በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በውኃ ላይ የሚበቅሉ ዛፎች

በውኃ ላይ የሚበቅሉ ዛፎች

በውኃ ላይ የሚበቅሉ ዛፎች

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠባቸው ለብዙ ዓይነት ተሳቢና አጥቢ እንስሳት እንዲሁም አእዋፍ መኖሪያነት ያገለግላሉ። በተጨማሪም ብክለት የሚያስከትሉ ነገሮችን ከውኃ ላይ በማጣራት አካባቢው እንዳይበላሽ ይጠብቃሉ። በደቡብ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በዓሣ ማጥመድ ስፖርት ከሚጠመደው 75 በመቶውና ለገበያ ከሚውለው ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነው የዓሣ ምርት የሚገኘው እነዚሁ ፍጥረታት ካሉባቸው አካባቢዎች ነው። ከዚህ በተጨማሪ የባሕር ዳርቻዎች በአውሎ ነፋስና በማዕበል እንዳይጠቁ ይከላከላሉ። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ማንግሩቭ በመባል የሚታወቁት በውኃ ላይ የሚበቅሉ ዕፅዋት ናቸው።

በዓለማችን ከሚገኙት ሞቃታማ የባሕር ዳርቻዎች ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ላይ የሚበቅሉት የማንግሩቭ ዕፅዋት፣ የተለያዩ ዝርያዎች ያሏቸው ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ናቸው። በአጠቃላይ ሲታይ ማንግሩቭ የሚባሉት ዕፅዋት የሚበቅሉት በየብስና በባሕር መካከል ባለ ጨዋማና ንጹሕ ውኃ ተቀላቅሎ በሚገኝበት እምብዛም ጥልቀት በሌለው ውኃ ላይ ነው። በውኃው ውስጥ ያለው የጨው መጠን ብዙ ዕፅዋት ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ቢሆንም ማንግሩቭ የተባሉት ተክሎች ይህን ተቋቁመው ማደግ ይችላሉ። እንዴት? በዚህ አካባቢ ለመኖር የሚረዷቸው በርካታ አስደናቂ ዘዴዎች ያሏቸው ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ዘዴዎቹን አንድ ላይ አጣምረው ይጠቀማሉ።

በጨው የተከበበ

አንዳንድ የማንግሩቭ ተክሎች ጨው አጣሪዎች በመባል የሚታወቁ ሲሆን ጨው በሥራቸው በኩል እንዳይገባ የሚከለክል ማጣሪያ አላቸው። እነዚህ ተክሎች ጨውን በማጣራት ረገድ በጣም ውጤታማ ከመሆናቸው የተነሳ ውኃ የተጠማ አንድ መንገደኛ ሥራቸውን በመስበር ንጹሕ ውኃ መጠጣት ይችላል። ሌሎቹ የማንግሩቭ ዝርያዎች ደግሞ ጨዉን ወደ ግንዶቻቸው በማስገባት ባረጁ ቅጠሎች ወይም በሌሎች ቦታዎች ውስጥ ካከማቹት በኋላ ያስወግዱታል።

ሌሎቹ ደግሞ ጨዉን ወደ ውስጥ የሚያስገቡ ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ በቅጠሎቻቸው ላይ በሚገኙት ልዩ የጨው ዕጢዎች አማካኝነት ወዲያውኑ ከውስጣቸው ያወጡታል። እንዲህ ያሉትን የማንግሩቭ ዕፅዋት ቅጠል በምላስህ ብትቀምስ ጨው ጨው ይልሃል። ይሁን እንጂ የምትቀምሰውን የማንግሩቭ ዓይነት በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል! ለምሳሌ ያህል፣ ዓይንን ለጊዜው የሚያሳውረው የማንግሩቭ ዝርያ የሚያመነጨው ፈሳሽ ዓይንህ ውስጥ ከገባ ለጊዜው ማየት ሊሳንህ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ፈሳሽ መድኃኒትነት ስላለው ቁስልንና ቃጠሎን ለማከምም ይውላል።

በሕይወት መኖር የቻሉት እንዴት ነው?

