በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ማሳደግ ጥበብ የሚጫወተው ሚና

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ማሳደግ ጥበብ የሚጫወተው ሚና

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ማሳደግ ጥበብ የሚጫወተው ሚና

“ወንድና ሴት ልጆቻችንን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ቢሆንም ምንጊዜም እንድንቆጣቸው የሚያደርግ ነገር ይኖራል። አንዳንድ ጊዜ፣ ‘በራስ የመተማመን ችሎታቸውን እየገነባንላቸው ነው ወይስ እያፈረስንባቸው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበናል። በጣም ጥብቅ ወይም በጣም ልል ላለመሆን መጣር እጅግ ተፈታታኝ ነው።”—ጆርጅና ሎረን፣ አውስትራሊያ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለን ልጅ ማሳደግ ትልቅ ጥረት ይጠይቃል። ወላጆች፣ ከልጆቻቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከመቋቋም በተጨማሪ ልጆቻቸው እያደጉ መሆናቸው የሚያስከትልባቸውን የሐዘንና የስጋት ስሜት ማሸነፍ ሊኖርባቸው ይችላል። “ልጆቻችን አንድ ቀን ትተውን እንደሚሄዱ ማሰብ በራሱ የሚያሳዝን ነገር ነው። ከእንግዲህ ሕይወታቸውን ልትቆጣጠሩ እንደማትችሉ አምናችሁ መቀበል ቀላል አይደለም” በማለት በአውስትራሊያ የሚኖር ፍራንክ የሚባል አንድ አባት ስሜቱን በግልጽ ተናግሯል።

በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ልያ ከላይ በተገለጸው ሐሳብ ትስማማለች። ልያ እንዲህ ብላለች:- “ልጄን እንደ ትልቅ ሰው አድርጌ ማየት ለእኔ ከባድ ነው፤ ምክንያቱም አሁንም የምመለከተው ገና እንደ ትንሽ ልጅ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት የገባበት ቀን ትናንት መስሎ ይታየኛል!”

ለመቀበል ከባድ ሊሆን ቢችልም፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ትንንሽ ልጆች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ‘በሥልጠና ላይ ያሉ ትልልቅ ሰዎች’ ሲሆኑ ወላጆች ደግሞ አሠልጣኞቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ናቸው። ይሁን እንጂ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ጆርጅና ሎረን እንደተገነዘቡት ወላጆች የልጃቸውን በራስ የመተማመን ችሎታ የመገንባትም ሆነ የማፍረስ ኃይል አላቸው። ታዲያ ወላጆች በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር ይዟል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አስፈላጊ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ለመስማት የፈጠኑ’ እና ‘ለመናገር የዘገዩ’ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል። (ያዕቆብ 1:19) ይህ ምክር በማንኛውም ዕድሜ ላይ ካሉ ልጆች ጋር በተያያዘ የሚሠራ ቢሆንም በተለይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን መስማት ወይም ማዳመጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ጥረት ሊጠይቅ ይችላል።

በብሪታንያ የሚኖር ፒተር የሚባል አባት እንዲህ ብሏል:- “ወንዶች ልጆቼ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ የመግባባት ችሎታዬን ማሳደግ ነበረብኝ። ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ ባለቤቴና እኔ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስንነግራቸው ይታዘዙ ነበር። አሁን ግን አድገዋል፤ ስለሆነም የምናዛቸውን ነገር ማድረግ ያለባቸው ለምን እንደሆነ በዝርዝር እናወያያቸውና በማሰብ ችሎታቸው ተጠቅመው እንዲወስኑ እናደርጋለን። በአጭሩ፣ ልባቸውን መንካት እንዳለብን ይሰማናል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:14

በተለይም ደግሞ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ማዳመጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 17:27) በብሪታንያ የምትኖረው ዳንየል ይህ እውነት መሆኑን ከራሷ ተሞክሮ አይታለች። እንዲህ ትላለች:- “አንደኛዋ ሴት ልጄ፣ አንድ ነገር እንድታደርግ ስጠይቃት መልስ የምትሰጥበት መንገድ ጥሩ እንዳልሆነ ተሰምቶኝ ነበርይሁን እንጂ እሷም ሁልጊዜ ትእዛዝ ስሰጣት እንደምጮኽባት ነገረችኝ። ይህን አለመግባባት ቁጭ ብለን በመነጋገርና ከልብ በመደማመጥ ፈታነው። እንዴት እንደማናግራትና ይህ ደግሞ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚያሳድርባት በግልጽ ነገረችኝ፤ እኔም የማስበውንና የሚሰማኝን በዝርዝር ገለጽኩላት።”

