በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሜድትራንያን ወርቃማ ፈሳሽ

የሜድትራንያን ወርቃማ ፈሳሽ

የሜድትራንያን ወርቃማ ፈሳሽ

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“ከአረንጓዴነት ወደ ጥቁርነት ተለወጥኩ፤ ከዚያም በጥንቃቄ ፈጭተው ጥሩ ወደሆነ ወርቅ ቀየሩኝ።” —የስፔናውያን ጥንታዊ እንቆቅልሽ

የወይራ ፍሬ ሲበስል መልኩ ከአረንጓዴነት ወደ ጥቁርነት ይለወጣል። ፍሬው ከውጭ ሲታይ ጥቁር ቢሆንም በውስጡ ግን ልዩ የሆነ ወርቃማ ፈሳሽ ይገኛል። በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከበሰሉ የወይራ ፍሬዎች የሚገኘውን ወርቃማ ፈሳሽ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ምግባቸውን ለማጣፈጥ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ይህ ወርቃማ ፈሳሽ ማለትም የወይራ ዘይት፣ ከፖርቹጋል እስከ ሶርያ ያሉትን ተራሮች አልብሰው ከሚገኙት የወይራ ዛፎች የሚገኝ ተወዳጅ ምርት ነው።

ችግር ከማይበግራቸው ከእነዚህ ዛፎች የሚገኘው ዘይት ልዩ የሆነ ጣዕም ያለው ሲሆን ለጤንነትም ጠቃሚ ነው። በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች “ዘይት” ሲባል ምንጊዜም ወደ አእምሯቸው የሚመጣው “የወይራ ዘይት” ነው። እንዲያውም በስፔን ቋንቋ “ዘይትን” ለማመልከት የሚሠራበት አሴቴ የሚለው ቃል የመጣው፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “የወይራ ጭማቂ” የሚል ፍቺ ካለው አዜት ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው። በእርግጥም የወይራ ዘይት ከተፈጩ የወይራ ፍሬዎች የሚገኝ ምንም ነገር ያልተጨመረበት ንጹሕ የፍራፍሬ ጭማቂ ነው። የወይራ ዘይት ምንም ዓይነት ማጣፈጫ ወይም ኬሚካል ካልተጨመረበት ተፈጥሯዊ ይዘቱን፣ ጣዕሙንና መዓዛውን አያጣም።

ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ወርቃማ ፈሳሽ

ኧርላ ዝዊንግል የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ የወይራ ዘይት “ለብዙ ዘመናት ለምግብነት፣ ለነዳጅነት ለቅባትነትና ለአምልኮ ሲያገለግል” መቆየቱን ገልጸዋል። አክለውም፣ “[በዛሬው ጊዜም] ከወይራ ዛፍ የሚገኘው ይህ ወርቃማ ፈሳሽ ከዘይቶች ሁሉ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነው” ብለዋል። ሰዎች የወይራ ዘይትን ለመጭመቅ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረው ቀላል ዘዴ አሁንም ድረስ አልተለወጠም። በመጀመሪያ፣ አምራቾቹ የዛፎቹን ቅርንጫፎች በበትር እየመቱ ፍሬዎቹን መሬት ላይ ያራግፋሉ። ከዚያም ፍሬዎቹን ይሰበስቧቸውና በወፍጮ ይፈጯቸዋል። ቀጥሎም ፈሳሹ ከተጨመቀው ፍሬ ይለያል። በመጨረሻም፣ ዘይቱ ከውኃው ይለይና ጥቅም ላይ ይውላል። *

