ብዙዎች ተስፋ የቆረጡት ለምንድን ነው?
ብዙዎች ተስፋ የቆረጡት ለምንድን ነው?
በዓለም ዙሪያ እየተከሰቱ ያሉት አሳሳቢ ችግሮች ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ ሲያስቡት ፍርሃት እንዲሰማቸው እያደረጉ ነው። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣ በርካታ ከተሞች ውስጥ ዜጎች በስውር በተተከሉ ካሜራዎች አማካኝነት ክትትል ይደረግባቸዋል። አሸባሪዎች በፈጠሩት ስጋት የተነሳ በርካታ መንገደኞችን የሚያስተናግዱ አውሮፕላን ማረፊያዎች የወታደሮች ካምፕ መስለዋል ማለት ይቻላል። ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ሌቦች እንዲሁም ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ኢንተርኔት ተጠቅመው የዋህነት የሚያጠቃቸውን ሰዎች ያጠምዳሉ። ከባቢያዊ ጉዳዮችን ካነሳን ደግሞ ብክለት፣ የደን ምንጠራ፣ የተለያዩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ከምድር ገጽ መጥፋት እንዲሁም የምድር ሙቀት መጨመር ወደፊት ፕላኔታችን ሕይወት አልባ ትሆናለች የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ከሁለትና ከሦስት ትውልዶች በፊት ያልነበሩ ነገሮች ቢሆኑም ዛሬ ዓለም አቀፍ ችግሮች ሆነዋል። ከዚህ የተነሳ ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉት ነገሮች እንዲሁም የእነሱም ሆነ የልጆቻቸው የወደፊት ዕጣ ቢያስጨንቋቸው ምንም አያስደንቅም። ሰዎች በአውቶቡስ፣ በባቡር ወይም በአውሮፕላን መሳፈር በጣም የሚያስፈራቸው ጊዜ እየመጣ ይሆን? ከኑሮ ውድነት እንዲሁም የምድር ሀብት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከመበዝበዙ አንጻር መጪዎቹ ትውልዶች ጥሩ ሕክምና፣ ጥራቱን የጠበቀ ምግብና በቂ ነዳጅ ማግኘት ይችሉ ይሆን?
አንድ ካናዳዊ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የሕክምና ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስመልክተው ሲናገሩ “የወደፊቱ ጊዜ በጣም፣ እጅግ በጣም አስፈሪ ይመስላል” ብለዋል። ብዙ ሰዎች የምግብና የነዳጅ ጉዳይም በጣም እያሳሰባቸው ነው። ለምን? አንዳንድ አገሮች ከቅሪተ አካል በሚገኝ ነዳጅ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ ሲሉ ከተክሎች ለሚገኙ እንደ ኢታኖል ላሉ ነዳጆች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ፈሰስ እያደረጉ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ መንግሥታት የመኪና ቤንዚን በርሜሎችን ለመሙላት የእርሻ መሬቶችን እየተሻሙ በመሆናቸው የሰው ሆድ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀናቃኝ እየተነሳበት ነው። አሁንም እንኳ ቢሆን የምግብ ዋጋ ቀስ በቀስ እያሻቀበ ነው።
በተጨማሪም በሀብታምና በድሃ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱ ማኅበራዊ ውጥረቱን እያባባሰው ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በ21ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ከጤና አጠባበቅ አኳያ በአንድ በኩል ከፍተኛ እመርታ ሲመዘገብ በሌላ በኩል ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ እየታየ ነው። በአንዳንድ ድሃ አገሮች ውስጥ የሰዎች አማካይ ዕድሜ ከሀብታም አገሮች ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያንሳል።” ለዚህ ዋነኛ መንስኤ የሚሆኑት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚታይባቸው አገሮች ውስጥ ያለው በሽታ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ናቸው።
ከዚህም በላይ ለበረሃማነት መስፋፋትና ለአየር መዛባት መንስኤ ሊሆን የሚችለውን የምድር ሙቀት መጨመር ተመልከት። የዚህን ችግር አሳሳቢነት የተረዱ ሰዎች ስለ ነገ ሲያስቡ ቢጨነቁ የሚያስደንቅ አይሆንም። “የጥፋት ቀን ሰዓትን” ያሠራው ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተሰኘው መጽሔት “የሳይንስ ሊቃውንት [የምድር ሙቀት መጨመር] በላይዋ ላይ ባለው ውስብስብ ሥነ ምሕዳር ላይ እያስከተለ ያለውን መጥፎ ውጤት ባስተዋሉ መጠን” መጪው ዘመን የተስፋ ጭላንጭል የማይታይበት አስፈሪ ጊዜ እንደሆነበት ገልጿል።
ይሁንና የወደፊቱ ጊዜ የሚባለውን ያህል ምንም የተስፋ ጭላንጭል የማይታይበት ነው? ወደፊት አስደሳች ሕይወት የመኖር ተስፋችን የተመካው በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በሳይንስ መስክ በተሰማሩ መሪዎች ላይ ነው? አንዳንድ ሰዎች ‘ሌላ ምን ምርጫ አለን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። አክለውም ‘እንዲህ ወዳለው ውጥንቅጥ ውስጥ የገባነው ራሳችን ነን፤ መውጫውን መፈለግ የሚኖርብንም እኛው ራሳችን ነን’ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህ ውጥንቅጥ ለመውጣት የሚያስችል መፍትሔ ማምጣት ከሰው አቅም በላይ እንደሆነና ወደፊት ከስጋት ነፃ የሆነ አስተማማኝ ሕይወት ለመኖር ተስፋችንን በአምላክ ላይ መጣል እንዳለብን ይሰማቸዋል። ይህ ከሆነ ታዲያ አምላክ የእኛ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ብሎም በራሳችን ላይ ከደቀንነው ጥፋት እንደሚያድነን ምን ዋስትና አለን? የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወደፊት አስደሳች ሕይወት የመኖር ተስፋችን የተመካው በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በሳይንስ መስክ በተሰማሩ መሪዎች ላይ ነው?