መሳደብ መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
መሳደብ መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?
“የትምህርት ቤት ጓደኞቼን መምሰል እፈልጋለሁ። መሳደብ ልማድ የሆነብኝም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል።”—ሜለኒ *
“መሳደብ ያን ያህል ከባድ ነገር እንደሆነ አይሰማኝም ነበር። ትምህርት ቤትም ሆነ ቤት ውስጥ ሰዎች ሁልጊዜ ሲሳደቡ እሰማለሁ።”—ዴቪድ
አዋቂዎች ሲሳደቡ ወይም ጸያፍ ነገር ሲናገሩ ብዙውን ጊዜ እንደ ስህተት የማይታየው፣ ወጣቶች እንዲህ ቢያደርጉ ግን እንደ ነውር የሚቆጠረው ለምንድን ነው? መሳደብ ተገቢ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው የአንድ ሰው ዕድሜ ነው? በርካታ ሰዎች አስጸያፊ ቃላትን የሚጠቀሙ ከመሆኑም በላይ ትልልቅ ሰዎች ቢሳደቡ ምንም ችግር እንደሌለው ወጣቶች እንዲህ ቢያደርጉ ግን ስህተት እንደሆነ ተደርጎ እንደሚታይ ማወቅህ “መሳደብ መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል።
አንድ ሰው መሳደብን የሚለምደው እንዴት ነው?
በርካታ ሰዎች እንደሚሳደቡ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች፣ በትምህርት ቤት ለሚሰሙት ለእያንዳንዱ አስጸያፊ ቃል አንድ ብር የሚሰጣቸው ቢሆን ኖሮ በጣም ሀብታም ከመሆናቸው የተነሳ ሥራ መሥራት እንደማያስፈልጋቸውና ወላጆቻቸውም ጡረታ መወጣት ይችሉ እንደነበር ይገልጻሉ። የ15 ዓመቷ ኢቭ እንዲህ ብላለች:- “ብዙውን ጊዜ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ተራ በሆነ ጭውውት መሃል እንኳ በእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ብዙ ጊዜ ይሳደባሉ። በየቀኑ እንዲህ ያለ ንግግር የምትሰማ ከሆነ ደግሞ እንደነሱ ከማድረግ መቆጠብ ከባድ ይሆንብሃል።”
አንተስ ልክ እንደ ኢቭ መሳደብ በሚቀናቸው ሰዎች ተከበሃል? አንተ ራስህ ይህ ልማድ ይኖርህ ይሆን? * ሁኔታህ እንዲህ ከሆነ እንድትሳደብ የሚያደርግህ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቆም ብለህ አስብ። የምትሳደብበትን ምክንያት ካወቅህ ይህን ልማድ ማስወገድ ቀላል ይሆንልሃል።
እንድትሳደብ የሚገፋፋህ ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር።
ብዙውን ጊዜ የምትሳደበው ለምንድን ነው?
□ የሚያስቆጣ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመኝ
□ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ
□ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት
□ ኃይለኛ መስዬ ለመታየት
□ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ለመቃወም
□ ሌሎች ምክንያቶች
ብዙውን ጊዜ መሳደብ የሚቀናህ በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
□ በትምህርት ቤት
□ በሥራ ቦታ
□ በኢ-ሜይል ወይም በፈጣን የመልእክት መለዋወጫ መንገዶች ስጠቀም
□ ብቻዬን ስሆን
ለመሳደብህ ምክንያት ነው ብለህ የምታቀርበው ምንድን ነው?