አብዛኞቹ ተክሎች በሕይወት ለመኖርና ለማደግ አየር በቀላሉ የሚያስገባ አፈር ላይ መተከል ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ማንግሩቭ የተባሉት ዕፅዋት የሚያድጉት ውኃ ባቆረ መሬት ላይ ነው። እንዲህ ባለ መሬት ላይ ማደግ የቻሉት፣ ከአፈሩ ውስጥ ወጥተው በሚያድጉት ሥሮቻቸው አማካኝነት ከከባቢ አየሩ ላይ በቀጥታ አየር መሳብ ስለሚችሉ ነው። የእነዚህ ዕፅዋት ሥሮች የተለያዩ ቅርጾች አሏቸው። ጉልበት መሳይ ቅርጽ ያላቸው ሥሮች ኒ ሩትስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ከመሬት ተነስተው ወደ ላይ ያድጉና ተመልሰው አፈር ውስጥ ይገባሉ፤ በመሆኑም የታጠፈ ጉልበት የሚመስል አበጥ ያለ ቅርጽ ይኖራቸዋል።

የችካል ወይም የእርሳስ ቅርጽ ያላቸው ፒግ እና ፔንስል ሩትስ የሚባሉት የሥር ዓይነቶች የሚያድጉት ወደ ላይ ቀጥ ብለው ነው። ፕሮፕ ሩትስ ወይም ደጋፊ ሥሮች በመባል የሚታወቁት ሥሮች ደግሞ መጀመሪያ ላይ ከዕፅዋቱ ግንድ የታችኛው ክፍል ላይ ተነስተው ቁልቁል በማደግ መሬቱን የሚመረኮዙ ሲሆን በኋለኛው የእድገት ደረጃቸው ላይ ግን የምርኩዝ ቅርጽ ስለሚኖራቸው ስቲልት ሩትስ ይባላሉ። ፕላንክ ወይም ሪባን የሚባሉት የሥር ዓይነቶች ደግሞ ከዛፉ ሥር ዙሪያውን ካደጉ በኋላ እንደገና ታጥፈው ወደ መሬት ይገባሉ፤ በዚህም የተነሳ ከአፈሩ በላይ ጉብ ጉብ ብሎ የሚታየው የላይኛው ክፍላቸው ብቻ ነው። እነዚህ የተለያዩ ዓይነት ሥሮች ተክሉ አየር እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን በሚዋልለው አፈር ላይ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቆምም ያስችሉታል።

ዘር የሚተኩበት መንገድ

ካኖንቦል የሚባለው የማንግሩቭ ዝርያ ወጣ ገባ ቅርጽ ያላቸው ዘሮች የሞሉበት ክብ የሆነ ትልቅ ፍሬ አለው። ፍሬው ሲበስል ይፈነዳና ዘሮቹ ውኃው ውስጥ ይበተናሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ዘሮች በሞገዱ ኃይል እየተገፉ ሲሄዱ ቆይተው በመጨረሻ መብቀል የሚችሉበት ምቹ ቦታ ያገኛሉ።

ሌሎች ዓይነት የማንግሩቭ ዝርያዎች ደግሞ በዋናው ዛፍ ላይ እንደተጣበቁ እዛው ይበቅላሉ። ይህ በዕፅዋት ዓለም በጣም ያልተለመደ ክስተት ነው። እነዚህ ዕፅዋት የሚያፈሯቸው ዘሮች ከዛፉ ላይ ከወደቁ በኋላ የሚበቅሉበት ተስማሚ ቦታ በመፈለግ ለብዙ ወራት፣ አልፎ ተርፎም ለአንድ ዓመት ያህል ወዲያ ወዲህ ሲሉ ሊቆዩ ይችላሉ።

ዘሩ የሚንሳፈፍበት መንገድ ጨዋማና ንጹሕ ውኃ ወደ ተቀላቀለበት ለእድገቱ ተስማሚ የሆነ ስፍራ ለመድረስ ያለውን አጋጣሚ ያሰፋለታል። ዘሩ፣ በቀላሉ ሊያንሳፍፈው በሚችለው ጨዋማ ውኃ ላይ አግድም ሲሄድ ይቆይና ብዙም ጨዋማ ያልሆነው ውኃ ጋር ሲደርስ በቁመቱ መንሳፈፍ ይጀምራል። በዚህም የተነሳ በጭቃ ላይ የማረፉ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል።

