በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ መወሰን ያለበት ማን ነው?

እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ መወሰን ያለበት ማን ነው?

እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ መወሰን ያለበት ማን ነው?

ኢየሱስ አንዳንድ የአምልኮ ዓይነቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው በግልጽ ተናግሯል። ኢየሱስ “ሐሰተኛ ነቢያት” እንደሚኖሩ የተናገረ ሲሆን እነዚህን ሰዎችም መጥፎ ፍሬ ከሚያፈራ ዛፍ ጋር አመሳስሏቸዋል፤ አክሎም እንዲህ ያለው ዛፍ “ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” በማለት ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ “‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም” ብሏል።—ማቴዎስ 7:15-22

እንዲያውም ኢየሱስ እሱን እንከተላለን ስለሚሉ አንዳንድ ሰዎች ሲናገር “‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ!’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 7:23) ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ አምላክ ለከዳተኞቹ እስራኤላውያን የተናገረው ሐሳብ በዘመኑ በነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ላይም እንደሚሠራ ሲናገር “በከንቱ [ያመልኩኛል]፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው” ብሏል።—ማርቆስ 7:6, 7

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በአምላክና በልጁ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሁሉም ዓይነት አምልኮ አይደለም። በመሆኑም ሁሉም ዓይነት አምልኮ እውነተኛ አምልኮ ነው ማለት አይቻልም። ይህ ሲባል ታዲያ እውነትን የሚያስተምረው አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው ማለት ነው? አምላክ አንዳንዶቹን ሃይማኖቶች ባይቀበልም እንኳን በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ሊጠቀም አይችልም? ወይም ደግሞ ሃይማኖቶቹ የሚያስተምሩት ትምህርት ምንም ይሁን ምን አምላክ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች የሚያቀርቡትን አምልኮ ሊቀበል አሊያም አምልኳቸውን ላለመቀበል ሊወስን አይችልም?

ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 1:10) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት ይመክራቸዋል:- “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ።”—ፊልጵስዩስ 2:2 የ1954 ትርጉም

እንዲህ ዓይነት አንድነት ካለ አንድ ሃይማኖት አለ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና [“ሃይማኖት፣” የ1954 ትርጉም] አንድ ጥምቀት” እንዳለ ይናገራል።—ኤፌሶን 4:4, 5

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ምን ያሳያል?

ከላይ የደረስንበት መደምደሚያ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህን ዘገባ ራስህ ብትመረምር አምላክ ለሕዝቡ አንድ የአምልኮ ሥርዓት ብቻ እንደሰጣቸው ትገነዘባለህ። በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ አምላክ ወኪሎቹ አድርጎ የተጠቀመው የእምነት አባቶችን ወይም የቤተሰብ ራሶችን ነበር። ከእነሱም መካከል ጎላ ብለው የሚጠቀሱት ኖኅ፣ አብራም (አብርሃም)፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ነበሩ።—ዘፍጥረት 8:18-20፤ 12:1-3፤ 26:1-4፤ 28:10-15

ከጊዜ በኋላ የያዕቆብ ዝርያዎች በግብጽ ባሪያዎች ሆኑ። እዚያ እያሉ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ቢጨቆኑም ቁጥራቸው እያደገ ሄዶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሆኑ። አምላክ እነሱን ከባርነት ነፃ በማውጣት ቀይ ባሕርን በተአምር ከፍሎ አሻገራቸው። ከዚያም እነሱን የራሱ ሕዝብ ያደረጋቸው ሲሆን መካከለኛ በነበረው በሙሴ በኩል ሕጎችን ሰጣቸው። በዚህ መንገድ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ወይም የአምላክ ሕዝብ ሆኑ።—ዘፀአት 14:21-28፤ 19:1-6፤ 20:1-17

አምላክ፣ የእስራኤል አጎራባች የነበሩ ሕዝቦች የሚያቀርቡትን አምልኮ እንዳልተቀበለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። እንዲያውም የራሱ ሕዝብ እሱ ከሰጣቸው ሕጎች በመራቅ የእነዚያን አጎራባች ሕዝቦች አምልኮ በተከተሉ ጊዜ ይቀጣቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 18:21-30፤ ዘዳግም 18:9-12

