በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ያለብኝን የጤና ችግር መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ያለብኝን የጤና ችግር መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምሳሌ 20:29 (የ1980 ትርጉም) “የወጣቶች መመኪያ ብርታታቸው ነው” ይላል። የጤንነት ችግር አሊያም የአካል ጉዳት ካለብህ ይህ ጥቅስ ፈጽሞ ለአንተ እንደማይሠራ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ጥቅሱ ለአንተም ይሠራል! እንዲያውም የአካል ጉዳት ያለባቸውም ሆኑ በከባድ ሕመም የሚሠቃዩ በርካታ ወጣቶች በጣም ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ችግሮችን መቋቋም ችለዋል። ንቁ! መጽሔት እንዲህ ላሉ አራት ወጣቶች ቃለ ምልልስ አድርጓል።

በጃፓን የሚኖረው ሂሮኪ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሴረብረል ፖልዚ በሚባል በሽታ ሲሠቃይ ቆይቷል። ሂሮኪ እንዲህ ብሏል:- “አንገቴ ጭንቅላቴን ቀጥ አድርጎ መያዝ አይችልም፤ እጆቼም እንደልብ አይታዘዙልኝም። ለሁሉም ነገር የሌሎች እርዳታ ያስፈልገኛል።”

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ናታሊ እና ወንድሟ ጄምስ ሲወለዱ ጀምሮ ድንክዬዎች ነበሩ። በተጨማሪም ናታሊ ስኮሊዎሲስ ማለትም የአከርካሪ አጥንት መጉበጥ ችግር አለባት። ናታሊ እንዲህ ብላለች:- “በአከርካሪዬ ላይ አራት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ተደርጎልኛል። አከርካሪዬ ጎበጥ ማለቱ ደግሞ የሳንባ ችግር አስከትሎብኛል።”

በብሪታንያ የሚኖረው ቲሞቲ፣ ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም በተባለ ኃይለኛ ድካም በሚያስከትል፣ ጡንቻ በሚያልፈሰፍስና የመንፈስ ጭንቀት በሚያመጣ በሽታ እንደተያዘ ያወቀው ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። ቲሞቲ እንዲህ ብሏል:- “ጤናማና ቀልጣፋ የነበርኩት ልጅ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እግሮቼ ሰውነቴን መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ አቅመ ቢስ ሆንኩ።”

በአውስትራሊያ የምትኖረው ዳንየል የ19 ዓመት ልጅ ሳለች የስኳር በሽታ እንዳለባት አወቀች። ዳንየል እንዲህ ብላለች:- “የስኳር ሕመም ምልክቶች በግልጽ ስለማይታዩ አንዳንድ ሰዎች በሽታው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ አይረዱም። ይህ በሽታ ሕይወቴን እንኳ ሊያሳጣኝ ይችላል።”

አንተም በአንድ ዓይነት ሕመም የምትሠቃይ ከሆነ ወይም የአካል ጉዳት ካለብህ ሂሮኪ፣ ናታሊ፣ ቲሞቲና ዳንየል የሚሰጧቸው ሐሳቦች የሚያበረታቱ ሆነው እንደምታገኛቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ጥሩ ጤንነት ካለህ ደግሞ እነሱ የሚሰጡት ሐሳብ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወይም በሕመም የሚሠቃዩ ሰዎችን ስሜት ይበልጥ እንድትረዳ ያስችልሃል።

ንቁ!:- ያላችሁበትን ሁኔታ ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ናታሊ:- ለእኔ በጣም ከባድ የሆነብኝ ሰዎች ሲመለከቱኝ ፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜት ነው። ፈጽሞ ነፃነት አይሰማኝም፤ ሰዎች ዓይናቸውን ከእኔ ላይ የሚነቅሉ አይመስለኝም።

ዳንየል:- የስኳር ሕመም ላለባቸው ሰዎች ትልቁ ፈተና፣ የሚበሉትን ምግብ ማወቅ እንዲሁም ምን ያህል መብላትና የትኞቹን ምግቦች መቀነስ እንዳለባቸው መወሰን ነው። በአመጋገብ ረገድ ጥንቃቄ ካላደረግሁ በደሜ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ሊያንስና ራሴን እስከ መሳት ሊያደርሰኝ ይችላል።

ሂሮኪ:- ላለብኝ አካላዊ ችግር እንዲስማማ ተደርጎ የተዘጋጀ ተሽከርካሪ ወንበር አለኝ። እዚህ ወንበር ላይ ወደ አንድ ጎን አዘንብዬ እንደተቀመጥኩ በየቀኑ ወደ 15 የሚጠጉ ሰዓታትን አሳልፋለሁ። ከዚህም በላይ ጥሩ እንቅልፍ የለኝም፤ ትንሽ ኮሽታ እንኳ ያነቃኛል።

ቲሞቲ:- መጀመሪያ ላይ የጤንነት ችግር እንዳለብኝ አምኖ መቀበል ትልቅ ፈተና ሆኖብኝ ነበር። ሁኔታዬ ያሸማቅቀኝ ነበር።

ንቁ!:- ሌላ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟችኋል?

