“ልጄን ምን ነካት?”
“ልጄን ምን ነካት?”
ስኮትና ሳንድራ * የ15 ዓመት ልጃቸው ወደ ሳሎን ስትገባ በድንጋጤ ፈዘው ቀሩ። ወርቃማ የነበረው ፀጉሯ አሁን ደማቅ ቀይ ቀለም ተቀብቷል! ይበልጥ ያስደነገጣቸው ደግሞ ለጠየቋት ጥያቄ የሰጠቻቸው መልስ ነበር።
“ፀጉርሽን ቀለም እንድትቀቢ ፈቅደንልሽ ነበር እንዴ?”
“ቀለም መቀባት እንደሌለብኝ አልነገራችሁኝም።”
“ለምን አልጠየቅሽንም?”
“እንደማትፈቅዱልኝ ስለማውቅ!”
ስኮትና ሳንድራ እንደገጠማቸው ሁሉ የጉርምስና ዕድሜ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለወላጆቻቸው ጭምር የሚያስጨንቅና ግራ የሚያጋባ ወቅት ነው። በእርግጥም ብዙዎቹ ወላጆች፣ ልጃቸው ወደ ጉርምስና ዕድሜ ሲደርስ የሚከሰቱትን ድንገተኛ ለውጦች ለማስተናገድ ራሳቸውን አያዘጋጁም። “ሴት ልጃችን ሳናስበው በድንገት ተለወጠችብን” በማለት በካናዳ የምትኖር ባርባራ የተባለች እናት ታስታውሳለች። “‘ልጄን ምን ነካት?’ ብዬ አስብ ጀመር። ልጃችን፣ ተኝተን ሳለ ተሰርቃ በሌላ የተተካች ያህል ሆናብን ነበር!”
ባርባራ ያጋጠማት እንግዳ ነገር ነው ሊባል አይችልም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች ወላጆች ለንቁ! መጽሔት የሰጡትን አስተያየት ተመልከት።
“ልጄ ሲጎረምስ በድንገት ከምንጊዜውም የበለጠ ሐሳበ ግትር እየሆነና ሥልጣናችንን መቀበል እየከበደው መጣ።”—ልያ፣ ብሪታንያ
“ሴት ልጆቻችን፣ ስለራሳቸው በተለይም ስለ መልካቸው ይበልጥ መጨነቅ ጀመሩ።”—ጆን፣ ጋና
“ወንዱ ልጄ የራሱን ውሳኔ ለማድረግ የሚፈልግ ሲሆን እንዲህ አድርግ ተብሎ እንዲነገረው አይፈልግም ነበር።”—ሴሊን፣ ብራዚል
“ሴት ልጃችን ከዚያ በፊት እናደርግ እንደነበረው እንድናቅፋት ወይም እንድንስማት አትፈልግም ነበር።”—አንድሩ፣ ካናዳ
“ልጆቻችን እያደር፣ አትንኩኝ ባዮች እየሆኑ ሄዱ። ውሳኔዎቻችንን ከመቀበል ይልቅ ጥያቄ ማንሳትና መከራከር ጀመሩ።”—ስቲቭ፣ አውስትራሊያ
“ልጄ ስሜቷን ትደብቃለች። ከዚህም በተጨማሪ በራሷ ትንሽ ዓለም ውስጥ ተዘግታ የምትውል ሲሆን ሐሳቧን እንድትገልጽልኝ ለማድረግ ስሞክር ትበሳጭብኛለች።”—ጆአን፣ ሜክሲኮ
“ወንዶች ልጆቻችን ድብቅ እየሆኑ የመጡ ሲሆን ለብቻቸው መሆንም ይፈልጋሉ። ብዙውን ጊዜ ከእኛ ጋር ከሚሆኑ ይልቅ ከጓደኞቻቸው ጋር መሆን ይመርጡ ነበር።”—ዳንኤል፣ ፊሊፒንስ
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ካሏችሁ ከላይ የተገለጹት አንዳንዶቹ አስተያየቶች እናንተ ከገጠሟችሁ ሁኔታዎች ጋር የሚመሳሰሉ ሆነው አግኝታችኋቸው ይሆናል። ከሆነ፣ በመካከላችሁ ያለውን ይህን “እንግዳ” ማለትም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወንድ ወይም ሴት ልጃችሁን ስሜት መረዳት ከአቅማችሁ በላይ እንደማይሆን እርግጠኞች ሁኑ። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳችሁ ይችላል። ግን እንዴት?
ጥበብና ማስተዋል
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት” ይላል። (ምሳሌ 4:5) ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ልጅ ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ሁለቱም ባሕርያት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ልጁ ከሚያሳየው ጠባይ በስተጀርባ ያለውን ነገር ከመገንዘብ አልፎ ልጁ ያለበትን ሁኔታ መረዳት ማስተዋልን ይጠይቃል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ልጃችሁን ኃላፊነት የሚሰማው ጎልማሳ እንዲሆን አድርጋችሁ ለማሳደግ ጥበበኞች መሆን ያስፈልጋችኋል።
በእናንተና በወንድ ወይም በሴት ልጃችሁ መካከል የተፈጠረው ክፍተት ይበልጥ እየሰፋ የሚሄድ ስለመሰላችሁ ብቻ የእናንተ እርዳታ እንደማያስፈልጋቸው አድርጋችሁ አታስቡ። እንዲያውም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች፣ የወላጆቻቸው ድጋፍ የሚያሻቸው ከመሆኑም በላይ ድጋፋቸውን ይፈልጉታል። ታዲያ ማስተዋልና ጥበብ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ እንድትሰጡ ሊያግዟችሁ የሚችሉት እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።