በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነት ይሄ ዛፍ ነው?

እውነት ይሄ ዛፍ ነው?

እውነት ይሄ ዛፍ ነው?

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በአውስትራሊያ ደረቅና ወጣ ገባ በሆነ አካባቢ ተንሰራፍቶ የሚገኘውና ድቡልቡል ቅርጽ ያለው ቦኣብ የተባለው ዛፍ መጀመሪያ ሲታይ እንግዳ መልክ ያለው አስቀያሚ ነገር ይመስል ይሆናል። በበጋው ወቅት ቅጠሎቻቸውን የሚያረግፉት ትላልቆቹ የቦኣብ ዛፎች እጆቻቸውን ወደ ሰማይ የዘረጉ ለየት ያሉ ፍጥረታት እንጂ ዛፎች አይመስሉም። አንድ የአቦርጂኒዎች አፈ ታሪክ፣ ዛፉ እንደዚህ ዓይነት መልክ ሊኖረው የቻለው በመረገሙ ምክንያት ስለተገለበጠ እንደሆነ ይገልጻል!

የቦኣብ ዛፎች ገና ትንሽ እያሉ በአንጻራዊ ሁኔታ ቀጠን ያሉና ማራኪ ናቸው። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን ግራጫ ቀለም ያለው የዛፎቹ ግንድ እየወፈረ ከመሄዱም ሌላ ሸንተረር ያወጣል። በ1837 ጆርጅ ግሬይ የተባለው አሳሽ ስለ ቦኣብ ዛፎች ሲጽፍ “በበሽታ የተጠቁ ይመስላሉ” ብሎ ነበር። የቦኣብ ዛፎችን ከአብዛኞቹ ዛፎች የተለዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? አቦርጂኒዎችን ጨምሮ በአውስትራሊያ ራቅ ያሉ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ለቦኣብ ዛፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት እንዲሁም ዛፉን የሚወዱት ለምንድን ነው?

አጠር ሲል ይሻላል

የቦኣብ ዛፎች በማዳጋስካር እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ ይገኛሉ። እነዚህ ዛፎች በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ቤኦባብ ተብለው የሚጠሩ ቢሆንም በአውስትራሊያ ቦኣብ የሚለው ስም ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት ቆይቷል። በጫካ ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ስሞችን አሳጥረው መጥራት ይወዳሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ከአካባቢው የማይጠፉት ዝንቦች ረዘም ያለ ነገር ሲያወሩ ወደ አፋቸው እንዳይገቡ ሲሉ እንደሆነ በቀልድ መልክ ይነገራል። ስለዚህ ቤኦባብ የሚለውን ስም አሳጥረው ቦኣብ ያሉት ሲሆን ብዙም ሳይቆይ አዲሱ መጠሪያ የቋንቋቸው ክፍል ሆነ።

ቦኣብ፣ የሞቱ አይጦች ዛፍ ተብሎም ይጠራል። እንዲህ ያለ ደስ የማይል ስም የተሰጠው ለምንድን ነው? የዛፉ ፍሬዎች ሲወዛወዙ ከሩቅ ለሚያያቸው በጅራታቸው የተንጠለጠሉ የሞቱ አይጦች ስለሚመስሉ ነው። ከዚህም ሌላ አበቦቹ ሲሰነጠቁ ወይም ጉዳት ሲደርስባቸው የበሰበሰ ሥጋ ዓይነት ጠረን ያመጣሉ። አበቦቹ ምንም ጉዳት ካልደረሰባቸው ግን ትላልቅና ነጭ ከመሆናቸውም ሌላ ግሩም መዓዛ ይኖራቸዋል።

አስቸጋሪ የአየር ጠባይን የሚቋቋም ዛፍ

የቦኣብ ዛፍ፣ በዌስተርን አውስትራሊያ በሚገኘው የኪምበርሊ አውራጃ እንዲሁም አጎራባች በሆነው ኖርዘርን ቴሪቶሪ በብዛት ይበቅላል። በእነዚህ አካባቢዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ ኃይለኛ ዝናብ የሚጥል ሲሆን በቀረው ጊዜ ግን ወቅቱ በጋ ነው።

