በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ሲል ምን ማለቱ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ሲል ምን ማለቱ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ሲል ምን ማለቱ ነው?

በአንድ ሱቅ መስኮት ላይ “የመጨረሻው ቀን” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል። የዚህ ማስታወቂያ መልእክት ግልጽ ነው። በአንድ በኩል ሱቁ የቅናሽ ሽያጭ የሚያደርግበት የመጨረሻው ዕለት ነው ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሱቁ ከዚያን ዕለት በኋላ ይዘጋል ማለት ሊሆን ይችላል። ይሁንና አንድ ሰው “የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ውስጥ ነው” ብሎ ቢናገር ምን ማለቱ ነው?

‘የመጨረሻው ቀን’ እና ‘የፍጻሜው ዘመን’ የሚሉት አገላለጾች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹት ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 የ1954 ትርጉም፤ ዳንኤል 12:4) ከ2,500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ዳንኤል ስለ ዓለም ኃያላን መንግሥታትና እነዚህ መንግሥታት እስከ “መጨረሻው ዘመን” ድረስ እርስ በርሳቸው ስለሚያደርጉት ጦርነት ራእይ ተመልክቶ ነበር፤ እንዲሁም የዚህ ራእይ ትርጉም በፍጻሜው ዘመን ውስጥ ግልጽ እንደሚሆን ተነግሮት ነበር። (ዳንኤል 8:17, 19፤ 11:35, 40፤ 12:9) በተጨማሪም ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ስለ መምጣቱና ስለ ዓለም መጨረሻ ምልክት’ ተጠይቆ መልስ በሰጠበት ወቅት “መጨረሻው” የሚል ቃል ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 24:3-42) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዳንኤልም ሆነ ኢየሱስ፣ በአሁኑ ጊዜ በምድራችን ላይ ያሉትንና ከዚህ ቀደም የኖሩትን ሰዎች ሁሉ የሚነካ አንድ አስደናቂ ለውጥ ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚከሰት መናገራቸው ነበር። ዳንኤል የሁሉንም ምድራዊ መንግሥታት ፍጻሜ በሚመለከት ጽፏል። ኢየሱስ ደግሞ ስለ “ዓለም መጨረሻ” ተናግሯል።

ታዲያ ይህ ሁኔታ አንተን ሊያሳስብህ ይገባል? አዎን፣ ሊያሳስብህ ይገባል። ይህ ማንኛውንም ሰው የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ አንተን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሰው ዘር ሊያሳስበው ይገባል። ይሁንና ብዙ ሰዎች ይህን ጉዳይ አቅልለው ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል:- “በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ ‘“እመጣለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ታሪክ ራሱን እየደገመ እንደሆነና ሕይወት ወደፊትም ለዘላለም እንዲሁ እንደሚቀጥል ይሰማቸዋል።

በእርግጥ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ? እስቲ እንመልከት።