በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙዚቃ—ልብን ደስ የሚያሰኝ የአምላክ ስጦታ

ሙዚቃ—ልብን ደስ የሚያሰኝ የአምላክ ስጦታ

ሙዚቃ—ልብን ደስ የሚያሰኝ የአምላክ ስጦታ

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሙዚቃ ኃይል አለው። ሊያረጋጋን፣ ሊያነቃቃንና መንፈሳችንን ሊያድስ ይችላል። ደስታችንንም ሆነ ሐዘናችንን ለመግለጽ ያስችለናል። ጥንትም ሆነ ዛሬ በሁሉም ባሕሎች ውስጥ የሚገኘው ሙዚቃ በአእምሮም ሆነ በልብ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አዎን፣ በእርግጥም ሙዚቃ የአምላክ ስጦታ ነው።—ዘፍጥረት 4:21

ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ አንድ ዓይነት ሙዚቃ ሰምተን እንደሚሆን የታወቀ ነው። ምናልባትም እናታችን እንቅልፍ እንዲወስደን እሹሩሩ እያለች አዚማልን ይሆናል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለን ደግሞ ልባችንን ደስ የሚያሰኝ ሙዚቃ ለመስማት ከፍተኛ ፍላጎት አድሮብን ሊሆን ይችላል። ትልልቅ ሰዎች ሆነንም እንኳ አብዛኞቻችን በሥራ ተጠምደን ከዋልን በኋላ ቤታችን ስንመለስ ወይም መኪና ስንነዳ ዘና የሚያደርግ ሙዚቃ መስማት ያስደስተናል።

የዘፈን ግጥም የአንድን አገር ባሕል ወይም ታሪክ የያዘ ሊሆን ይችላል። የጥንቶቹ እስራኤላውያን ልዩ ክንውኖችን የሚያወሱ መዝሙሮች ነበሯቸው። (ዘፀአት 15:1-21፤ መሳፍንት 5:1-31) ነቢዩ ሙሴ፣ የእስራኤላውያንን ታሪክ ጨምሮ ለሕዝቡ ግሩም ምክር የያዘ መዝሙር አዘጋጅቶ ነበር። (ዘዳግም 32:1-43) እንዲህ ያሉ መዝሙሮች እስራኤላውያን ክንውኖቹን ለማስታወስ እንደረዷቸው አያጠራጥርም።

መዝፈን ትችላለህ!

‘እኔ መዝፈን አይሆንልኝም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እስቲ ለደቂቃ ያህል ስለ ድምፅህ አስብ። ማንኛውም ሰው የተለያየ ድምፅ ማውጣት ስለሚችል በሙዚቃ መሣሪያ ታግዞም ይሁን ያለ ሙዚቃ መሣሪያ በተወሰነ መጠን መዝፈን ይችላል። የሚያስፈልግህ ነገር ቢኖር ድምፅህን አውጥተህ መዝፈን ብቻ ነው። ይህን በምታደርግበት ጊዜ ሰዎች አድናቆት ያዥጎደጉዱልኛል ብለህ አትጠብቅ፤ ከዚህ ይልቅ ሳትጨነቅ ዝፈን። ከተለማመድክ ደግሞ ማሻሻል ትችላለህ።

ሳይኮሎጂስ የተባለ በስፓንኛ የተዘጋጀ መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ድምፃችን በውስጣችን ከሚሰማን ጥልቅ ስሜት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፤ እንዲሁም ስሜታችንን በመግለጽ ረገድ ከድምፅ የተሻለ መሣሪያ የለም።” አኢኖኣ አርቴታ የተባለች የኦፔራ አቀንቃኝ “[መዝፈን] በጣም ያስደስታል። . . . የውስጥ ስሜቱን በዘፈን መግለጽ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ያለአንዳች ማመንታት በነፃነት እንዲዘፍን እመክራለሁ” ብላለች።

ሙዚቃ በልብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር መራጮች መሆን አለብን። ለምሳሌ ማራኪ የሆኑ ዜማዎች፣ ሰዎች ጥላቻንና የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም ዓመጽን የሚያበረታቱ መጥፎ ግጥሞችን ችላ ብለው እንዲመለከቱ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው አሊያም አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እንዲህ ዓይነት ሙዚቃዎችን በመስማት አይዝናናም። (ኤፌሶን 4:17-19፤ 5:3, 4) የአምላክ ቃል “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” ይላል። (ምሳሌ 4:23) አዎን፣ የዘፈን ምርጫህን አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም። *

ጥሩ ሙዚቃ ፍቱን መድኃኒት ሊሆን ይችላል

ፕሪንሲፕልስ ኤንድ ፕራክቲስ ኦቭ ስትሬስ ማኔጅመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ሙዚቃ በሁሉም ባሕል ውስጥ እንዲኖር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ በሰዎች ጤንነትና ደህንነት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ነው።” አንድ ሌላ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ደግሞ በምንዘፍንበት ጊዜ መላው ሰውነታችን ድምፃችንን ከማስተጋባቱም ሌላ እንደሚነዝር ተናግሯል። እንዲህ ያለው መጠነኛ ንዝረት ሕብረ ሕዋሳት ዘና እንዲሉና እንዲፍታቱ ስለሚያደርግ ሕመም ለማስታገስ ሊረዳ ይችላል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሐኪሞች፣ በጭንቀት የሚሠቃዩ ሕመምተኞች ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎች እንዲሰሙ ያበረታታሉ፤ እነዚህ ሙዚቃዎች ደግሞ አንድ ሰው ጥሩ ስሜት እንዲኖረው ሊረዱት ይችላሉ። አንዳንድ ሆስፒታሎች ልዩ የሕክምና ክትትል በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ሳይቀር ሙዚቃ እንዲከፈት ያደርጋሉ። ማራኪ ዜማዎች ጊዜያቸው ሳይደርስ በተወለዱ ሕፃናትና ቀዶ ጥገና ባደረጉ ሕመምተኞች ላይ ብዙውን ጊዜ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ፕሪንሲፕልስ ኤንድ ፕራክቲስ ኦቭ ስትሬስ ማኔጅመንት እንዳለው ከሆነ፣ ለስለስ ያለ ሙዚቃ መስማት “በቀዶ ጥገና ወቅት ውጥረት እንዲፈጠር የሚያደርገውን የሆርሞን መጠን ለመቀነስ እንደሚረዳ” ጥናቶች ያሳያሉ።

