በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ደስታ የሰፈነበት ሕይወት ማምጣት ይችላሉ?

ሰዎች ደስታ የሰፈነበት ሕይወት ማምጣት ይችላሉ?

ሰዎች ደስታ የሰፈነበት ሕይወት ማምጣት ይችላሉ?

ቤት ቀይረህ አስተማማኝ በሚመስልና ከጡብ በተሠራ በጣም የሚያምር አዲስ ቤት ውስጥ መኖር ጀምረሃል እንበል። ከድሮ ጀምሮ እንዲህ ባለ ቤት ውስጥ ለመኖር ትመኝ ነበር። ስለ መጪው ጊዜ ስታስብ ግሩም ሆኖ ታየህ! ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤቱ ከባድ የአሠራር ጉድለት እንዳለበት ስለታወቀ እንዲፈርስ ተወሰነ። በዚህ ጊዜ በጣም አዘንክ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። በአካባቢህ ያሉ ሌሎች ቤቶችም ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው። ችግሩ ሲጠና መንስኤው የመሐንዲስ ችሎታ ማነስ እንዲሁም ሠራተኞቹ ጉድለት ያለባቸው ወይም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ጡቦች መጠቀማቸው እንደሆነ ተደረሰበት።

እንደዚያ ቤት ሁሉ ይህ ዓለምም ከባድ ችግሮች አሉበት። በማኅበራዊውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ መሻሻል ለማምጣት ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሙከራዎች ቢደረጉም እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ መስክ ከተአምር የማይተናነሱ እድገቶች ቢመዘገቡም የኅብረተሰቡ መዋቅር በመፈራረስ ላይ ያለ ይመስላል። በበርካታ አገሮች ውስጥ ሕገ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት በጣም የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ መድረሳቸው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ብሎም ጥሩ አስተዳደር እንዲመሠርቱ ያስገድዳቸው ይሆን? አንዳንድ ባለ ሥልጣናት የሰው ልጅ ያስመዘገበውን ታሪክ አስመልክተው የተናገሩትን ተመልከት።

“ያልሞከርነው ነገር የለም”

ዓለምን የተሻለች መኖሪያ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከግሪካዊው ፈላስፋ ከፕላቶ አንስቶ የፖለቲካ ፈላስፋና የሶሻሊስት አራማጅ እስከሆነው እስከ ጀርመናዊው ካርል ማርክስ ድረስ በርካታ ምሑራን የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶች እንዲሞከሩ ሐሳብ አቅርበው ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኒው ስቴትስማን በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር:- “ድህነትን ማጥፋትም ሆነ ሰላምን ማምጣት አልቻልንም። እንዲያውም ፍጹም ተቃራኒ ውጤት ያገኘን ይመስላል። ይህ የሆነው ጥረት ሳናደርግ ቀርተን አይደለም። ከኮሚኒዝም እስከ ነፃ ገበያ፣ ጦርነትን ለማስቀረት ደግሞ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን ከማቋቋም አንስቶ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን እስከ ማከማቸት ድረስ ያልሞከርነው ነገር የለም። ‘ጦርነትን እንዴት ማስቆም እንደምንችል እናውቃለን’ በሚል ስሜት ስንትና ስንት ጦርነቶች ውስጥ ገብተናል፤ በዚህም ምክንያት ከተሞቻችን የጦርነት ቀጠና መስለዋል።” ጽሑፉ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “የሳይንስ ሊቃውንት ይታደጉናል የሚል እምነት ስለነበረን [20ኛውን] መቶ ዘመን የጀመርነው በከፍተኛ ጉጉት ነበር፤ በመደምደሚያው ላይ ግን እነሱ በሚናገሩት በአንዱም ቃል ላይ እምነት መጣል አልቻልንም።”

በለንደን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ታሪክ ፕሮፌሰር የነበሩት ኤሪክ ሆብስባም፣ መንግሥታት “ሰዎች የሚያደርጓቸው ነገሮች በተፈጥሮም ሆነ በምድር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተሉ የሚገነዘቡበት ጊዜ እንደሚመጣ” በ2001 ጽፈው ነበር። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወይም ለማቅለል “ሕዝቡ ድምፀ ውሳኔ ቢሰጥ ወይም የሸማቾች ፍላጎት ቢጠና ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል የማይስማማባቸውን ወሳኝ እርምጃዎች መውሰድ ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ለዲሞክራሲም ሆነ ለምድር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ተስፋ ሰጪ አይደለም።”

የፊዚክስ ሊቅና ታዋቂ ደራሲ የሆኑት ስቲቨን ሆኪንግ የሰው ልጅ ከፊቱ መዓት እንደተጋረጠበት ካስተዋሉ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ጠይቀዋል:- “በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በአካባቢያዊ ሁኔታ ረገድ በችግር እየታመሰ ባለው ዓለም ውስጥ የሰው ዘር ከዚህ በኋላ 100 ዓመት መኖር እንዴት ይችላል?”

