ዕጹብ ድንቅ የሆነው ባሕረ ሰላጤ
ዕጹብ ድንቅ የሆነው ባሕረ ሰላጤ
ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በሜክሲኮ እና በባጃ ካሊፎርኒያ ባሕረ ገብ መሬት መካከል ሰማያዊ ቀለም ያለው የካሊፎርኒያ ባሕረ ሰላጤ (ከታች ያለው) ተንጣሎ ይታያል፤ ይህ ባሕረ ሰላጤ ቀደም ሲል የኮርቴዝ ባሕር በመባል ይታወቅ ነበር። በረሃማ የባሕር ዳርቻዎች የሚገኙበትንና ወጣ ገባ መሬት ያላቸው ደሴቶችን የያዘውን የዚህን ባሕረ ሰላጤ አብዛኛውን ክፍል፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል። ይህን አካባቢ ልዩ ያደረገው ምንድን ነው?
ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመትና በአማካይ 153 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የካሊፎርኒያ ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም አካባቢው እጅግ ማራኪ ከመሆናቸውም ሌላ በተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት የተሞሉ ናቸው። ይህ ባሕረ ሰላጤ በምድር ላይ ከሚገኙት ከፍተኛ ማዕበል ከሚነሳባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሰሜናዊው ዳርቻ የውኃው ከፍታ እስከ 9 ሜትር ይደርሳል። በቂ የፀሐይ ብርሃን መኖሩና ውኃው በማዕድናት የበለጸገ መሆኑ ፕላንክተን የሚባሉትን ጥቃቅን ዕፅዋትንና እንስሳትን ጨምሮ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በብዛት እንዲገኙ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው የጠራ ውኃ በብዛት መኖሩ፣ በውቅያኖስ ውስጥ ምርምር የሚያካሂዱት ዣክ-ኢቭ ኩስቶ ይህን ባሕረ ሰላጤ “የዓለም የዓሣ ገንዳ” ብለው እንዲጠሩት ገፋፍቷቸዋል።
ከ890 በላይ የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙበት ይህ ባሕረ ሰላጤ፣ በባሕር ውስጥ ያሉትን ፍጥረታት ለማጥናት የሚያስችል ግሩም የተፈጥሮ ቤተ ሙከራ ነው፤ ከዓሣ ዝርያዎቹ መካከል 90 የሚያህሉት በዚያ አካባቢ ብቻ የሚገኙ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን፣ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነውን ቫኪታ የተባለ ከፖርፖይዝ ዝርያ የሚመደብ ዓሣን ጨምሮ በርካታ ዝርያዎች ቁጥራቸው እየተመናመነ ሄዷል። ቫኪታ የሚለው የስፓንኛ ቃል “ትንሽ ላም” የሚል ትርጉም አለው።
ከፖርፖይዝ ዝርያ መካከል ትንሹ የሆነው ቫኪታ ርዝመቱ እስከ ሜትር ከግማሽ ይደርሳል። የቆዳው ቀለም ከአመድማ እስከ ፈዛዛ ቡኒ ድረስ የሚለያይ ሲሆን ዓይኑ አካባቢ ደግሞ ጥቁር ነው። ይህ ትንሽና ድንጉጥ ዓሣ የሚኖረው የኮሎራዶ ወንዝ ከባሕረ ሰላጤው ጋር በሚቀላቀልበት አካባቢ በሚገኘው ጥልቀት በሌለው ድፍርስ ውኃ ውስጥ ሲሆን ብዙ ጊዜ የማይታይ ከመሆኑም ሌላ ባሕርዩም በደንብ አይታወቅም። እንዲያውም በባጃ ካሊፎርኒያ የባሕር ዳርቻ ላይ ሦስት የራስ ቅሎች እስከተገኙበት እስከ 1958 ድረስ ይህ የዓሣ ዝርያ መኖሩ አይታወቅም ነበር።
