ከመጫወቻነት ያለፉ አሻንጉሊቶች
ከመጫወቻነት ያለፉ አሻንጉሊቶች
ግብፃውያን ከቁርጥራጭ እንጨቶች፣ ጃፓናውያን ከተጣጠፉ ወረቀቶች፣ ጀርመናውያን ከሸክላ፣ ኤስኪሞዎች ደግሞ ከአቆስጣ (seal) ቆዳ ይሠሯቸዋል። ትልልቅ ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማሰባሰብ ጥረት ያደርጋሉ። ልጆች ደግሞ በጣም ይወዷቸዋል። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? አሻንጉሊቶች ናቸው።
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው ይላል:- “በጥንት ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ አሻንጉሊት መሰል ቅርጻ ቅርጾች መጫወቻዎች ሳይሆኑ አስማታዊ ኃይል ያላቸው ወይም ከአምልኮ ጋር ለተያያዘ ዓላማ የሚውሉ ነበሩ።” የጥንት ግብፃውያን የመቅዘፊያ ቅርጽ ባላቸው ትንንሽ እንጨቶች ላይ ልዩ ልዩ ዲዛይን ያላቸውን ልብሶች በቀለም ስለውባቸው በጫፋቸው ላይ ፀጉር እንዲመስል ከሸክላ የተሠሩ ዶቃዎችን በማሰር ያስጌጧቸው ነበር። እነዚህን ‘መቅዘፊያ መሰል በሆኑ ትንንሽ እንጨቶች የተሠሩ አሻንጉሊቶች’ በመቃብር ውስጥ ያስቀምጧቸዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ከሞት በኋላ አለ ተብሎ በሚታመነው ሕይወት፣ ለሞቱት ሰዎች አገልጋዮች ይሆናሉ ብለው ስለሚያምኑ ነበር። በምዕራብ ኢንዲስ የሚኖሩ ባላጋራዎቻቸውን የመበቀል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጠላቶቻቸውን ለመጉዳት በማሰብ ቩዱ ተብለው በሚጠሩት አሻንጉሊቶች ላይ መርፌ ይሰካሉ።
በብዙ ባሕሎች ውስጥ አሻንጉሊቶች ከመራባት አምልኮ ሥርዓት ጋር ተዛማጅነት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ ግሪክ ልጃገረዶች ከማግባታቸው ጥቂት ቀደም ብለው፣ የመዋለድ አምላክ እንደሆነች አድርገው በሚያስቧት በአርጤምስ መሠዊያ ላይ አሻንጉሊቶቻቸውን ያስቀምጡ ነበር። በዛሬው ጊዜም በጋና፣ አፍሪካ የሚገኙ የአሻንቲ ጎሣ ተወላጅ የሆኑ ሴቶች የሚያማምሩ ልጆች ለመውለድ እንደሚረዳቸው ተስፋ በማድረግ ወገባቸው ላይ አሻንጉሊት የማሰር ልማድ አላቸው። በሶርያ ያሉ አንዳንድ ልጃገረዶችም ማግባት ወደሚችሉበት ዕድሜ ላይ እንደደረሱ ለማሳወቅ በመስኮቶቻቸው ላይ አሻንጉሊቶች ይሰቅላሉ።
በየዓመቱ መጋቢት 3 በጃፓን በሚደረገው ሂና ማትሱሪ ወይም የአሻንጉሊት በዓል ተብሎ በሚጠራው ክብረ በዓል ላይ አሻንጉሊቶች ይቀርባሉ። “በርካታ ባሕሎችን አጣምሮ የያዘው” ይህ ሥነ ሥርዓት የልጃገረዶች በዓል በመባል እንደሚታወቅም ጃፓን—አን ኢለስትሬትድ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። ከእነዚህ ባሕሎች መካከል “አንዱ በሦስተኛው የጨረቃ ወር መጀመሪያ ላይ በወንዝ ዳርቻ የሚደረገው የቻይናውያን የመንጻት ሥርዓት ነው። በሄያን ዘመን (794-1185) የቤተ መንግሥት ባለሟሎች በደላቸውን ከእነሱ አውጥተው በወረቀት
በተሠሩ አሻንጉሊቶች ላይ በማድረግ . . . ወደ ወንዝ ወይም ወደ ውቅያኖስ እንዲጥሉላቸው በሦስተኛው ወር በሦስተኛው ቀን ጠንቋዮችን የመሰብሰብ ልማድ ነበራቸው።”ለመጫወቻ የሚያገለግሉ አሻንጉሊቶች
በጃፓን የኢዶ ዘመን (1603-1867) በተለይ ለልጆች ተብለው የሚሠሩት አሻንጉሊቶች በገሃዱ ዓለም ያሉትን ሰዎች እንዲመስሉ ይደረጉና የተለያዩ ዓይነት አልባሳት ይዘጋጅላቸው ነበር። ሌሎች አሻንጉሊቶች ደግሞ በወፍራም ሽቦ፣ በስፕሪንግ፣ በመዘውሮችና ጥርስ በወጣላቸው እንጨቶች አማካኝነት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጉ ነበር። እንዲያውም እንደነዚህ ካሉት አሻንጉሊቶች መካከል አንዱ በሻይ የተሞላ ሲኒ ይዞ ለእንግዳ ማድረስና ባዶ የሆነውን ሲኒ ይዞ መመለስ ይችል ነበር!
