በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጀል የሚወገድበት ጊዜ ቅርብ ነው

ወንጀል የሚወገድበት ጊዜ ቅርብ ነው

ወንጀል የሚወገድበት ጊዜ ቅርብ ነው

“ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም።”—መዝሙር 37:10

ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ በጥልቅ ያስባል፤ አንዳንዶች እንደሚያምኑት ለሰው ልጆች ደንታ የሌለው አምላክ አይደለም። (መዝሙር 11:4, 5) ከዚህም በላይ ሰዎች የማያዩትንም ጨምሮ ማንኛውንም ወንጀልና የፍትሕ መጓደል ይመለከታል። “የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ።” (ምሳሌ 15:3) ክፉዎች በእርግጥም “በሚያዳልጥ ስፍራ” ላይ እንደተቀመጡ ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 73:12, 18

ይሁን እንጂ ነቀፋ የሌለባቸውና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በድህነት መኖራቸው ሳያንስ ግፍ ቢፈጸምባቸውም ወደፊት ድንቅ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት “ንጹሐንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 37:37) ይህ ጥቅስ በቅርቡ በመላው ምድር ላይ ሲፈጸም የማየት ተስፋ ስላለን በዛሬው ጊዜ ላለነው ለእኛ ልዩ ማጽናኛ ይዞልናል።

የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው

ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከወደፊቱ ጊዜ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ጠይቀውት ነበር። “እስቲ ንገረን፤ . . . የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:3) የኢየሱስ መልስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ በዝርዝር ቀርቧል። እነዚህ እርስ በርስ የሚደጋገፉ የወንጌል ዘገባዎች፣ ይህ ዓለም ወደ መጨረሻው ሲቃረብ ጦርነት፣ ረሀብ፣ በሽታና ታላላቅ የምድር መናወጦች እንደሚኖሩ እንዲሁም ክፋት እንደሚገን ይገልጻሉ።

ኢየሱስ በትንቢት የተናገራቸው አስጨናቂ ሁኔታዎች ከ1914 ጀምሮ እየተፈጸሙ ነው። ኤሪክ ሆብስባም የተባሉ የታሪክ ምሑር ኤጅ ኦቭ ኤክስትሪምስ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት 20ኛው መቶ ዘመን “በታሪክ ዘመናት ሁሉ የከፋ ደም መፋሰስ የታየበት ዘመን እንደነበር ጥርጥር የለውም።”

በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን የክፋት መግነን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ፣ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፣ ለዘላለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 92:7 የ1954 ትርጉም) አዎን፣ ማስረጃው ግልጽ ነው:- ሰብል ሲያሸት የሚታጨድበት ወቅት መድረሱን እንደሚጠቁም ሁሉ በዛሬው ጊዜ ሕገ ወጥነት መብዛቱም የክፉዎች ጥፋት መቅረቡን ያመለክታል! ታዲያ ይህ የምሥራች አይደለም?—2 ጴጥሮስ 3:7

“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ”

መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። ማንኛውም ዓይነት ወንጀልና የፍትሕ መጓደል ፈጽሞ አይኖርም። ስለዚህ ከወንጀል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ይኸውም የሌባ ማስጠንቀቂያ ደወሎች፣ ቁልፎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ጠበቆች፣ ፖሊሶችና እስር ቤቶች አይኖሩም። መጽሐፍ ቅዱስ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 65:17

አዎን፣ ምድርና ሰብዓዊው ማኅበረሰብ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ያደርጋሉ። (ኢሳይያስ 11:9፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ጠንካራ ተስፋ ይህ ነው፤ አንተንም ይህ ተስፋ በቅርቡ እውን እንደሚሆን ራስህ መርምረህ እንድትገነዘብ ይጋብዙሃል። ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈሱ ያስጻፈው አምላክ ‘የማይዋሽ’ መሆኑን አስታውስ።—ቲቶ 1:2

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለሕግ ታራሚዎች መንፈሳዊ እርዳታ ማድረግ

ባለፉት በርካታ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በድምሩ 4,169 በሚሆኑ ማረሚያ ቤቶች፣ የወኅኒ ቤት ሆስፒታሎች እንዲሁም የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች ከሱሳቸው እንዲላቀቁ እርዳታ በሚያገኙባቸው ማዕከሎች ውስጥ ከሚገኙ ወንጀለኞች የተላኩ ደብዳቤዎች ደርሰዋቸዋል። አንዳንድ እስረኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲላክላቸው የጠየቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ብቃት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ግለሰቦች ክትትል ያደርጉላቸዋል። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም መንፈሳዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ወንድም ሆነ ሴት የሕግ ታራሚዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ወደ ወኅኒ ቤቶቹ አዘውትረው ይሄዳሉ። ከእነዚህ ውስጥ በርካታዎቹ በባሕርያቸው ላይ አስደናቂ ለውጥ በማድረግ ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆነዋል፤ አሁን ሕግ አክባሪ ዜጎች ናቸው።