በዓለም ውስጥ ያለ ሌላ ዓለም

የማንግሩቭ ዕፅዋት እጅግ ውስብስብ ለሆነው የምግብ ሠንሠለት መሠረት ሆነው ያገለግላሉ። ከእነዚህ ዕፅዋት ላይ የሚራገፈው ቅጠልና የተክሎቹ ብስባሽ አንድ ሴል ላላቸው ጥቃቅን ፍጥረታት የምግብ ምንጭ ነው። እነዚህን ጥቃቅን ፍጥረታት ደግሞ ሌሎች እንስሳት ይመገቧቸዋል። በመሆኑም በርካታ ሕያዋን ፍጥረታት የማንግሩቭ ዕፅዋትን መኖሪያቸው፣ መመገቢያቸው፣ መራቢያቸው ወይም ልጆችን ማሳደጊያቸው አድርገው ይጠቀሙባቸዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአእዋፍ ዝርያዎች የማንግሩቭ ዕፅዋትን ለመኖሪያነት፣ ምግባቸውን ለማግኘት ወይም በሚፈልሱበት ወቅት ለጊዜው ለማረፍ ይጠቀሙባቸዋል። በቤሊዝ የሚገኘው የማንግሩቭ ደን ብቻውን 500 ለሚሆኑ የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎች መጠለያ ሆኖ ያገለግላል። ብዙ ዓሦችም ሕይወታቸው የሚጀምረው አለዚያም ምግባቸውን የሚያገኙት ከእነዚህ ዕፅዋት አሊያም ዕፅዋቱ ካሉበት አካባቢ ነው። በሕንድና በባንግላዴሽ መካከል ባለው ሳንዳርባንስ ተብሎ በሚጠራው የማንግሩቭ ደን ውስጥ ከ120 የሚበልጡ የዓሣ ዝርያዎች ሲጠመዱ ቆይተዋል።

በማንግሩቭ ደን ውስጥ እጅግ በርካታ የዕፅዋት ዓይነቶችም ይገኛሉ። በአውስትራሊያ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ ላይ ባሉት የማንግሩቭ ዛፎች ላይ 105 ዓይነት የሻጋታ ዝርያዎች እንደሚበቅሉ ታውቋል። በዚህ አካባቢ ፈርን፣ ኦርኪድና ሚስልቶ የሚባሉትን ጨምሮ ሌሎች ተክሎችም በብዛት ይገኛሉ። በእርግጥም በዓለም ላይ ያሉት የማንግሩቭ ተክሎች ከሻጋታ አንስቶ እስከ ነብር ድረስ ላሉ ፍጥረታትም ሆነ ለሰው ልጆች ጠቃሚ አገልግሎት ይሰጣሉ።

ለሰው ልጆች የሚሰጡት በርካታ ጥቅሞች

የማንግሩቭ ዕፅዋት አካባቢ እንዳይበከል ከመርዳታቸውም ሌላ የማገዶ እንጨትን፣ ከሰልንና ታኒን የተባለ አሲድን፣ የእንስሳት ድርቆሽን እንዲሁም ለመድኃኒትነት የሚውሉ ንጥረ ነገሮችን ጨምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጥቅም ላይ የሚውሉ ብዙ ምርቶችን ያስገኛሉ። በተጨማሪም እነዚህ ዕፅዋት ያሉበት አካባቢ እንደ ዓሣ፣ ሸርጣን፣ ባለ ዛጎል ፍጥረታትና ማር ላሉት ጣፋጭ ምግቦችም መገኛ ነው። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንዳንድ ባሕረተኞች ኦይስተር ተብለው የሚጠሩትን የዓሣ ዝርያዎች በማዕበል ምክንያት ውኃው ሲሸሽ ተጋልጠው በሚታዩት የማንግሩቭ ሥሮች ላይ በቀላሉ ያገኟቸው ስለነበር ዓሦቹ በዛፍ ላይ የሚበቅሉ ናቸው ብለው ያስቡ ነበር።

በተጨማሪም የማንግሩቭ ተክሎች ለወረቀት፣ ለጨርቃ ጨርቅና ለቆዳ ፋብሪካዎች እንዲሁም ለግንባታ ቁሳቁሶች የሚሆኑ ንጥረ ነገሮችን ያስገኛሉ። ከማንግሩቭ ዕፅዋት ጥቅም ከሚያገኙ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች መካከል ዓሣ ማስገርና ቱሪዝም ይገኙበታል።

ስለ ማንግሩቭ ደን ጠቃሚነት ያለው ግንዛቤ እየጨመረ ቢመጣም በየዓመቱ በግምት 100,000 ሄክታር ያህል እየቀነሰ ይገኛል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ዕፅዋት የሚመነጠሩት እንደ እርሻና የቤት ግንባታ ላሉት ይበልጥ አትራፊ ለሚመስሉ ፕሮጀክቶች ቦታ ለማስለቀቅ ሲባል ነው። ብዙ ሰዎች የማንግሩቭ ዕፅዋት ያሉበትን ረግረጋማ መሬት የሚመለከቱት ጭቃማ፣ መጥፎ ጠረን ያለውና በትንኞች የተወረረ እንደሆነ አድርገው ሲሆን መጥፋት እንዳለበትም ይሰማቸዋል።