እነዚህ ዛፎች ራሳቸውን በማደስ ችሎታቸው የታወቁ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ለበርካታ መቶ ዓመታት ይኖራሉ። ስለ ዕፅዋት የሚያጠኑት ዲ ኤ ኼርን እንዲህ ብለዋል:- “ዛፉ በእሳት ተቃጥሎ ውስጡ ቢቦረቦር ወይም በዙሪያው ያለው ቅርፊት ሙሉ በሙሉ ቢላጥም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ አይደርቅም፤ የደረሰበትን ጉዳት ከጠገነ በኋላ ማደጉን ይቀጥላል።” * ኼርን አክለውም “ዛፉ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ እስካልጠፋ ድረስ እንደ ቀድሞው እድገት ማድረጉን ይቀጥላል” ብለዋል። በቀላሉ የማይደርቀው ይህ ዛፍ በአንድ ወቅት ወደ ሌላ አገር ሊላክ በሣጥን ውስጥ በተቀመጠበት ጊዜ ሥሮቹን በሣጥኑ ክፍተቶች መካከል በማሳለፍ ከታች ባለው አፈር ውስጥ ሥር ሰዷል!

ድንጋይ በብዛት በሚገኝባቸው ጅረቶች፣ አለት በበዛባቸው ገደላማ አካባቢዎች እንዲሁም በአሸዋ በተሸፈኑ ሜዳዎች ላይ የሚበቅሉት የቦኣብ ዛፎች አብዛኛውን ጊዜ በዙሪያቸው ከሚገኙት ዛፎች ረዘም ብለው ይታያሉ። በኪምበርሊ ኘላቱ ላይ የሚገኙ አንዳንድ የቦኣብ ዛፎች ቁመታቸው እስከ 25 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ የሚደርስ ሲሆን ስፋታቸውም የዚያኑ ያህል ነው።

የቦኣብ ዛፎች ግዙፍ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ውኃ ነው። የቦኣብ እንጨት እንደ ስፖንጅ ለስላሳ ከመሆኑም ሌላ ቃጫ ስላለው ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ ማጠራቀም ይችላል። ኃይለኛ ዶፍ በሚጥልበት ወቅት ዛፉ ብዙ ውኃ መጥጦ ስለሚይዝ ግንዱ ያብጣል። የበጋው ወቅት እየገፋ ሲሄድ ዛፉ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ መጠኑ ይመለሳል።

በርካታ ዛፎች ከባድ የሆነውን የቅዝቃዜ ወቅት የሚያልፉት ቅጠላቸውን በማርገፍ ነው። የቦኣብ ዛፎች ግን ቅጠላቸውን የሚያረግፉት ረጅም በሆነው የበጋ ወቅት ነው። የበጋው ወቅት እየተገባደደ ሲመጣ የቦኣብ ዛፎች የሚያብቡ ሲሆን አዳዲስ ቅጠሎችንም ያወጣሉ። እነዚህ ምልክቶች የዝናቡ ወቅት መቃረቡን ስለሚያበስሩ የአካባቢው ነዋሪዎች አንዳንድ ጊዜ የቦኣብ ዛፍን የቀን መቁጠሪያ ተክል በማለት ይጠሩታል።

የዛፉ አበቦች የሚፈኩት በምሽት ብቻ ሲሆን የሚቆዩትም ለተወሰኑ ሰዓታት ነው፤ ፀሐይዋ ከወጣች በኋላ ይጠወልጋሉ። ፍሬዎቹ ሲያድጉ የዱባ ቅርጽ የሚኖራቸው ሲሆን መሬት ላይ ወድቀው ሲሰነጠቁ ዘሩ ይበተናል።

የሕይወት ዛፍ

በኪምበርሊ የሚኖሩ አቦርጂኒዎች የቦኣብ ፍሬዎችን፣ ቅጠሎችንና ከዛፉ የሚገኘውን ሙጫ እንዲሁም የዛፉን ሥሮች ጠቃሚ ምግብ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ፍሬዎቹ ከመድረቃቸው በፊት ለስላሳ፣ ነጭ እንዲሁም ጣፋጭ የሆነ የሚበላ ክፍል አላቸው። የዛፉ እንጨትና ሥሮች እርጥበት ስላላቸው ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ አቦርጂኒዎች ያኝኳቸዋል። በክረምቱ ወቅት ኃይለኛ ዝናብ ከጣለ የአካባቢው ነዋሪዎች በግንዱ ላይ በሚገኙት ጎድጎድ ያሉ ቦታዎች እንዲሁም ግንዱና ቅርንጫፎቹ በሚጋጠሙባቸው ቦታዎች ላይ ያቆረውን ውኃ ማግኘት ይችላሉ።