ከዚህም በላይ ሙዚቃ ሰውነትን ዘና ስለሚያደርግ በምጥና በወሊድ ጊዜ የሚፈጠረውን ውጥረት ለመቀነስ ሊረዳ ይችላል። የጥርስ ሐኪሞችም በጭንቀት የተዋጡ ሕመምተኞቻቸውን ዘና ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ይከፍታሉ። ይሁን እንጂ ሙዚቃና መዝሙር ከዚህ የበለጠ ጥቅም አላቸው። ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ይረዱናል።

‘አምላክን በዝማሬ አመሰግነዋለሁ’

አንድ አሥረኛ የሚያህለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈው በመዝሙር መልክ መሆኑን ታውቅ ነበር? ከእነዚህ መካከል የመዝሙር፣ የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን እና የሰቆቃወ ኤርምያስ መጻሕፍት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መዝሙር ከሚናገሩት ሦስት መቶ ከሚያህሉ ሐሳቦች መካከል አብዛኞቹ ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ናቸው። የተዋጣለት ሙዚቀኛና የሙዚቃ አቀናባሪ የነበረው የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት ‘አምላክ ብርታቴ ነው፤ በዝማሬም አመሰግነዋለሁ’ በማለት ጽፏል።—መዝሙር 28:7

እንዲያውም ዳዊት፣ ከሌዊ ነገድ የሆኑ 4,000 ወንዶች ሙዚቀኞችና መዘምራን ሆነው በኢየሩሳሌም እንዲያገለግሉ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ከእነዚህ መካከል 288 የሚያህሉት “ወደ እግዚአብሔር በሚቀርበው ዜማ የሠለጠኑና የተካኑ ነበሩ።” (1 ዜና መዋዕል 23:4, 5፤ 25:7) እነዚህ መዘምራን በትጋት ይለማመዱ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም ሙዚቃ በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ነበረው፤ በመሆኑም መዘምራኑ በሥራቸው ላይ ማተኮር እንዲችሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከሚከናወኑ ሌሎች አገልግሎቶች ሁሉ ነፃ ይሆኑ ነበር።—1 ዜና መዋዕል 9:33

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር አቅርቧል፤ ምናልባትም ይህ፣ ከመዝሙር 113 እስከ 118 የሚገኙትን መዝሙራት የሚያካትት ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ መዝሙራት “የሃሌል መዝሙራት” ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በፋሲካ በዓል ሰሞን ይዘመሩ ነበር። (ማቴዎስ 26:26-30) “የሃሌል መዝሙራት” የሚለው ስያሜ የተሰጣቸው “ሃሌ ሉያ!” ማለትም “ያህን አመስግኑ” የሚለው ሐረግ በመዝሙራቱ ውስጥ በብዛት ስለሚገኝ ነው። “ያህ” የሚለው ቃል ይሖዋ የሚለው ስም ምኅጻረ ቃል ሲሆን ይህ ስም ደግሞ ከሁሉም በላይ ልዑል የሆነው አምላክ መጠሪያ ነው።—መዝሙር 83:18 NW

ክርስቲያኖችም መዝሙርን የአምልኳቸው ክፍል አድርገው ተቀበሉት። ዘ ሂስትሪ ኦቭ ሚውዚክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በኅብረትም ሆነ በተናጠል በሚያካሂዱት የአምልኮ ሥርዓት ላይ የመዘመር ልማድ ነበራቸው። ወደ ክርስትና የተለወጡት አይሁዶች ቀደም ሲልም በየምኩራቦቻቸው [የመዘመር] ልማድ ነበራቸው፤ . . . በአዲሱ እምነት ውስጥ ከዕብራይስጥ መዝሙራት በተጨማሪ አዳዲስ መዝሙራት ይዘጋጁ ነበር።” በዛሬው ጊዜም ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች በግላቸውም ሆነ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ ይሖዋን በመዝሙር ያወድሳሉ።

ሙዚቃ ስሜታችንን አውጥተን ለመግለጽ ስለሚያስችለንና በልብ፣ በአእምሮና በሰውነት ላይ ኃይለኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር “ከሰማይ” ላገኘነው ለዚህ “ፍጹም በረከት” ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:17) አዎን፣ ይህን ስጦታ አዘውትረን ብሎም በጥበብ እንጠቀምበት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 አምላክንና ሰዎችን የሚወዱ ግለሰቦች ጥላቻን፣ የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም ዓመጽን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን ብቻ ሳይሆን የጣዖት አምልኮን፣ ብሔርተኝነትን አሊያም ሃይማኖታዊ የሐሰት ትምህርቶችን የሚያወድሱ ሙዚቃዎችንም ከመስማት ይቆጠባሉ።—ኢሳይያስ 2:4፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-18፤ 1 ዮሐንስ 5:21