□ ጓደኞቼ ስለሚያደርጉት
□ ወላጆቼ ስለሚያደርጉት
□ አስተማሪዎቼ ስለሚያደርጉት
□ የመዝናኛው ዓለም በስድብ የተሞላ መሆኑ
□ የተናገርኩት ነገር ከልቤ ባለመሆኑ ምንም ችግር እንደሌለው ስለሚሰማኝ
□ የምሳደበው እንዲህ ማድረጌ ከማይረብሻቸው ሰዎች ጋር ስሆን ብቻ ነው
□ ሌሎች ምክንያቶች
ይህን ልማድ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መሳደብ በእርግጥ መጥፎ ነገር ነው? እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።
‘የተናገርኩት ነገር ከልቤ አይደለም’ ማለት አይቻልም። ኢየሱስ “ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራል” ብሏል። (ሉቃስ 6:45) የምንናገረው ነገር ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን ጭምር እንደሚጠቁም ልብ በል። አስጸያፊ ቃላትን የምትናገረው ሌሎች እንዲህ ስለሚያደርጉ ብቻ ቢሆን እንኳ የእነሱን ምሳሌ መኮረጅህ ‘ብዙዎችን እንደምትከተልና’ የራስህ የሆነ የሥነ ምግባር መሥፈርት እንደሌለህ ያሳያል።—ዘፀአት 23:2
መሳደብህ ስለ አንተ ሌላም ነገር ያሳያል። የቋንቋ ምሑር የሆኑት ጄምስ ኦኮነር “የሚሳደቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሰዎች ጋር የማይስማሙ፣ ነቃፊዎች፣ ተጠራጣሪዎች፣ ቁጡዎች፣ ተከራካሪዎችና ደስታ የራቃቸው ከመሆናቸውም በላይ የማማረር ዝንባሌ ይታይባቸዋል” ብለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ነገሮች እነሱ ባሰቡት መንገድ ባለመሄዳቸው ምክንያት ሁልጊዜ የሚሳደቡ ሰዎች፣ ሁሉም ነገር እንደጠበቁት መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ደግሞ ስህተትን ማለፍ አይችሉም ማለት ነው። በተቃራኒው ግን ኦኮነር፣ የማይሳደቡ ሰዎች “ብዙውን ጊዜ ረጋ ያሉ፣ . . . በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም የሚችሉ ጎልማሳ ሰዎች” እንደሆኑ ገልጸዋል። አንተ የትኛውን ዓይነት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?
መሳደብ ስምህን ያጎድፋል። እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች ሁሉ አንተም ስለ መልክህ ትጨነቅ ይሆናል። ሰዎች ለአንተ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ ትፈልጋለህ። ይሁን እንጂ የምትናገርበት መንገድ፣ ከውጫዊ ገጽታህ የበለጠ ሌሎች ለአንተ ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ታውቃለህ? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ንግግርህ ቀጥሎ እንደተዘረዘሩት ባሉ ጉዳዮች ረገድ ተጽዕኖ ይኖረዋል:-
▪ ጓደኞችህ ለመሆን በሚፈልጉ ሰዎች
▪ በአንድ ሥራ ላይ በመቀጠርህ ወይም መቀጠር ባለመቻልህ
▪ ሰዎች ለአንተ በሚኖራቸው አክብሮት
ሰዎች መልካችንን በማየት ስለ እኛ የሚኖራቸው አመለካከት፣ መናገር ስንጀምር ወዲያው እንደሚቀየር አይካድም። ኦኮነር እንዲህ ብለዋል:- “በግድ የለሽነት በምትናገራቸው መጥፎ ቃላት የተነሳ አዲስ ጓደኛ ለማፍራት የሚያስችሉህን ምን ያህል አጋጣሚዎች እንደምታጣ ወይም ስንት ጊዜ ከሰዎች ጋር እንደምትራራቅ አሊያም ሰዎች ለአንተ ያላቸው አክብሮት ምን ያህል እንደሚቀንስብህ በጭራሽ ማወቅ አትችልም።” ከዚህ ምን መማር ትችላለህ? አስጸያፊ ቃላትን የምትጠቀም ከሆነ እየጎዳህ ያለኸው ራስህን ነው።
መሳደብ የመናገር ችሎታ ለሰጠህ ፈጣሪ አክብሮት እንደሌለህ ያሳያል። ለአንድ ጓደኛህ ሸሚዝ በስጦታ ሰጠኸው እንበል። ጓደኛህ የሰጠኸውን ሸሚዝ ቆሻሻ መጥረጊያ ወይም በር ላይ ምንጣፍ ቢያደርገው ምን ይሰማሃል? ፈጣሪያችን በስጦታ የሰጠንን የመናገር ችሎታ አግባብ ባልሆነ መንገድ ስንጠቀምበት ምን ሊሰማው እንደሚችል አስብ። የአምላክ ቃል “መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ” ማለቱ ምንም አያስገርምም።—ኤፌሶን 4:31
ከዚህ ማየት እንደምትችለው መሳደብ እንድታቆም የሚገፋፋህ በቂ ምክንያት
አለህ። ሆኖም ይህ ልማድህ ሥር የሰደደ ከሆነ ልታስወግደው የምትችለው እንዴት ነው?በመጀመሪያ ደረጃ:- የመለወጥን አስፈላጊነት መገንዘብ አለብህ። አነጋገርህን መቀየርህ ምን ጥቅም እንዳለው እስካልተገነዘብክ ድረስ መሳደብህን አታቆምም። ከታች ከተገለጹት ሐሳቦች መካከል መሳደብ እንድታቆም የሚያነሳሱህ የትኞቹ ናቸው?