የወይራ ዘይት ልክ እንደ ወይን ጠጅ በተለያየ መልክ ይዘጋጃል። በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን የሚያህሉ የወይራ ዛፎች በመልማት ላይ ይገኛሉ። * የአትክልት ጥናት ባለሙያዎች ከ680 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የወይራ ዛፍ ዓይነቶች እንዳሉ ማወቅ ችለዋል። የተለያዩ ዓይነት የወይራ ዛፍ ዝርያዎች ከመኖራቸውም ሌላ የአፈሩ ዓይነት፣ የአየሩ ጠባይ፣ የወይራ ፍሬው የሚመረትበት ወቅት (ከኅዳር ጀምሮ እስከ የካቲት) እንዲሁም የሚጨመቅበት መንገድ በዘይቱ ጣዕም፣ ቀለምና መዓዛ ላይ ልዩነት ያመጣሉ። ዘይት በመቅመስ ሙያ ላይ የተሠማሩ የተለያዩ ቡድኖች የወይራ ዘይቶችን ጣዕም ጣፋጭ፣ የሚሰነፍጥ፣ የፍራፍሬ ለዛ ያለው ወይም ደስ የሚል በማለት ይመድቡታል። ቀማሾቹ ምርቱ ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

የሜድትራንያን የአየር ጠባይ ለወይራ ዛፎች ተስማሚ ነው። ከዚህም የተነሳ ከጠቅላላው የወይራ ዘይት ምርት ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው በሜድትራንያን ባሕር አቅራቢያ ባሉ አገሮች ነው። ግሪክን፣ ጣሊያንን፣ ሞሮኮን፣ ፖርቹጋልን፣ ስፔንን፣ ሶርያን፣ ቱኒዝያንና ቱርክን የሚጎበኙ ሰዎች ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እጅብ ብለው የበቀሉ የወይራ ዛፎችን ማየት ይችላሉ። በእርግጥም በእነዚህ አካባቢዎች የሚመረተው የተትረፈረፈ የወይራ ዘይት “የሜድትራንያን ወርቃማ ፈሳሽ” ነው ሊባል ይችላል።

ለጤና ተስማሚ የሆነው የሜድትራንያን ምግቦች ማጣፈጫ

ለብዙ መቶ ዘመናት፣ በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምግቦቻቸውን ለማጣፈጥ የወይራ ዘይት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። የወይራ ዘይት ምግብን ለመጥበስና ለማጣፈጥ እንዲሁም ሥጋን ዘፍዝፎ ለማቆየት ሊያገለግል ይችላል። ዋና የወጥ ቤት ሠራተኛ የሆኑት ሆሴ ጋርቲያ ማሪን፣ የወይራ ዘይት በስፔን የምግብ አዘገጃጀት ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ “ለ4,000 ዓመታት ያህል ለምግብነት ሲያገለግል የኖረ ምርት በጣም ጥሩ መሆን አለበት” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥንቃቄ የተሞላባቸው የማምረቻ ዘዴዎች ሥራ ላይ በመዋላቸው የዚህ ‘የአበባ ማር’ ጥራት ይበልጥ ተሻሽሏል” ብለዋል።

ተመራማሪዎች፣ ባሕላዊውን የሜድትራንያን የአመጋገብ ልማድ የሚከተሉ ሰዎች ከጤንነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ ከተገነዘቡ ቆይተዋል። * በቅርቡ፣ የምግብ ጥናት ባለሙያዎች ቨርጅን የወይራ ዘይት ለጤንነት በሚሰጠው ጥቅም ላይ ለመወያየት ዓለም አቀፍ ስብሰባ አድርገው ነበር። በስብሰባው ላይም ቨርጅን የወይራ ዘይትን ጨምሮ በሜድትራንያን አካባቢ የሚዘወተሩ ምግቦች ለጤንነት ተስማሚና ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በቨርጅን የወይራ ዘይት የተሠራ ምግብ ለልብ ሕመምና ለካንሰር የመጋለጥን አጋጣሚ ለመቀነስ ሊረዳ ይችላል። በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች እንደሚከተለው ብለዋል:- “ቨርጅን የወይራ ዘይት በብዛት የሚገኝባቸውን የሜድትራንያን አካባቢ ምግቦችን የሚመገቡ ሕዝቦች . . . በካንሰር የመያዝ አጋጣሚያቸው በሰሜን አውሮፓ አገሮች ከሚኖሩ ሰዎች ዝቅተኛ ነው።”

