በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደ ጥናት መሠረት “በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ 15 ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር ወሲብ እንደፈጸሙ የተናገሩት ወንዶች 29 በመቶ ሲሆኑ የዚህን ያህል ቁጥር ያላቸው የፆታ ተጓዳኞች የነበሯቸው ሴቶች 9 በመቶ ናቸው።”—ሴንተርስ ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሪቬንሽን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ግሪክ ውስጥ “ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ከሆኑ ልጆች 62 በመቶ የሚሆኑት ልጆች በሞባይል ስልካቸው ላይ ወሲባዊ ምሥሎችን እንደጫኑ ተናግረዋል።—ኤልኤፍቴሮፒያ፣ ግሪክ

በብሪታንያ ውስጥ በአንድ ጥናት ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል 82 በመቶ የሚሆኑት “ሃይማኖት፣ መከፋፈልና ውጥረት እንደሚያስከትል” ይሰማቸዋል።—ዘ ጋርዲያን፣ ብሪታንያ

ለ64 ዓመታት የቆየ ራስ ምታት

ከ60 ዓመት በላይ “በኃይለኛ ራስ ምታት” ሲሠቃዩ የኖሩ አንዲት ቻይናዊት፣ ዶክተሮች ከጭንቅላታቸው ውስጥ ሦስት ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ጥይት ባወጡላቸው ጊዜ የሕመማቸውን መንስዔ ማወቅ ችለዋል። እኚህ አረጋዊት በ13 ዓመታቸው በጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው መስከረም 1943 ጃፓን፣ በሲንዪን ግዛት የሚገኝ መንደርን በወረረችበት ወቅት ነበር። የራስ ምታታቸው መንስኤ ይህ ይሆናል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም። ራስ ምታቱ እየባሰባቸው ሲሄድ የተደረገላቸው የራጅ ምርመራ በጭንቅላታቸው ውስጥ ጥይት መኖሩን እንዳሳየ ሲንሁኣ የተባለው የዜና ወኪል ዘግቧል። እኚህ ሴት አሁን 77 ዓመታቸው ሲሆን “በጥሩ ጤንነት” ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

ረዥም ዕድሜ የኖረው ዓሣ ነባሪ

የአላስካ ተወላጆች የሆኑ አዳኞች ቦውሄድ በመባል የሚጠራውን ዓሣ ነባሪ በ2007 በገደሉበት ወቅት፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ዓሣ ነባሪ ወግቶ ለመግደል ይውል የነበረ ጦር መሳይ መሣሪያ ጫፎችና ቁርጥራጮች በሰውነቱ ውስጥ አግኝተዋል። እነዚህ መሣሪያዎች “በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ [በማሳቹሴትስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ] ኒው ቤድፎርድ ከተማ የተሠራ የሚፈነዳ ጦር ቁርጥራጮች” መሆናቸው እንደታወቀ ዘ ቦስተን ግሎብ ይናገራል። ይህ ዓይነቱ ጦር ብዙም ሳይቆይ ከአገልግሎት ውጭ በመሆኑ ዓሣ ነባሪው የተወጋው “በ1885 እና በ1895 መካከል በነበረው ጊዜ” እንደነበረ በኒው ቤድፎርድ የዓሣ ነባሪ ማጥመድ ሙዚየም የሚገኙት ታሪክ ጸሐፊዎች ገልጸዋል። በመሆኑም ዓሣ ነባሪው በሞተበት ጊዜ ቢያንስ 115 ዓመቱ ነበር። ግሎብ የተባለው ጋዜጣ እንደሚናገረው “ተመራማሪዎች፣ ቦውሄድ የተባለው የዓሣ ነባሪ ዝርያ በምድር ላይ ካሉት አጥቢ እንስሳት ሁሉ ረጅም ዕድሜ እንዳለውና እስከ 150 ዓመት መኖር እንደሚችል” ካመኑ ቆይተዋል። ይህ ግኝት ደግሞ “ተጨማሪ ማስረጃ” ሆኖላቸዋል።

ወደ ቅሪተ አካልነት የተለወጠ ደን

የስነ ምድር ተመራማሪዎች ወደ ቅሪተ አካልነት የተቀየሩ ልዩ ልዩ ዕፅዋት የነበሩበት ሰፊ ደን በቁፋሮ ያገኙ ሲሆን ዝርያቸው ከምድር ገጽ ከጠፋው ከእነዚህ ዕፅዋት አንዳንዶቹ ቁመታቸው እስከ 40 ሜትር ይደርሳል። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ደን የሚገኘው በኢሊኖይስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለ የድንጋይ ከሰል ማውጫ መተላለፊያዎች ውስጥ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ደን ከምድር በታች እንዲቀበር ያደረገው ኃይለኛ የመሬት መናወጥ እንደሆነ ያምናሉ። በደኑ ላይ ምርምር ያደረገው ቡድን መሪ የሆኑት ቢል ዲሚካል “በጣም የሚያስደንቅ ነው” በማለት ተናግረዋል። “ከሞላ ጎደል ደኑ በሕይወት እያለ በውስጡ እንደምንሄድ አድርገን በአእምሯችን መሳል እንችላለን” ብለዋል።

ያረጀ ምርጥ ወይን ጠጅ ቆፍሮ ማውጣት

ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ጎብኚዎች “በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሕብረ ብሔሩ ጦር ወታደሮች . . . ትተውት የሄዱትን ያረጀ ወይን ጠጅ ቆፍረው ለማውጣት” የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሪፑብሊክ ወደነበረችው መቄዶንያ እየተጓዙ መሆናቸውን ካቲሜሪኒ—ኢንግሊሽ ኤድሽን የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። በአብዛኛው ከፈረንሳይ የሚሄዱት ጎብኚዎች ካርታዎችን ይዘው የተተዉ የወታደሮች መጋዘኖችን ይቆፍራሉ። በአሁኑ ወቅት እዚያ ተቀብሮ የሚገኝ ወይን ጠጅ ቢያንስ የ90 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ጋዜጣው እንደሚገልጸው ከሆነ “ሳይበላሽ የተገኘ አንድ ጠርሙስ ወይን ጠጅ . . . እስከ 2,675 የአሜሪካ ዶላር ሊያወጣ ይችላል።” ወይንና ኮኛክ ቆፍረው ያወጡ የአካባቢው ሰዎች “ከዚህ የተሻለ ጣዕም ያለው መጠጥ ቀምሰው እንደማያውቁ” ተናግረዋል።