□ የመናገር ችሎታ የሰጠህን ፈጣሪ ለማስደሰት ያለህ ፍላጎት
□ ሌሎች ይበልጥ እንዲያከብሩህ ስለምትፈልግ
□ የምትጠቀምባቸውን ቃላት ለማሻሻል ያለህ ፍላጎት
□ ባሕርይህን ለማሻሻል ያለህ ፍላጎት
በሁለተኛ ደረጃ:- እንድትሳደብ የሚያደርግህን ምክንያት ለማወቅ ሞክር። ሚለኒ እንዲህ ብላለች:- “መሳደብ ኃይለኛ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ሰዎች እንዲጫኑኝ አልፈልግም። እኔም ልክ እንደ ጓደኞቼ ሰዎችን በመዝለፍ የበላያቸው መሆኔን ማሳወቅ እፈልግ ነበር።”
አንተስ? የምትሳደብበትን ምክንያት ማወቅህ ችግሩን ለማስወገድ የሚረዳህ ቁልፍ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የምትሳደበው ሌሎች ሰዎች ስለሚሳደቡ ብቻ ከሆነ በራስህ ባሕርያት መተማመንን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያስፈልግሃል። ትክክል እንደሆነ ለምታምንበት ነገር መቆም የጉልምስና ምልክት ከመሆኑም በላይ የመሳደብ ልማድህን ማስወገድ እንድትችል በጣም ይረዳሃል።
በሦስተኛ ደረጃ:- ሐሳብህን የምትገልጽባቸውን አማራጭ መንገዶች ፈልግ። ይህን ማድረግ የምትችለው ለመሳደብ የሚገፋፋህን ስሜት በመቆጣጠር ብቻ አይደለም። መጥፎ ቃላት የመጠቀም ልማድህን ለማሸነፍ “አዲሱን ሰው” መልበስ ያስፈልጋል። (ኤፌሶን 4:22-24) አዲሱን ሰው መልበስህ ራስን የመግዛት ባሕርይን ይበልጥ እንድታዳብር የሚረዳህ ከመሆኑም ባሻገር ለራስህም ሆነ ለሌሎች አክብሮት እንዲኖርህ ያደርጋል።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ጥቅሶች አዲሱን ሰውነት መልበስና ለብሰኸው መቀጠል እንድትችል ይረዱሃል።
ቈላስይስ 3:2:- “አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ [ይሁን]።”
ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? አእምሮህ ትክክል በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር እንዲችል አሰልጥነው። የምታስበው ነገር በንግግርህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ምሳሌ 13:20:- “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”
ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? የጓደኞችህ የአነጋገር ዘይቤ በአንተ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
መዝሙር 19:14:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን።”
ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? ይሖዋ፣ በስጦታ የሰጠንን የመናገር ችሎታ እንዴት እንደምንጠቀምበት ይመለከታል።
ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት ትፈልጋለህ? አንድን መጥፎ ቃል ምን ያህል ጊዜ እንደተጠቀምክ በማስተዋል የምታደርገውን መሻሻል ለመከታተል እንድትችል ከላይ በሚገኘው ሰንጠረዥ ለምን አትጠቀምም? የምትጠቀምባቸውን ቃላት በሚያስገርምህ ፍጥነት ማሻሻል ትችላለህ!
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask . . .” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ “የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ” እንዲሁም “ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን” ስለሚል ክርስቲያኖች ስድብን እንዲያስወግዱ የሚገፋፋቸው በቂ ምክንያት አላቸው።—ኤፌሶን 4:29፤ ቈላስይስ 4:6
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
መሳደብ በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
▪ ጓደኞችህ ለመሆን በሚፈልጉ ሰዎች
▪ በአንድ ሥራ ላይ በመቀጠርህ ወይም መቀጠር ባለመቻልህ
▪ ሌሎች ለአንተ በሚኖራቸው አመለካከት
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የምታሳየውን መሻሻል ተከታተል
ሰኞ ማክሰኞ ረቡዕ ሐሙስ ዓርብ ቅዳሜ እሁድ
ሳምንት 1 ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․
ሳምንት 2 ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․
ሳምንት 3 ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․
ሳምንት 4 ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․ ․․․․․․․ ․․․․․․․
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትልቅ ዋጋ ያለውን ስጦታ አላግባብ አትጠቀምበትም፤ ታዲያ በስጦታ የተሰጠህን የመናገር ችሎታ ለምን አላግባብ ትጠቀምበታለህ?