በ1856 በኦገስተስ ግሪጎሪ የሚመራው ቡድን ወደ ኪምበርሊ ኘላቱ በተጓዘበት ወቅት የቡድኑ አባላት ስከርቪ በተባለ በቫይታሚን ሲ እጥረት የሚመጣ በሽታ ተይዘው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሰዎቹ የቦኣብን ፍሬ ውስጠኛ ክፍል በመቀቀል “ግሩም ማርማላት” ሠሩ። ፍሬው በቫይታሚን ሲ የበለጸገ በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ሰዎቹ ጤንነታቸው ተመለሰ።

የቀድሞውን ዘመን የሚያስታውሱ ምልክቶች

ባለፉት ዘመናት አቦርጂኒዎችም ሆኑ አውሮፓውያን በቦኣብ ዛፎች ላይ መልእክት ይጽፉ ነበር። በ1820 መርሜድ የተባለችው መርከብ ጥገና እንዲደረግላት በኪምበርሊ የባሕር ዳርቻ ላይ መልሕቋን ጣለች። ካፒቴን ፊሊፕ ፓርከር ኪንግ፣ ቡድኑ ያረፈበትን ቦታ የሚጠቁም የማያሻማ ምልክት እንዲተው የሚያዘውን የብሪታንያ የባሕር ኃይል መመሪያ በመከተል በአንድ ግዙፍ የቦኣብ ዛፍ ላይ “ኤች ኤም ሲ መርሜድ 1820” የሚል ጽሑፍ ቀረጸ።

የመርሜድ ዛፍ ተብሎ የተሰየመው ይህ የቦአብ ዛፍ በዚያን ጊዜ 8.8 ሜትር ስፋት ነበረው። በዛሬው ጊዜ የዚህ ዛፍ ስፋት ከ12 ሜትር በላይ ይሆናል። በግንዱ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ በአሁኑ ወቅት በግልጽ ባይታይም የቀድሞዎቹን አሳሾች ያስታውሰናል። ረጅም ዕድሜ ባስቆጠሩ አንዳንድ የቦኣብ ዛፎች ላይ በደንብ ተቦርቡረው የተቀረጹት መልእክቶች አሁንም በግልጽ የሚታዩ ሲሆን ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ጎብኚዎችም ይመለከቷቸዋል።

አውሮፓውያን ሰፋሪዎች ወደ ኪምበርሊ ኘላቱ በመጡበት ወቅት በዚህ አዲስ አካባቢ የሚገኙት ግዙፍ የቦኣብ ዛፎች፣ የመሰብሰቢያና የማረፊያ ቦታ እንዲሁም ምልክት ሆነው አገልግለዋቸዋል። ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩ ከብት አርቢዎች፣ አስገራሚ ስም በተሰጣቸው የቦኣብ ዛፎች ሥር ከብቶቻቸውን ያሳርፉ ነበር፤ ለዛፎቹ ከተሰጧቸው ስሞች መካከል ኦሪየንታል ሆቴል፣ ክለብ ሆቴል ወይም ሮያል ሆቴል የሚሉት ይገኙበታል።

በ1886 አንዳንድ አቦርጂኒዎች፣ ኦገስት ሉካነስ የተባለውን ጀርመናዊ ሰፋሪ ጀልባ በሰረቁበት ወቅት እሱና አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ወደ ዊንደም ከተማ ለመድረስ 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ የነበረባቸው ሲሆን በመንገዳቸው ላይ ደግሞ አዞ ያለባቸው ጅረቶችና ወንዞች ነበሩ። ሉካነስ ከጊዜ በኋላ እንደጻፈው እሱና አብረውት ይጓዙ የነበሩት ሰዎች ከዚያ ቀደም በአካባቢው የነበረ አንድ አሳሽ በዕለት ማስታወሻው ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ አንብበው ነበር። ከዚህ በመነሳት፣ አሳሹ “በፒት ስፕሪንግስ አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ትልቅ የቦኣብ ዛፍ በታች አንዳንድ የአናጢ መሣሪያዎችን እንደቀበረ” ማወቅ ቻሉ፤ ሰውየው በዛፉ ላይ የስሙን የመጀመሪያ ፊደላት ቀርጾ ነበር። የሚገርመው ነገር ሉካነስና የጉዞ ባልደረቦቹ ዛፉንና መሣሪያዎቹን አገኟቸው። ከዚያም “አንድ ትልቅ የቦኣብ ዛፍ” ቆርጠው በጥሩ ሁኔታ ሊንሳፈፍ የሚችል ታንኳ በአምስት ቀናት ውስጥ ሠሩ። በዚህ መንገድ ሁሉም በሰላም ወደ ቤታቸው መመለስ ችለዋል።