ዳንየል ‘ለመስማት የፈጠነች’ መሆኗ ልጇ እንደዚያ ዓይነት መልስ እንድትሰጣት ምክንያት የሆነውን ነገር እንድታስተውል እንደረዳት ተገንዝባለች። ዳንየል እንዲህ ብላለች:- “አሁን ልጄን በትዕግሥት ለመያዝ እሞክራለሁ፤ እንዲሁም እሷን ባልተናደድኩበት ጊዜ ብቻ ለማነጋገር እጥራለሁ። ግንኙነታችን ይበልጥ እየተሻሻለ ነው።”

ምሳሌ 18:13 “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል” ይላል። በአውስትራሊያ የሚኖር ግሬግ የተባለ አባት ይህ እውነት መሆኑን ተገንዝቧል። “አንዳንድ ጊዜ ከልጆቻችን ጋር አለመግባባት የሚፈጠረው ባለቤቴና እኔ እነሱን ሳናዳምጥና ስሜታቸውን ሳንረዳ ቸኩለን ምን ማድረግ እንደነበረባቸው መምከር ስለምንጀምር ነው። በልጆቹ አመለካከት ጭራሽ ባንስማማ እንኳ አስፈላጊውን እርማት ወይም ምክር ከመስጠታችን በፊት ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማድረግ በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተነዋል።”

ምን ያህል ነፃነት?

ብዙ ጊዜ በወላጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ልጆች መካከል የሚፈጥረው አለመግባባት ከልጆች ነፃነት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆች ምን ያህል ነፃነት ሊሰጣቸው ይገባል? አንድ አባት “አንዳንድ ጊዜ ለሴት ልጄ አንዲት ስንዝር ነፃነት ከሰጠኋት አንድ ክንድ እንዲሆንላት እንደምትፈልግ ይሰማኛል” ብሏል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለወጣቶች ገደብ የሌለው ነፃነት መስጠት መዘዝ ያስከትላል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 29:15) በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ጥብቅ መመሪያዎች የሚያስፈልጓቸው ሲሆን ወላጆች ደግሞ አፍቃሪዎች ሆኖም የቤተሰቡን ደንቦች በተገቢው መንገድ የሚያስፈጽሙ መሆን አለባቸው። (ኤፌሶን 6:4) ያም ሆኖ፣ ወጣቶች ትልቅ ሰው በሚሆኑበት ጊዜ ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ ለማሠልጠን መጠነኛ ነፃነት ሊሰጣቸው ይገባል።

ለምሳሌ ያህል፣ መራመድ የተለማመድክበትን መንገድ ለማሰብ ሞክር። ሕፃን ሳለህ መጀመሪያ ላይ የሚያዝልህ ሰው ያስፈልግ ነበር። ከጊዜ በኋላ መዳህና ከዚያም መራመድ ጀመርክ። እርግጥ ነው፣ ለአንድ ትንሽ ልጅ ብቻውን ወዲያና ወዲህ ማለት አደገኛ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ወላጆችህ በቅርበት ይከታተሉህ ምናልባትም ደረጃዎችን ጨምሮ አደገኛ ወደሆኑ አካባቢዎች እንዳትደርስ ማገጃ ያበጁልህ ይሆናል። በተደጋጋሚ ጊዜ መውደቅህ የማይቀር ቢሆንም እንኳ ወዲያና ወዲህ እንድትል ስለፈቀዱልህ ራስህን ችለህ መራመድ ችለሃል።

ለልጆች ነፃነት መስጠትም ተመሳሳይ የሆነ ሂደት ያካትታል። በዚህ ረገድም በመጀመሪያ ላይ ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸውን ያዝሏቸዋል ለማለት ይቻላል። ይህንንም የሚያደርጉት ለልጆቻቸው ውሳኔ በማድረግ ነው። በኋላም ልጆቹ መጠነኛ ብስለት ሲያሳዩ ወላጆች በምሳሌያዊ አባባል እንዲድሁ ይፈቅዱላቸዋል። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ምርጫዎችን እንዲያደርጉ ይፈቅዱላቸዋል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ማገጃ አጥሮቹ በቦታቸው ስላሉ ወጣቶችን ከጉዳት ይጠብቋቸዋል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው እየጎለመሱ ሲሄዱ ራሳቸውን ችለው “እንዲራመዱ” ይለቋቸዋል። በመሆኑም ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ ‘የራሳቸውን ሸክም መሸከም’ ይችላሉ።—ገላትያ 6:5

ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ መማር

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ መጠነኛ ነፃነት ሰጥተውት ነበር፤ ይሁን እንጂ ነፃነቱን አላግባብ አልተጠቀመበትም። እንዲያውም ኢየሱስ ወላጆቹን ‘በመታዘዝ’ “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።” —ሉቃስ 2:51, 52

ወላጅ እንደመሆንህ መጠን አንተም ከዚህ ምሳሌ ልትማርና ትንንሽ ልጆችህ ነፃነታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት መሆናቸውን ሲያሳዩ እያደር ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ልትሰጣቸው ትችላለህ። አንዳንድ ወላጆች በዚህ ረገድ ስላገኟቸው ተሞክሮዎች የተናገሩትን ልብ በል።

“በልጆቼ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከልክ በላይ ጣልቃ እገባ ነበር። በኋላ ላይ ግን መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተማርኳቸውና በተማሩት መሠረት ውሳኔ እንዲያደርጉ ፈቀድኩላቸው። ከዚያ በኋላ ውሳኔዎቻቸውን በጥንቃቄ መመዘን እንደጀመሩ አስተዋልኩ።”—ሱ ሂዩን፣ ኮሪያ

“ባለቤቴና እኔ ለልጆቻችን ምን ያህል ነፃነት መስጠት አለብን የሚለው ጉዳይ ሁልጊዜ ያስጨንቀን ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ስጋታችን ልጆቻችን ተገቢውን ነፃነት አግኝተው ነፃነታቸውን ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ ከመጠቀም እንዲያግዳቸው አልፈለግንም።”—ዳርያ፣ ብራዚል

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወንድ ልጄ የሰጠሁትን ነፃነት በጥሩ መንገድ ሲጠቀምበት ማመስገን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እሱ እንዲያደርግ የምጠብቅበትን ነገር እኔ ራሴም አደርገዋለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ የት እንደምሄድና ምን እንደምሠራ እነግረዋለሁ። የምዘገይ ከሆነም ቀደም ብዬ አሳውቀዋለሁ።”—አና፣ ጣሊያን

“በቤታችን ውስጥ ነፃነት ማግኘት ወንዶች ልጆቻችን እንደ መብት የሚያገኙት ሳይሆን እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ማስመስከራቸው የሚያስገኝላቸው ዋጋ መሆኑን በጥብቅ እናስገነዝባቸዋለን።”—ፒተር፣ ብሪታንያ

የዘሩትን ማጨድ

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው” በማለት ይናገራል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27) አንድ ወጣት የኃላፊነት ቀንበር ሊሸከም ከሚችልባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” የሚለውን ሐቅ በራሱ ተሞክሮ መማሩ ነው።—ገላትያ 6:7

አንዳንድ ወላጆች፣ በቅንነት ተነሳስተው ቢሆንም እንኳ ልጆቻቸው የፈጸሙት ጥበብ የጎደለው ተግባር ከሚያስከትልባቸው መጥፎ ውጤት ይጋርዷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ልጅ ገንዘቡን ባልረባ ነገር አባክኖ ዕዳ ውስጥ ገባ እንበል። አባቱና እናቱ ዕዳውን ቢከፍሉለት የሚያገኘው ትምህርት ይኖራል? በሌላ በኩል ደግሞ የልጁ ወላጆች ዕዳውን ራሱ መክፈል የሚችልበትን ዕቅድ እንዲነድፍ ቢረዱትስ?

