በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

የክርስትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? (የካቲት 2007) የተናገራችሁት በአብዛኛው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው፤ እኔም በሐሳባችሁ እስማማለሁ። ሆኖም በመጽሔታችሁ ውስጥ ቅር ያሰኙኝ ሁለት ጉዳዮች አሉ። አንደኛው፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን መናገራችሁ ሲሆን ሌላው ደግሞ ራሳችሁን ከሌሎች የተሻላችሁ አድርጋችሁ የምታዩ መሆናችሁ ነው። ሁላችንም ስምምነት ቢኖረንና የአንድ እምነት ተከታይ ብንሆን ኖሮ ግሩም ነበር፤ እውነታው ግን እንደዛ አይደለም። አንዱን ቤተ ክርስቲያን ወይም ሃይማኖት ከሌላው የተሻለ እንደሆነ አድርጌ አልመለከትም።

ኤስ. ኤስ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሌላ ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አንቃወምም እንዲሁም ራሳችንን ከሌሎች እንደተሻልን አድርገን አንቆጥርም። ሁሉም [ሰዎች] ኀጢአትን እንደሠሩና የአምላክም ክብር እንደጐደላቸው’ እናምናለን። (ሮሜ 3:23) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸውን አስደናቂ ተስፋዎች ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ቤታቸው ድረስ ሄደን ለሰዎች ለመንገር ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ሀብታችንን እናውላለን። ሆኖም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ግብዝነትንና ሃይማኖታዊ ስህተቶችን በድፍረት እንዳጋለጡ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ ያደርጋሉ።

መልስህ ምንድን ነው? ከዚህ በፊት ይህን ክፍል ከሁለቱ ልጆቼ ጋር ሆኜ የማነበው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። አሁን ግን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በልጆቼ ልብ ውስጥ ለመትከል የሚያስችል ጥሩ አምድ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ከዚህም በላይ እኔም ራሴ እምነቴን ለማጠናከር ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ኢ. ኤች.፣ ቼክ ሪፑብሊክ

በምን ርዕስ ላይ የግል ጥናት ማድረግ እንዳለብኝ ሐሳብ ስለሚሰጠኝ ለዚህ ግሩም አምድ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ጥቃቅን የሚመስሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ጨምሮ ሁሉም ነገሮች በጥንቃቄ የተዘጋጁ ናቸው! ጥበበኛ አባት ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል።

አ. ሸ.፣ ሩሲያ

“ይሖዋ እባክህ እንዳገለግልህ ፍቀድልኝ” (ሐምሌ 2007) የዳንዬል ሆልን የሕይወት ታሪክ ማንበቤ በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል። ትንሽ ልጅ በነበረችበት ጊዜ በትምህርት ቤቷ ለሚገኙት ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ለመናገር አትፈራም ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ተማሪዎች እንደዚህ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነኝ።

ኣ. አር.፣ ማዳጋስካር

የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነኝ። እኔና እናቴ የዳንዬልን ተሞክሮ ገና አሁን አንብበን መጨረሳችን ነው። ወላጆቼ በእውነት ውስጥ መሆናቸውንና ይሖዋን ለማገልገል ምንም እንቅፋት የሌለብኝ መሆኔን በአድናቆት ልመለከተው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝቦኛል። ‘የምንኖረው የትም ይሁን የት ይሖዋ ምንጊዜም ከእኛ ጋር ነው’ የሚለውን ሐሳብ በጣም ወድጄዋለሁ። በተጨማሪም ዳንዬል ከትምህርት ቤት ስትመለስ በአልጋዋ ላይ ቁጭ ብላ ልክ እንደ ወላጅ አባቷ ለይሖዋ ስለ ውሎዋ ትነግረው የነበረ መሆኑ እንዳደንቃት አድርጎኛል። እኔም ከዚህ ትምህርት አግኝቼያለሁ!

ኣ. ዴ.፣ ጣሊያን

“የወጣቶች ጥያቄ . . . ሰዎች ሁልጊዜ የሚያገሉኝ ለምንድን ነው?” (ሐምሌ 2007) በጣም ግሩም ርዕስ ነው፤ ለእኔ እንደተጻፈ ያህል ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጥያቄዎቹን በጣም የወደድኳቸው ከመሆኑም በላይ ለመልስ መጻፊያ የሚሆን ባዶ ቦታ መተዉም አስደስቶኛል። አመሰግናችኋለሁ። ርዕሱ በጣም ረድቶኛል።

ኬ. ኣ.፣ ካናዳ