በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጨረሻው ቀን የሚባለው የትኛው ዘመን ነው?

የመጨረሻው ቀን የሚባለው የትኛው ዘመን ነው?

የመጨረሻው ቀን የሚባለው የትኛው ዘመን ነው?

“ከአንድ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ምድር የተቃጠለች፣ ባዶና ጠፍ፣ እልም ያለች በረሃ እንደምትሆን እንጠብቃለን። ከዚያ በኋላ ምድር ብዙ ሴል ያላቸው ሕያዋን ነገሮች ይኖሩባታል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው” በማለት በቅርቡ የወጣ ስካይ ኤንድ ቴሌስኮፕ የተሰኘ መጽሔት ዘግቧል። ምክንያቱ ምን ይሆን? አስትሮኖሚ የተባለው መጽሔት “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚመጣው የፀሐይ ብርሃን ባሕሩን ያፈላውና የምድር ሙቀት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል” በማለት ይናገራል። አክሎም “ይህ አስፈሪ ትንበያ ለጆሮ የማይጥም ሐቅ ብቻ ሳይሆን የማይቀር ዕጣ ፈንታችን ነው” ይላል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 104:5) ምድርን የፈጠረ አምላክ ሕልውናዋ እንዲቀጥልም ማድረግ ይችላል። እንዲያውም እሱ “ምድርን ያበጃት . . . የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን” አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) ይሁን እንጂ እሱ የሚፈልገው ክፉና ሟች የሆኑ የሰው ልጆች እንዲኖሩባት አይደለም። አምላክ በዳንኤል 2:44 ላይ በተነገረለት መንግሥት አማካኝነት የራሱን አገዛዝ መልሶ የሚያቋቁምበትን ጊዜ ወስኗል።

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ሰብኳል። እንዲሁም ብሔራትና ሕዝቦች ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከደረሱት መከራዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ መከራ እንደሚከሰት አስጠንቅቋል። ከዚህም በላይ ይህ የምንኖርበት ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ መቅረቡን እንድናውቅ ለመርዳት ብዙ ገጽታዎች ያሉት ምልክት ሰጥቷል።—ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 13:19፤ ሉቃስ 21:7-11፤ ዮሐንስ 12:31

ኢየሱስን የመሰለ ታላቅ ሰው እንዲህ ያሉ ነገሮችን መናገሩ ብዙ ሰዎች ስለ ጉዳዩ ቆም ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች የሚከሰቱት መቼ ይሆን? አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በመመርመርና ዘመናትን በማስላት የዓለም መጨረሻ የሚመጣበትን ጊዜ በትክክል ለማወቅ ጥረት አድርገዋል። ስለዚህ ጉዳይ ምርምር ካደረጉት ሰዎች መካከል የስበትን ሕግ ያገኘውና ካልኩለስን የፈለሰፈው የ17ኛው መቶ ዘመን የሒሳብ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተን ይገኝበታል።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቁ ለእናንተ አልተሰጣችሁም” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:7) እንዲሁም ‘የመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ’ ምን እንደሆነ በተናገረበት ወቅት “ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም” በማለት ገልጿል። (ማቴዎስ 24:3, 36) ከዚያም በኖኅ ዘመን በነበረው ክፉ ዓለም ላይ የደረሰውን ጥፋት “የሰው ልጅ ሲመጣ” ከሚከሰተው ጥፋት ጋር ካነጻጸረ በኋላ “እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:39, 42

“የዓለም መጨረሻ” የሚሆንበት ጊዜ በትክክል ባይገለጽልንም እንኳ ኢየሱስ የሰጠው “ምልክት” ‘የመጨረሻው ቀን’ ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ የምንገኝ መሆናችንን እንድናውቅ ይረዳናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ መፈጸሙ ከማይቀረው ‘ከዚህ ሁሉ ነገር ማምለጥ’ እንድንችል ‘ሁልጊዜ መትጋት’ ይኖርብናል።—ሉቃስ 21:36

ኢየሱስ ምልክቱን ከመናገሩ በፊት እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ ነበር:- “እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ በማለት፣ ደግሞም፣ ‘ጊዜው ቀርቦአል’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እናንተ ግን እነርሱን አትከተሏቸው። ስለ ጦርነትና ስለ ሕዝብ ዐመፅ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ መሆን የሚገባው ነውና፤ መጨረሻው ግን ወዲያውኑ አይሆንም።”—ሉቃስ 21:8, 9

ምልክቱ ምንድን ነው?