የሰው ልጅ ሊሳካለት ያልቻለው ለምንድን ነው?

የሰው ልጅ ራሱን በራሱ በማስተዳደር ረገድ ሊሳካለት ያልቻለው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ ማብራሪያ ሊሰጥ የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። አንደኛ ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያስችል ግልጽ ማብራሪያ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን አራት መሠረታዊ ሐቆች ተመልከት።

ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም። “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23) አንድ ሕንፃ መፈራረሱ ሕንፃው የተሠራባቸው ጡቦች ጉድለት እንደነበረባቸው ሊጠቁሙ እንደሚችሉት ሁሉ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚታዩት ድክመቶች ሰዎች ፍጽምና እንደሚጎድላቸው ያንጸባርቃሉ። ከእነዚህ ድክመቶች መካከል እንደ ሙስና፣ ማጭበርበር፣ ስግብግብነትና በሥልጣን አላግባብ እንደ መጠቀም የመሳሰሉት ዝንባሌዎች ይገኙበታል። ይህ በእርግጥ አዲስ ነገር አይደለም። ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት አንድ ጠቢብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ” በማለት ተናግሯል።—መክብብ 8:9

በአስተዳደርና በዳኝነት መስክ አመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ፍጽምና እንደሚጎድለን እንዲሁም ድክመት እንዳለብን አምነው ስለሚቀበሉ እነዚህን ጉድለቶቻችንን ብዙ ሕግ በማውጣት ለማካካስ ይሞክራሉ። ሆኖም ይህን ሲያደርጉ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ወይም ሕግ አክባሪዎች እንዲሆኑ የሚያስገድዱ ሕጎችን ማውጣት እንደማይቻል አሳምረው ያውቃሉ።

ሁላችንም ሟቾች ነን። “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” (መዝሙር 146:3, 4) በጠቢብነታቸው ከታወቁት ገዥዎች መካከል አንዱ የሆነው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ልፋቱ ሁሉ ምን ያህል ከንቱ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና። እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም . . . ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።”—መክብብ 2:18, 19

ራሳችንን በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር ከአቅማችን በላይ ነው። “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤርምያስ 10:23) ፍጽምና ጎድሎን ይቅርና ፍጹማን ብንሆን እንኳ ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ አንጻር እኛ ሰዎች ራሳችንን በተሳካ ሁኔታ ለማስተዳደር መብትም ሆነ ችሎታ እንዳልተሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሌሎች ሰዎች ሲነግሯቸው ወይም የሥነ ምግባር መመሪያ ሲያወጡላቸው ደስ የማይላቸው ለምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ፣ ከሰው በላይ በሆነ ባለ ሥልጣን የመመራት ፍላጎት እንዲኖረን ተደርገን ስለተፈጠርን ነው የሚል ነው። ይህ ባለ ሥልጣን ደግሞ አምላክ ነው።—ኢሳይያስ 33:22፤ የሐዋርያት ሥራ 4:19፤ 5:29

ሰዎች በአንድ ስውር ገዥ ቁጥጥር ሥር ናቸው። “መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን።” (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ክፉ ገዥ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። የአንድ ኩባንያ አመራር በሙስና ከተዘፈቀና በማንም የማይገረሰስ ከሆነ፣ ተራው ሠራተኛ ነገሮችን ለማስተካከል ምን ማድረግ ይችላል? ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር እንኳ ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። በሰይጣን የበላይ አመራር ሥር ያሉት የዚህ ዓለም ስውር ገዥዎች የፈጠሩትን ችግር ለማስተካከል በመሞከር ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዓይን የማይታዩትን እነዚህን ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ‘የዚህ ጨለማ ዓለም ገዦች፣’ “ሥልጣናት” እና ‘በሰማያዊ ሥፍራ ያሉ ርኩሳን መናፍስት ሠራዊት’ በማለት ይገልጻቸዋል።—ኤፌሶን 6:12

