በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍል ውኃ መታጠቢያዎች የሞሉባት ምድር

የፍል ውኃ መታጠቢያዎች የሞሉባት ምድር

የፍል ውኃ መታጠቢያዎች የሞሉባት ምድር

ከ2,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ኬልት የተባሉት ሕዝቦች፣ አያሌ ፍል ውኃዎች ባሉበት አካባቢ መንደር መሠረቱና አክ-ኢንክ ብለው ሰየሙት፤ ትርጉሙም “ብዙ ውኃ” ማለት ነው። በዛሬው ጊዜ አክ-ኢንክ፣ የሃንጋሪ ዋና ከተማ የሆነችው ቡዳፔስት ስትሆን ከአውሮፓ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ናት። የቀድሞዎቹ ሰፋሪዎች፣ መንፈስን በሚያድሱትና ሕመምንና ሥቃይን በሚያስታግሱት ሞቅ ያሉ ፍል ውኃዎች ውስጥ አልፎ አልፎ ይዋኙ ነበር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይህ የአውሮፓ ክፍል በሮም ግዛት ሥር ወደቀ። ሮማውያን ይህን መንደር በማስፋፋት እዚህ ቦታ ላይ የጦር ሠፈር ገነቡና ክዊንኩም ብለው ሰየሙት። ይህ ስም የተወሰደው ውኃ የሚል ትርጉም ካለው የኬልቲክ ቃል አሊያም ደግሞ “አምስት ውኃዎች” የሚል ትርጉም ካለው አኩዋ ኩዊንክዌ የተሰኘ የላቲን አባባል እንደሆነ ይታመናል። ሮማውያን ትላልቅ የውኃ ቧንቧዎችን፣ የፍሳሽ መውረጃ ቦዮችንና የግልም ሆነ የሕዝብ መታጠቢያዎችን ገነቡ። በመሆኑም የቡዳፔስት መታጠቢያዎች የረጅም ዘመን ታሪክ አላቸው።

የሮም አገዛዝ ከወደቀ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ እነዚህ መታጠቢያዎች እንደገና ታዋቂ ሆኑ። በ15ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች በሃንጋሪ ዋና ከተማ አቅራቢያ የነበሩትን የፍል ውኃ መታጠቢያዎች ማድነቃቸው ከተማዋ ዝነኛ እንድትሆን አደረጋት። ሃንጋሪን ከ1458 እስከ 1490 የገዛው ንጉሥ መታየስ ኮርቫይነስ፣ ራች የሚባለውን የሚወደውን የፍል ውኃ መታጠቢያ ጣሪያ ባለው መተላለፊያ አማካኝነት ከንጉሣዊ መኖሪያው ጋር አገናኝቶት እንደነበረ ይነገራል። በመሆኑም በማንኛውም የአየር ሁኔታ በመታጠቢያው መጠቀም ይቻል ነበር።

በ16ኛውና በ17ኛው መቶ ዘመን ቱርኮች፣ የሃንጋሪን ዋና ከተማ ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ተቆጣጠሩት። እነሱም የእንፋሎት እንዲሁም የፍል ውኃ መታጠቢያዎች ሠሩ፤ እነዚህ መታጠቢያዎች በሙስሊም ሃይማኖት በሚከናወነው የመታጠብ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚያገለግሉ ከመሆኑም በላይ በቱርኮች ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። ቱርኮቹ የሠሯቸው በጣም የሚያምሩ መታጠቢያዎች ክብ ቅርጽ ያለው ጣሪያ ሲኖራቸው ዙሪያቸውን በደረጃዎች የተከበቡ ነበሩ። ውኃው እስከ ትከሻ የሚደርስ ጥልቀት ነበረው። መሃል ላይ በሚገኘው ኩሬ ዙሪያ መታጠቢያ ገንዳዎችና ማረፊያ ቦታዎች የተሠሩ ሲሆን ወንዶችና ሴቶች በተራ በተራ ይጠቀሙ ነበር። ከእነዚያ መታጠቢያዎች አንዳንዶቹ እስካሁን ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ።