ከ17ኛው መቶ ዘመን በፊት በነበሩት ዘመናት በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ “ዛሬ የምናውቀው ዓይነት የልጅነት ጊዜ አልነበረም” በማለት አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። “ልጆች እንደ ትንንሽ ጎልማሶች ተደርገው ይታዩ ስለነበር የጎልማሳነት ጠባይ እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸው ነበር። አሻንጉሊቶች ለልጆች ተብለው የሚዘጋጁትን ያህል ለአዋቂዎችም ይሠሩ ነበር። ይሁንና በ1800ዎቹ ዓመታት ጨዋታ ለልጆች እድገት አስፈላጊ መሆኑ እየታመነበት መጣ። በመሆኑም በአውሮፓ የአሻንጉሊት ኢንዱስትሪ እጅግ ተስፋፋ።
በ1824 የጀርመን አሻንጉሊት ሠሪዎች አሻንጉሊቶቻቸው “ማማ” እና “ፓፓ” የሚሉትን ቃላት እንዲያሰሙ የሚያደርግ ዘዴ ፈለሰፉ። ቆየት ብሎም በዚያው መቶ ዘመን፣ የሚራመዱ አሻንጉሊቶችን መሥራት ቻሉ። አሜሪካዊው የፈጠራ ሰው ቶማስ ኤዲሰን አንዳንድ አሻንጉሊቶችን የሚናገሩ የሚያስመስል በጣም አነስተኛ ቴፕ እስከ መሥራት ደርሶ ነበር። በመሃሉ ፈረንሳዮች ቤቤ ጉርማን ተብሎ የሚጠራ ምግብ መብላት የሚችል አሻንጉሊት ሠሩ። ከዚህም በተጨማሪ ፈረንሳዮች የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሰው ለሽያጭ የሚቀርቡ የሚያማምሩ አሻንጉሊቶችን በመሥራትም የታወቁ ነበሩ። ለእነዚህ አሻንጉሊቶች ባለቤቶቻቸው እንደ ማበጠሪያ፣ ባለፀጉር ልብስ፣ ማራገቢያና የቤት ቁሳቁሶች የመሳሰሉ ተጨማሪ ዕቃዎች ሊገዙላቸው ይችሉ ነበር።
ሃያኛው መቶ ዘመን በአሻንጉሊት ምርት ረገድ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ እድገት አስመዝግቧል። በ1940ዎቹ ፕላስቲክ ጥቅም ላይ መዋሉ አሻንጉሊት ሠሪዎች በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡ ሆኖም ውስብስብ የሆኑ አሻንጉሊቶችን እንዲሠሩ አስችሏል። ባርቢ ተብላ የምትታወቀው የፕላስቲክ አሻንጉሊት በ1959 በገበያ ላይ ከዋለችበት ጊዜ አንስቶ የአሻንጉሊት ኢንዱስትሪውን ተቆጣጥራው ቆይታለች። ከአንድ ቢሊዮን በላይ ባርቢ አሻንጉሊቶች የተሸጡ ሲሆን በ1997 ብቻ ለሠሪያቸው 1.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
አሻንጉሊቶች እንደ አስተማሪ
በደቡባዊ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ፑብሎ ተብለው የሚጠሩት የሕንድ ጎሣዎች ልጆቻቸውን ስለ አማልክቶቻቸው ለማስተማር ከቁልቋል ሥር ወይም ከጥድ የተሠሩ ካቺና የሚባሉ አሻንጉሊቶችን ይጠቀሙ ነበር። በአንድ ልዩ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ የዚህ ጎሣ አባል የሆነ አንድ ሰው ከአማልክቱ አንዱን ሆኖ ድራማ ተጫውቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲጫወቱበትና እግረ መንገዳቸውንም ከአምላካቸው ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ ለመርዳት በማሰብ በዚያ ሰው መልክ የተሠራ አሻንጉሊት ሰጧቸው።