ምግቦቹ ለጤንነት ጠቃሚ የሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህም መካከል አንዱ በወይራ ዘይት ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ኦሊይክ አሲድ (እስከ 80 በመቶ ይደርሳል) በደም ዝውውር ሥርዓት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የወይራ ዘይት በሚዘጋጅበት ወቅት ኬሚካልም ሆነ ረጅም ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ ሲባል ቅመማ ቅመሞች ስለማይጨመሩበት በበሰለው የወይራ ፍሬ ውስጥ ይገኙ የነበሩት ቫይታሚኖች፣ ሞኖሳቹሬትድ ፋትስ ተብለው የሚጠሩት የቅባት ዓይነቶችና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ይዘታቸው አይለወጥም።

የወይራ ዘይት፣ እንደ ቫይታሚን ኢ እና ፖሊፊኖል (መዓዛ ያላቸው ነገሮች) ያሉትን ንጥረ ነገሮች በውስጡ ይዟል፤ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ኦክስጅንን የማትነን ኃይል ስላላቸው የወይራ ዘይት ቆዳ እንዳይጎዳ ይከላከላል። በመሆኑም የተለያዩ መዋቢያዎችን፣ የቆዳ ቅባቶችን እንዲሁም የፀጉር ሻምፑዎችንም ሆነ ሌሎች ሳሙናዎችን ለማዘጋጀት ያገለግላል። የጥንቶቹ ግሪካውያንና ሮማውያን ቆዳቸውን ለማለስለስና ለማጽዳት ከሌሎች ቅጠላ ቅጠሎች ጋር ተቀላቅሎ የተዘጋጀን የወይራ ዘይት ይቀቡ ነበር። ቆየት ብሎም በስድስተኛው መቶ ዘመን የፈረንሳይ የእጅ ባለሙያዎች የወይራ ዘይትን ከባሕር ውስጥ ተክሎች ከሚገኝ አመድ ጋር በማቀላቀል ሳሙና መሥራት ጀመሩ።

የወይራ ዘይት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የወይራ ዘይት ለምግብነት፣ ለመዋቢያነት፣ ለነዳጅነት፣ ለመድኃኒትነትና ለሌሎችም ዓላማዎች በስፋት ያገለግል ነበር። የወይራ ዘይት አንድም በዘይትነቱ አሊያም ጥሩ መዓዛ ባላቸው ዘይቶች ውስጥ ዋና ቅመም በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ250 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል።

ቅዱሳን መጻሕፍት የወይራ ዘይት በእስራኤላውያን የቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው በግልጽ ያሳያሉ። የወይራ ዘይት ዋነኛ ምግባቸው የነበረ ሲሆን በብዛት መኖሩ ደግሞ ብልጽግናን ያመለክት ነበር። (ኢዩኤል 2:24) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቆዳቸውን ለማለስለስ የወይራ ዘይት ይቀቡ ነበር። ሩት ወደ ቦዔዝ ከመሄዷ በፊት ‘ሽቶ [“ዘይት፣” NW] ተቀብታለች።’ (ሩት 3:3) ንጉሥ ዳዊት ሰባት ቀን ከጾመ በኋላ “ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና [“ዘይት ከተቀባና፣” NW] ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ሄዶ ሰገደ።”—2 ሳሙኤል 12:20

በጥንት ዘመን የነበሩ መብራቶችም ቢሆኑ ለነዳጅነት የሚጠቀሙት እንደ ልብ የሚገኘውን የወይራ ዘይት ነበር። (ማቴዎስ 25:1-12) በምድረ በዳ በነበረው የመገናኛ ድንኳን ውስጥ ለመብራትነት ይውል የነበረው “ጥሩ፣ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት” ነበር። (ዘሌዋውያን 24:2 የ1954 ትርጉም) በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን የወይራ ዘይት በዓለም አቀፉ ንግድ ተፈላጊ ሸቀጥ ነበር። (1 ነገሥት 5:10, 11) ነቢያት ነገሥታትን ሲሾሙ ዘይት ይቀቧቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 10:1) በተጨማሪም ደግ የሆኑ እንግዳ ተቀባዮች፣ የእንግዶቻቸውን ራስ ዘይት በመቀባት ጥሩ አቀባበል ያደርጉላቸው ነበር። (ሉቃስ 7:44-46) በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ደጉ ሳምራዊ በተደበደበው ሰው ቁስል ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አስሮለታል።—ሉቃስ 10:33, 34