ኢየሱስ በመቀጠል በመጨረሻው ቀን ውስጥ እንደምንኖር ለይተው የሚያሳውቁት ነገሮች ምን እንደሆኑ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ አስፈሪ ነገር እንዲሁም ከሰማይ ታላቅ ምልክት ይሆናል።” (ሉቃስ 21:10, 11) በተጨማሪም “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ የዓለም መጨረሻ ምልክት አድርጎ የጠቀሳቸው እንደ ጦርነት፣ የምድር መናወጥ፣ ቸነፈርና ረሃብ ያሉት ነገሮች በራሳቸው አዲስ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ሲፈጸሙ የነበሩ ነገሮች ናቸው። ልዩ የሚያደርጋቸው ሁሉም በአንድ ወቅት የሚፈጸሙ መሆናቸው ነው።

ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ:- ‘የወንጌል መጻሕፍት የጠቀሷቸው እነዚህ የምልክቱ ገጽታዎች በሙሉ የተፈጸሙበት ዘመን መቼ ነው?’ ሰዎች ከ1914 ጀምሮ ከተመለከቷቸው ነገሮች መካከል አውዳሚ የዓለም ጦርነቶች፣ እንደ ሱናሚ ያሉ አሳዛኝ ውጤት ያስከተሉ ታላላቅ የምድር መናወጦች፣ እንደ ወባ፣ ኢንፍሉዌንዛና ኤድስ ያሉ ሰፊ ስርጭት ያላቸው ገዳይ በሽታዎች፣ በምግብ እጦት ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ቅጠል መርገፋቸው፣ በሽብርተኝነትና አውዳሚ በሆኑ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች የተነሳ በመላው ዓለም ፍርሃት መንገሡ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች በሰማይ የተቋቋመውን የአምላክ መንግሥት በሚመለከት በመላው ዓለም የሚያካሂዱት የስብከት ሥራ ይገኙበታል። እነዚህ ክስተቶች ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው ተፈጽመዋል።

ከዚህም ሌላ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን ሐሳብ ልብ በል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አዎን፣ በሕገ ወጥነቱ፣ በአምላክ የለሽነቱና በጨካኝነቱ ተለይቶ የሚታወቀው ‘አስጨናቂ ጊዜ’ በመላው ምድር እየታየ መሆኑ ግልጽ ነው። *

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ቀን’ በማለት የሚጠራው ጊዜ የሚጀምረው ገና ወደፊት ነው? የሚጀምረው መቼ እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ሌላ ማስረጃ አለ?

‘የመጨረሻው ዘመን’ የሚጀምረው መቼ ነው?

ነቢዩ ዳንኤል ከብዙ ዓመታት በኋላ ስለሚፈጸሙ ክስተቶች የሚገልጽ ራእይ ከተቀበለ በኋላ “በዚያን ዘመን [ማለትም በዳንኤል 11:40 ላይ በተጠቀሰው “በመጨረሻው ዘመን”] ስለ ሕዝብህ የሚቈመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” የሚል መልእክት ተነግሮታል። (ዳንኤል 12:1) ሚካኤል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያደርግ ይሆን?

የራእይ መጽሐፍ፣ ሚካኤል ንጉሥ ሆኖ ስለሚገዛበት ዘመን እንዲህ በማለት ይናገራል:- “በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣ በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።”—ራእይ 12:7-9, 12

ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መረዳት እንደሚቻለው፣ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ለማስወገድ የሚካሄደው ይህ ጦርነት በምድር ላይ ታላቅ ወዮታ ያስከትላል፤ ለዚህ ምክንያቱ ሰይጣን ምድርን ለመግዛት የቀረው ጊዜ በጣም አጭር መሆኑን አውቆ በታላቅ ቁጣ መውረዱ ነው። የሰይጣን ቁጣ በአርማጌዶን ጦርነት ሙሉ በሙሉ ድል እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ባሉት የመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እየጨመረ ይሄዳል።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:11, 15፤ 20:1-3

ሐዋርያው ዮሐንስ፣ በሰማይ የተደረገው ይህ ጦርነት ያስከተለውን ውጤት ከጠቀሰ በኋላ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ ‘አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና መንግሥት፣ የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቶአል። ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።’” (ራእይ 12:10) ይህ ጥቅስ በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት መቋቋሙን እንደሚያስታውቅ ልብ ብለሃል? ይህ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመው በ1914 ነበር። * ይሁን እንጂ መዝሙር 110:2 እንደሚያመለክተው የአምላክ መንግሥት ምድርን መግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ ኢየሱስ የሚገዛው ‘በጠላቶቹ መካከል’ ይሆናል።—ማቴዎስ 6:10

