በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት ማግኘት ይቻላል?

እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት ማግኘት ይቻላል?

እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት ማግኘት ይቻላል?

አንዳንድ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት ይጠይቃሉ:- ‘ከአምላክ ዘንድ የመጣ እውነት ካለ ይህን እውነት ለማግኘት እኔ መፈለግ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው? አምላክ ለሰው ዘር በሙሉ የሚሆን አስፈላጊ መልእክት ካለው ሰዎች መመራመር ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ ለመረዳት በሚያስችላቸው መንገድ ግልጽ አድርጎ አያስተላልፍላቸውም ነበር?’

አምላክ እንዲህ ለማድረግ ችሎታው እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ለሰዎች እውነትን ለማስተላለፍ የመረጠው በዚህ መንገድ ነው?

አምላክ እውነትን የሚያስተላልፈው እንዴት ነው?

አምላክ መልእክቶቹን የሚያስተላልፈው እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች ምርምር አድርገው ሊያገኟቸው በሚችሉበት መንገድ ነው። (መዝሙር 14:2) ከብዙ ዘመናት በፊት አምላክ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ያስተላለፈውን መልእክት ተመልከት። መልእክቱ የተላከው ዓመጸኛ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ሲሆን ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ሊያጠፏት እንደሆነ የሚገልጽ ነበር።—ኤርምያስ 25:8-11፤ 52:12-14

ሆኖም ኤርምያስ ትንቢት በሚናገርበት ወቅት ሌሎች ነቢያትም ከአምላክ የተላከ መልእክት እንደሚናገሩ ይገልጹ ነበር። ሐናንያ በኢየሩሳሌም ሰላም እንደሚሰፍን የሚገልጽ ትንቢት ይናገር ነበር። ይህ ደግሞ ኤርምያስ ከተናገረው መልእክት በጣም የተለየ ነበር። ታዲያ በዚያን ጊዜ የነበረ ሰው ማንን ማመን ይችላል? ኤርምያስን ወይስ ከእሱ ጋር የሚቃረን መልእክት የሚናገሩትን ነቢያት?—ኤርምያስ 23:16, 17፤ 28:1, 2, 10-17

ቅን ልብ ያላቸው አይሁዳውያን ማን ትክክል እንደሆነ ለማወቅ እንዲችሉ ይሖዋን ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። የእሱን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲሁም ስለ ኃጢአት ያለውን አመለካከት ማወቅ ነበረባቸው። እንዲህ በማድረግም አምላክ በኤርምያስ አማካኝነት የተናገረው “ማንም ስለ ክፋቱ ንስሓ የገባ የለም” የሚለው መልእክት እውነት መሆኑን ይቀበሉ ነበር። (ኤርምያስ 8:5-7) ከዚህም በላይ ሕዝቡ የነበረበት ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በኢየሩሳሌምም ሆነ በነዋሪዎቿ ላይ መጥፎ ነገር እንደሚያመጣ ያስተውሉ ነበር።።—ዘዳግም 28:15-68፤ ኤርምያስ 52:4-14

ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም የተናገረው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ከተማዋን አጠፏት።

አለመታዘዝ የሚያስከትለው መዘዝ ከረዥም ጊዜ በፊት በትንቢት የተነገረ ቢሆንም አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መድረሱን ለመገንዘብ ጥረት ያስፈልግ ነበር።

ስለ ክርስትና እውነትስ ምን ማለት ይቻላል?

በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለተነገረው እውነትስ ምን ሊባል ይችላል? ይህ እውነት ከአምላክ ዘንድ የተላከ መልእክት መሆኑን ሁሉም ሰው ተገንዝቦ ነበር? አልነበረም። ኢየሱስ ራሱ በእስራኤል ሕዝብ መካከል በአካል ተገኝቶ ያስተምርና ተአምራትን ይፈጽም የነበረ ቢሆንም ከአድማጮቹ መካከል አብዛኞቹ እሱ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ፣ ክርስቶስ ወይም የተቀባ መሆኑን አላስተዋሉም ነበር።

ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ለጠየቁት ፈሪሳውያን መልስ ሲሰጥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም” ብሏል። አክሎም “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ብሏል። (ሉቃስ 17:20, 21) አምላክ የሾመው ንጉሥ፣ ኢየሱስ በመካከላቸው ነበር! ይሁን እንጂ እነዚያ ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡት ትንቢቶች በእሱ ላይ እየተፈጸሙ እንዳሉ ለማየትና እሱ “ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” መሆኑን አምነው ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም።—ማቴዎስ 16:16

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላወጁት እውነትም ቢሆን ሰዎች የሰጡት ምላሽ ተመሳሳይ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የፈጸሟቸው ተአምራት አምላክ እንደሚደግፋቸው የሚያሳዩ ቢሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች እውነትን መረዳት አልቻሉም። (የሐዋርያት ሥራ 8:1-8፤ 9:32-41) ኢየሱስ፣ ሰዎችን እያስተማሩ ‘ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጓቸው’ ለተከታዮቹ ተልእኮ ሰጥቷቸው ነበር። እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን በማዳመጣቸውና በመማራቸው አማኞች ሊሆኑ ችለዋል።—ማቴዎስ 28:19፤ የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ 17:2-4, 32-34

ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ወንጌል የሚሰበከው “በሚታዩ ምልክቶች” ማለትም በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ ከአምላክ የተላከ መልእክት እንደሆነ በግልጽ ለመገንዘብ በሚያስችለው መንገድ አይደለም። ሆኖም የአምላክን እውነት መረዳት የሚቻል ከመሆኑም በላይ ይህ እውነት አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማምለክ የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል።—ዮሐንስ 10:4, 27

አንተም ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሔት እያነበብክ መሆንህ በራሱ እውነትን ከልብህ እንደምትፈልግ ያሳያል። ታዲያ እውነትን እያስተማረ ያለው የትኛው ሃይማኖት እንደሆነ እንዴት ለይተህ ልታውቅ ትችላለህ?

እውነተኛውን ሃይማኖት ለመለየት የሚረዳ ውጤታማ ዘዴ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የቤርያ ነዋሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ሲያስተምራቸው ምላሽ የሰጡበት መንገድ በእሱ ዘንድ ምስጋናን አትርፎላቸዋል። ጳውሎስ የተናገረውን ነገር እንደሰሙ፣ እውነት ነው ብለው አልተቀበሉም፤ ሆኖም በአክብሮት አዳመጡት። እኛም የቤርያ ሰዎች መልእክቱን ከሰሙ በኋላ ካደረጉት ነገር ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ “የቤርያ ሰዎች ከተሰሎንቄ ሰዎች ይልቅ አስተዋዮች ነበሩ፤ ምክንያቱም ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል። ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎቹ አመኑ” በማለት የሚናገረውን ሐሳብ ልብ በል። (የሐዋርያት ሥራ 17:10-12) ከዚህ ለመረዳት እንደምንችለው ፍለጋ ያደረጉት እንዲሁ ላይ ላዩን አልነበረም። ከጳውሎስ ጋር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ አጠር ያለ ውይይት በማድረግ ብቻ የመጨረሻ እልባት ላይ ለመድረስ አልጠበቁም ነበር።

የቤርያ ሰዎች “ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል” መባሉንም ልብ በል። ይህም የቤርያ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲያጠኑ ስለነበራቸው አመለካከት የሚነግረን ነገር አለ። የሰሙትን ሁሉ ያላንዳች ጥያቄ የሚቀበሉ ተላሎች ባይሆኑም የሰሙትን ሁሉ የሚጠራጠሩ ሰዎችም አልነበሩም። የአምላክን መልእክት የሚያስተላልፈው ጳውሎስ፣ የሚያብራራውን ነገር የመተቸት ዝንባሌም አልነበራቸውም።