በጣም ታዋቂ ከሆኑት የቦኣብ ዛፎች ሁለቱ ደርቢ እና ዊንደም ወኅኒ ቤት የሚባሉት ዛፎች ሲሆኑ ስያሜያቸውን ያገኙት በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ከተሞች ነው። ውስጣቸው የተቦረቦረውና እያንዳንዳቸው በርካታ ሰዎች መያዝ የሚችሉት እነዚህ ግዙፍ ዛፎች በ19ኛው መቶ ዘመን እንደ ወኅኒ ቤት ያገለግሉ እንደነበር ይነገራል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አንዳንድ የታሪክ ምሑራን ይህንን ሐሳብ አይቀበሉትም። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ዛፎች አስደናቂ ናቸው፤ በርካታ ሰዎችም ዛፎቹን መጎብኘት ያስደስታቸዋል።

የሥነ ጥበብ ሥራዎች

በአንድ ወቅት ሰዎች በቦኣብ ዛፍ ግንዶች ላይ ሥዕሎችንና መልእክቶችን ይቀርጹ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በአውስትራሊያ ራቅ ያሉ አካባቢዎች የሚገኙት የሥነ ጥበብ ባለሞያዎች ሥዕሎቹን የሚቀርጹት በግንዶቹ ላይ ሳይሆን የእንቁላል ቅርጽ ባላቸው የቦኣብ ፍሬዎች ላይ ነው፤ የዛፉ ፍሬ 25 ሴንቲ ሜትር ርዝመትና 15 ሴንቲ ሜትር ስፋት ሊኖረው ይችላል።

የሥነ ጥበብ ባለሞያዎቹ ለሥራቸው ተስማሚ የሆነ ፍሬ ከመረጡ በኋላ ቡናማ መልክ ባለው የፍሬው ቅርፊት ላይ በጣም የሚያምሩ ሥዕሎችን በሰንጢ ይቀርጻሉ። ከተለመዱት ሥዕሎች መካከል በአካባቢው የሚገኙት እንስሳት እንዲሁም የሰዎች ፊትና አካል ይገኙበታል፤ አቦርጂኒዎች ሲያድኑ የሚያሳዩ ሥዕሎችም አሉ። እነዚህን የሥነ ጥበብ ሥራዎች የሚሰበስቡ ሰዎችም አሉ። ጎብኚዎችና በአካባቢው የሚገኙ ሱቆችም ሥዕሎቹን ይገዛሉ።

የቦኣብ ዛፍ በግዙፍነቱ ከሴኮያ ዛፍ ጋር አይወዳደር ይሆናል፤ ወይም የአኻያ ዛፍን ያህል ግርማ ሞገስ ላይኖረው ይችላል። አሊያም ደግሞ የዋርካን ያህል ማራኪ ላይሆን ይችላል። ያም ቢሆን አስቸጋሪ የአየር ጠባይ የማይበግረውና ራሱን የማደስ ችሎታ ያለው ይህ ዛፍ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩት ሰዎች ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፤ ከዚህም በላይ ለፈጣሪው ክብር ያመጣል። እንዲሁም አምላክ በሚያስቁ ነገሮች መደሰት እንደሚችል ያሳያል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 አንድ ዛፍ በዙሪያው ያለው ቅርፊት በክብ ቅርጽ መላጡ ፈሳሽ ማግኘት እንዳይችል ያደርገዋል፤ አብዛኞቹ ዛፎች እንዲህ ሲደረጉ ይደርቃሉ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቦኣብ ዛፍ አበቦች የሚፈኩት በምሽት ሲሆን ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ይጠወልጋሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእንሽላሊት ምስል የተቀረጸበት የቦኣብ ፍሬ