ዳንየል:- ያለብኝ የስኳር ሕመም ከፍተኛ የድካም ስሜት አስከትሎብኛል። እኩዮቼ ከሚያስፈልጋቸው የበለጠ እንቅልፍ ማግኘት አለብኝ። ከዚህም በተጨማሪ የስኳር በሽታ መድኃኒት ያልተገኘለት ከባድ የጤና ችግር ነው።

ናታሊ:- ድንክ መሆኔ በሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው። ረዘም ካሉ መደርደሪያዎች ላይ ዕቃ እንደ ማውረድ ያሉ ቀላል ነገሮች እንኳ ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ናቸው። ብቻዬን ወደ ገበያ ከሄድኩ በጣም እቸገራለሁ።

ቲሞቲ:- አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመኝ የመንፈስ ጭንቀት በተጨማሪ የሚሰማኝን የማያቋርጥ ሕመም መቋቋም ግድ ሆኖብኛል። በዚህ በሽታ ከመያዜ በፊት በጣም ቀልጣፋ ነበርኩ። ሠራተኛ የነበርኩ ከመሆኑም ሌላ መንጃ ፈቃድ ነበረኝ። እንደ እግር ኳስና ስኳሽ የመሳሰሉ ጨዋታዎችን እጫወት ነበር። አሁን ግን ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አልችልም።

ሂሮኪ:- አጥርቶ የመናገር ችግር አለብኝ። ይህ ችግሬ ተስፋ ስለሚያስቆርጠኝ ከሰዎች ጋር ጭውውት ከመጀመር ወደኋላ እንድል ያደርገኛል። እጆቼን መቆጣጠር ስለማልችል አንዳንድ ጊዜ ሳላስበው ሰዎችን ልመታ እችላለሁ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ከተፈጠረ ደግሞ የመናገር ችግር ስላለብኝ “ይቅርታ” ማለት እንኳ አልችልም።

ንቁ!:- ያላችሁበትን ሁኔታ እንድትቋቋሙ የረዳችሁ ምንድን ነው?

ዳንየል:- ባሉኝ መልካም ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ እሞክራለሁ። ጥሩ ቤተሰብ ያለኝ ከመሆኑም በላይ በጉባኤ ውስጥ አፍቃሪ ጓደኞች አሉኝ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ ከጎኔ እንዳለ ይሰማኛል። በተጨማሪም የስኳር ሕመምን በሚመለከት በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ። ጤንነቴን የመንከባከቡ ኃላፊነት የእኔው ስለሆነ ራሴን ለመጠበቅ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።

ናታሊ:- ጸሎት የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ያሉብኝን ችግሮች በአንድ ጊዜ ሳይሆን በየተራ ለመፍታት እጥራለሁ። ራሴን በሥራ ማስጠመዴ በአፍራሽ አስተሳሰቦች እንዳልዋጥ ረድቶኛል። ከዚህም ባሻገር ችግሬን የማካፍላቸው አሳቢ ወላጆች አሉኝ።

ቲሞቲ:- ለአጭር ጊዜ ቢሆንም እንኳ በየቀኑ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ አንድ ነገር አከናውናለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት የዕለቱን ጥቅስ አነባለሁ። የግል ጥናትና ጸሎት በተለይ በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ በጣም ጠቅመውኛል።

ሂሮኪ:- ምንም ለውጥ ላመጣ በማልችለው ነገር ላይ በማሰብ ላለመጨነቅ እሞክራለሁ። እንዲህ ማድረግ ጊዜ ከማባከን ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊነቴን ለማጠናከር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፣ በተጨማሪም ያለሁበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን ላለማጥናት ሰበብ እንዲሆነኝ አልፈልግም። እንቅልፍ እምቢ ካለኝ ለመጸለይ እንደሚያስችለኝ አጋጣሚ አድርጌ እመለከተዋለሁ።—ሮሜ 12:12ን ተመልከት።

ንቁ!:- ከሌሎች ምን ማበረታቻ አግኝታችኋል?

