በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጨረሻው ቀን በኋላ ምን ይከተላል?

ከመጨረሻው ቀን በኋላ ምን ይከተላል?

ከመጨረሻው ቀን በኋላ ምን ይከተላል?

ንዳንድ ሰዎች ‘የመጨረሻው ቀን’ አስቸጋሪ እንደሚሆን ስለሚሰማቸው ስለዚያ ዘመን ማሰቡ ብቻ እንኳ ያስፈራቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 የ1954 ትርጉም) ታዲያ በየዘመናቱ የኖሩ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የመጨረሻውን ቀን በተስፋ የተጠባበቁት ለምንድን ነው? ምክንያቱም የመጨረሻው ቀን ከዚያ በኋላ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ስለሚያበስር ነው።

ለአብነት ያህል፣ ሰር አይዛክ ኒውተን የመጨረሻውን ቀን ተከትሎ በሚመጣው በአምላክ መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ዓለም አቀፍ ሰላምና ብልጽግና የሚሰፍንበት አዲስ ዘመን እንደሚመጣ በጥብቅ ያምን ነበር። ኒውተን፣ በሚክያስ 4:3 እና በኢሳይያስ 2:4 ላይ የተነገረው “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነትን ትምህርት አይማሩም” የሚለው ትንቢት የሚፈጸመው በዚያ ጊዜ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።

ኢየሱስም ስለ ፍጻሜው ዘመን በተናገረ ጊዜ ተከታዮቹ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው አሳስቧቸዋል። በታላቁ መከራ ወቅት ስለሚኖረው ችግር፣ ጭንቀትና ፍርሃት ከተናገረ በኋላ “እናንተም እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለ ተቃረበ፣ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ወደ ላይ ቀና አድርጉ” ብሏል። (ሉቃስ 21:28) የሚድኑት ከምንድን ነው?

አምላክ የሰጠው ተስፋ

ዛሬ የሰውን ዘር ቀስፈው ከያዙትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በፍርሃትና በሥጋት እንዲኖሩ ካደረጓቸው ችግሮች መካከል ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ወንጀል፣ ዓመጽና ረሃብ ጥቂቶቹ ናቸው። አንተም እንዲህ ባሉት ችግሮች ውስጥ አልፈህ ሊሆን ይችላል። እንግዲያስ አምላክ የሰጠውን ተስፋ ልብ በል:-

“ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11

“ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 32:18

“[ይሖዋ] ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:9

“እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4

“በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ። ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ።”—መዝሙር 72:16

“የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”—ምሳሌ 1:33

በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አስደሳች ሁኔታዎች ባሉበት አካባቢ የምንኖር ቢሆንም እንኳ ሁላችንም ከሕመምና ከሞት ማምለጥ አንችልም። እነዚህም ነገሮች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አይኖሩም። በመሆኑም በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ተነስተው ለማየት በጉጉት መጠበቅ እንችላለን። የሚከተለውን ተመልከት:-

“በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24 የ1954 ትርጉም

“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:4

“የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:26

“በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል።”—ዮሐንስ 5:28, 29

ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ሁሉ እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል:- “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) በመላዋ ምድር ላይ ጽድቅ እንዲሰፍን ከተፈለገ ይህን ሁኔታ የሚያውክ ማንኛውም ፍጡር መወገዱ ግድ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብሔራት ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው፤ እነዚህ ብሔራት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማሳደድ ከፍተኛ ግጭትና ደም መፋሰስ ስላስከተሉ ይወገዳሉ። ምድራዊ አገዛዞች በሙሉ ተወግደው በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት ይተካሉ። የአምላክን አገዛዝ በተመለከተ የሚከተለው ማረጋገጫ ተሰጥቶናል:- “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ . . . የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።”—ኢሳይያስ 9:7

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል” በማለት ማረጋገጫ ስለሚሰጠን ወደፊት እነዚህን ነገሮች እንደምታገኝ መተማመን ትችላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) እንግዲያው ዛሬ ነገ ሳትል የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝልህን እውቀት ለመቅሰም ጥረት አድርግ። (ዮሐንስ 17:3) ይህን መጽሔት ከሚያዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተህ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስጠኑህ በመጠየቅ ይህን እውቀት መቅሰም ትችላለህ።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እዚችው ምድር ላይ በምትቋቋመው ገነት ውስጥ ሰላምና ፍጹም ጤንነት አግኝተህ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ማድረግ ትችላለህ