እንደ እውነታው ከሆነ ግን የማንግሩቭ ዕፅዋት በጣም ጠቃሚ አልፎ ተርፎም ሕይወት አድን ተግባር ያከናውናሉ። ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር በቀላሉ የሚላመዱትና ጨው የሚያጣሩት ሥሮቻቸው ለበለጸገና ውስብስብ ለሆነ ሥነ ምሕዳር መሠረት ናቸው። በባሕር ዳርቻዎች ላይ ለሚካሄዱት የዓሣ ንግድና የእንጨት ምርት ኢንዱስትሪ እንዲሁም ለዱር አራዊት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የማንግሩቭ ዕፅዋት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊገድሉ የሚችሉትን ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች ውጠው በማስቀረት የባሕር ዳርቻዎች እንዳይሸረሸሩ ይከላከላሉ። በእርግጥም እነዚህ በውኃ ላይ የሚበቅሉ ዕፅዋት በመኖራቸው አመስጋኝ መሆን ይኖርብናል!

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በማንግሩቭ ደን ውስጥ የዱር ማር መፈለግ

ከዓለም ትልቁ የማንግሩቭ ደን የሚገኘው ሳንዳርባንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ይህ ቦታ ሕንድንና ባንግላዴሽን የሚያቋርጠው ጋንጀስ ወንዝ ከባሕር ጋር የሚገናኝበት ደለላማ ምድር ክፍል ነው። በዚያ አካባቢ ከሚኖሩት ሕዝቦች መካከል መተዳደሪያቸውን በማንግሩቭ ዕፅዋት ላይ ያደረጉት ሞዋሊስ የሚባሉ ጎሳዎች ይገኙበታል። የእነዚህ ሰዎች መተዳደሪያ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ለአደጋ ያጋልጣሉ ከሚባሉት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ሞዋሊሶች የዱር ማር አሳሾች ናቸው። በየዓመቱ በሚያዝያና በግንቦት ወር ላይ፣ ትልልቅ ንቦች የሚሠሩትን የማር እንጀራ ፍለጋ የማንግሩቭ ዕፅዋት ወደሚገኙበት ተለዋዋጭ መልክዓ ምድር ወዳለው ስፍራ አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ። ንቦቹ በጣም ትልልቅ ሲሆኑ ርዝመታቸው ከሦስት ሴንቲ ሜትር ሊበልጥ ይችላል። በተጨማሪም በጣም ተናዳፊዎች ከመሆናቸው የተነሳ ዝሆኖችን እንኳን ሊገድሉ ይችላሉ!

ስለሆነም ማር አሳሾቹ ንቦቹን በጭስ ለማባረር ከማንግሩቭ ጭራሮ የተሠራ ችቦ ይይዛሉ። ጥበበኛ የሆኑ ማር አሳሾች ከዓመት ዓመት የማያቋርጥ የማር ምርት ለማግኘት ንቦቹ መልሰው እንዲሠሩበት የቀፎውን የተወሰነ ክፍል ባለበት ትተው ይሄዳሉ።

ለማር አሳሾቹ ስጋት የሚፈጥሩባቸው ንቦቹ ብቻ አይደሉም። በማንግሩቭ ደን ውስጥ የሚኖሩ እንደ አዞና መርዘኛ እባብ ያሉት ፍጥረታትም ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ። በተጨማሪም ከጫካው ያገኙትን ማርና ሰም ይዘው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሌቦች አድፍጠው ሊጠብቋቸው ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች በማር አሳሾቹ ላይ ጉዳት ሊያደርሱባቸው ቢችሉም ከሁሉ የከፋው ግን ሮያል ቤንጎል በመባል የሚታወቀው የነብር ዝርያ ነው። ይህ እንስሳ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ማር አሳሾችን ይገድላል።

[ምንጭ]

Zafer Kizilkaya/Images & Stories

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ማንግሩቭና ቡቃያዎቻቸው አብዛኞቹ ዛፎች መብቀል በማይችሉበት አካባቢ ተመችቷቸው ያድጋሉ

[ምንጮች]

ከላይ በስተቀኝ:- Zach Holmes Photography/Photographers Direct; ከታች በስተቀኝ:- Martin Spragg Photography (www.spraggshots.com)/Photographers Direct