ከዚህም በላይ የቤርያ ሰዎች ስለ ክርስትና ሲሰሙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንደነበረም ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። የሰሙት መልእክት ግሩም እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል፤ ምናልባትም መልእክቱ በጣም ጥሩ ከመሆኑ የተነሳ እውነት መሆኑን ለማመን ከብዷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የሰሙትን ነገር አንቀበልም ከማለት ይልቅ ‘ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ነገር እንደዚህ ይሆንን?’ በማለት እርግጠኞች ለመሆን ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ መረመሩ። በተጨማሪም በቤርያም ሆነ በተሰሎንቄ እንዲህ ዓይነት ትጋት የታከለበት ምርምር ያካሄዱ ሰዎች አማኞች ለመሆን እንደቻሉ ልብ በል። (የሐዋርያት ሥራ 17:4, 12) እውነት ሊገኝ አይችልም ብለው በማሰብ ተስፋ አልቆረጡም። እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተው አውቀዋል።

እውነት በሰዎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

አንድ ሰው እንደ ቤርያ ሰዎች እውነትን ሲያገኝ ይህንን ለሌሎች ለማካፈል ይጓጓል። አንዳንዶች ግን አንድ ሰው ሌሎች ሃይማኖቶችም ትክክል ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰቡ ትሑት መሆኑን እንደሚያሳይ ስለሚያምኑ ያገኘውን እውነት ለሌሎች የሚያካፍለውን ግለሰብ ይነቅፉት ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካገኘ እምነት ይኖረዋል። ከዚያ ወዲያ እውነትን ማግኘት ይቻል ይሆን? ወይም ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መዳን ያደርሱ ይሆን? የሚል ጥርጣሬ አይኖረውም። ይሁን እንጂ እውነትን ለማግኘት መጀመሪያ ጥልቅ ምርምር ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ደግሞ ትሕትና ይጠይቃል።

የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነት ምርምር በማድረጋቸው እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኙት ያምናሉ። አንተም በዛሬው ጊዜ እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እነማን እንደሆኑ ለይተህ ለማወቅ እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር ይጋብዙሃል። ይህን ማድረግ የተወሰኑ ነጥቦችን ከመመርመር የበለጠ ነገርን የሚጠይቅ ቢሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች አስመልክቶ በዚህ ገጽ ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች ምርምርህን ለመጀመር መንደርደሪያ ሊሆኑህ ይችላሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ ድረስ መጥተው መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያስጠኑህ ፈቃደኛ በመሆን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ በጥልቀት መመርመር ትችላለህ። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማወቅህ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ለማወቅ ያስችልሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የእውነተኛው ሃይማኖት ገጽታዎች

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያደረጓቸውንና ያስተማሯቸውን ነገሮች ልብ በል:-

የአምላክን ቃል እንደ መመሪያቸው አድርገው ተቀብለዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 1:21

ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ፣ ከአምላክ የተለየ አካል እንደሆነ እንዲሁም የአምላክ የበታች እንደሆነ አስተምረዋል።—1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 1 ጴጥሮስ 1:3

ሙታን ወደፊት በትንሣኤ አማካኝነት ወደ ሕይወት እንደሚመለሱ አስተምረዋል።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

በቡድን ደረጃ፣ በመካከላቸው ባለው ፍቅር ተለይተው ይታወቁ ነበር።—ዮሐንስ 13:34, 35

አምልኳቸውን ያከናውኑ የነበሩት በግለሰብ ደረጃ በተናጠል ሳይሆን በጉባኤዎች ተደራጅተው ነበር፤ ከዚህም በላይ የኢየሱስን ራስነት በሚቀበሉ የበላይ ተመልካቾችና በሽማግሌዎች አካል ሥር ሆነው በአንድነት ያመልኩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 14:21-23፤ 15:1-31፤ ኤፌሶን 1:22፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1-13

የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ በቅንዓት ይሰብኩ ነበር።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 1:8

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤርምያስ ከሚናገረው መልእክት ጋር የሚቃረን ሐሳብ የሚናገሩ ሌሎች ነቢያት እያሉ ኤርምያስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ሰዎች ሊያውቁ የሚችሉት እንዴት ነበር?

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቤርያ የነበሩት ሰዎች ጳውሎስን ካዳመጡ በኋላ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መርምረዋል

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መመርመርህ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል