ታላቅ ግዛት ያቋቋሙት የእስያ ዘላኖች
ታላቅ ግዛት ያቋቋሙት የእስያ ዘላኖች
ሩሲያ ፍርሃትና ግራ መጋባት ቀስፎ ይዟታል። የጦር ፈረሰኞች ጭፍሮች እንደ አንበጣ መንጋ ከምሥራቅ ተነስተው በሣር የተሸፈነውን አውላላ ሜዳ በማቋረጥ ያገኙትን ሁሉ እየገደሉ፣ እየዘረፉና የተቃወማቸውን ሠራዊት እየደመሰሱ ወደ ሩሲያ መጡ። በዚህ ወረራ ያልተነካው የሩሲያ ክፍል የኖቭጎሮድ ግዛት ብቻ ነበር። በዚያ የነበረና በተፈጸመው ነገር ግራ የተጋባ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ይህንን ወረራ ያካሄዱት እንግዳ ቋንቋ ያላቸው “የማይታወቁ ጎሣዎች” እንደሆኑ ገልጿል።
ወራሪዎቹ ሞንጎሊያውያን ሲሆኑ ዛሬ ሞንጎሊያ ተብሎ ከሚጠራው በማዕከላዊና ሰሜን ምሥራቅ እስያ ከሚገኘው በሣር የተሸፈነ አውላላ ሜዳ የመጡ ሕዝቦች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች ከ13ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መባቻ ጀምሮ እንደ መብረቅ ፈጣን በሆነ አካሄድ ያገኙት ድል የእስያንና የከፊል አውሮፓን ታሪክ ለውጦታል። ሞንጎሊያውያን በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሮማውያን በ400 ዓመታት ውስጥ ከተቆጣጠሩት ክልል የሚበልጥ ስፋት ባለው አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችን ድል አድርገው መግዛት ችለዋል። በጣም ኃያል ሆነው በነበረበት ወቅት ከኮሪያ እስከ ሃንጋሪ እንዲሁም ከሳይቤሪያ እስከ ሕንድ ያለውን በጽሑፍ በሰፈረ ታሪክ ከተገለጹት ሰፋፊ ግዛቶች አንዱን ማስተዳደር ችለው ነበር!
በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ ብቻ የዘለቀው የሞንጎሊያውያን ግዛት ታሪክ የእስያንና የአውሮፓን ታሪክ ለማወቅ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ተፈጥሮና ሰው ሰውን ለመግዛት ስላደረገው ጥረት የሚያስተምረው ነገር እውነት መሆኑን ያረጋግጥልናል። ከእነዚህ እውነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- ሰብዓዊ ክብር ከንቱና አላፊ ነው። (መዝሙር 62:9፤ 144:4) “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክብብ 8:9) እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተገለጸው ኃያል ፖለቲካዊ መንግሥታት በሌሎች ብሔራት ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የሚወስዱት ጠብ አጫሪነት የሚንጸባረቅበት እርምጃ የአራዊት ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው ያሳያል። *
ሞንጎሊያውያን እነማን ነበሩ?
ሞንጎሊያውያን ከብት በማርባት፣ በንግድና በአደን የሚተዳደሩ ዘላን ጎሣዎች ሲሆኑ በፈረስ ግልቢያም ከፍተኛ ችሎታ ነበራቸው። አብዛኞቹ ብሔራት ወታደራዊ ሥልጠና እና ትጥቅ የሚሰጡት ከአጠቃላይ ዜጎቻቸው ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ብቻ ቢሆንም በሞንጎሊያውያን ዘንድ ግን እያንዳንዱ ወንድ ፈረስና ቀስት ያለው ጠንካራና ጨካኝ ጦረኛ ነበር። እንዲሁም እያንዳንዱ ጎሣ ካን ተብሎ ለሚጠራው መሪው የማያወላውል ታማኝነት ነበረው።
ቴምዩጂን (1162 ገደማ እስከ 1227) የሚባል አንድ ካን 20 ለሚያህሉ ዓመታት ከተዋጋ በኋላ 27 የሚያህሉ ጎሣዎችን አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ መግዛት ጀመረ። ከጊዜ በኋላም ታታር ተብለው የሚጠሩ ከቱርኪክ የመጡ ሙስሊሞች ከሞንጎሊያውያን ጋር ግንባር ፈጥረው ተዋግተዋል። እንዲያውም የማይበገሩት ሞንጎሊያውያን ጦረኞች ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሲዘምቱ በፍርሃት የተዋጡ አውሮፓውያን እነዚህን ወራሪዎች ታርታር ብለው ጠርተዋቸው ነበር። * በ1206 ቴምዩጂን 40 ዓመት እንዳለፈው ሞንጎሊያውያን ጀንጊስ ካን የሚል ማዕረግ የሰጡት ሲሆን ትርጉሙም “ኃያል መሪ” ወይም “ዓለም አቀፍ መሪ” ማለት ሊሆን ይችላል። ታላቁ ካን ተብሎም ይጠራ ነበር።
ቀስተኞች የነበሩት የጀንጊስ ካን ተዋጊዎች በፈረስ እየጋለቡ ብዙውን ጊዜ በርካታ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ ፈጣንና ኃይለኛ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር። ጀንጊስ ካን በወታደራዊ ችሎታ ረገድ “ከታላቁ እስክንድር ወይም ከቀዳማዊ ናፖሊዮን ጋር ይመጣጠናል” በማለት ኢንካርታ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። ከጀንጊስ ካን ጋር በአንድ ዘመን የኖረው ጁስጃኒ የሚባል ፋርሳዊ ታሪክ ጸሐፊ ይህን የጦር መሪ “የታላቅ ኃይል፣ የማስተዋል፣ የተሰጥኦና የእውቀት ባለቤት” በማለት የገለጸው ሲሆን አክሎም “አራጅ” የሚል ቅጽል ስም ሰጥቶታል።
ከሞንጎሊያ ማዶ
ሰሜናዊ ቻይናን ማንቹ የተባለው ሥርወ መንግሥት ተቆጣጥሮት የነበረ ሲሆን ይህን ሥርወ መንግሥት ጂን ወይም “ወርቃማ” ብለውም ይጠሩት ነበር። ሞንጎሊያውያን ወደ ማንቹ የግዛት ክልል ለመድረስ አስፈሪውን የጎቢ በረሃ ማቋረጥ ቢኖርባቸውም ካስፈለጋቸው ከፈረስ በሚያገኙት ወተትና ደም ሕይወታቸውን ማቆየት ለሚችሉት ለእነዚህ ዘላኖች ይህ ያን ያህል ትልቅ እንቅፋት አልፈጠረባቸውም። ጀንጊስ ካን ግዛቱን እስከ ቻይናና ማንቹሪያ ድረስ ያስፋፋ ቢሆንም ውጊያው 20 ዓመት ያህል ፈጅቷል። ጀንጊስ ካን ከቻይናውያን መካከል ለከበባ የሚያገለግሉ ሞተሮችን፣ ጥንታዊ የሚሳይል ማስወንጨፊያዎችን እንዲሁም ከጥይት ባሩድ የተሠሩ ቦምቦችን የሚሠሩለት ምሑራን፣ የእጅ ባለሞያዎች፣ ነጋዴዎችና መሐንዲሶች መልምሎ ነበር።
ጀንጊስ ካን በስተ ምዕራብ ርቀው ወደሚገኙ አገሮች የሚወስዱትን ሲልክ ሮድ በመባል የሚታወቁ የንግድ መሥመሮችን በቁጥጥሩ ሥር ካደረገ በኋላ ከአጎራባቹ የቱርኪክ ሱልጣን ሙሐመድ ጋር የንግድ ሽርክና ለመመሥረት ፈለገ። ሱልጣኑ የዛሬዎቹን ቱርክሜኒስታን፣ ታጂኪስታን፣ አፍጋኒስታን፣ ኡዝቤክስታንና አብዛኛውን ኢራን ጠቅልሎ የያዘ በጣም ሰፊ ግዛት ነበረው።
በ1218 የንግድ ተልእኮን ሽፋን ያደረገ የሞንጎሊያውያን ልዑካን ወደ ሱልጣኑ ግዛት ወሰን ደረሰ። የአካባቢው ገዥ ግን ልዑካኑን ስለገደላቸው ሞንጎሊያውያን በሙስሊሞች ምድር ላይ የመጀመሪያውን ወረራ እንዲያካሂዱ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተፈጠሩ። ከጉንዳን እንደሚበዙ የሚነገርላቸው ሞንጎሊያውያን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከተሞችንና እርሻዎችን ከመመዝበራቸውና ከማቃጠላቸውም በላይ ከሱልጣን ሙሐመድ ሕዝቦች መካከል እነሱ የሚፈልጉት ሙያ ያላቸውን ሰዎች ብቻ በማስቀረት ብዙዎቹን ፈጇቸው።
ከዚያም ቁጥራቸው 20,000 እንደሚሆን የሚገመቱት ሞንጎሊያውያን ተዋጊዎች፣ 80,000 ወታደሮች የነበሩትን የሩሲያ ጦር ኃይል ጨምሮ በመንገዳቸው ላይ የገጠማቸውን ማንኛውንም ሠራዊት እያንበረከኩ በአዘርባጃንና በጆርጂያ በኩል አድርገው በካውኬዢያ በስተ ሰሜን ወዳለው ሜዳማ አካባቢ ገሰገሱ። ሞንጎሊያውያን፣ በፈረሰኛ ሠራዊት ታሪክ በጣም ታላቅ ጀብድ እንደሆነ የሚቆጠረውን 13,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጉዞ በማድረግ የካስፒያን ባሕርን ዙሪያ ዞረውታል። ያገኙት ተከታታይ ድል ከዚያ በኋላ ምሥራቅ አውሮፓን ለመውረር ለመጡ ሞንጎሊያውያን ገዥዎች ፈር ቀዳጅ ሆኗል።
የጀንጊስ ካን ተተኪዎች
ጀንጊስ ካን ከመጀመሪያ ሚስቱ ከወለዳቸው አራት ወንዶች ልጆች መካከል ኦጎዴይ ተብሎ የሚጠራው ሦስተኛው ልጁ ቀጣዩ ታላቅ ካን እንዲሆን ተደረገ። ኦጎዴይ ድል የተደረጉትን
አገሮች በቁጥጥሩ ሥር መሆናቸውን ከማረጋገጡና በእነዚህ አገሮች ላይ ከተሾሙት እንደራሴዎች ግብር ከመቀበሉም በተጨማሪ በሰሜናዊ ቻይና የነበረውን የጂን ሥርወ መንግሥት ድል ለማድረግ የተጀመረውን ዘመቻ አጠናቀቀ።ኦጎዴይ፣ ግዛቱን ለማስጠበቅ እንዲሁም ሞንጎሊያውያን የለመዱትን የቅንጦት ኑሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ሲል እንደገና ወደ ጦርነት ለመሄድ ወሰነ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት የዘመተው ቀደም ሲል ወዳልተመዘበሩት አገሮች ነበር። ኦጎዴይ፣ በስተ ምዕራብ ባሉት የአውሮፓ አገሮችና በደቡባዊ ቻይና በሚገኘው የሶንግ ሥርወ መንግሥት ላይ ጥቃት በመሰንዘር በሁለት ግንባር ጦርነት ከፈተ። በአውሮፓውያን ላይ ባደረገው ዘመቻ ቢቀናውም በቻይና ግን አልተሳካለትም። ሞንጎሊያውያን መጠነኛ ድል ቢቀዳጁም ዋናውን የሶንግ ክልል ግን መቆጣጠር አልቻሉም።
የምዕራቡ ዘመቻ
በ1236 በግምት 150,000 የሚሆኑ ጦረኞች በስተ ምዕራብ ወደ አውሮፓ ገሰገሱ። በመጀመሪያ ያነጣጠሩት በቮልጋ ወንዝ ዳርቻ ላይ ባሉት ክልሎች ላይ ነበር፤ ከዚያም በሩሲያ የከተማ መስተዳድሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኪየቭን አመድ አደረጓት። ሞንጎሊያውያን፣ ነዋሪዎቹ ከሁሉም ነገር አንድ አሥረኛውን ከሰጧቸው ከተማዎቹን እንደማያጠፏቸው ቃል ይገቡ ነበር። ይሁን እንጂ ሩሲያውያን ለመዋጋት መረጡ። ሞንጎሊያውያን ማስወንጨፊያዎችን በመጠቀም በጠላቶቻቸው ላይ ድንጋይ፣ የተቀጣጠለ ናፍጣና ፈንጂ አዘነቡባቸው። የከተማዎቹ ግንቦች ሲደረመሱ ወራሪዎቹ ወደ ውስጥ በመጉረፍ ሕዝቡን ይጨፈጭፉ ነበር፤ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ሁኔታውን ሲገልጹ “ለሞቱት ለማልቀስ የተረፈ ሰው አልነበረም” በማለት ጽፈዋል።
የሞንጎሊያውያን ሠራዊት በፖላንድና በሃንጋሪ ከፍተኛ ውድመት በማድረስ ወደ አሁኗ ጀርመን ድንበር ተቃርቦ ነበር። ምዕራብ አውሮፓ ጥቃቱን ለመመከት ተዘጋጅታ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሞንጎሊያውያን ወደዚያ አልሄዱም። ታኅሣሥ 1241 ኦጎዴይ ካን ሞተ። በዚህም ምክንያት የሞንጎሊያውያን የጦር አዛዦች አዲስ ገዥ ለመምረጥ 6,000 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ካራኮረም ወደሚባለው ዋና ከተማቸው በአስቸኳይ ተመለሱ።
ጉዩክ የሚባለው የኦጎዴይ ልጅ በአባቱ ምትክ መሪ ሆነ። አንድ ጣሊያናዊ፣ ጉዩክ ዘውድ ሲጭን የዓይን ምሥክር ለመሆን በቅቶ ነበር፤ ግለሰቡ ከጳጳስ ኢኖሰንት አራተኛ የተላከውን ደብዳቤ ለማድረስ በሞንጎሊያውያን ቁጥጥር ሥር ያለውን ክልል አቋርጦ ለ15 ወራት ተጉዟል። ጳጳሱ፣ አውሮፓ እንደገና እንደማትወረር ማረጋገጫ ለማግኘት ፈልገው የነበረ ሲሆን ሞንጎሊያውያንንም ክርስትናን እንዲቀበሉ አበረታቷቸዋል። ጉዩክ ግን ምንም ለማድረግ ቃል አልገባም። ከዚህ ይልቅ ጳጳሱ ከነገሥታቱ ልዑካን ጋር ወደ ካኑ መጥተው እጅ እንዲነሱት ነገራቸው!
በሁለት ግንባሮች ላይ የተሰነዘረ ሌላ ጥቃት
ቀጣዩ ታላቅ ካን ሞንግኬ ሲሆን ሥልጣኑን የያዘውም በ1251 ነበር። ኩብላይ ከተባለው ወንድሙ ጋር በመሆን በምሥራቃዊ ቻይና በሚገኘው የሶንግ ሥርወ መንግሥት ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ሌላው ሠራዊት ደግሞ ወደ ምዕራብ አመራ። ወደ ምዕራብ ያመራው ሠራዊት ባግዳድን የደመሰሳት ሲሆን ደማስቆን ደግሞ እጅ እንድትሰጥ አደረጋት። በሙስሊሞች ላይ የመስቀል ጦርነት አውጀው የነበሩት ክርስቲያን ተብዬዎች በዚህ በጣም ተደሰቱ፤ እንዲያውም በባግዳድ የሚኖሩት “ክርስቲያኖች” ሙስሊም ጎረቤቶቻቸውን ይዘርፏቸውና ይገድሏቸው ነበር።
ሞንጎሊያውያን የሙስሊሙን ዓለም ሊደመስሱ የተቃረቡ በመሰሉበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ታሪክ ራሱን ደገመ። ሞንግኬ እንደሞተ የሚገልጽ ዜና መጣ። በዚህ ጊዜም ወራሪዎቹ ድንበሩን እንዲጠብቁ 10,000 ሰዎችን ብቻ ትተው እንደገና ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ትተውት የሄዱት አነስተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት ከግብፅ በመጣ ሠራዊት ተደመሰሰ።
ሞንጎሊያውያን በምሥራቃዊ ቻይና በነበረው ባለጠጋ የሆነ የሶንግ ሥርወ መንግሥት ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ግን ድል ተቀዳጁ። እንዲያውም ኩብላይ ካን፣ ዩዋን የሚባል አዲስ የቻይና ሥርወ መንግሥት እንደመሠረተ አሳወጀ። የዚህ ሥርወ መንግሥት አዲሱ ዋና ከተማ የነበረበት ሥፍራ በዛሬው ጊዜ ቤይጂንግ ተብሎ ይጠራል። ኩብላይ በ1270ዎቹ መገባደጃ ላይ ቀሪዎቹን የሶንግ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ድል ካደረገ በኋላ የታንግ ሥርወ መንግሥት በ907 ከወደቀበት ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ በሆነችው ቻይና ላይ መግዛት ቻለ።
መከፋፈልና መውደቅ
በ14ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ ኃያሉ የሞንጎሊያውያን ግዛት መፈራረስ ጀመረ። ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ነገሮች ብዙ ናቸው። መጀመሪያ ነገር፣ በጀንጊስ ካን ዝርያዎች መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ፣ ግዛቱ በበርካታ ካኖች በሚተዳደሩ ግዛቶች እንዲሸነሸን አደረገ። በተጨማሪም ሞንጎሊያውያን ድል አድርገው የያዟቸውን አገሮች ባሕል ተቀበሉ። በቻይና ይደረግ የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ የኩብላይ ዝርያዎችን ሥልጣን አዳከመው። በ1368 ቻይናውያን ብቃት የሌለው አመራር፣ ሙስናና ከባድ ቀረጥ ስለሰለቻቸው የዩዋን ሥርወ መንግሥት ጌቶቻቸውን በመገልበጥ ወደ ሞንጎሊያ እንዲመለሱ አስገደዷቸው።
እንደ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ፈጣን የነበረው የሞንጎሊያውያን ወረራ ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ ቢያልፍም በአውሮፓና በእስያ ታሪክ ላይ አሻራውን ጥሏል፤ እንዲሁም ሞንጎሊያም ሆነ ቻይና አንድነት እንዲኖራቸው አድርጓል። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ያሉት ሞንጎሊያውያን የመጀመሪያው ታላቅ ካን የሆነውን ጀንጊስ ካንን የብሔራቸው አባት እንደሆነ አድርገው ማወደሳቸው ምንም አያስገርምም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 አራዊትና ፖለቲካዊ አገዛዞች ወይም መንግሥታት የተጠቀሱባቸውን የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ልብ በል:- ዳንኤል 7:6, 12, 17, 23፤ 8:20-22፤ ራእይ 16:10፤ 17:3, 9-12
^ አን.7 አውሮፓውያን፣ ታታር ተብለው የተጠሩት ሰዎች “ከታርታሩስ” የወጡ ዲያብሎሶች እንደሆኑ ያስቡ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:4 የግርጌ ማስታወሻ) በመሆኑም እነዚህን ወራሪዎች ታርታር ብለው ጠሯቸው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከድል አድራጊነት ወደ ንግድ ልውውጥ
ኩብላይ ካን ያቋቋመው የዩዋን ሥርወ መንግሥት ገናና በነበረበት ወቅት ንግድንና ከቦታ ቦታ መጓጓዝን ያበረታታ ስለነበር “በአውሮፓና በእስያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ የንግድ መስፋፋት” እንዲኖር አድርጎ ነበር። ማርኮ ፖሎ የተባለው ታላቁ ጣሊያናዊ ተጓዥ (1254-1324) የኖረው በዚህ ዘመን ነበር። * የአረብ፣ የፋርስ፣ የሕንድና የአውሮፓ ነጋዴዎች ፈረሶችን፣ ምንጣፎችን፣ የከበሩ ድንጋዮችንና ቅመማ ቅመሞችን ይዘው በየብስ ወይም በመርከብ በመጓዝ በሸክላ ዕቃዎች፣ ለጌጥነት በሚያገለግሉ ቀለም ቅብ ዕቃዎችና በሐር ይለውጧቸው ነበር።
በ1492 ክሪስቶፈር ኮለምበስ፣ ከሞንጎሊያ ግዛት ጋር እንደገና የንግድ ግንኙነት ለመመሥረት ተስፋ በማድረግ ስለ ማርኮ ፖሎ ጉዞ የሚዘግብ ጽሑፍ ይዞ ከአውሮፓ በመነሳት ወደ ምዕራብ በመርከብ ተጓዘ። ይሁን እንጂ የሞንጎሊያ ግዛት ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ከሕልውና ውጪ እንደሆነ አላወቀም ነበር! የሞንጎሊያ ግዛት መውደቅ የመልእክት ልውውጥ እንዳይኖር ያደረገ ሲሆን ሙስሊሞች ደግሞ ከአውሮፓ ወደ ምሥራቅ የሚወስደውን የየብስ መንገድ ዘግተውት ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.33 ማርኮ ፖሎ ወደ ቻይና ያደረገውን ጉዞ በሚመለከት በሰኔ 8, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የቀረበውን ዘገባ ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በሃይማኖታዊ መቻቻል ይታወቁ ነበር
