዳታ በትዕግሥት መጠቀም ያስፈልጋል። (ሉቃስ 11:9-13፤ ገላትያ 5:22, 23) ለዚህም ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ፈጽመው የታሰሩ ቅን ልብ ያላቸው ወንዶችንና ሴቶችን መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስጠናት በመላው ዓለም ወደሚገኙ እስር ቤቶች አዘውትረው ይሄዳሉ። * በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በበርካታ እስር ቤቶች ውስጥ በየሳምንቱ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ።—ዕብራውያን 10:24, 25

ምንም እንኳን ቀደም ሲል ወንጀለኛ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አኗኗራቸውን ለውጠው እውነተኛ ክርስቲያኖች ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ክፋት እንደሚገን’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:12) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይህ ትንቢት ታላቅ የምሥራች የያዘ ሰፊ ትንቢት ክፍል ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በተለይ አእምሯቸው የታወከ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ በሚዘዋወሩባቸውና መሣሪያ ማግኘት በሚችሉባቸው አገሮች፣ የአእምሮ ሕመም ለአንዳንድ ወንጀሎች በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ርዕሰ ትምህርት ውስብስብ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ አይደለም።

^ አን.11 ከወንጀል ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 22, 1998 ንቁ! ገጽ 3-9 ላይ “ወንጀል የሌለበት ዓለም—መቼ?” (እንግሊዝኛ) የሚለውንና በነሐሴ 8, 1985 ንቁ! ገጽ 3-4, 4-6, 7-9, 10-12 ላይ “ጎዳናዎቻችን ከወንጀል ነፃ ይሆኑ ይሆን?” (እንግሊዝኛ) የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.14 ንቁ! እና መጠበቂያ ግንብ የተባሉት መጽሔቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የወንጀለኝነት ሕይወታቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ስላነሳሳቸው ግለሰቦች ብዙ ጊዜ ዘግበዋል። ንቁ! ሐምሌ 2006 እትም ገጽ 11-13ን፣ ጥቅምት 8, 2005 እትም ገጽ 20-21ን (እንግሊዝኛ)፣ እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ ጥር 1, 2000 እትም ገጽ 4-5ን፣ ጥቅምት 15, 1998 እትም ገጽ 27-29ን እና የካቲት 15, 1997 እትም ገጽ 21-24ን ተመልከት።

^ አን.21መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይላል?” የሚለውን በገጽ 10 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.21ለሕግ ታራሚዎች መንፈሳዊ እርዳታ ማድረግ” የሚለውን በገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ድህነትን ተቋቁመው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወንጀልን እንደ መፍትሔ አድርገው አይመለከቱትም

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ እስር ቤት መመለስ”

በለንደን፣ እንግሊዝ የሚታተመው ዘ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ከላይ በሠፈረው ርዕስ ሥር እንደዘገበው በብሪታንያ ቤት ሰብሮ በመዝረፍና በስርቆት ወንጀል ተፈርዶባቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደገና ሌላ ወንጀል ፈጽመው ይፈረድባቸዋል። ብዙዎቹ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ከፍተኛ ወጪ ለሚጠይቀው ጎጂ ሱሳቸው ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ በማይሉት የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እስር ቤቶች “የወንጀል ትምህርት ቤቶች” ናቸው?

“እስር ቤቶች የወንጀል ትምህርት ቤቶች ናቸው” በማለት በካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጆን ብራዝዋት ሎው ሪቪው በተባለው መጽሔት ላይ ጽፈዋል። ዶክተር ስታንተን ሳሜኖ ኢንሳይድ ዘ ክሪሚናል ማይንድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ “አብዛኞቹ ወንጀለኞች ከተሞክሮ ይማራሉ” ብለዋል፤ ይሁን እንጂ የሚማሩት ማኅበረሰቡ እንዲማሩ የሚፈልገውን ነገር አይደለም። ሳሜኖ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በእስር ቤት አንድ ሰው የተሻለ ወንጀለኛ ለመሆን ትምህርት የሚያገኝበት ሰፊ ጊዜና አጋጣሚ ያገኛል። . . . እንዲያውም አንዳንዶች የባሰውን በወንጀል ውስጥ በመዘፈቅ የተካኑ ወንጀለኞች ከመሆናቸውም በላይ ከመያዝ ለማምለጥ የሚያስችላቸውን ዘዴ ይማራሉ።”

ሳሜኖ በመጽሐፋቸው ውስጥ በሌላ ምዕራፍ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “እስራት የወንጀለኛውን ባሕርይ አይለውጥም። ወንጀለኛው በጎዳና ላይም ይሁን በእስር ቤት ከሌሎች ጋር ግንኙነት ይመሠርታል፤ አዳዲስ የወንጀል ዘዴዎችን ይማራል፤ እንዲሁም ለሌሎች ወንጀለኞች ልምዱን ያካፍላል።” አንድ ወጣት ወንጀለኛ “መታሰሬ የወንጀል አስተማሪ ለመሆን ብቃት እንዲኖረኝ አድርጎኛል” ብሏል።