የአምላክ አገዛዝ የሚያመጣው አስተማማኝ ሕይወት
የአምላክ አገዛዝ የሚያመጣው አስተማማኝ ሕይወት
በቅርቡ አምላክ ፕላኔቷን ምድራችንን በመንግሥቱ አማካኝነት መግዛት ስለሚጀምር ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከሚሰማን ስጋት እንገላገላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ይህንን ድንቅ ተስፋ በአእምሮው ይዞ ነበር።—ማቴዎስ 6:9, 10
የአምላክ መንግሥት ከፖለቲካ መሪዎች ጋር አይተባበርም፤ ወይም ደግሞ ዓላማውን ለማስፈጸም በእነሱ አይጠቀምም። ከዚህ ይልቅ ዳንኤል ስለ “መጨረሻው ዘመን” በተናገረው በሚከተለው ትንቢት ላይ እንዳመለከተው የአምላክ መንግሥት የሰብዓዊ አገዛዝን ርዝራዥ እንኳ ሳያስቀር ድምጥማጡን ያጠፋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) እነዚህ ቃላት ሰብዓዊ አገዛዝን ለሚመርጡ ሰዎች የሚያጽናኑ ወይም ተስፋ ያዘሉ ባይሆኑም የአምላክ ሉዓላዊነት በመንግሥቱ አማካኝነት ተረጋግጦ ለማየት ለሚናፍቁ ሁሉ ግን ታላቅ ተስፋ ይፈነጥቃሉ።
አስደናቂ ተስፋ!
የአምላክ መንግሥት መላውን ምድር መግዛት ሲጀምር ዜጎቹ በፖለቲካ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በካርታ ላይ በተሳለ የድንበር ምልክት አይከፋፈሉም። ከዚህ ይልቅ በሃይማኖታዊ እውነትና በእውነተኛ ፍቅር ተሳስረው ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ይመሠርታሉ። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 17:3, 17) አዎን፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ጽድቅ የሚሰፍን” ከመሆኑም በላይ “ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7
ከእነዚህ ነገሮች በተጨማሪ የአምላክ መንግሥት በሽታን፣ መከራንና ሞትን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በአእምሮም ሆነ በአካል ፍጽምና ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል። (ራእይ 21:3, 4) ውጤቱስ ምን ይሆናል? ምድራችን ሙሉ በሙሉ ገነት ስለምትሆን በኤደን ገነት የተነገረው የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጸማል። *—ዘፍጥረት 1:28
ተወዳዳሪ የሌለው እውነተኛ ምሥራች
ኢየሱስ “የዓለም መጨረሻ” ምልክቱ ምን እንደሆነ በተናገረበት ወቅት አንድ ትኩረት የሚስብ ነገር አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-7) እንዲህ ብሏል:- “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
በ236 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መልኩ በ2007 የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች በመስበኩ ሥራ ላይ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሰዓት አሳልፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እንዲህ ያለ ጽኑ እምነት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው? መልሱ በጣም ቀላል ነው። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንደሚያብራራው አምላክ ምንጊዜም ቃሉን የሚፈጽም በመሆኑ ነው።—ሮሜ 3:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 በገጽ 10 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—ምድር ገነት ትሆናለች?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ‘ሰላም እንደሚበዛ’ ይናገራል