በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በአምላክ መንፈስ መመራት”

“በአምላክ መንፈስ መመራት”

“በአምላክ መንፈስ መመራት”

የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ

▪ ከግንቦት 23 እስከ 25 ባሉት ቀናት በዩናይትድ ስቴትስ የሚጀምሩት እነዚህ የሦስት ቀን ስብሰባዎች በመጪዎቹ ወራት ውስጥ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሺህ በሚቆጠሩ ከተሞች ውስጥ ይካሄዳሉ። በ2007 ተደርገው በነበሩት 3,200 የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተገኝተዋል!

በዚህ ዓመት፣ በብዙ ቦታዎች ላይ ስብሰባው በሦስቱም ቀናት ከጠዋቱ 3:20 በሚሰማው ሙዚቃ ይጀምራል። የዓርቡ ዕለት ጭብጥ “መንፈስ . . . ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” የሚል ሲሆን የተመሠረተው በዮሐንስ 16:13 ላይ ነው። መጀመሪያ ላይ ከሚቀርቡት ንግግሮች መካከል “‘በአምላክ መንፈስ መመራት’ ያለብን ለምንድን ነው?” እና “መንፈስ ቅዱስ—በፍጥረት ሥራ ድርሻ ነበረው!” የሚሉት ይገኙበታል። “በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎች—በአምላክ መንፈስ ተመርተዋል” በሚል ጭብጥ የሚቀርበው ሲምፖዚየም “በሙሴ ዘመን፣” “በመሳፍንት ዘመን” እና “በመጀመሪያው መቶ ዘመን” የሚሉ ንግግሮችን ያካትታል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ፣ “የይሖዋን ዓላማ ዳር በማድረስ ረገድ መንፈስ ቅዱስ የሚጫወተው ሚና” የሚል ርዕስ ባለው የስብሰባውን ጭብጥ በሚያብራራ ንግግር ይደመደማል።

ዓርብ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመጀመሪያው ንግግር “መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በመቀጠልም “መንፈስ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል” እና “የአምላክን ቃል የምትሰሙና የምታደርጉ ሁኑ” የሚሉ ንግግሮች ይቀርባሉ። “እናንት ወጣቶች—በመንፈስ ኑሩ!” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ሲምፖዚየም “በትምህርት ቤት፣” “በሥራ ቦታ፣” “በቤተሰብ ፣” “በጉባኤ፣” “በማኅበራዊ ግብዣዎች” እና “ብቻችሁን ስትሆኑ” የሚሉ ንግግሮችን ይዟል። የዕለቱ ፕሮግራም የሚደመደመው የስብሰባው ጉልህ ክፍል በሆነው “ወጣቶች—ከይሖዋ ጋር የመሠረታችሁትን ዝምድና ጠብቁ” በሚል ርዕስ በሚቀርበው ንግግር ይሆናል። ንግግሩ፣ ወጣቶች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚረዷቸውን ምክሮች ይዟል።

የቅዳሜው ስብሰባ ጭብጥ “መንፈስን ለማስደሰት መዝራት” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የተመሠረተውም በገላትያ 6:8 ላይ ነው። በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ላይ “በአገልግሎታችን በአምላክ መንፈስ መመራት” በሚል ርዕስ ሦስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዚየም ይቀርባል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በጥምቀት ንግግር ይደመደማል፤ ከዚያም ብቃቱን ያሟሉ የጥምቀት ዕጩዎች ይጠመቃሉ።

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የመጀመሪያ ንግግር “በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች” የሚል ነው። በመቀጠልም “መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል” “ፈተናዎችን ለመጋፈጥ፣” “የድካምና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለማሸነፍ፣” “በስደት ለመጽናት፣” “ጎጂ የሆኑ የእኩዮች ተጽዕኖን ለመቋቋም” እና “መከራን ችሎ ለማለፍ” የሚሉ አምስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዚየም ይቀርባል። የዕለቱ ፕሮግራም የሚደመደመው የአውራጃ ስብሰባው ጉልህ ክፍል በሚሆነው “ከአምላክ ፍቅር አትውጡ” በሚለው ንግግር ይሆናል።

የእሁዱ ጠዋት ፕሮግራም በገላትያ 5:16 ላይ የተመሠረተውን “በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ጭብጥ የሚያብራራ ይሆናል። “የመንፈስን ፍሬ አዳብሩ” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ዘጠኝ ክፍሎች ያሉት ሲምፖዚየም በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተጠቀሱትን የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንድ በአንድ ያብራራል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “በይሖዋ መንፈስ በሚመራው ንጉሥ አማካኝነት የሚገኘውን በረከት እጨዱ!” በሚል ጭብጥ በሚቀርበው የሕዝብ ንግግር ይደመደማል። የከሰዓት በኋላውን ስብሰባ ለየት የሚያደርገው “የቀድሞ ፍቅራችሁን አትተዉ” በሚል ጭብጥ የሚቀርበው ጥንታዊ አለባበስ የሚንጸባረቅበት ድራማ ነው። ይህ ድራማ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በነበሩ ክርስቲያኖች መካከል ሊኖር የሚችለውን ጠባይና ሁኔታ ያሳያል። የአውራጃ ስብሰባው የሚደመደመው “በይሖዋ መንፈስ ከሚመራው ድርጅት ጋር በታማኝነት ማገልገል” በሚል ጭብጥ በሚቀርበው ንግግር ይሆናል።

በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ ያውጡ። ስብሰባው በአቅራቢያዎ የሚካሄድበትን ቦታ ለማወቅ ከፈለጉ በአካባቢዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው መጠየቅ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ይችላሉ። የመጋቢት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስብሰባው በኢትዮጵያ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ዝርዝር ይዞ ወጥቷል።