በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው?

እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው?

እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው?

ይህ ጥያቄ አንዳንድ ሰዎችን ቅር ያሰኛቸዋል። በመላው ዓለም እጅግ በርካታ ሃይማኖታዊ እምነቶች መኖራቸው እየታወቀ፣ ‘እውነተኛው ሃይማኖት የእኔ ብቻ ነው’ የሚል ሰው ጠባብ አስተሳሰብ ያለው እንዲያውም እብሪተኛ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ፣ ሌላው ቢቀር በአብዛኞቹ ዘንድ የተወሰነ ጥሩ ነገር እንደሚገኝ ማመኑ ተገቢ እንደሆነ ያስባሉ። አንተም እንደዚህ ይሰማሃል?

እርግጥ ነው፣ የተለያዩ አመለካከቶች ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችል መቀበል አስተዋይነት የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ለጤንነቱ ተስማሚ እንደሆነ የሚያምንበት አመጋገብ ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ ጤናማ ለመሆን የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ይህ ዓይነቱ አመጋገብ ብቻ ይመስል ሁሉም ሰው እሱ ተስማሚ እንደሆነ የሚያምንበትን አመጋገብ እንዲከተል ጫና ማድረግ ይኖርበታል? የሌላውም ሰው የምግብ ምርጫ፣ ሌላው ቢቀር ለመረጠው ሰው ጥሩ ምናልባትም የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ከግምት ማስገባቱ አስተዋይነትና ትሕትና የተንጸባረቀበት አካሄድ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።

በሃይማኖት ረገድስ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው? አንድ ሰው አስተዳደጉንና የመረዳት ችሎታውን መሠረት በማድረግ መምረጥ የሚችላቸው ተቀባይነት ያላቸው የተለያዩ አማራጮች አሉ? ወይስ ለሁሉም የሰው ዘሮች የሚሆኑ ሃይማኖታዊ እምነቶችን ያቀፈ አንድ እውነት አለ? እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት። በመጀመሪያ፣ በእርግጥ እውነትን ማግኘት ይቻላል? የሚለውን ነጥብ አንስተን እንወያያለን። ምክንያቱም እውነትን ማግኘት የማይቻል ከሆነ እውነተኛ የሆነውን አንድ ሃይማኖት መፈለጉ ትርጉም አይኖረውም።

ሃይማኖታዊ እውነትን ማግኘት ይቻላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሮማዊው ገዢ በጲላጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ለጲላጦስ “ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” ብሎት ነበር። ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” ሲል፣ እውነት የሚባል ነገር መኖሩን እንደሚጠራጠር መግለጹ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 18:37, 38) በሌላ በኩል ኢየሱስ ስለ እውነት በግልጽ ከመናገር ወደኋላ አላለም። እውነት ስለመኖሩ ጥርጣሬ አልነበረውም። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ለተለያዩ ሰዎች የተናገራቸውን ከዚህ በታች የቀረቡትን አራት ሐሳቦች ተመልከት።

“የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው።”—ዮሐንስ 18:37

“መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ።”—ዮሐንስ 14:6

“እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”—ዮሐንስ 4:23, 24

“በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”—ዮሐንስ 8:31, 32

ኢየሱስ እውነት እንዳለና እውነትን ልናውቀው እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገሩ፣ ሃይማኖታዊ እውነት መኖሩንና ሊገኝ መቻሉን እንድንመረምር ሊያነሳሳን አይገባም?

ፍጹም እውነት የሚባል ነገር አለ?

ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን የምትችልባቸው አንዳንድ ነገሮች መኖራቸውን እንደምትቀበል አያጠራጥርም። በሕይወት እየኖርክ መሆኑንና በዙሪያህ ያሉት ነገሮች በእውን ያሉ መሆናቸውን እርግጠኛ ነህ። ዛፎች፣ ተራሮች፣ ደመና፣ ፀሐይና ጨረቃ በአጠቃላይ ግዑዙ ዓለም በምናብህ የፈጠርካቸው ነገሮች አይደሉም። እርግጥ ነው፣ በፍልስፍና ተጠቅመው እነዚህም ነገሮች እውን መሆናቸው አጠራጣሪ እንደሆነ የሚገልጹ ጥቂት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ከመሰለው ጽንፈኛ አስተሳሰብ ጋር ልትስማማ አትችልም።

የተፈጥሮ ሕጎችንም እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህንንም በተመለከተ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ከገደል ላይ ብትዘል ትወድቃለህ፤ ምግብ መብላት እምቢ ብትል ይርብሃል፤ ለረጅም ጊዜ ምግብ ሳትበላ ከቆየህ ደግሞ ትሞታለህ። እንደነዚህ ያሉት የተፈጥሮ ሕጎች በአንዳንዶች ላይ ቢሠሩም በሌሎች ላይ ግን ላይሠሩ ይችላሉ ብለህ አታስብም። እነዚህ ሕጎች በሁሉም የሰው ዘሮች ላይ ስለሚሠሩ ዓለም አቀፋዊ ሕጎች ሊባሉ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?” ብሎ በመጠየቅ እንዲህ ካሉት ዓለም አቀፋዊ ሕጎች አንዱን ጠቅሷል። በእርግጥም ይህ ጥቅስ በተጻፈበት ወቅት ልብስ ከእሳት ጋር ከተገናኘ መቃጠሉ ዓለም አቀፋዊ እውነት ነበር። ይሁን እንጂ ከላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ይህን ሐቅ ሲጠቅስ አንድ ትልቅ ቁም ነገር እየገለጸ ነበር:- “ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛ” ሰው የከፋ መዘዝ ይደርስበታል።—ምሳሌ 6:27, 29