ቫኪታዎች በጥቂት መቶዎች ብቻ የሚቆጠሩ በመሆናቸው የመጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው ዝርያዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ያም ሆኖ ግን በየዓመቱ በርካታ ቫኪታዎች በአካባቢው በሚገኙ ዓሣ አስጋሪዎች ይያዛሉ። ሜክሲኮ፣ ቁጥራቸው እየተመናመነ የሄደውን የእነዚህን አጥቢ እንስሳት ሕይወት ለመታደግ፣ እነሱ የሚኖሩበትን ጨምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ወስናለች። በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በቋሚነት ከሚኖሩትና ከሌላ ቦታ ከሚመጡት እንስሳት መካከል ዓሣ ነባሪዎች፣ ጃያንት ማንታ ሬይስ፣ የባሕር ዔሊዎች፣ አስቆስጣዎችና እጅብ ብለው የሚጓዙ ቱና የሚባሉ ዓሣዎች ይገኙበታል።
የሳይንስ ሊቃውንት፣ ሰዎች እምብዛም የማያውቋቸውን በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ፍጥረታትን በባሕረ ሰላጤው ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው ጥልቅ ውኃ ውስጥ አግኝተዋል። እነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት 2,000 ሜትር ያህል ጥልቀት ባለው በጉአይማስ ሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ በመሆናቸው ሰዎች እንደ ልብ ሊያዩዋቸው አይችሉም። ፍል ውኃዎች በሚፈልቁበት በዚህ ጥልቅ ቦታ ውስጥ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ይገኛሉ፤ እነዚህ ፍጥረታት ኃይል የሚያገኙት ከፀሐይ ብርሃን ሳይሆን ከሃይድሮጅን ሰልፋይድ ነው። በእነዚህ ፍል ውኃዎች አቅራቢያ ከሚኖሩት ፍጥረታት መካከል አንዱ ቲዩብ ወርም በመባል የሚታወቀው ትል ሲሆን አፍም ሆነ ሆድ የለውም። ይህ ትል ከላዩ ቀላ ያለ ላባ መሰል ነገር ያለው ሲሆን እንደሱ ካሉ ሌሎች ትሎች ጋር አብሮ ይኖራል። ቲዩብ ወርም በአንድ በኩል ያለውን የሰውነቱን ክፍል ከባሕሩ ወለል ጋር በማጣበቅ አንዴ ወደ ቀዝቃዛው አንዴ ወደ ሙቅ ውኃው ወዲያ ወዲህ ይላል። እያንዳንዱ ትል በሰውነቱ ውስጥ ባክቴሪያዎች አሉት፤ እነዚህ ባክቴሪያዎች ደግሞ ትሉ በሕይወት እንዲኖር ይረዱታል። ቀላ ያለው ላባ መሰል ነገር ደግሞ የመተንፈሻ አካል ሆኖ ያገለግለዋል።
የባሕረ ሰላጤው ብዝሃ ሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የወደፊቱ ጊዜ ግን ብሩሕ ተስፋ ይዟል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ፈጣሪ ሁኔታው ስለሚያሳስበው ነው። እንዲያውም ለመላው ምድር በጣም ስለሚያስብ ፕላኔታችንን ከጥፋት ለመታደግ በቅርቡ ጣልቃ ይገባል፤ እንዲህ በማድረግም ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር ያደርሳል። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ ራእይ 11:18) በዚያን ጊዜ የካሊፎርኒያ ባሕረ ሰላጤ ምን ያህል ውብ እንደሚሆን መገመት ያዳግታል! በእርግጥም ሙሉ በሙሉ “ዕጹብ ድንቅ” የሚባልለት ጊዜ ይመጣል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፊን ዌል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቲዩብ ወርምስ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
የሳተላይት ፎቶ:- NASA/The Visible Earth (http://visibleearth.nasa.gov/); reef: © Dirscherl Reinhard/age fotostock
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
የባሕር ዳርቻ:- Mexico Tourism Board; whale: © Mark Jones/age fotostock; tube worms: © Woods Hole Oceanographic Institution