ወላጆች፣ ልጆቻቸው የፈጸሙት የግዴለሽነት ተግባር ከሚያስከትልባቸው መዘዝ እንዲማሩ ሳያደርጉ ቢቀሩ እየጠቀሟቸው አይደለም። እንዲህ ማድረግ ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ ለሚጠብቃቸው ሕይወት ከማዘጋጀት ይልቅ በአስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ የሚደርስላቸውና የሠሩትን ስህተት የሚሸፋፍንላቸው ሰው እንዳለ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች የዘሩትን እንዲያጭዱና ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲማሩ አጋጣሚ መስጠት ከሁሉ የተሻለ ነው። ይህ “መልካሙን ከክፉው ለመለየት” እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን ማሠልጠን የሚቻልበት አንዱ ጠቃሚ መንገድ ነው።—ዕብራውያን 5:14

“በመለወጥና በማደግ ላይ ያለ ሰው”

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ተፈታታኝ ሥራ እንደተደቀነባቸው ጥርጥር የለውም። ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ ሲጥሩ አንዳንድ ጊዜ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንባቸውን ማፍሰሳቸው አይቀርም።—ኤፌሶን 6:4

በመጨረሻም፣ ልጅን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ሲባል የመቆጣጠር ሳይሆን ትክክለኛ የሆኑ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የማስተማርና በልባቸው ውስጥ የመቅረጽ ጉዳይ ነው። (ዘዳግም 6:6-9) ይህን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ግሬግ እንዲህ ይላል:- “አብሮን ያለው በመለወጥና በማደግ ላይ ያለ ሰው ነው። ይህ ማለት ደግሞ በየጊዜው አዳዲስ ለውጦችን ከሚያሳየው ከዚህ ሰው ጋር ዘወትር መተዋወቅና ራሳችንን ከእሱ ጋር ማስማማት አለብን ማለት ነው።”

በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ተጣጣር። ከልጆችህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን። ይሁን እንጂ በሕይወታቸው ውስጥ ምንጊዜም አርዓያ ሁንላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ይላል።—ምሳሌ 22:6

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ነፃነት ማግኘት፣ መራመድ ከመለማመድ ጋር ይመሳሰላል—ቀስ በቀስ የሚመጣ ነገር ነው

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ መጠነኛ ነፃነት ተሰጥቶት ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ሥልጣናችሁን ይበልጥ እንዲገነዘቡ ማድረግ”

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ በጣልክበት ገደብ መበሳጨቱ ሥልጣንህን ከመጠቀም ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሕይወት ተሞክሮ እንደሚጎድላቸውና አሁንም መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው አስታውስ።—ምሳሌ 22:15

ጆን ሮዝሞንድ፣ ኒው ፓረንት ፓወር! በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ወላጆች የልጆቻቸው በስሜት መገንፈል በቀላሉ ሊያስፈራቸውና ከእንካ ሰላንትያ ለመገላገል ሲሉ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ኃላፊነት እንዲሸከሙ መፍቀድ ሊጀምሩ ይችላሉ። ነገር ግን ወላጆች ማድረግ ያለባቸው ተቃራኒውን ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲፈጠር ልጆቻችሁ ሥልጣናችሁን ይበልጥ እንዲገነዘቡ ማድረግ እንጂ ሥልጣናችሁን ችላ እንዲሉ መፍቀድ የለባችሁም። ከዚህም በተጨማሪ፣ ልጆቹ ሐሳቡን ባይቀበሉትም እንኳ ወላጆቻቸው እነሱን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የመምራት ሥልጣን እንዳላቸው መማር አለባቸው።”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተጨማሪ ነፃነት መስጠት

ብዙውን ጊዜ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ሊኖራቸው ከሚገባው በላይ ነፃነት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወላጆች፣ ለልጆቻቸው የሚሰጡት ነፃነት ሊሰጧቸው ከሚገባው ያነሰ ነው። በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መሃል ሚዛናዊ ቦታ አለ። ይህን ሚዛናዊ ቦታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ለመነሻ ያህል፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሐሳቦች ላይ ልታስብባቸው ትፈልግ ይሆናል። ወንድ ወይም ሴት ልጅህ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ያሳዩት በየትኛው መስክ ነው?

□ የጓደኛ ምርጫ

□ የልብስ ምርጫ

□ የገንዘብ አጠቃቀም

□ የሰዓት እላፊ ገደብን ማክበር

□ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማጠናቀቅ

□ የትምህርት ቤት ሥራን መሥራት

□ ለሠሩት ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ

□ ሌላ ․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ ከላይ በተዘረዘሩት በአብዛኞቹ ነጥቦች ላይ ብስለት እንዳለው ካሳየ ተጨማሪ ኃላፊነት ልትሰጠው የምትችልባቸውን መንገዶች ለምን አታስብም?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ዓይነት እርማት ወይም ምክር ከመስጠታችሁ በፊት ስሜታቸውን እንዲገልጹ ፍቀዱላቸው

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማስተማር ያስፈልጋቸዋል