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ጉድለት እንዳለባቸው እንዲሁም ዓለምን የሚገዙት በዓይን የማይታዩ ኃይላት እንደሆኑ በማጋለጥ ብቻ አይወሰንም። ለችግሮቻችን ሁሉ አስተማማኝ መፍትሔ የሚሆነው ምን እንደሆነ የሚገልጽ ምሥራች በመንገር ተስፋ እንዲኖረን የሚያስችል በቂ ምክንያት ይሰጠናል።

ፈጣሪያችን ይታደገናል!

ረዳት ባይኖረን ኖሮ ለእነዚህ ችግሮች ፈጽሞ መፍትሔ ማግኘት አንችልም ነበር። ከመካከላችን በጣም ብልህ፣ ኃያል ወይም ባለጠጋ የሚባለው ሰው እንኳ በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት አራት ድክመቶች ውስጥ አንዱን እንኳ ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል የለውም። * ይሁንና በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንደተብራራው ፈጣሪያችን አልረሳንም ወይም አልተወንም። እንዲያውም ምድርን የማስተዳደር መብት ያለው ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ከፊታችን የተደቀኑና ደስታ የሚያሳጡ እንቅፋቶችን በሙሉ ያስወግድልናል። (1 ዮሐንስ 4:8) ደግሞም በቅርቡ እንዲህ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን እንዴት እናውቃለን?

ባለፈው ወር የንቁ! መጽሔት እትም ላይ እንደተብራራው በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ክስተቶችና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ወደዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ ጠልቀን እንደገባን በጣም ግልጽ ያደርጉልናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 የ1954 ትርጉም፤ ማቴዎስ 24:3-7) ይህ ሥርዓት የሚጠፋው በኑክሌር እልቂት ወይም በምድራችንና በአንድ የሰማይ አካል መካከል በሚፈጠር ግጭት አሊያም ደጎችም ሆኑ ክፉዎች በጅምላ እንዲያልቁ በሚያደርግ ሌላ ዓይነት መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በክፉዎች ላይ ብቻ በሚያነጣጥረው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት አማካኝነት ነው። በዚያ ጊዜ ከሚጠፉት መካከል የሰው አገዛዝ እንዲቀጥል የሚሟገቱ ሰዎች ይገኙበታል። (መዝሙር 37:10፤ 2 ጴጥሮስ 3:7) በዚያ ጊዜ አምላክ እንዲህ ያሉት የእሱ ጠላቶች ያስከተሉትን ማንኛውንም ዓይነት መከራ ያስወግዳል። *2 ተሰሎንቄ 1:6-9

ከዚያ በኋላ ፈጣሪ ‘የአምላክ መንግሥት’ ተብሎ ለሚጠራው መስተዳድሩ በምድር ላይ የመግዛት ሙሉ ሥልጣን በመስጠት ከአገዛዝ ጋር የተያያዙ ችግሮቻችንን በሙሉ ይፈታልናል። (ሉቃስ 4:43) ቀጥሎ እንደምንመለከተው መላውን ዓለም የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት ስለ መጪው ጊዜ አዲስ የተስፋ ብርሃን ይፈነጥቅልናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን “ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔው በጎ አድራጎት ነው?” የሚለውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከት።

^ አን.18 “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 106 ላይ ተብራርቷል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የተገነባባቸው “ጡቦች” ጉድለት

▪ ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም።

▪ ሁላችንም ሟቾች ነን።

▪ ራሳችንን በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር ከአቅማችን በላይ ነው።

▪ ሰዎች በአንድ ስውር ገዥ ቁጥጥር ሥር ናቸው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምድር በሰዎች እንደተበላሸች አትቀርም!

መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ምድርን ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ሰዎች ምቹና ሰላማዊ መኖሪያ እንድትሆን የማድረግ ዓላማ እንዳለው የሚገልጽ በቂ ማስረጃ ይዟል። እስቲ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት።

“ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት።”—መዝሙር 104:5

“ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።”—መዝሙር 119:90

“ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4

“ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።”—ኢሳይያስ 11:9

“ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር [ነው]።”—ኢሳይያስ 45:18