አሻንጉሊቶች “አንድ ልጅ ቂሙን፣ ንዴቱንና ሌሎችንም ስሜቶቹን የሚወጣባቸው ነገሮች ናቸው” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። አክሎም “በአሻንጉሊቶች መጫወት ልጆች ሲያድጉ ሊያከናውኑት የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት እንዲለማመዱ ያስችላቸዋል” ብሏል። በጃፓን በየዓመቱ በግንቦት ወር በሚከበረው የልጆች ቀን ለትርኢት የቀረበ አንድ አሻንጉሊት ባሕላዊውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ያደረገ ጦረኛ ወጣት ይመስል ነበር። ይህ አሻንጉሊት ወጣት ወንዶች ሲያድጉ እንደሱ እንዲሆኑ፣ ማለትም በአካባቢው ባሕል መሠረት ጠንካራና የተከበሩ የኅብረተሰቡ አባላት ለመሆን እንዲጥሩ ለማበረታታት አገልግሏል።
በልጆችና በአሻንጉሊቶቻቸው መካከል ስሜታዊ ትስስር ስለሚኖር አንዳንድ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች አሻንጉሊቶች በልጆቻቸው እድገት ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተጽዕኖ በቁም ነገር ያስቡበታል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች፣ አሻንጉሊቶች ማራኪ መልክና ማለቂያ የሌለው ቅያሪ ልብስ ያላቸው መሆኑ በሴት ልጆች ላይ ጎጂ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል
ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው አንዲት ሴት እንዳሉት ከሆነ አሻንጉሊቶቹ “ትንንሽ ሴት ልጆችን ከውስጣዊ ውበት ይልቅ ከውጭ በሚታየው መልካቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማበረታታት” ሊያበላሿቸው ይችላሉ።ልጆች በአሻንጉሊት ሲጫወቱ ለተመለከተ ማንኛውም ሰው፣ አሻንጉሊቱ የተሠራው ከጨርቅ ይሁን ከወረቀት፣ ከእንጨት ሆነ ከፕላስቲክ ወይም ከሌላ፣ ከመጫወቻነት ያለፈ ነገር መሆኑን መገንዘቡ አይቀርም። አሻንጉሊት ለልጆች፣ የልጅነት ጊዜያቸውን አብረውት የሚያሳልፉት ጓደኛቸው፣ አጫዋቻቸውና ታማኝ ሚስጥረኛቸው ነው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የድሮ አሻንጉሊቶች ተወዳጅነት እያገኙ ነው
አሻንጉሊቶችን ማሰባሰብ በጣም ተወዳጅ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ እየሆነ መጥቷል። ይህ ድርጊት በ1970ዎቹ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ የአሻንጉሊቶች ሽያጭ በዓለም አቀፉ ገበያ ትልቅ ቦታ እስከማግኘት ደርሶ ነበር። አሻንጉሊት ሰብሳቢዎች የሚፈልጉት ጥቂት ዶላር የሚያወጡ የፕላስቲክ አሻንጉሊቶችን ወይም በካምር እና በራይንሃርት እንደተዘጋጀው ያሉ በብዛት የማይገኙ አሻንጉሊቶችን ነው። በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጀርመን ከተሠሩት ከእነዚህ አሻንጉሊቶች ውስጥ አንዱ በ277,500 የአሜሪካ ዶላር በጨረታ ተሸጦ ነበር! እጅግ ብዙ የአሻንጉሊት ስብስቦች ለእይታ ከቀረቡባቸው ቦታዎች አንዱ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ዮርክ በሮችስተር ከተማ የሚገኘው ስትሮንግ ናሽናል ሙዚየም ኦቭ ፕሌይ ሲሆን 12,000 የሚያህሉ አሻንጉሊቶች ነበሩት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በወላጆች ላይ ስጋት የሚፈጥሩ አሻንጉሊቶች