በ1673 የታተመ ስለ ጉዞ የሚያወሳ ጽሑፍ፣ አሁን ቡዳፔስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የነበሩት መታጠቢያዎች “ከፍል ውኃው ብዛትና ከመፈወስ ኃይላቸው እንዲሁም መታጠቢያዎቹ ከነበሩባቸው ሕንፃዎች ስፋትና ውብ ከሆነው አሠራራቸው” አንጻር አውሮፓ ውስጥ ከነበሩት ሁሉ እጅግ ምርጥ እንደነበሩ ገልጿል። በ19ኛው መቶ ዘመን የፊንላንድ መታጠቢያ ወይም ሳውና ይበልጥ እየታወቀ ሲመጣ በቡዳፔስት የነበሩት መታጠቢያዎች ተጨማሪ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ በቡዳፔስት መታጠቢያዎች ውስጥ ሳውና፣ የእንፋሎት ክፍሎችና የቀዝቃዛ ውኃ መዋኛዎች ተጨመሩ።

የአካባቢው ስነ ምድራዊ ሁኔታ

በቡዳፔስት ያሉት 123 ፍል ውኃዎችና 400 የመራራ ውኃ ምንጮች በየቀኑ 70 ሚሊዮን ሊትር የሚያህል ውኃ ያፈልቃሉ። ይህ ሁሉ ውኃ የሚመጣው ከየት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ በአካባቢው ስነ ምድራዊ ሁኔታ ላይ የተመካ ነው።

ቡዳፔስትን አቋርጦ የሚያልፈው የዳንዩብ ወንዝ በስተ ምዕራብ ያሉትን የቡዳ ኮረብቶች በስተ ምሥራቅ ካሉት የፔስት ረባዳ ሜዳዎች ይለያቸዋል። ከብዙ ዘመናት በፊት በአንድ ወቅት ይህ አካባቢ በባሕር የተሸፈነ ስለነበረ በቦታው ላይ እንደ በሃ ድንጋይ ያሉ ድንጋዮች ክምችት አለ። እነዚህ አለቶች በሸክላ አፈር፣ ከኖራ ጋር በተቀላቀለ ሸክላ፣ በአሸዋና በከሰል ድንጋይ ተሸፈኑ።

የመሬት ገጽ ሲሰነጠቅ የዝናብ ውኃ ወደ መሬት ውስጥ ይሰርጋል፤ በዚህ ጊዜ ጥልቀት ባለው ክፍል ላይ የሚገኙት የጋሉና በማዕድን የበለጸጉ ድንጋዮች ውኃውን ያሞቁታል። ከዚያም ከፍተኛ ሙቀት ያለው ይህ ውኃ ስንጥቅ ባገኘበት ቦታም ሆነ በምንጮች በኩል በኃይል ተፈትልኮ እየተትጎለጎለ ወደ ላይ ይወጣል።

ይህ ስነ ምድራዊ ሁኔታ የሚገኘው በቡዳፔስት ብቻ ሳይሆን በመላው ሃንጋሪ ነው። በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ብዙ አካባቢዎች፣ በአንዳንዶች ዘንድ መድኃኒትነትና የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው የሚታመንባቸው በማዕድን የበለጸጉ ውኃዎችና ውብ መታጠቢያዎች ሞልተዋል። *

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የፍል ውኃ ምንጮች በብዙ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ አድናቆት ሲቸራቸው ኖሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳ በሙት ባሕርና በአቃባ ባሕረ ሰላጤ መካከል በሚገኘው በሴይር ምድረ በዳ የፍል ውኃ ምንጮች እንደተገኙ ተገልጿል።—ዘፍጥረት 36:24

የሰው ልጅ በምንኖርባት ፕላኔት ላይ ስላሉት ውስብስብ ነገሮች ገና ብዙ ያላወቀው ነገር አለ። ለመሆኑ፣ አምላክ ምድርን የመሠረተውና በላይዋ ላይ እነዚህን ሁሉ ድንቅ ነገሮች የሠራው እንዴት ነው? ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች እንዲህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላቸው ገደብ የለሽ በሆነው የፈጣሪ ጥበብ በአድናቆት እንዲዋጡ ያደርጋቸዋል።—ኢዮብ 38:4-6፤ ሮሜ 1:20

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ንቁ! ማንኛውንም የሕክምና ዓይነት የሚደግፍ ሐሳብ አያቀርብም።

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጌላርት ሆቴል የሚገኘው የፍል ውኃ መታጠቢያ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቱርኮች የሠሯቸው የሩዶሽ መታጠቢያዎች

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሳቼንዪ መታጠቢያዎች በክረምት ወራት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች:- Courtesy of Tourism Office of Budapest