ሂሮኪ:- የጉባኤ ሽማግሌዎች አቅሜ በፈቀደው መጠን የማደርጋቸውን ጥቂት ነገሮች በማንሳት ያመሰግኑኛል። በተጨማሪም በጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ ይዘውኝ ይሄዳሉ።—ሮሜ 12:10ን ተመልከት።

ዳንየል:- ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ በጉባኤ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ከልባቸው ሲያመሰግኑኝ መስማት ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ ለእኔ ጥሩ አመለካከት እንዳላቸው እንዲሰማኝ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በጥረቴ እንድገፋበት ያበረታታኛል።

ቲሞቲ:- በጉባኤያችን ውስጥ አንዲት አረጋዊት እህት አሉ፤ እኚህ እህት በስብሰባ ቀናት እኔን ሳያናግሩኝ ላለመሄድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎችና ሚስቶቻቸውም ማበረታቻ የሚሰጡኝ ከመሆኑም ባሻገር ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችን ይለግሱኛል። የ84 ዓመት አረጋዊ የሆነ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን እንዳወጣ ረድቶኛል። አንድ የጉባኤ አገልጋይ ደግሞ አብሬው አገልግሎት እንድወጣ የሚጋብዘኝ ሲሆን ለተሽከርካሪ ወንበሬ አመቺ በሆነ አካባቢ እንድናገለግል ዝግጅት ያደርጋል።—መዝሙር 55:22ን ተመልከት።

ናታሊ:- ወደ መንግሥት አዳራሽ እንደገባሁ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ሞቅ ያለ ሰላምታ ይሰጡኛል። አረጋውያን ምንም እንኳ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባቸውም ሁልጊዜ ለሌሎች የሚያካፍሉት አንድ የሚያበረታታ ሐሳብ አያጡም።—2 ቆሮንቶስ 4:16, 17ን ተመልከት።

ንቁ!:- አዎንታዊ አመለካከት ይዛችሁ እንድትቀጥሉ የረዳችሁ ምንድን ነው?

ሂሮኪ:- የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን ብሩሕ ተስፋ ያላቸው ሰዎችን ያቀፈ ድርጅት አባል ነኝ። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ መሆኔን ማወቄ አዎንታዊ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል።—2 ዜና መዋዕል 15:7ን ተመልከት።

ዳንየል:- የአምላክን ዓላማ ማወቅ ውድ መብት መሆኑን ሁልጊዜ አስባለሁ። ጥሩ ጤንነት ቢኖራቸውም በሕይወታቸው የእኔን ያህል ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ።—ምሳሌ 15:15ን ተመልከት።

ናታሊ:- ብሩሕ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ይሖዋን በማገልገል ላይ ስለሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የሚናገሩ ተሞክሮዎችን ማንበብ ያበረታታል። እንዲሁም ወደ ጉባኤ ስብሰባ ስሄድ ማበረታቻ እንደማገኝና የይሖዋ ምሥክር መሆን ትልቅ መብት መሆኑን የሚያስታውስ ሐሳብ አግኝቼ እንደምመለስ እርግጠኛ ነኝ።—ዕብራውያን 10:24, 25ን ተመልከት።

ቲሞቲ:- አንደኛ ቆሮንቶስ 10:13 እንደሚናገረው ይሖዋ ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም። ፈጣሪዬ ይህን ችግር ይቋቋመዋል ብሎ ከተማመነብኝ፣ እኔ ከአቅሜ በላይ ነው የምልበት ምን ምክንያት አለ?

 

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

  •  ሂሮኪም ሆነ ቲሞቲ ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አይችሉም። የአንተም ሁኔታ ተመሳሳይ ከሆነ እነሱ የሰጡት ሐሳብ አዎንታዊ አመለካከት እንድትይዝ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

  •  ዳንየል “የስኳር በሽታ ምልክቶች በግልጽ ስለማይታዩ አንዳንድ ሰዎች በሽታው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ አይረዱም” ብላለች። አንተስ ‘ሰዎች በቀላሉ በማይረዱልህ’ ሕመም እየተሠቃየህ ነው? ከሆነ ዳንየል ከተናገረችው ሐሳብ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

  •  ናታሊ በጣም ተፈታታኝ የሆነባት ነገር ሰዎች ሲመለከቷት ፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜት እንደሆነ ገልጻለች። እንደ ናታሊ ያለ ሰው የመሸማቀቅ ስሜት እንዳይሰማው ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? እንደ ናታሊ እንዲሰማህ የሚያደርግ ሕመም ወይም የአካል ጉዳት ካለብህ ልክ እንደ እሷ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የምትችለው እንዴት ነው?

  •  የአካል ጉዳት ያለባቸው ወይም በከባድ በሽታ የሚሠቃዩ የምታውቃቸውን ሰዎች ስም ጻፍ።

  •  እነዚህን ሰዎች ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ23 ዓመቱ ሂሮኪ፣ ጃፓን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ20 ዓመቷ ናታሊ፣ ደቡብ አፍሪካ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ20 ዓመቱ ቲሞቲ፣ ብሪታንያ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ24 ዓመቷ ዳንየል፣ አውስትራሊያ