ደስ የሚለው ነገር ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን በሚመለከት ለነቢዩ ዳንኤል ያሳወቀው መልአክ “ዳንኤል ሆይ፤ አንተ ግን፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የመጽሐፉን ቃል ዝጋ፤ አትመውም። ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል” በማለት አክሎ ነግሮታል። (ዳንኤል 12:4) ይህ ሐሳብ ዛሬ የምንገኘው “በፍጻሜው ዘመን” ውስጥ ለመሆኑ ያለንን ማስረጃ ያጠናክርልናል። ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ እነዚህ ትንቢቶች ምን ትርጉም እንዳላቸው በግልጽ የታወቀ ከመሆኑም በላይ ይህ እውቀት በመላው ዓለም በመታወጅ ላይ ነው። *

‘የመጨረሻው ቀን’ የሚያበቃው መቼ ነው?

የመጨረሻው ቀን፣ ምን ያህል ርዝማኔ እንደሚኖረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ በመጨረሻው ቀን ውስጥ ሰይጣን ሊጠፋ የቀረው ጊዜ እያጠረ በመጣ መጠን በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎችም እየተባባሱ እንደሚሄዱ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” በማለት አስቀድሞ አስጠንቅቋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13) ኢየሱስ ደግሞ ገና ወደፊት ስለሚመጡት ነገሮች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፣ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና። ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሮአል።”—ማርቆስ 13:19, 20

ወደፊት ይከሰታሉ ተብለው ከሚጠበቁት ነገሮች መካከል የአርማጌዶንን ጦርነት የሚያካትተው “ታላቅ መከራ” እና በምድር ላይ ምንም ዓይነት መጥፎ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ሲባል ሰይጣንና አጋንንቱ መታገዳቸው ይገኙበታል። (ማቴዎስ 24:21) “የማይዋሸው አምላክ” እነዚህ ነገሮች እንደሚፈጸሙ አረጋግጦልናል። (ቲቶ 1:2) የአርማጌዶን ጦርነት መምጣትና የሰይጣን ወደ ጥልቁ መጣል አምላክ እጁን ጣልቃ እንዳስገባ የሚያሳዩ ውጤቶች ይሆናሉ።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክ ከሚወስደው የጥፋት እርምጃ በፊት ምን ነገር እንደሚፈጸም በመንፈስ አነሳሽነት ተናግሮ ነበር። ‘ዘመናትንና ወራትን’ በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ የጌታም ቀን እንዲሁ እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ። ሰዎች፣ ‘ሰላምና ደኅንነት ነው’ ሲሉ፣ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት እንዲሁ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም።” (1 ተሰሎንቄ 5:1-3) ሰዎች “ሰላምና ደኅንነት ነው” በማለት በሐሰት እንዲለፍፉ የሚገፋፋቸው ምን እንደሆነ የሚነግረን ጊዜ ብቻ ይሆናል፤ ነገር ግን እንዲህ ያለው ልፈፋ የይሖዋ የፍርድ ቀን እንዳይመጣ ሊያግድ አይችልም። *

እነዚህ ትንቢቶች እውን መሆናቸው እንደማይቀር በጥብቅ የምናምን ከሆነ ይህን ሐቅ በሚመለከት ያገኘነው እውቀት እርምጃ እንድንወስድ ሊገፋፋን ይገባል። በምን መንገድ? ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል!” (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) ሆኖም ‘ይህ ሁሉ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 ስለ “መጨረሻው ዘመን” ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን ሚያዝያ 2007 ንቁ! ገጽ 8-10⁠ን እና መስከረም 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4-7⁠ን እንዲሁም ጥቅምት 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4-7⁠ን ተመልከት።

^ አን.18 የመጽሐፍ ቅዱስን የዘመን ስሌት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ገጽ 215-218 ተመልከት።

^ አን.19 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተሰኘውን መጽሐፍና የ2008 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 31-39 ተመልከት።

^ አን.23 ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተሰኘውን መጽሐፍ (የ2006 እትም) ገጽ 250-251 አንቀጽ 13⁠ና 14ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ “ያን ቀንና ሰዓት” የሚያውቀው አምላክ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል ]

ሰር አይዛክ ኒውተን

[ምንጭ]

© A. H. C./age fotostock

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ከ1914 ጀምሮ ሲፈጸም ቆይቷል

[ምንጮች]

© Heidi Bradner/Panos Pictures

© Paul Smith/Panos Pictures