በጥንት ዘመን የወይራ ዘይት ለመድኃኒትነት በሰፊው ያገለግል ስለነበር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚያስደስት ምክርና ማጽናኛ ጋር ተመሳስሏል። ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል።”—ያዕቆብ 5:14, 15

የወይራ ዛፍ፣ ምርት የሚሰጠው ለጥቂት ጊዜ አይደለም። አንድ የወይራ ዛፍ ለባለቤቶቹ፣ በየዓመቱ ከሦስት እስከ አራት ሊትር ዘይት እየሰጠ ለብዙ መቶ ዓመታት ሊኖር ይችላል! ይህ ወርቃማ ፈሳሽ ጤንነታችን እንዲሻሻል፣ ቆዳችን እንዲለሰልስና ምግባችን ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ፈሳሹ ክፍል ከፍሬው ከተለየ በኋላ በቀጥታ ለምግብነት የሚውሉት የወይራ ዘይት ዓይነቶች ኤክስትራ ቨርጅን ወይም ቨርጅን የሚባሉት ናቸው። ሪፋይንድ ወይም ኮመን እንዲሁም ኦሊቭ ፖመስ የተባሉት የወይራ ዘይት ዓይነቶች ግን የዘይቱን ኃይለኛ ጣዕም ለማስተካከል የሚረዳ ኬሚካል ይጨመርባቸዋል።

^ አን.8 እነዚህ ዛፎች በየዓመቱ 1.7 ቢሊዮን ሊትር የወይራ ዘይት ያስገኛሉ።

^ አን.12 በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምግብ አብዛኛውን ጊዜ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ያካትታል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የወይራ ዘይትን የተመለከቱ አንዳንድ እውነታዎች

▪ የወይራ ዘይት ሳይበላሽ ለአንድ ዓመት ተኩል መቆየት ይችላል

▪ ብርሃን ዘይቱን ስለሚያበላሸው መቀመጥ ያለበት በቀዝቃዛና ጨለም ባለ ቦታ ላይ ነው።

▪ የወይራ ዘይት ለመጥበሻነት ከአንድ ጊዜ በላይ ከዋለ ኦክስጅን የማትነን ኃይሉን ያጣል።

▪ የምግብ ጥናት ባለሙያዎች፣ ሰዎች የወይራ ዘይት በጤንነታቸው ላይ ከሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ማግኘት ከፈለጉ ዕድሜያቸውን በሙሉ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይናገራሉ።

▪ የወይራ ዘይት ዓሣ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬና ፍራፍሬ በብዛት በሚገኝበት በሜድትራንያን ምግብ ውስጥ ሲጨመር ለጤና ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ባሕላዊ የወይራ ዘይት አጨማመቅ ዘዴ

ሠራተኞች የወይራውን ቅርንጫፎች እየመቱ ፍሬውን ያራግፋሉ

የወይራ ፍሬው በድንጋይ ወፍጮ ይፈጫል

ይህ መሣሪያ ዘይቱን ከተጨመቀው ፍሬ ይለያል

የወይራ ዘይት ተጨምቆ ሲወጣ

[ምንጭ]

ወፍጮና ማሽን:- Museo del Olivar y el Aceite de Baena

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ:- በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖሩ ችምችም ብለው የበቀሉ የወይራ ዛፎች

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተ ቀኝ:- በወይራ ዘይት የሚሠራ ጥንታዊ መብራት

[ምንጭ]

መብራት:- Museo del Olivar y el Aceite de Baena

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተ ቀኝ ራቅ ብሎ የሚገኘው:- ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት አሥሩ ልጃገረዶች በዘይት የሚሠሩ መብራቶቻቸውን ይዘው