ይህ ሐሳብ ፍጹም እውነት መሆኑን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? አንዳንዶች እንዲህ ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ። የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከሰው ወደ ሰው እንደሚለያዩና በእያንዳንዱ ግለሰብ አስተዳደግ፣ እምነትና ሁኔታ ላይ የተመኩ እንደሆኑ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ውስጥ ጥቂቶቹን እናንሳና እነዚህ ሕጎች ዓለም አቀፋዊ እውነቶች ለመባል ይበቁ እንደሆነና እንዳልሆነ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝርን ያወግዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አንዳንድ ሰዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ እንደ እውነት አድርገው ስለማይቀበሉት ምንዝር ይፈጽማሉ። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ሰዎችም ጭምር ብዙውን ጊዜ ይህ አካሄዳቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ያጭዳሉ፤ ምንዝር አብዛኛውን ጊዜ ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል የሕሊና መረበሽና ፍቺ እንዲሁም ድርጊቱ በሚነካቸው ሁሉ ላይ የሚደርሰው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የስሜት ጠባሳ ተጠቃሾች ናቸው።

ስካርም ቢሆን በአምላክ ዘንድ የተወገዘ ነው። (ምሳሌ 23:20፤ ኤፌሶን 5:18) ሰካራሞች ምን ይደርስባቸዋል? አብዛኛውን ጊዜ ሥራቸውንና ጤንነታቸውን እንዲሁም አብረዋቸው በስሜት የሚሠቃዩትን ቤተሰቦቻቸውን ያጣሉ። (ምሳሌ 23:29-35) መስከር ስህተት እንደሆነ የማያምኑ ሰዎችም ጭምር እንዲህ ዓይነቶቹ መዘዞች አይቀሩላቸውም። ታዲያ የእነዚህ የሥነ ምግባር ሕጎች እውነተኝነት በእያንዳንዱ ግለሰብ እምነት ወይም ግንዛቤ ላይ የተመካ ነው ማለት ይቻላል?

መልካም እንድናደርግ የሚያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕጎችም እንደ ምሳሌ እናንሳ፤ ከእነዚህ መካከል ባል ሚስቱን እንዲወድና ሚስትም ባሏን እንድታከብር እንዲሁም ለሌሎች መልካም እንድናደርግ የሚያዙት ሕጎች ይገኙበታል። (ማቴዎስ 7:12፤ ኤፌሶን 5:33) እነዚህን ትእዛዛት ማክበር ጠቃሚ ውጤቶች ያመጣል። እንደነዚህ ያሉት የሥነ ምግባር ሕጎች ለአንዳንድ ሰዎች ቢሠሩም ለሌሎች ግን አይሠሩም ብሎ የሚከራከር ይኖራል?

የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕጎች መታዘዝም ሆነ አለመታዘዝ በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ውጤት አለ። ይህ ሐቅ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ሕጎች እንዲሁ የተለያዩ አመለካከቶች ብቻ እንዳልሆኑ ያረጋግጣል። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሕጎች እውነት ናቸው። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕጎች ሲያከብሩ እንደሚጠቀሙ፣ ይህን ሳያደርጉ ሲቀሩ ግን እንደሚጎዱ ማስረጃው ያሳያል።

ስለዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር ሕጎች ለሁሉም የሰው ዘሮች የሚሠሩ ከሆነ አምልኮን በተመለከተ በአምላክ ቃል ውስጥ ስለሰፈሩት መመሪያዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ስንሞት ምን እንደምንሆን ስለሚገልጸው ሐሳብ እንዲሁም ዘላለማዊ ሕይወትን አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋስ ምን ሊባል ይቻላል? እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችም ቢሆኑ ለሁሉም የሰው ዘሮች የተሰጡ እውነቶች ናቸው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በመከተላቸው የሚጠቀሙትም ሆነ መመሪያዎቹን ባለመታዘዛቸው የሚጎዱት እነዚህ ሕጎች እውነት እንደሆኑ የሚያምኑ ሰዎች ብቻ አይደሉም።

እንግዲያው እውነትን ማግኘት ይቻላል። ኢየሱስ፣ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) ያም ሆኖ እውነትን ማግኘት የማይቻል ነገር ይመስል ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም እጅግ ብዙ የሆኑ የተለያዩ ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንደሚያስተምሩ ይገልጻሉ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት የሚያስተምረው የትኛው ሃይማኖት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው አንድ ሃይማኖት ብቻ እንደሆነ ሊሰማን ይገባል? እውነት፣ ወይም ሌላው ቢቀር የተወሰኑ የእውነት ገጽታዎች በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ሊገኙ አይችሉም?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እሳትን መታቀፍ የሚያስከትለው መዘዝ የአምላክን ሕጎች ካለመታዘዝ ጋር ሊዛመድ የሚችለው እንዴት ነው?