የጥንቶቹ ሞንጎላውያን ይከተሉ የነበሩት የአካባቢያቸውን ባሕላዊ ሃይማኖት ቢሆንም ሌሎች ሃይማኖቶችን አይቃወሙም ነበር። ዘ ዴቭልስ ሆርስሜን የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ምዕራባውያን፣ የሞንጎላውያን ዋና ከተማ ወደነበረችው ካራኮረም ሲገቡ ያስገረማቸው ብልጽግናዋ ብቻ ሳይሆን በከተማዋ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ ነፃነት ጭምር ነበር። አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችና መቅደሶች ጎን ለጎን ተሠርተው ነበር።
ስመ ክርስትናን ለሞንጎላውያን ያስተማሯቸው ከባይዛንታይን ወይም ከምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን የተገነጠሉ ኔስቶሪያን የሚባሉ ወገኖች ናቸው። ኔስቶሪያኖች፣ ከእስያ ቱርኪክ ጎሣዎች መካከል ብዙ ሰዎችን ወደ ራሳቸው ሃይማኖት የለወጡ ሲሆን ሞንጎላውያን ደግሞ ከእነዚህ ሰዎች ክርስትናን ተምረዋል። እንዲያውም ከእነዚህ አዳዲስ አማኞች መካከል አንዳንዶቹ ሴቶች ከሞንጎላውያን ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ተጋብተው ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያሉት ሞንጎላውያን የተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶችን ይከተላሉ። ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል የአካባቢውን ባሕላዊ ሃይማኖት የሚከተሉት 30 በመቶ ሲሆኑ 23 በመቶ የሚሆኑት የላማን (የቲቤታውያንን) ቡድሂስት ሃይማኖት፣ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የእስልምናን ሃይማኖት ይከተላሉ። ቀሪው ሕዝብ በአብዛኛው ሃይማኖት የለውም።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሞንጎሊያውያን ተጽዕኖ ያሳደሩባቸው ግዛቶች
ሃንጋሪ
ሩሲያ
ኪየቭ
ቮልጋ ወንዝ
ሳይቤሪያ
የካስፒያን ባሕር
ደማስቆ
ኢራን
ባግዳድ
ኡዝቤክስታን
ሞንጎሊያ
ካራኮረም
ጎቢ በረሃ
ኮሪያ
ቻይና
ቤይጂንግ
ሕንድ
ኖቭጎሮድ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፈረስ መንጋ፣ ሞንጎሊያ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀንጊስ ካን
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Bildarchiv Preussischer Kulturbesitz/Art Resource, NY
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
Scenic: © Bruno Morandi/age fotostock; Genghis Khan: © The Stapleton Collection/The Bridgeman Art Library