ወላጆች፣ አንዳንድ አሻንጉሊቶች ሊያስከትሉ ከሚችሉት ጎጂ ተጽዕኖ ልጆቻቸውን መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ዘ ዋሽንግተን ፖስት እንደሚከተለው በማለት ምሬቱን ገልጿል:- “እንደ ቀድሞው የትንባሆ ኢንዱስትሪ ሁሉ የመዝናኛና የአሻንጉሊት ኢንዱስትሪዎችም አብዛኛውን ጊዜ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የሚክዱ ከመሆናቸውም በላይ በራሳቸው ተነሳሽነት ምንም ዓይነት ለውጥ የሚያደርጉ አይመስልም።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በዚህ ረገድ ወላጆች ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ለልጆቻቸው በየዕለቱ ጠቃሚ ምክር እንዲሰጧቸው ያዛቸዋል። (ዘዳግም 6:6-9፤ ምሳሌ 22:6) ታዲያ ወላጆች፣ አንዳንድ አሻንጉሊቶች ከሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ልጆቻቸውን መምከር የሚችሉት እንዴት ነው? አንዲት እናት፣ ለሴት ልጇ ልከኛ ልብስን በሚመለከት በ1 ጢሞቴዎስ 2:9 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ እንዳነበበችላትና በጉዳዩ ላይ እንዳወያየቻት ገልጻለች። ጭውውታቸው የሚከተለውን ይመስል ነበር:-
እናት:- እነዚህ አሻንጉሊቶች ምን ይመስላሉ? ልጅ ወይስ ትልቅ ሴት?
ልጅ:- ትልቅ ሴት።
እናት:- ትልቅ ሴት ይመስላሉ ያልሽው ለምንድን ነው?
ልጅ:- ምክንያቱም ሰውነታቸው የትልልቅ ሴቶችን ይመስላል፤ የለበሱት ልብስና ያደረጉት ጫማም የትልልቅ ሴቶች ዓይነት ነው።
እናት:- ልክ ነሽ። አሁን ካነበብነው ጥቅስ አንጻር ስታዪው ክርስቲያኖች የእነዚህ አሻንጉሊቶች ዓይነት ልብስ መልበስ የሚገባቸው ይመስልሻል?
ልጅ:- አይመስለኝም።
እናት:- ለምን?
ልጅ:- ምክንያቱም ቀሚሶቻቸው በጣም አጫጭር ናቸው፤ . . . ከላይ ያደረጉት ደግሞ ደረትን የሚያጋልጡ . . . ጨርቆቹም ሰውነታቸው ላይ የተጣበቁ ናቸው።
በእርግጥ ልጆቻችሁ ራሳቸው ወደዚህ ዓይነቱ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ የአምላክን መመሪያ ማስተማር ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጋችሁ የሚክስ ነው! ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መቅረጽ እንዲችሉ ለመርዳት ታስቦ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ ብዙ ወላጆችን ጠቅሟቸዋል።
አንተም የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ በሚለው አድራሻ በመጻፍ ጥሩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሉትን ይህን ባለ 256 ገጽ መጽሐፍ ማግኘት ትችላለህ። ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተሰኘውን መጽሐፍ ማግኘት እንደምትፈልግ ገልጸህ ጻፍ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጃፓናውያን ሻይ አሳላፊ አሻንጉሊት
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሩ በመባል የምትጠራው የፈረንሳይ አሻንጉሊት
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ከላይ:- © SHOBEI Tamaya IX; መሃል:- Courtesy, Strong National Museum of Play, Rochester, New York; ከታች:- © Christie’s Images Ltd