ከእስራኤላውያን አጎራባች ሕዝቦች መካከል እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ የሚፈልጉ ግለሰቦችስ ምን ማድረግ ነበረባቸው? እነሱም ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ሆነው ይሖዋ አምላክን ለማምለክ በመጀመሪያ የቀድሞ የሐሰት አምልኳቸውን መተው ያስፈልጋቸው ነበር። በእስራኤል ዙሪያ ከነበሩት ሕዝቦች መካከል ብዙ ሰዎች የአምላክን ሞገስ አግኝተው የእሱ ታማኝ አገልጋዮች ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል እንደ ከነዓናዊቷ ረዓብና ሞዓባዊቷ ሩት ያሉት ሴቶችና እንደ ኬጢያዊው ኦርዮና ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ያሉት ወንዶች ይገኙበታል፤ በቡድን ደረጃ ደግሞ ገባኦናውያንን መጥቀስ ይቻላል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን፣ ከላይ እንደተጠቀሱት ግለሰቦች ላሉ ከአምላክ ሕዝብ ጋር ሆነው በእውነተኛው አምልኮ ለሚካፈሉ ሰዎች በሙሉ ልባዊ ጸሎት አቅርቧል። *2 ዜና መዋዕል 6:32, 33

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ

ኢየሱስ ወደ ምድር ከተላከ በኋላም የእሱ ትምህርቶች እውነተኛውን አምልኮ ለማወቅ መሠረት ሆነዋል፤ የአምላክ ዓላማዎችም በላቀ መንገድ በግልጽ ታወቁ። ከጊዜ በኋላ እውነተኛ አምላኪዎች “ክርስቲያን” ተብለው መጠራት ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) በመሆኑም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የፈለጉ አይሁዳውያን ቀድሞ ይከተሉት የነበረውን አምልኮ መተው ነበረባቸው። ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓትና ኢየሱስ ካቋቋመው አምልኮ አንዱን መምረጥ ወይም በግለሰብ ደረጃ የራሳቸውን አምልኮ ማቅረብ አይችሉም ነበር። በአምላክ ቃል ውስጥ እንደተመለከትነው እውነተኛ አምላኪዎች ‘በአንድ እምነት’ የተሳሰሩ ነበሩ።—ኤፌሶን 4:4, 5

በዛሬው ጊዜ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት የሚያደርገው በአንድ ሃይማኖት በኩል ብቻ ነው የሚለው ሐሳብ ለአንዳንድ ሰዎች ጽንፈኝነት የተንጸባረቀበትና ለመቀበል የሚከብድ ይመስላቸው ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚመራን ወደዚህ መደምደሚያ ነው። ቀደም ሲል በራሳቸው መንገድ አምልኳቸውን ሲያከናውኑ የኖሩ ብዙ ግለሰቦች ይህን ሐቅ ተቀብለውታል። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች ጋር የተባበሩ ሲሆን መጀመሪያ ላይ የነበራቸው የጥርጣሬ ስሜት እያደር ጠፍቶ ብዙ በረከትና ደስታ አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰው ክርስትናን ተቀብሎ ከተጠመቀ በኋላ “ደስ እያለውም ጕዞውን ቀጠለ” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 8:39

በዛሬው ጊዜም እውነተኛውን ሃይማኖት ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ በረከቶችን ያገኛል። ይሁን እንጂ ብዙ ሃይማኖቶች ስላሉ እውነተኛ የሆነውን አንድ ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ስለ እነዚህ ሰዎች ለማወቅ ቀጥሎ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ልታነብ ትችላለህ:- ኢያሱ 2:1-7፤ 6:22-25፤ ሩት 1:4, 14-17፤ 2 ሳሙኤል 11:3-11፤ ኤርምያስ 38:7-13፤ ኢያሱ 9:3-9, 16-21

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ ሃይማኖት ምን ይደረጋል?