በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ማሳደግ—ማስተዋል የሚጫወተው ሚና
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ማሳደግ—ማስተዋል የሚጫወተው ሚና
ቋንቋውን መናገር ወደማትችልበት አንድ የባዕድ አገር ለጉብኝት ሄደሃል እንበል። በዚያ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር መግባባት አስቸጋሪ እንደሚሆንብህ ግልጽ ነው፤ ይህ ሲባል ግን ከነዋሪዎቹ ጋር ፈጽሞ መግባባት አትችልም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የቋንቋውን ደንብ የሚያስተምር መጽሐፍ መጠቀምህ የሄድክበትን አገር ቋንቋ መሠረታዊ ቃላትና ሐረጎች ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል። ወይም ደግሞ ከሌሎች ጋር እንድትግባባ አንድ ሰው ሊያስተረጉምልህ ይችላል።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችን የሚያሳድጉ ወላጆች አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ይሰማቸው ይሆናል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ጠባይ መረዳት ልክ እንደ ባዕድ አገር ቋንቋ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይህ ሲባል ግን ፈጽሞ መግባባት አይቻልም ማለት አይደለም። ቁልፉ፣ ወላጆች አንዳንዴ አስደሳች ብዙውን ጊዜ ደግሞ ግራ የሚያጋባ በሆነው በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ የሚከሰቱትን ነገሮች ለመረዳት ጥረት ማድረጋቸው ነው።
የልጆች ባሕርይ የሚለወጥበት ምክንያት
አንድ ወጣት በራሱ ለመመራት መፈለጉ ሁልጊዜ የማመጽ ምልክት ነው ሊባል አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ በኋላ ‘ሰው ከአባቱና ከእናቱ እንደሚለይ’ መናገሩን አስታውሱ። (ዘፍጥረት 2:24) ወጣቶች ለአካለ መጠን ሲደርሱ ለሚያጋጥሟቸው ታላላቅ ኃላፊነቶች ለመዘጋጀት ውሳኔ በማድረግ ረገድ መጠነኛ ተሞክሮ ሊኖራቸው ያስፈልጋል።
ከዚህ በመቀጠል በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ወላጆች የገለጿቸው በልጆቻቸው ላይ ያስተዋሏቸው የጠባይ ለውጦች ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት።
በብሪታንያ የምትኖረው ልያ እንደሚከተለው በማለት ምሬቷን ገልጻ ነበር:- “ልጄ በድንገት ከምንጊዜውም ይበልጥ ሐሳበ ግትር እየሆነና ሥልጣናችንን መቀበል እየከበደው መጣ።”
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ልክ እንደ ትንንሽ ልጆች በተደጋጋሚ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ይሁን እንጂ አሁን፣ አጭርና ቀላል የሆነ መልስ ላያረካቸው ይችላል። ለውጡን ያመጣው ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ . . . አሰላ ነበር” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ወጣቶች የማመዛዘን ችሎታቸውን እያሳደጉ ሲሄዱ ‘መልካሙን ከክፉው የመለየት’ ችሎታቸው እንዲሠለጥን ተጨማሪና ሰፊ ማብራሪያ ማግኘት ይፈልጋሉ።—ዕብራውያን 5:14
በጋና የሚኖረው ጆን “ሴት ልጆቻችን፣ ስለራሳቸው በተለይም ስለ መልካቸው ይበልጥ መጨነቅ ጀመሩ” ብሏል።
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚታየው እድገት ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ወይም በትክክለኛው ጊዜ ይምጣ፣ ብዙ ወጣቶችን ስለ መልካቸው ከልክ በላይ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ልጃገረዶች በሰውነታቸው ላይ የሚታየውን አዲስ ለውጥ የሚቀበሉት በደስታ ወይም በፍርሃት አለዚያም ሁለቱንም በቀላቀለ ስሜት ሊሆን ይችላል። በዚህ ላይ ብጉር ሲታከልበት ወይም መዋቢያ ቅባቶች መጠቀም ሲጀምሩ ደግሞ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጃገረዶች ትምህርታቸውን በማጥናት ከሚያጠፉት ጊዜ ይልቅ ፊታቸውን በመስተዋት በማየት የሚያሳልፉት ጊዜ የሚበልጠው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
በፊሊፒንስ የሚኖረው ዳንኤል እንደሚከተለው ብሏል:- “ልጆቻችን ድብቅ እየሆኑ የመጡ ሲሆን ለብቻቸው መሆንም ይፈልጋሉ። ብዙውን ጊዜ ከእኛ ጋር ከሚሆኑ ይልቅ ከጓደኞቻቸው ጋር መሆን ይመርጡ ነበር።”
ድብቅነት አደገኛ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 5:12) ለብቻ መሆን መፈለግ ግን ድብቅ ከመሆን የተለየ ነው። ኢየሱስም እንኳ ወደ “ገለልተኛ ስፍራ” ሄዶ ለብቻ መሆን ጠቀሜታ እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። (ማቴዎስ 14:13) ወጣቶች እያደጉ ሲሄዱ ለብቻቸው የሚሆኑበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ትልልቅ ሰዎችም ይህንን እንዲያከብሩላቸው ይፈልጋሉ። በተወሰነ መጠን ለብቻ መሆን ወጣቶች የማመዛዘን ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ የሚጠቅማቸው በጣም አስፈላጊ ችሎታ ነው።
በተመሳሳይም ጓደኝነት መመሥረትን መማር አንዱ የእድገት ክፍል ነው። እውነት ነው፣ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” (1 ቆሮንቶስ 15:33) በሌላ በኩል ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 17:17) ጤናማ ጓደኝነት መመሥረትና ወዳጅነትን ጠብቆ ማቆየት ልጆቹ ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑም አብሯቸው የሚዘልቅ ችሎታ ነው።
ወላጆች ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ልጆቻቸውን ጠባይ በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዱ ማስተዋል ሊኖራቸው ይገባል። እርግጥ ነው፣ ወላጆች አስተዋይ ከመሆን በተጨማሪ ጥበብ ማለትም ለአንድ ሁኔታ ከሁሉ የተሻለ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ምላሽ የመስጠት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል። ታዲያ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ይህን ዓይነቱን ጥበብ ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወጣቶች የማመዛዘን ችሎታቸውን እያሳደጉ ሲሄዱ በቤተሰባቸው ውስጥ ስላሉት ደንቦች ሰፊ ማብራሪያ ይበልጥ ማግኘት ይፈልጋሉ